Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት አራት ኃላፊዎች ክስ እንዲሻሻል ትዕዛዝ ተሰጠ

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት አራት ኃላፊዎች ክስ እንዲሻሻል ትዕዛዝ ተሰጠ

ቀን:

  • ቀሪዎቹ ኃላፊዎች የእምነት ክህደት ቃል ሰጡ

የመንግሥትን ሥልጣን በማያመች አኳኋን በመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ የቀረበባቸው የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አራት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ክስ ዓቃቤ ሕግ አሻሽሎ እንዲያቀርብ፣ ፍርድ ቤት ሰኞ ታህሳስ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

ክሳቸው እንዲሻሻልና ተነጥሎ እንዲቀርብ ትዕዛዝ የተሰጠው፣ የድርጅቱ የጭነት ማስተላለፍ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ተፈራና የኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ አባፈርዳ ላይ በጋራ የቀረበው ክስ ላይ ነው፡፡

በሁለቱ ተከሳሾች ላይ በጋራ የቀረበው ክስ በአራት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ማለትም ከኮሜት፣ ከበከልቻ፣ ከዕለት ደራሽ ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበራትና ከባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በድምሩ 280 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ግዢ ጋር በተገናኘ ሁለቱ ኃላፊዎች፣ 7,546,500 ብር በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል የሚል መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ተከሳሾቹ በጠበቆቻቸው አማካይነት ባቀረቡት የቅድመ ክስ መቃወሚያ እንዳብራሩት፣ በተከሳሾቹ (ደንበኞቻቸው) ክስ ላይ የተጠቀሰው የሕግ ድንጋጌ ሌላ ሆኖ ሳለ፣ የክሱ ድምዳሜ የሚለው ግን ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ነው፡፡ ለመልካም አፈጻጸም የተያዘው 457,264.58 ዩሮ ወይም 10,601,313 ብር በድርጅቱ ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፊንፊኔ ቅርንጫፍ ገቢ መደረጉን የሚገልጽ ሰነድ ዓቃቤ ሕግ ከፌዴራል ፖሊስ ወስዷል፡፡ ገንዘቡ ተሽከርካሪዎቹን ከሚያቀርበው ድርጅት ለመልካም አፈጻጸም የተያዘ ሲሆን፣ በቀረበለት ዝርዝር መሥፈርት መሠረት ላቀረበበት በልዩነት ለመንግሥት 3,054,813 ብር ገቢ ተደርጎ እያለ 7,546,500 ብር ጉዳት ደርሷል መባሉ ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩል የሁለቱ ተከሳሾች የጥፋት ወይም ድርጊት ተነጥሎ መቅረብ ሲገባው ተጣምሮ እንዲከሰሱ መደረጉ ጊዜ የሚወስድና የተፋጠነ ፍትሕ እንዳያገኙ ስለሚያደርግ፣ ተነጥሎ ሊቀርብ እንደሚገባ በቅድመ ክስ መቃወሚያቸው አመልክተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግም በመልሱ እንደገለጸው ተከሳሾች ያቀረቡት መቃወሚያ ተገቢ እንዳልሆነ፣ የሕግ አንቀጽ ሲጠቀስ በስህተት መጠቀሱንና ሌላው ክርክር በማስረጃና ምስክሮች ከማረጋገጥ በስተቀር ሊሻሻልም ሆነ ሊነጠል የሚችልበት አግባብ አለመኖሩን ጠቅሶ መቃወሚያው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን እንዳብራራው፣ ተከሳሾች ያቀረቡትን የቅድመ ክስ መቃወሚያና የዓቃቤ ሕግን ምላሽ ከተገቢው ሕግ ጋር በማድረግ መርምሯል፡፡ ሁለቱ ተከሳሾች የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ወይም አላደረሱም የሚለው በማስረጃ የሚጣራ በመሆኑ መቃወሚያውን እንዳልተቀበለው አስታውቋል፡፡  

ነገር ግን የክሱ መደምደሚያ ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል መባሉ፣ ከተጠቀሰው የሕግ ድንጋጌ ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ ክሱ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 119(1) መሠረት ተሻሽሎ እንዲቀርብ ብይን ሰጥቷል፡፡ ለተፋጠነ ፍትሕ አሰጣጥ ይረዳ ዘንድ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 117(2) መሠረት የአቶ መስፍንና የአቶ ሲሳይ ክስ ተነጥሎ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ከድርጅቱ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል አከባበር የተለያዩ ግዥዎች ጋር በተገናኘ ከ1,458,217 ብር በመንግሥትና ሕዝብ ላይ ጉዳት ማድረስ የሙስና ክስ የተመሠረተባቸው፣ የድርጅቱ የጂቡቲ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ሲራጅ አብዱላሂም በጠበቃቸው አማካይነት የቅድመ ክስ መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡ ጉዳት መድረስ አለመድረሱ በማስረጃ የሚጣራ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በመግለጽ መቃወሚያውን አልተቀበለውም፡፡ ነገር ግን በተከሳሹ ላይ የቀረበው ክስና ማስረጃ ከሌሎች ክሶችና ተከሳሾች ጋር የሚያጣምረው ነገር በሌለበት ሁኔታ፣ በአንድ ላይ መቅረብ ስለሌለበት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 117(2) መሠረት ነጥሎ እንዲያቀርብ ለዓቃቤ ሕግ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

በድርጅቱ ላይ 65,594,160 ብር ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ተብለው ክስ የተመሠረተባቸው የድርጅቱ ሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቺፍ ኢንጂነር አለሙ አምባዬ ናቸው፡፡ እሳቸውም እንደ ሌሎቹ ተከሳሾች የመጀመርያ የክስ መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡ የተጠቀሰው ጉዳት እውነት ነው ወይስ አይደለም የሚለው በማስረጃ የሚጣራ በመሆኑም፣ መቃወሚያቸውን እንዳልተቀበለው ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ነገር ግን የቀረበባቸው ክስና ማስረጃዎች ከሌሎች ተከሳሾች ማስረጃዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው ጠቁሞ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 117(2) መሠረት ዓቃቤ ሕግ ክሱን ነጥሎ እንዲያቀርብ ታዟል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የሚሻሻሉትን ክሶች በማሻሻልና የሚነጠሉትን በመነጠል ለሐሙስ ታህሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል፡፡፡ የቀረቡት የቅድመ ክስ መቃወሚያዎች ሙሉ በሙሉ ውድቅ የተደረገባቸው የድርጅቱ የወደብና ተርሚናል አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ደሳለኝ ገብረ ሕይወት፣ የየብስ ወደቦች ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ መምርያ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ተናገር ይስማውና የፋይናንስና አካውንትስ መምርያ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ሳሙኤል መላኩ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ድርጊቱን መፈጸም አለመፈጸማቸውን ፍርድ ቤቱ ጠይቋቸው፣ ሁሉም ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምንም፣ ጥፋተኛም አይደለንም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ተከሳሾቹ ክደው የተከራከሩ በመሆናቸው፣ ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ ያስረዱልኛል ያላቸውን ምስክሮች ከየካቲት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲያሰማ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