Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር‘ጨው ሆይ ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ…’

‘ጨው ሆይ ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ…’

ቀን:

በመርሃጽድቅ መኮንን አባይነህ

ታዋቂው ናይጄሪያዊ ጸሐፊ ችንዋ አቸቤ “Things Fall Apart” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ.  በ1959 በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽፎ ያሳተመውን ዝነኛ መድበል የአገራችን ሰዎች ወደ አማርኛ ቋንቋ በመለሱበት ወቅት (ነገሮች ተሰባብረው ሲወድቁ) ብለውት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ እውነቱን ለመናገር ለዚያ ርዕስ በግርድፉ የተሰጠው አቻ ትርጓሜ ትክክለኛነት ወይም ኢ-ትክክለኛነት አሁን ላይ ሆኜ ያን ያህል አብዝቶ አያስጨንቀኝም፡፡ ይሁን እንጂ በየትኛውም መስክ ቢሆን ነገሮች ከናካቴው ተሰባብረው እስኪወድቁና ደብዛቸው እስኪጠፋ መጠበቅ ወይም በቸልተኝነት እያዩ ማለፍ ፈጽሞ የሚመከር ጉዳይ እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥቼ ለማሳየት ብቻ፣ ለዚህ ጽሑፍ በመንደርደሪያነት ተጠቅሜበታለሁ፡፡

የመንደራችን ሰዎች ‘ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው’ በማለት ልብሶቻቸውን እያወለቁ ለዋና ልምምድ ወደ አካባቢው ወንዞች የሚሯሯጡ ልጆቻቸውን ሲመክሩ እሰማ ነበር፡፡ ትዝ እንደሚለኝ በጣና ሐይቅ ዳርቻ ላይ ሆኖ ዋና የሚለማመድ ማንኛውም ሰው በእርግጥም ጥልቀት ወዳለው የውኃው ክፍል መግባት ከፈለገ ለዚሁ በሚያበቃው ቁመና ላይ የደረሰ መሆኑን ማረጋገጥ ነበረበት፡፡ ለጊዜው የቆመ መስሎት አጥጋቢ ችሎታ ሳይኖረውና በቂ ጥንቃቄ ሳያደርግ በውሱን አቅሙ እየተንበጫረቀ ወደ መሀል ለመዝለቅ ቢሞክር፣ በውኃው ኃይል ተገፍቶ የመውደቁንና ለሕልፈተ ሕይወት የመዳረጉን አደጋ ራሱ ሊያፋጥን ይችላል፡፡

እኔ እንደማምነው የመንግሥት ሥልጣንም ቀለል ተደርጎ ሲታይ ቀስ በቀስ እያሳሳቀ የሚወስድ ውኃን ይመስላል፡፡ ስለሆነም በልምምድ ያሉ ዋናተኞች ለጊዜው መዝናናታቸውን ብቻ ማዕከል አድርገው ላንዳፍታም ቢሆን ውኃውን በትክክል ከመቅዘፍ መዘናጋት የለባቸውም፡፡ አለበለዚያ ሥልጣን ፈጽሞ በእጅ ሊጨበጥ ወደማይችል አንዳች ፈሳሽ ነገር የመለወጥ አደጋ ስላለው፣ እንዳሰቡት ዋኝተውና ከውኃው ጋር የተፈጠረውን ግብግብ በቀላሉ አሸንፈው የመውጣት ዕድላቸው የመነመነ ይሆናል፡፡

በሰው ልጅ ጤናማ እንቅስቃሴ ውስጥ ዕድሎችና ፈተናዎች የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም ዕድሎችን ብቻ እየመረጡ በመጠቀም ፈተናዎችን ማንገዋለል አይቻልም፡፡ ይልቁንም ችግሮችን ፈርቶ ከሩቁ ከመሸሽ ወይም ከናካቴው መኖራቸውን ሽምጥጥ እያደረጉ ከመካድ ይልቅ የማሸነፊያውን ብልኃት ሰንቆ ፊት ለፊት መጋፈጡ እንደሚበጅ ይታመናል፡፡

