አቶ ካሌብ ፀጋዬ፣ የትምህርት ለተቸገሩ ሕፃናት ሥራ አስኪያጅ
ትምህርት ለተቸገሩ ሕፃናት (ኤዱኬሽን ፎር ኒዲ ፒፕል አሶሴሽን) ባጭሩ ኤንፓ በተራድኦ ድርጅትነት የተመሠረተው ከስድስት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ በተለያዩ የሕፃናት ማሳደጊያዎች ውስጥ ያደጉ ግለሰቦች ተሰባስበው ያቋቋሙት ድርጅት ሲሆን፣ ቤተሰቦቻቸው ሊያስተምሯቸው አቅም የሌላቸው ሕፃናት በአፀደ ሕፃናትና መዋለ ሕፃናት (የነርሰሪና ኪንደር ጋርደን) ትምህርት በነፃ እንዲያገኙ ያደርጋሉ፡፡ ድርጅቱ ሕፃናቱ ለትምህርት ከሚገለገሉባቸው ቁሳቁሶች ባሻገር በምግብና አልባሳትም ይደጉማል፡፡ ቤተሰቦቻቸው ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ በተለያየ ሙያ በማሠልጠንም እገዛ ይሰጣል፡፡ ስለ ድርጅቱ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ከመሥራቾቹ አንዱ የሆነውን ሥራ አስኪያጁ አቶ ካሌብ ፀጋዬን ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅቱ የተመሠረተው እንዴትና ምን ዓላማ አንግቦ ነበር?
አቶ ካሌብ፡‑ የድርጅቱ መሥራቾች በአጠቃላይ በተለያዩ የሕፃናት ማሳደጊያዎች ያደግን ነን፡፡ በአሁኑ ሰዓት በተለያየ ሙያ ተሰማርተን የየራሳችንን ሥራ በመሥራት ላይ ነን፡፡ እኛን በጥሩ ሁኔታ መንግሥትና የኢትዮጵያ ሕዝብ እዚህ አድርሶናልና እኛም በተራችን ለሌሎች ሰዎች እንትረፍ ከሚል በጎ ሐሳብ የመነጨ ነው፡፡ የጀመርነው አንድ ቤት ተከራይተን 75 ሕፃናትን በማስተማር ነበር፡፡ ልጆቹን ቤት ለቤት በማሰስና በአካባቢያችን ያለ ዕድር ውስጥ በማጠያየቅ ነው ያገኘናቸው፡፡ ሰዎች በሚነግሩን መሠረት በጣም የተቸገሩና ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው ትምህርት ማግኘት ያልቻሉ ሕፃናትን ለመደገፍ የተቋቋመ ነው፡፡ በበጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ ተመዝግቦ ትክክለኛ ቅርፅ ይዞ መሥራት የጀመረው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ዘንድሮ 80 ተማሪዎች ያሉን ሲሆን እስካሁን ከ230 በላይ ሕፃናት ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተዋል፡፡ ብዙዎቹ ልጆች በጣም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ናቸው፡፡ እናቶቻቸው ልብስ ማጠብና እንጨት መልቀምን የመሰሉ ሥራዎች የሚሠሩ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ እናቶች ልጆቻቸውን ከአባት ውጪ ማሳደጋቸው ሥነ ልቦናዊ ጫናም አሳድሮባቸዋል፡፡ እናቶቹ ከሚያገኙት ደመወዝ የቤት ኪራይ ከፍለውና የዕለት ጉርሳቸውን ሸፍነው ማስተማር አይችሉም፡፡ ቁርስ ወይም ምሳ ቋጥረው ሲመጡ ባቄላ ወይም ባዶ ሰሀን የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ስለዚህ ልጆቹ ከትምህርት ባሻገር ምሳና መክሰስ እንዲያገኙም ይደረጋል፡፡ የምንሠራበት አካባቢ መጠለያ ይባላል፡፡ ከኤርትራ ተፈናቅለው የመጡ ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያ የተሰጣቸው እዚህ ነበር፡፡ ሥራችንን እዚህ አካባቢ ያደረግነውም በርካታ ችግረኞች ያሉበት በመሆኑ ነው፡፡ የተቸገሩ ቤተሰቦች በጣም ብዙ በመሆናቸው ወረዳው ከመዘገባቸው መካከል በጣም ችግረኛ የሆኑትን እንመርጣለን፡፡ ቤት ለቤት እየሄድንም ያሉበትን ሁኔታ እናያለን፡፡ ብዙ ልጆች መቀበል ብንፈልግም ካለን ቦታ ጥበት አንፃር በዓመት 30 ሕፃናት ብቻ ነው የምንቀበለው፡፡
ሪፖርተር፡- ለሕፃናት መሠረታዊ ትምህርት መስጠት የድርጅታችሁ ዋነኛ ትኩረት የሆነው ለምንድነው?
