– ሁዋዌ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ድርሻውን ለማስከረብ ተጀጋጅቻለሁ ይላል
በ1.6 ቢሊዮን ዶላር የማስፋፊያ ሥራው ሲካሄድ የቆየው የቴሌኮም ኔትወርክ ማስፋፊያ ተጠናቆ ይፋዊ የርክክብ ሒደቱ እየተጠበቀ ነው፡፡ የተካሄደው የቴሌኮም ኔትወርክ ማስፋፊያ ሥራ ከዚህ ቀደም የነበረውን የ20 ሚሊዮን ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም ወደ 80 ሚሊዮን መድረሱም ይነገርለታል፡፡
የመላ አገሪቱን የሞባይል ኔትወርክ ስርጭት በ3G እንደሚያዳርስ እንደ አዲስ አበባ ባሉት ዋና ዋና ከተሞችም የሞባይል ሥርጭቱ ወደ 4G ማደጉ በሚነገርበት በዚህ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ምላሽ የሚሹ የኔትወክር ጥራትና የዋጋ ጥያቄዎች የኢትዮ ቴሌኮምን ምላሽ ይሻሉ፡፡
በአዲስ አበባም ሆኑ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ አካባቢዎች የተዘረጋው የኔትወርክ መስመር ከጥራት አኳያ አሁንም ገና መሻሻል ያለበት እንደሆነ በግልና በመንግሥት ተቋማት እንዲሁም በግለሰብ ተጠቃሚዎች የሚነሳው ቅሬታ አለመቆሙ አንዱ አመላካች ነው፡፡
ከአራት ዓመት በፊት የማስፋፊያ ሥራው የተጀመረው የኔትወርክ ፕሮጀክት በሁለት እያንዳንዳቸው 800 ሚሊዮን ዶላር በወሰዱ ሁለት የቻይና ኩባንያዎች ሲካሄድ መቆየቱ፣ በመሃል ግን የስዊድኑ ኤሪክሰን ኩባንያ እንደተቀላቀላቸው ይታወቃል፡፡
ይሁንና በተለያየ ምክንያት የኔትወርክ ዝርጋታ ሥራቸውን አጓተውብኛል ያላቸውን ዜድቲኢና ኤሪክሰን የያዟቸውን የተለያዩ የኔትወርክ ፕሮጀክቶች ከአንዱ እየነጠቀ ለሌላኛው ሲሰጥ የቆየው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በአሁኑ ወቅት ግን በመላ አገሪቱ ሲካሄድ የቆየው የኔትወርክ ዝርጋታ በአብዛኛው በመጠናቀቁ ርክክብ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩን አስታውቋል፡፡ ከቀናት በፊት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ እንዲሁም የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረጽዮን ወልደሚካኤል የተመሩ በርካታ የውስጥ ስብሰባዎች ሲካሄዱ ሰንብተዋል፡፡ ዶ/ር ደብረጽዮን ከመሯቸው ስብሰባዎች ባሻገር በየሥራ ዘርፉ የተመደቡ ሠራተኞችንም የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ አንዷለም አድማሴ ሲመሩ መሰንበታቸው ታውቋል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን በተጠናቀቀው የኔትወርክ ግንባታ ላይ በብዛት የተሳተፈው ሁዋዌ ቴክኖሎጂስ፣ አብዛኞቹን ኔትወርክ የዘረጋባቸውን ቦታዎች በማጠናቀቁ ለማስረከብ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ የሁዋዌ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጆን ሹ ለሪፖርተር እንዳብራሩት ከሆነ፣ የሁዋዌ ድርሻ የሆኑ የኔትወርክ ሥራዎችን ለማስረከብ ጥቂት የማጠናቀቂያ ሥራዎች ብቻ ይቀራሉ፡፡
ከተጠናቀቀው የኔትወርክ ማስፋፊያ በተጓዳኝ ተጨማሪ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ይፋ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው አዲሱ ማስፋፊያ የተያዘለት በጀትም ሆነ ስፋቱ ምን ያህል እንደሆነ ኢትዮ ቴሌኮም ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡ ይሁንና 14 ያህል ኩባንያዎች በጨረታው ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸውን አቶ አንዷለም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ተጫራቾች ያስገቡት ሰነድ እየታየ፣ የቴክኒክ ምዘና ሒደት ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶቹን አጠናቆ እንደሚያስረክብ ያስታወቀው ሁዋዌ፣ ከኔትወርክ ዝርጋታ ጎን ለጎን ‹‹ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር›› በተሰኘው መርሐ ግብሩ አንድ ሺሕ አፍሪካውያንን ወደ ቻይና ልኮ ለማሠልጠን የወጠነው ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያንን እያሳተፈ ይገኛል፡፡ እስካሁን 50 ተማሪዎችን ከኢትዮጵያ በመውሰድ፣ ዋና መሥሪያ ቤቱ በሚገኝባት ሼንዘን ከተማ በመላክ የሁለት ሳምንት ጉብኝትና የሥልጠና ዕድል እንዲያገኙ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ባለፈው ሳምንትም 12 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካል የሆነው የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተማሪዎችን ወደ ቻይና በማቅናት ሥልጠናቸውን ተከታትለው መመለሳቸውን በማስመልከት ዝግጅት ተካሂዶ ነበር፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ይህ መርሐ ግብር፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ባልደረቦችንም አሳትፏል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት 30 የኮሚሽኑ ሠራተኞች ወደ ቻይና አቅንተው ተመልሰዋል፡፡
ሁዋዌን ጨምሮ ከ500 በላይ የቻይና ኩባንባዎች በኢትዮጵያ እንደሚንቀሳቀሱ ያስታወቀው፣ የቻይና የንግድና የኢኮኖሚ ቆንስላ፣ ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጋቸውንም ቆንስላዋ ሊ ዩ ለሪፖርተር ከሰጡት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተማሪዎች ከቻይና ሥልጠናቸውን ጨርሰው መምጣታቸውን በማስመልከት በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ ተገኝተው ነበር፡፡ ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ ሁዋዌ በኢንፎርሜሽንና መገናኛ ዘርፍ ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠውን ድጋፍ እንዲያጠናክር፣ ማኅበራዊ ኃላፊነቱንም ይበልጥ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ኤክዚኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ኢሳይያስ ገብረ ዮሐንስ በበኩላቸው፣ የአይሲቲ የልቀት ማዕከል በኢንስቲትዩቱ ለመክፈት ሁዋዌ እንዲተባበር ጠይቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ በባቡር፣ በመንገድ፣ በሎጂስቱክ፣ በኢነርጂና በመሳሰሉት መስኮች ላይ በማተኮር የልቀት ማዕከል እያስፋፋ እንደሚገኝ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በተለይ በቅርቡ የአፍሪካ ልማት ባንክ በሰጠው የስድስት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በምሥራቅ አፍሪካ የባቡር ቴክኖሎጂ ላይ ሥልጠና የሚሰጥ ማዕከል ለመክፈት መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡ በጥቂት ወራት ውስጥ ሥልጠና መስጠት የሚጀምረው፣ የባቡር ቴክኖሎጂ የልቀት ማዕከል በዓመት ከ20 እስከ 25 ሠልጣኞችን ይቀበላል ብለዋል፡፡