Saturday, December 9, 2023

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንትና የቀድሞ ምክትላቸው ከጦርነት አትራፊ መሆናቸው በሪፖርት ይፋ ሆነ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና የቀድሞ ምክትላቸው ዶ/ር ሪክ ማቻር ከሥልጣን ጋር በተያያዘ ምክንያት ከተጋጩ፣ ግጭቱም ብሔርን መሠረት ካደረገ ሁለት ዓመት አልፎታል፡፡

በዚህ ከሁለት ዓመት በላይ በተደረገው ውጊያ በአሥር ሺሕ የሚቆጠር ሰላማዊ ሕዝብ አልቋል፡፡ ሚሊዮኖች ቆስለዋል፣ ተገርፈዋል፣ ተደፍረዋል እንዲሁም ተርበዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተሰደዋል፡፡ በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብት፣ ንብረትና የሰብል ውድመት እንደደረሰም በተለያዩ ወቅት የወጡ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡

አገሪቱ ከገባችበት ቀውስ ትወጣ ዘንድ የአካባቢው አገሮች፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የመሩዋቸው በርካታ ድርድሮችና ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ የውይይቶቹ ውጤቶች ግን ፍሬ ያፈሩ አይደሉም፡፡

ከበርካታ ወራት ድርድር በኋላ ወደ ርዕሰ መዲናዋ ጁባ ተመልሰው የምክትል ፕሬዚዳንትነት ሥልጣኑን ዳግም ይዘው የነበሩት ዶ/ር ሪክ ማቻር ዳግም አገሪቷን ለቀው ወጥተዋል፡፡ በምትካቸውም ጄኔራል ታባን ዴንግ የምክትል ፕሬዚዳንትነት መንበሩን ተቆናጠዋል፡፡

በመከራዎችና በሕዝቡ እንግልት የተሞላችው ደቡብ ሱዳን ካላት ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ክምችትና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብት አንፃር፣ የመሪዎቿ መከፋፈልና አለመስማማት ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በቅጡ እንዳትጠቀም አድርጓታል፡፡

ምንም እንኳን አብዛኛው የአገሪቱ ዜጋ ከአገሪቱ የተፈጥሮ ሀብትና ነዳጅ ከሚገኘው ጥቅም ተጠቃሚና ተቋዳሽ ባይሆንም፣ መሪዎቹ ለግል ጥቅማቸው የአገሪቷን ሀብት እንዳዋሉ የሚጠቅሱ በርካታ ሪፖርቶች ወጥተዋል፡፡

በታዋቂው አሜሪካዊ የፊልም ባለሙያ ጆርጁ ክሉኒና አጋሮቹ ድጋፍ የተከናወነ የጥናት ሪፖርት በዚህ ሳምንት ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ በሪፖርቱም የአገሪቱ ፕሬዚዳንትና የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት የጦርነቱ ዋነኛ ተጠቃሚ እንደሆኑ ይፋ አድርጓል፡፡

‹‹ምንም እንኳን አገሪቷና ዜጐቿ እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ተጐጂዎችና የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሾች ቢሆኑም፣ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካና የመከላከያ ልሂቃን ግን በጦርነቱ ራሳቸውን ሀብታም አድርገዋል፤›› ይላል ሪፖርቱ፡፡

ጆርጅ ክሉኒ በጋራ በመሠረተው ዘ ሴንቸሪ በተሰኘ የምርመራ ቡድን የተከናወነው ጥናት ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደ ሲሆን፣ በርካታ ማስረጃዎችንና የምስክርነት ቃል መሰብሰቡን ገልጿል፡፡