አቶ ካሌብ፡‑ የሁሉም ነገር መሠረት ትምህርት ነው፡፡ ሕፃናት እስከ ሰባት ዓመት ያላቸው ዕድሜ ደግሞ ወርቃማ ነው፡፡ በዛ ዕድሜ በደንብ ከተያዙ የትምህርት ፍቅር ያድርባቸዋል፡፡ ከሁሉም ነገር በፊት ትምህርት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ ሕፃናቱ ነገ የአገር ተረካቢዎች ናቸው፡፡ ልጆቹ ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ ማገዝ በእግዚአብሔር ዘንድና ለህሊናችንም ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ መጀመሪያ የሰው አዕምሮ ላይ ከተሠራ ሰውየው ሌላውን ነገር ይሠራዋል፡፡ ዕድገትም ይመጣል፡፡
ሪፖርተር፡- ልጆቹ በድርጅቱ ውስጥ ተምረው ከወጡ በኋላ ድጋፉ ይቀጥላል?
አቶ ካሌብ፡‑ ከጊዜ ወደ ጊዜ የኑሮ ውድነት በሚያሳድርብን ጫና ሳቢያ ብዙ ነገሮች እያጠሩን ነው፡፡ በፊት ልጆቹ ከድርጅቱ ከወጡ በኋላ የቱቶሪያል (አጋዥ) ትምህርት እንዲያገኙ እናደርግ ነበር፡፡ አሁን ግን ይኼን ማድረግ ከአቅማችን በላይ ነው፡፡ የተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ አቅማችን እየተወሰነ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ተግባር የሁሉንም ሰው ድጋፍ ይፈልጋል፡፡ እኛ ብናልፍም ሥራው መቀጠል መቻል አለበትና እገዛ ያሻናል፡፡ ልጆቹ ከድርጅቱ ከወጡ በኋላ በመድኃኔዓለምና ኪዳነምሕረት በዓላት ላይ ስለ ድርጅቱ የተጻፉ ብሮሸሮች በመበተን ድርጅቱን ሊያስተዋውቁ ይሞክራሉ፡፡ ኤንፓ የተሰኘ የእግር ኳስ ቡድን አቋቁመው በመብራት ኃይል ሜዳ የሚጫወቱ የቀድሞ ተማሪዎቻችንም አሉ፡፡ በመለስ ፋውንዴሽን ከ16 ቡድኖች ተወዳድረው የመጨረሻ አራት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ዋንጫ ከወሰዱ ድርጅቱን የሚደግፉ አካላት ትኩረት እንደሚስቡ ያምናሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ያሉባችሁ ችግሮች ምንድናቸው? ከመንግሥትና ከማኅበረሰቡስ ምን ዓይነት ድጋፍ እንዲደረግላቸሁ ትፈልጋላችሁ?
