Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግል የባንኮች የተበላሸ የብድር መጠን እየወረደ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ ባንኮች የብድር ክምችት ከ232 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል

በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የግል ባንኮች የተበላሸ ብድር መጠናቸው ዝቅ እያለ በመምጣት፣ በ2008 በጀት ዓመት 2.8 በመቶ ደረሰ፡፡

የግል ባንኮቹን የተበላሸ ብድርና መጠን የሚያመለክቱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በበጀት ዓመቱ በአማካይ የተመዘገበው የተበላሸ የብድር መጠን ወደ 2.8 በመቶ አካባቢ ሲደርስ፣ ባንኮች የተበላሸ ብድር መጠናቸው እየቀነሰ መምጣቱንና የብድር አሰጣጣቸውንም ጤናማነት እየተሻሻለ መሄድ ያመለክታል ተብሏል፡፡

አሥራ ስድስቱ የግል ባንኮች ባለፈው ዓመት የተመዘገበው የተበላሸ የብድር መጠናቸው 3.4 በመቶ ስለነበር፣ ዘንድሮ የታየው ለውጥ መልካም መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተበላሸ የብድር መጠን ከአምስት በመቶ በላይ መብለጥ እንደሌለበት የሚደነግግ ሲሆን፣ ከተጠቀሰው መጠን በላይ ከሆነ ግን የባንኩን የሥራ ኃላፊዎች የሚጠይቅበት አሠራር አለ፡፡ ለብሔራዊ ባንክ በየሩብ የበጀት ዓመቱ የተበላሸውን ብድር የሚያመለክት ሪፖርት መቅረብ ይኖርበታል፡፡ የተበላሸውን የብድር መጠን በሚሰጣቸው የጊዜ ገደብ ከአምስት በመቶ በታች ማድረስ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ግን አስተዳደራዊ ዕርምጃ በባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ሊወስድ ይችላል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን በተበላሸ የብደር መጠናቸው ልክ ባንኮች መጠባበቂያ እንዲይዙ ይገደዳሉ፡፡ መመለስ ባለበት ጊዜ ያልተመለሰ ብድር እንደቆየበት ጊዜ ተሰልቶ በተበላሸው ብድር መጠባበቂያ መቀመጡን ብሔራዊ ባንክ ያረጋግጣል፡፡ ለምሳሌ ብድሩ ሳይመለስ 365 ቀናት ከቆየ ሳይመለስ የቀረውን ብድር ያህል ባንኮቹ መጠባበቂያ መያዝ እንዳለባቸው የብሔራዊ ባንክ መመርያ ያስገድዳቸዋል፡፡

በጥቅል ሲታይ የ16ቱ የግል ባንኮች አማካይ የተበላሸ የብድር መጠን 2.8 በመቶ ይድረስ እንጂ፣ በተናጠል ሲታይ አንድ ባንክ የግል የተበላሸ የብድር መጠኑ ከአምስት በመቶ በላይ ሆኗል፡፡ ሌላ አንድ ባንክ ደግሞ የተበላሸ የብድር መጠኑ 4.7 በመቶ ሲሆን፣ ዘጠኝ ባንኮች ደግሞ የተበላሸ የብድር መጠናቸው ከሁለት እስከ 3.8 በመቶ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

አራት ባንኮች ግን የተበላሸ የብድር መጠናቸው ከሁለት በመቶ በታች ነው፡፡ እንዲሁም አንድ ባንክ የተበላሸ የብድር መጠኑ ከአንድ በመቶ በታች 0.6 በመቶ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የተበላሸ ብድር መጠን ጎልቶ የሚታየው በመንግሥታዊ ባንኮች ላይ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከ11 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡ ሆኖም ይህንን በ2009 ዓ.ም. ወደ ስምንት በመቶ ለማውረድ የሚያስችለውን ሥራ እንደሚሠራ የ2009 በጀት ዓመት ዕቅዱን በተመለከተ በቅርቡ በወጣው ሪፖርት ላይ አመልክቷል፡፡

የአገሪቱ ባንኮች በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የብድር ክምችታቸው መጠን ከ232 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡

ሁሉም የመንግሥትና የግል ባንኮች በ2008 በጀት ዓመት መዝጊያ ላይ የነበራቸው የብድር ክምችት 217.2 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች