በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የማይገባውን ቦታ ይዞ እየሠራ የሚገኝ ማንኛውም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛ ራሱን እንዲያጋልጥ የተሰጠው የጊዜ ገደብ፣ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ተራዘመ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃይል ልማት ቢሮ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ ማንኛውም በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እየሠራ የሚገኝ ኃላፊና ሠራተኛ፣ ከኅዳር 10 ቀን 2010 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ራሱን እንዲያጋልጥ አስጠንቅቆ ነበር፡፡
ነገር ግን በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ራሳቸውን ያጋለጡ ሠራተኞች ከ20 የማይበልጡ በመሆናቸው፣ ቢሮው ለመጨረሻ ጊዜ ያስቀመጠውን ቀነ ገደብ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ማራዘሙ ከሕዝብ ግንኙነት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዚህ ጊዜ በኋላ በየመሥሪያ ቤቱ የተቋቋሙ ኮሚቴዎች ምርመራ እንደሚጀምሩና በተሰበሰቡ ጥቆማዎች፣ እንዲሁም በሚካሄደው ምርመራ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ በመመርያው መሠረት ያላግባብ የተጠቀመውን ጥቅም እንዲከፍል ይደረጋል፣ በሕጉ መሠረትም ይቀጣል ተብሏል፡፡
ነገር ግን በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሥራ ልምድና የሙያ ብቃት ማስረጃዎችን በመጠቀም፣ በመንግሥት ተቋማት በኃላፊነትም ሆነ በፈጻሚነት እየሠራ የሚገኝ ሠራተኛ ይቅርታ ከጠየቀ በሕግ ከመጠየቅም ሆነ ከሥራ ከመታገድ እንደሚድን ተገልጿል፡፡፡
‹‹አስተዳደሩ ይቅርታ የሚያደርግላቸው ሠራተኞችና ኃላፊዎች ትክክለኛ የትምህርት ማስረጃቸውን አቅርበው በሚመጥናቸው የሥራ መደብ ላይ እንደገና ይመደባሉ፤›› ሲል ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በሥሩ በሚገኙ መሥሪያ ቤቶች በአጠቃላይ ከ105 ሺሕ በላይ ሠራተኞች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከእነዚህ ሠራተኞች መካከል በትክክለኛ የትምህርት ማስረጃ ቦታ የያዙ እንዳሉ ሁሉ፣ በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የማይገባቸውን ቦታ የያዙ መኖራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡
በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የተቀጠሩ ሠራተኞችና ኃላፊዎች፣ በከተማ አስተዳደሩ ለሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑም ተገልጿል፡፡