አቶ ካሌብ፡‑ እዚህ የሚያስተምሩ መምህራን ደመወዝ ዝቅተኛ ቢሆንም በደስታ ያስተምራሉ፡፡ እኛ ደመወዛቸውን መክፈል እስኪያቅተን ድረስ ችግር ውስጥ ገብተናል፡፡ ኅብረተሰቡ ቢተባበር መምህራኑ እንዳይለቁ ሌሎችም ባለሙያዎችም መጥተው እንዲሠሩ ማድረግ እንችላለን፡፡ ለልጆቹ የምንመግበው መኮሮኒ፣ ሩዝ፣ እንጀራ በሽሮና ዳቦ በወተት ነው፡፡ አቅም ቢኖረን በሳምንት ሦስት ቀን ብቻ ከመመገብ ሳምንቱን በሙሉ መመገብ እንችላለን፡፡ በማንኛውም መንገድ ድጋፍ አደርጋለሁ የሚል አካል ካለ በራችን ክፍት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የዕርዳታ ድርጅት ሲባል የሚፈሩ ሰዎች አሉ፡፡ የዕርዳታ ድርጅቶችን የሚያቋቁሙ ሰዎች የሚያገኙትን ድጎማ ያላግባብ ለራሳቸው ጥቅም ያውሉታል የሚል የተሳሳተ ግምት አለ፡፡ ይህንን አመለካከት መቀየር አለብን፡፡ ሰዎች በአካል መጥተው በማየትና በመከታተል ሕፃናቱን መርዳት ይችላሉ፡፡
ትልቁ ጫና የሆነብን ነገር የቤት ኪራይ ነው፡፡ የምንከፍለው ወደ 12,000 ብር ነው፡፡ ሁልጊዜም መክፈልና አለመክፈላችን በምናገኘው ዕርዳታ ይወሰናል፡፡ ቦታው ዘለቄታዊ እንዲሆን መንግሥት ለትምህርት ቤት የሚሆን ቦታ ቢሰጠን ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ቤት ለቤት እየተዘዋወርን ስንመለከት ብዙ አካል ጉዳተኛ ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት ሳይሄዱ ቤት ቀርተው አይተናል፡፡ በአካቶ ትምህርት (በኢንክሉሲቭ ኤዱኬሽን) አራት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ተቀብለናል፡፡ አሁንም ግን ቤተሰቦች መገለልን እየፈሩ አካል ጉዳተኛ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት አያመጡም፡፡ ተቋሙ ሰፍቶ በዚህ ረገድ ብዙ መሠራት አለበት፡፡ ትልቁ ተግዳሮታችን የሆነው የቦታ ችግር ከተፈታ ኅብረተሰቡ በተለያየ መንገድ እንደየአቅሙ ሊደግፈን ይችላል፡፡ ብዙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በበጀት እጥረት ሳቢያ ይዘጋሉ፡፡ ይኼ መሆን የለበትም፡፡ የማኅበረሰቡ ችግሮች የሚቀረፉት አንድም በተራድኦ ድርጅቶች በመሆኑ መዘጋት የለባቸውም፤ መቀጠል አለባቸው፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ዕርዳታ የሚያደርጉላችሁ ግለሰቦች ወይም ተቋማት አሉ? እናንተስ ገቢ ለማግኘት የምታደርጉት ጥረት አለ?
አቶ ካሌብ፡‑ በምንሠራበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች በጣም ይደግፉናል፡፡ በጣልያን ትምህርት ቤት ውስጥ ያስተምሩ የነበሩ አራት መምህራን የኮንትራት ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው ሳይመለሱ በፊት ከፍተኛ ዕርዳታ ያደርጉልን ነበር፡፡ ዕርዳታ መስጠት ለውጭ ዜጎች ብቻ የተተወ ሳይሆን እኛው ለእኛውም ማድረግ እንችላለን፡፡ የዕርዳታ ድርጅት ቢሆንም የምንሰጠው ትምህርት ጥራቱን የጠበቀ ነው፡፡ ልጆቹ ማወቅ የሚገባቸውን እንዲያውቁ መምህራኑ በፍቅር ያስተምሯቸዋል፡፡ ትምህርቱ ሥነ ጥበብን ያማከለ እንዲሆን ለማድረግም ጥረት ይደረጋል፡፡ ልጆቹን ለማበረታታት ሽልማት ይሰጣቸዋል፡፡ ልጆቹ ሲያድጉ እንደእኛ ዓይነት ድርጅት ለመክፈት እንደሚፈልጉ ሲናገሩ ስሰማ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ገቢ ለማግኘት የምናደርገው ጥናት ካለን ቦታ ጥበት አንፃር ከባድ ነው፡፡ መንግሥት የዕርዳታ ድርጅቶች ከሚረዷቸው ሰዎች ጋር ወጪ መጋራት (ኮስት ሼሪንግ) ያድርጉ የሚል አሠራር አለው፡፡ እኛ የምንረዳቸው ሰዎች በቂ ገቢ ስለሌላቸው ይህንን ማድረግ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ገቢ ማግኛ እንቅስቃሴ የግድ ያስፈልጋል፡፡ ገቢ ለማግኘት ካሰብናቸው ነገሮች መካከል ዶሮ እርባታ፣ ከብት እርባታ ይገኝበታል፡፡ ላም ብንገዛ ልጆቹ ከሚጠጡት ወተት ባለፈ መሸጥ ይቻላል፡፡ የቦታ ችግራችን ሲፈታ የምናከናውናቸው ይሆናሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ልጆቹ በድርጅታችሁ አቅራቢያ ያሉ የዕርዳታ ድርጅቶችን እንዲጎበኙ ታደርጋላችሁ፡፡ ለምን?
አቶ ካሌብ፡‑ በአቅራቢያችን መቄዶኒያ የዕርዳታ ድርጅት አለ፡፡ ድርጅቱ እየሠራ ያለው ነገር በጣም የሚያስደስትና የሚያስደንቅ ነው፡፡ ሕፃናቱም ሄደው እንዲጎበኙት አድርገናል፡፡ ልጆቹ በቁርስ ሰዓት የሚሰጣቸውን ዳቦ ይዘው ሄደው ለአረጋውያኑ ሠጥተዋል፡፡ አረጋውያንን ስለመንከባከብ የሚያሳይ ድራማ በማሳየትም አዝናንተዋቸዋል፡፡ ለሰንደቅ ዓላማ ቀንና ሌሎችም በዓላት እየሄዱ በጎ ስለማድረግ እንዲማሩ እናደርጋለን፡፡ ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው የሚለውን የመቄዶንያ መሪ ቃል ጽፈው ሄደው ነበር፡፡ እኛ ሕፃናት ብንሆንም ባለን ነገር ዕርዳታ ከማድረግ ዕድሜያችን አይገድበንም የሚል አስተሳሰብ እንዲያድርባቸው ለማድረግ አስበን ነው፡፡ ሥነ ልቦናቸው ለሰዎች በጎ የማድረግን ነገር እንዲረዳ ለማድረግ ነው፡፡ ልጆቹ አካባቢያቸውን እንዲያውቁም ወደተለያዩ ቦታዎች ትምህርታዊ ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ በአካባቢያችን ያለው መላጣ ጋራ ተራራ ይጠቀሳል፡፡ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በወንድማማቾቹ ኢዛናና ሳይዛና የተቆረቆረው ዋሻ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ይገኛል፡፡ በጣሊያን ወረራ ጊዜ በፈንጂ ተመቶ ቢፈርስም ጥንታዊነቱ እንደተጠበቀ ነው፡፡ አንድ የለስላሳ ፋብሪካና ቦርን ፍሪ የእንስሳት ማቆያን የልጆቹን ሁኔታ ገልፀን ክፍያው እንዲቀነስልን በማድረግ ጎብኝተዋል፡፡ ለ150 ልጆች 7,500 ብር ወጪ ያስወጣ የነበረውን የኢትዮጲስ ዝግጅት ልጆቹ በነፃ እንዲገቡ ለማድረግም ተችሏል፡፡ ልጆቹ ማንም የለንም የሚል ስሜት እንዳይሰማቸውና ማኅበረሰቡ ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ጋር አብረው መሄድ እንዲችሉ ለማድረግ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የሕፃናቱ ቤተሰቦች ሕይወታቸውን እንዲለውጡ ስለምትሰጧቸው ሥልጠናዎች ቢገልጹልን?
አቶ ካሌብ፡‑ በተደጋጋሚ የቤት ሥራ የማይሠሩ ልጆችን ቤተሰቦች ምክንያቱን ስንጠይቃቸው ባለመማራቸው ልጆቻቸውን በትምህርት መርዳት እንደማይችሉ ይገልጹልናል፡፡ ከመምህራኑ ጋር በጋራ በመመካከር ለቤተሰቦች መሠረታዊ ትምህርት መስጠት ጀመርን፡፡ ከቤተሰቦቹ ጥሩ ምላሽ ስናገኝ ቦሌ ክፍለ ከተማ እናቶቹን እንዲያሠለጥንልን ድጋፍ ጠየቅን፡፡ በመጀመሪያው ዙር የትራንስፖርትና የትምህርት ቤት ክፍያ ችለን 14 እናቶች ሠለጠኑ፡፡ ከዛ በኋላ ወደ 42 እናቶች በምግብና ፀጉር ሥራ እንዲሠለጥኑ ተደረገ፡፡ ሻል ያለ ትምህርት ያላቸው እናቶች ደግሞ የኮምፒዩተር ትምህርት እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ ሥልጠናው ዘላቂነት ያለው ሥራ አግኝተው ቤተሰባቸውን እንዲደግፉ ለማድርግ ያለመ ነበር፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው እንዲሠሩ ለማድረግ የሞከርናቸው ሙከራዎች ባይሳኩም ጥረታችንን ቀጥለንበታል፡፡ ሪፖርተር፡- የድርጅቱ መሥራቾች በዕርዳታ ድርጅቶች ከማደጋችሁ አንፃር በጎ አድራጎታችሁን እንዴት ትገልጸዋለህ?
አቶ ካሌብ፡‑ አንዳንዴ ተስፋ ስቆርጥ ባለቤቴ ይህን ሥራ ለምን አትተወውም ትለኛለች፡፡ ነገር ግን መልካም እንቅልፍ የማገኘው ይህንን የበጎ አድራጎት ሥራ በመሥራት ነው፡፡ ብዙ ፈታኝ ነገሮች ቢኖሩትም፣ ልጆቹ መንገድ ላይ መጥተው ሲያቅፉኝ የሚሰማኝን ደስታ የሚያክል ነገር የለም፡፡ ቁሳቁስ ያልፋል፣ ልጆቹ ግን ስማችንን ያስጠራሉ፡፡ የድርጅቱ መሥራቾች ደከመን ሰለቸን ሳይሉ በመሥራታቸው ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ፡፡ የበጎ አድራጎት ሥራዎች በዙ የሚሉ አሉ፡፡ ካለው ችግር ስፋት አንፃር ግን ምንም አልተጀመረም፡፡ ባለፈው የትምህርት ሚኒስቴር ስብሰባ ጠርቶን በሰጠን መረጃ መሠረት ከ30,000 በላይ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው፡፡ የዕርዳታ ድርጅቶች እነዚህን ክፍተቶች ይሸፍናሉ፡፡ ኢትዮጵያ እንደምትቀየርና ከድህነት ወለል በታች የሆነ ኑሮ እንደሚለወጥ እናምናለን፡፡ ይህ ዕውን የሚሆነው አንዱ ሌላውን ሲደግፍ ነው፡፡