ብዙኃኑ ኢትዮጵያዊያን አሁን አሁን አገራዊ ችግሮችን በውል ለይቶና ዙሪያ መለስ ምክሮችን በሚገባ አዳምጦ ለሕዝብ ጥያቄዎች በወቅቱ አመርቂ ምላሽ የመስጠት ሙሉ አቅም ያለው፣ ደፋር የሆነና በሕግ በተሰጠው ሥልጣን ተጠቅሞ ለሚያሳልፈው ውሳኔም ሆነ ለሚወስደው ዕርምጃ ኃላፊነት የሚወስድ ቁርጠኛ አመራር ያላቸው መስሎ አይሰማቸውም፡፡ እንዲያውም በሠለጠኑት አገሮች አዘውትሮ እንደሚከናወነው ነፃ የሕዝብ አስተያየት የሚጠየቅበት፣ የሚሰበሰብበት፣ የሚተነተንበትና መልሶ ለሕዝብ ይፋ የሚደረግበት ሳይንሳዊ አሠራር ቢኖር ዜጎች በገዛ መንግሥታቸው ያላቸው እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መምጣቱን ማረጋገጥ እምብዛም የሚገድ አይመስልም፡፡ ከዚህ የአመራር ክፍተት (Leadership Deficit) የተነሳ ጥንቃቄ በጎደለው አካሄድ ወደ አስከፊ እንጦርጦስ እየወረድን መሆኑን ለመረዳት ነቢይ ሆኖ መገኘትን አይጠይቅም፡፡

እነሆ ይህ አነስተኛ መጣጥፍ በዋነኝነት የሚያተኩረው በአገር ላይ ያንዣበበውን አደጋ ለመቀልበስ ሕዝባችን ከመሪዎቹ በሚጠብቃቸው ትሩፋቶች ላይ ይሆናል፡፡ ያለጥልቅ ጥናትና ምርምር መሪነት በዚህ ጸሐፊ አስተያየት ከሁሉ በፊት ግንባር ቀደም ሆኖ በመሠለፍና ተከታዮችን እኩል በማነቃነቅ ለአንድ ለታለመ የጋራ ግብ ማብቃት ነው፡፡ በተናጠልም ተዋቀረ በቡድን የመሪነት ማዕከላዊ እሴቶች ደግሞ ቅንነት፣ ታታሪነት ወይም ትጋት፣ አርቆ አስተዋይነት፣ የማያወላውል ውሳኔ ሰጪነትና ራስን ለተከታዮች ዘላቂ ጥቅም አሳልፎ መስጠት ናቸው፡፡ እንዲያውም መልካም እረኛ የሚባለው ከራሱ ምቾት ይልቅ ለመንጎቹ ደኅንነት አጥብቆ የሚጨነቅ መሆን አለበት፡፡

መሪነት በአጭር ቃል ባላደራነት ነውና ሸክሙ ከባድና ፅናትን የሚጠይቅ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መሪ ለመሆን በብዙኃኑ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ያሻል፡፡ ለብዙኃኑ ፍላጎት ዋጋ የማይሰጥና የሕዝብን አመኔታ ያላተረፈ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን ጥሩ መሪ መሆን አይችልም፡፡

ከዚህ ሀቅ ብንነሳ መሪነት በቁሙ ሲወሰድ ዕድለኝነት እንደሆነ አያከራክርም፡፡ አበው ‹‹ከሰው መርጦ ለሹመት ከእንጨት መርጦ ለታቦት›› ይሉናል፡፡ በአግባቡ ካልተያዘና ካልተሠራበት ግን የኋላ ኋላ በተመሪዎች ዘንድ ቅሬታን ማሳደሩና ሲብስም ተጠያቂነትን ማስከተሉ አይቀርም፡፡

‘አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ’ ነውና አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እየራቃት እንደመጣ ፈጽሞ መደባበቅ ወደማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ለዚሁ ሰላም መታጣትና ለግጭቶች መበራከት በሚሰነዘሩት መንስዔዎች ላይ ግን መንግሥትና ማኅበረሰቡ የሚሰጧቸው ምክንያቶች የተለያዩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ መንግሥት እነዚህን ደም አፋሳሽ ሁከትና ብጥብጦች በአመዛኙ ዕድገቱ የወለዳቸውና የሚጠበቁ ናቸው ሲል ይደመጣል፡፡ በእርግጥ ይህንን ድምዳሜ በቅጡ ማስረዳት ሳያዳግት አይቀርም፡፡ ድርጅታዊና መንግሥታዊ መግለጫዎች ደጋግመው እንደሚወተውቱት ልማትና ዕድገት ተጨማሪ ፍላጎቶችን እንደሚፈጥሩ በደምሳሳው ሊታመን ቢችል እንኳ፣ ከዚህ አልፎ ለምን ይህንን ያህል የአገራዊ ብጥብጥና ትርምስ መንስዔ እስከመሆን ሊደርስ እንደሚችል ግን ፈጽሞ ግልጽ አይደለም፡፡

ወደድንም ጠላንም በመሬት ላይ የሚታየውን እውነታ ስንከታተል ማኅበረሰቡ በዘላቂ የሰላም ጠንቅነት አዘውትሮ የሚያነሳቸው ቅሬታዎች ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን አባባል የሚቃረኑ ናቸው፡፡ አሁን አሁን የማይናቅ ቁጥር ያላቸው ወገኖች ሕገ መንግሥቱ እንዳልተከበረ፣ በአገሪቱ ውስጥ የሕግ የበላይነት እንዳልተጠበቀ፣ የዜጎችና የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ዘወትር እንደሚጣሱ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንደሌለና ሙስና ክፉኛ እንደተንሰራፋ እንደ ወትሮው በለሆሳስ ሳይሆን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በአደባባይ እያሰሙ ሲያማርሩ መስማት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡

ይኸው ዘርዘር ሲል ደግሞ የውጭ ጉዳይ፣ የመከላከያ፣ የፖሊስና የደኅንነት መዋቅሩ በአንድ ዘር ብቸኛ ቁጥጥር ሥር እንደዋለ፣ የንግድና የኢኮኖሚ አውታሩም ተመሳሳይ ዕጣ እንደገጠመው፣ የአንዳንድ ክልሎች ፖለቲካዊ ድንበር ታሪካዊና ሕገ መንግሥታዊ መሥፈርቶችን ግምት ውስጥ ሳያስገባ ከደርግ ውድቀት በኋላ ወታደራዊ የበላይነት በነበረው ቡድን ፍላጎት ብቻ እንደተሰመረ በአማራ ክልል ብቻ የወልቃይት ጠገዴን፣ የሰቲት ሁመራን፣ የራያና አዘቦንና የመሳሰሉትን አካባቢዎች በምሳሌነት እየጠቀሱ በአድሎዓዊነት የተከናወነ ነበር የሚሉት ከአጎራባች ሕዝቦች መሬት በኃይል እየቀሙና እያስፋፉ የመከለል ዕርምጃ እንደገና እንዲከለስና እንዲታረም ተጨባጭ ችግሮችን በማሳያነት የሚያነሱ የማኅበረሰብ ክፍሎችም አሉ፡፡

እንግዲህ እነዚህንና የመሳሰሉትን የሕዝብ ቅሬታዎችና ስሞታዎች ጀሮ ዳባ ልበስ ብሎ ማለፍ ግዙፍ የመሪዎች ጉድለት ይሆናል፡፡ ከዚያ ይልቅ ጉዳዮችን በጊዜውና በወጉ እየተቀበሉ ማጣራትና ተፈላጊውን ውሳኔ መስጠት፣ በየትኛውም ደረጃ ላይ የሚገኝ አመራር የሚጠበቅበት ቁልፍ የሥራ ድርሻ ይሆናል፡፡ ይህ በብርቱ የኃላፊነት ስሜት ካልተከናወነ ግን (ያደረ ጉበት ወደ አጥንት ስላለመለወጡ) እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡

ስለሆነም የታሪክ አጋጣሚ ፈቅዶላቸው በከፍተኛ የአመራር እርከን ላይ ያሉ የፖለቲካ ሥዩማን አገርና ሕዝብን ከአሳዛኝ ጥፋት ለማዳን ወይም ለመታደግ በግልም ሆነ በቡድን ደረጃ ትንሿን መስዋዕትነት ለመክፈል ፈጽሞ ማመንታት የለባቸውም፡፡ ይልቁንም መሪዎቻችን አገር ከጊዜያዊ የፖለቲካ ሥልጣን በላይ መሆኑን በውል መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ቀድሞ ነገር አገር ከሌለ መንበረ ሥልጣን የሚተከልበትና ባንዲራ የሚውለበለብበት ሥፍራ አይኖርም፡፡ በዜግነት ስም የሚመራና በግብር ከፋይነት የሚተዳደር ሕዝብም እንዲሁ፡፡ ከሰው ልጅ የመማር ችሎታ ብዙ ጊዜ ያነሰ አቅም ያላት የዱር እንስሳ እንኳ የትኛውን እሾህ በቅድሚያ እናውጣልሽ ቢሏት ‘በመጀመሪያ የመቀመጫዬን’ አለች ይባላል፡፡ ቀሪውን እሾህ መሬት ከያዘች በኋላ ራሷ ልትለቅመው እንደምትችል ከወዲሁ በመተማመን ይመስላል፡፡

ከደርግ ውድቀት ማግሥት ኢሕአዴግ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በርግጥ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ጨው ሆኖ ብቅ ማለቱን ማንም ጨርሶ የሚዘነጋው አይደለም፡፡ ጨው ደግሞ ራሱ ምግብ ባይሆን እንኳ ዓይነተኛ የምግብ ማጣፈጫ ለመሆኑ አሌ የሚል ሰው የለም፡፡ እንዲያ ከሆነ ታዲያ ግንባሩ የመንግሥት ሥልጣን ከተቆናጠጠ በኋላ መሠረታዊ የጨውነት ባህርዩን መለወጥ ባልተገባው ነበር፡፡ እነሆ አሁንም ቢሆን ቢመሽ እንኳ አልጨለመበትምና ቢያንስ ለራሱ ሲል እንደ ቀድሞው መጣፈጡን መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ይህ ሳይሆን የቀረ እንደሆነ ወትሮውኑም ቢሆን ያልደቀቀ አሞሌ ጨው በቅርፁ ድንጋይ ነውና ተፈላጊውን ጣዕም መፍጠር ካልቻለ እንደ ኮረት ተቆጥሮ በቀላሉ ሊጣል ወይም ሊወረወር ይችላል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ መሪዎቻችን ለጥቂት ቀናት ሱባኤ ተቀምጠው ከቆዩ በኋላ ሲለያዩ በሚያወጧቸው ድርጅታዊ መግለጫዎች ታድሰናል ወይም ልንታደስ ነው እያሉ የገዛ ሕዝባቸውን ለመደለል ቢሞክሩ ‹‹የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባዬ›› ይሆንባቸዋል፡፡

ከዚያ ይልቅ አሁን ከምንገኝበት ምስቅልቅል በአፋጣኝ ሊያወጣን ከፈለገ ኢሕአዴግ በሚመራው መንግሥት አማካይነት ቀጥሎ የተመለከቱትን ዕርምጃዎች መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡

  • አገር ያወቃቸውንና ፀሐይ የሞቃቸውን ችግሮቻችንን ትክክለኛ ገጽታ ያለ ኃፍረት በመሸፋፈን እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ መግለጫዎችን እያከታተሉ ከማውጣት ተቆጥቦ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ በበርካታ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ውስጥ በተከሰቱት ደም አፋሳሽና አውዳሚ ግጭቶችና ብጥብጦች ሕይወታቸውንም ሆነ አካላቸውን ያጡትንና ሀብትና ንብረት የወደመባቸውን ዜጎች በኦፊሴል ይቅርታ ቢጠይቅ፣ አቅሙ እስከፈቀደ ድረስም በሁከቱ ከባድ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የመልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ ቢያደርግ፡፡
  • የወልቃይት ፀገዴ የአማራ ማንነት ይታወቅልን ንቅናቄ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ የመብት ጥያቄ አቅራቢዎች ወይም ሰላማዊና ሕጋዊ ተቃዋሚዎች ሆነው መንቀሳቀሳቸው የሚታወቅ ሆኖ ሳለ፣ የተለያዩ ታፔላዎች ያላግባብ እየተለጠፉባቸው ተይዘው ዘብጥያ የወረዱ ዜጎች የሰላሙን ሒደት ለማቀላጠፍ ሲባል ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ቢደረግና አቋሞቻቸውን በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲያራምዱ ቢፈቀድላቸው፡፡
  • በፌዴራልም ሆነ በክልል መንግሥታት ይዞታ ሥር የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን ሥራቸውን በነፃነት የሚያከናውኑበትና የሁሉም ወገኖች ድምፅ እኩል የሚሰማበት ምቹ ሁኔታ ቢፈጠር፡፡
  • በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳውን ክፍት አድርጎ ከአገር ውስጥም ሆነ ከባህር ማዶ ተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ለመገናኘት ቢፈቅድና የአገሪቱን መፃኢ ዕድል አስመልክቶ ታዋቂ ምሁራንን፣ የአገር ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት መሪዎችን ጭምር ያሳተፈ ነፃና ግልጽ የብሔራዊ ዕርቅ ውይይት ቢጀምር፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...