ሪፖርቱ ከወጣ በኋላ በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ተቆርቋሪ እንደሆነ የሚነገርለት ጆርጅ ክሉኒ፣ ‹‹ማስረጃዎቹ የተብራሩና ሊካዱ የማይችሉ ናቸው፤›› በማለት የሪፖርቱን ጥንካሬ ገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በዚህ ዓመታት በፈጀው ጦርነት ተጠቃሚ የሆኑት የአገሪቷ መሪዎች በሕገወጥ መንገድ ሀብት ለማጋበስ በሚያደርጉት ጥረት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ባንኮች፣ ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች፣ እንዲሁም የሪል ስቴት ተቋማት ተሳትፎ እንደነበራቸውም ጆርጅ ክሉኒ አስረድቷል፡፡

መሪዎቿ ከአገሪቷ የመዘበሩትን ገንዘብ ተከታዮቻቸውን ለማስታጠቅ እንደሚጠቀሙበትም ተመልክቷል፡፡ ‹‹ከአሁኑ ዕርምጃ መውሰድ አለብን፡፡ ይህን ካላደረግን በመጪዎቹ አሠርት ዓመታት የሚፈጠረውን ችግር ማዳፈን ላይ እንሠራለን፤›› በማለት ክሉኒ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

የሪፖርቱ ግኝቶች

“War Crimes Shouldn’t Pay” በሚል ርዕስ ይፋ የተደረገው ሪፖርት የአገሪቷ መሪዎችና የጦር ጄኔራሎች በአገሪቷ ለተፈጠረው የሕዝብ ዕልቂትና ውድቀት ተጠያቂ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ከሚያገኙት መካከለኛ የመንግሥት ደመወዝ አንፃር ከፍተኛ የሆነ ሀብት ከአገሪቷ ጦርነት በትርፍ አጋብሰዋል በማለት ይኮንናል፡፡

የአገሪቷ የፖለቲካና የመከላከያ ልሂቃን ከእርስ በርሱ ጦርነት ተጠቃሚ የሆኑት የተወሰኑት ራሳቸው ከፍተኛ የንግድ ድርድር ውስጥ በመግባት በንግድ በመሰማራት ሲሆን፣ የተወሰኑት ደግሞ መቀመጫቸውን ደቡብ ሱዳን ካደረጉና የተለያዩ ሥራዎችን ከሚሠሩ ኩባንያዎች በሚፈጸምላቸው ክፍያ አማካይነት እንደሆነ ሪፖርቱ ይፋ ያደርጋል፡፡

ሥልጣናቸውን መከታ አድርገው የአገሪቱን ሀብት እየዘረፉ ነው የሚለው ሪፖርቱ፣ የአገሪቷን ከፍተኛ የሆነ ሀብት ለመቆጣጠርና ለግል ጥቅም ለማዋል የሚደረገው ሽኩቻ የአገሪቷን የእርስ በርስ ጦርነት ለማፋፋም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሆነም ይገልጻል፡፡

ከፍተኛ የሆነ የሀብት ትስስር (ኔትወርክ) እንደተፈጠረ የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ ሁለቱ ተቃራኒ መሪዎች ከጀርባቸው የብሔር ማንነትን መጠጊያ በማድረግና የጦር ነጋሪት በመጐሰም ለሥርዓቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የጦር ጄኔራሎች የገቢ ምንጭ አድርገውታል በማለት ይፋ አድርጓል፡፡

አብዛኛዎቹ የባለሥልጣናቱ ሀብቶች ምንጭ በውጭ አገር የሚገኙ ውድ ዋጋ የሚያወጡ ንብረቶች፣ የግልና የመንግሥት ንብረት የሆኑ በርካታ ተቋማትን በባለቤትነት መያዝና ከነዳጅ ሽያጭ ውል የሚገኙ እንደሆነ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና የዶ/ር ሪክ ማቻር ቤተሰቦች የሚኖሩት ከደቡብ ሱዳን ውጪ እንደሆነ በመግለጽ፣ ሁለቱ ተፃራሪ ወገኖች በኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ አፕማርኬት በተባለ የመኖሪያ ሠፈር ውስጥ የሚኖሩበት ቅንጡ የመኖሪያ ቤቶች እንዳሉዋቸው ያትታል፡፡    

የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የ12 ዓመት ወንድ ልጅ በአንድ የአክሲዮን ድርጅት ውስጥ የ25 በመቶ ድርሻ እንዳለው፣ ሌሎች ሰባት የፕሬዚዳንቱ ልጆችና ባለቤታቸው ቀዳማዊ እመቤት ሜሪ አየን ማያርዲት በበርካታ ዘርፎች የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንደሚሳተፉና ጠቀም ያለ ድርሻ እንዳላቸው ይኼው ሪፖርት ይገልጻል፡፡

ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች ይህን ሥልጣንን መሠረት ያደረገውን የአገሪቷን ሀብትና ንብረት መቀራመት ሥርዓት በማደራጀት መሳተፋቸው በሪፖርቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ሌሎቹ ዓለም አቀፍ ተዋናዮችም እየተካሄደ ካለው የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ግጭት ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ይፋ አድርጓል፡፡

‹‹ጥቂት ግለሰቦች የደቡብ ሱዳንን ኢኮኖሚ ተቆጣጥረውት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ጥቂት ሰዎች ደግሞ በአገሪቷ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እየተሳተፉ የሚገኙና ዋነኛ ተዋናዮች ናቸው፤›› በማለት የሪፖርቱ ጸሐፊ ጅንየር ማይሌይ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሪክ ማቻር በሩሲያ ደላሎች አማካይነት ከዩክሬን መሣሪያ አምራቾች ጋር መደራደራቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

‹‹ከዶ/ር ሪክ ማቻር ጋር በተያያዘ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ነዳጅ በመሸጥ መሣሪያ ለመግዛት ተደራድረዋል፤›› በማለት ጸሐፊው ይፋ አድርገዋል፡፡

በሪፖርቱ ከተካተቱት ዝርዝር ማስረጃዎች ውስጥ ከሚገኙ ፎቶግራፎች ውስጥ የፖለቲከኞቹና የጄኔራሎቹ መኖሪያዎች እንደሆኑ የሚያሳዩ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በኡጋንዳና በአውስትራሊያ የሚገኙ ቅንጡ ቪላዎች ይገኛሉ፡፡

የአገሮቹ መሪዎችና የጦር ጄኔራሎች የአገሪቷን ሀብትና ንብረት ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው በተደጋጋሚ እየተገለጸ ባለበት ወቅት፣ በተመድ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) አገሪቷ ለአስከፊ የምግብ እጥረት የተጋለጠች መሆኗን አስታውቋል፡፡

እንደ ድርጅቱ አኃዝ ከሆነ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ አምስት ሚሊዮን ዜጐች ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ካልተረጋጋና ግጭቶች የሚቀጥሉ ከሆነ ለምግብ እጥረት የሚጋለጡ ዜጐች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡

በእንቅርት ላይ … እንዲሉ በአገሪቱ ዳግም በተቀሰቀሰው ጦርነት በመንግሥትና በተቃዋሚዎች መካከል በተከሰተው ግጭት በግምት 30 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የዕርዳታ እህል፣ ከሁለት የተመድ ተቋማት መዘረፉን ድርጅቱ በተጨማሪ አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ12,000 በላይ የሰላም አስከባሪ ኃይል በደቡብ ሱዳን የተሰማራ ሲሆን፣ በቅርቡ ዳግም ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ተመድ ተጨማሪ 4,000 ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሰማራ ወስኗል፡፡

ምንም እንኳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር መጀመሪያ ላይ ውሳኔው ሉዓላዊነትን መጣስ ነው በማለት ተጨማሪ ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ደቡብ ሱዳን እንደማይገባ ተቃውመው የነበሩ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ግን ስምምነታቸውን በመግለጻቸው ተጨማሪ 4,000 ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ አገሪቱ እንደሚገባ መተማመኛ ተገኝቷል፡፡

ተመድ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው በአገሪቱ ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት እያደረሰ ካለውና ሊያደርስ ከሚችለው የከፋ ቀውስ ለመታደግ እንደሆነ አስታውቋል፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -