Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚከሰት ግጭትን መቆጣጠር እንዳልተቻለ ተገለጸ

በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚከሰት ግጭትን መቆጣጠር እንዳልተቻለ ተገለጸ

ቀን:

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣው ግጭት መቆጣጠር እንዳልተቻለ ተገለጸ፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር እሑድ ታኅሳስ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ጅግጅጋ በሚገኘው ጽሕፈት ቤታቸው እንደተናገሩት፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለውን ግጭት መቆጣጠር አልተቻለም፡፡ ከዚህ በፊት ወሰን አካባቢ ግጭት ሲከሰት በቀላሉ በአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች አማካይነት ግፋ ቢል ደግሞ በወረዳና በዞን አመራሮች ይፈታ ነበር ብለዋል፡፡

አሁን የሚከሰት ግጭት ግን ከዚህ በላይ እንደሆነና ከበስተጀርባም ብዙ ተዋንያን እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አንድ ኦሮሞና ሶማሌ ሲጋጭ መላው የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች እንደተጋጩ አድርጎ የማቅረብ ድርጊት እየተለመደ መጥቷል ብለዋል፡፡

- Advertisement -

ከ2010 መግቢያ ጀምሮ በአወዳይና በሌሎች አካባቢዎች እየተፈጠሩ ባሉ ግጭቶች በአንድ ካምፕ ብቻ ከ50 ሺሕ በላይ ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ የሶማሌ ክልል ተወላጆች እንዳሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡ ተፈናቃዮች በሰባት የመጠለያ ካምፖች እንደሚገኙ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ትልልቅ የመንግሥት ኃላፊዎችና ሚዲያዎች ሲያወሩት የነበረው 350 የሶማሌ ተወላጆች ብቻ እንደተፈናቀሉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አቶ አብዲ በተመሳሳይ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ የተፈናቀሉት ግን ከጅግጅጋና ከውጫሌ አካባቢዎች ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁንም ድረስ በጅግጅጋና በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ያለ ሥጋት የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች እንዳሉ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ከዚህ በኋላ በሥጋት እንዳይፈናቀሉ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት ቁርጠኛ ሆኖ እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አቶ አብዲ ኢትዮጵያ ካደገችና ከፈለገችው ግብ ከደረሰች አደጋ ነው ብለው የሚያስቡ የውስጥና የውጭ ኃይሎች የፈጠሩት ግጭት መሆኑን አውስተዋል፡፡ ‹‹ዋናው ጠላታችን ድህነት ነው፡፡ የሶማሌ ጠላቱ ኦሮሞ አይደለም፡፡ የኦሮሞ ጠላቱ ሶማሌ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ከፈለገችው የዕድገት ደረጃ ላይ እንዳትደርስ የማይፈልጉ ፀረ ሰላም ኃይሎች፣ ኪራይ ሰብሳቢዎችና አክራሪዎች አገሪቱ መንገራገጭ እንዲገጥማት ለማድረግ ነው ግጭቱን የፈጠሩት፤›› ብለው፣ ግጭቱን የፈጠሩት በተለይ የሶማሌ ክልልን ዕድገት የማይፈልጉ ኃይሎች እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ትናንት ሶማሌ ክልል እንደ ሁለተኛ ዜጋ በጥርጣሬ ሲታይ ነበር፤›› በማለት አክለዋል፡፡

በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች እያጋጠሙ ባሉ ግጭቶች ሳቢያ የበርካታ ዜጎች ሕይወት ከመጥፋቱ ባሻገር፣ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸው መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ግጭቱን ኮንትሮባንዲስቶች የፈጠሩት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረው ነበር፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ የፌዴራል መንግሥት ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሠራ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በምዕራብ ሐረርጌ ሃዊና ዳሮ ወረዳዎች በድጋሚ በተቀሰቀሰ ግጭት ከ60 በላይ ዜጎች ሕይወት እንዳለፈ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርጊቱን ካወገዙና ከኮነኑ በኋላ ‹‹ጅምላ ጭፍጨፋ›› መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡ አቶ አብዲም ድርጊቱም ጅምላ ጭፍጨፋ ነው ብለዋል፡፡ ከቀውሱ በኋላ በምግብና በውኃ እጥረት የሚሰቃዩ ወገኖች እንዳሉ ጠቁመው፣ ችግሩን ለመፍታት በፌዴራል መንግሥት ዕቅድ ወጥቶ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በድጋሚ ግጭት እንዳይከሰት፣ በሥጋት ዜጎች እንዳይፈናቀሉና ከቀዬአቸው እንዳይሄዱ ለማድረግ የፌዴራል መንግሥቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በፊት በፍርኃት ከክልሉ የወጡ ዜጎችን መለመን ባለመቻላቸው እንደሚቆጫቸው የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በክልሉ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች እንዳይፈናቀሉ የክልሉ መንግሥት ከመላው አመራርና ሕዝብ ጋር እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

‹‹በክልላችን አሁንም ድረስ ባሉት ወረዳዎች ያለ ሥጋት የሚኖሩ ዜጎች እንዳሉ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ ብዙ የኦሮሞ ተወላጆች የንግድ ሥራቸውን ያለ ሥጋት እያከናወኑ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ብዙ የኦሮሞ ተማሪዎች አሉ፡፡ እንዲወጡ ተነግሯቸው እንኳን መውጣት ያልፈለጉ በተለያዩ ወረዳዎችና በፕሬዚዳንት ቢሮም ብዙ የክልሉ ተወላጆች ተቀጥረው እየሠሩ ነው፡፡ ሁለቱም ሕዝቦች በባህል፣ በቋንቋና በእምነት አንድ ናቸው፡፡ አንድነታቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ መንግሥት ቁርጠኛ ሆኖ ይሠራል፤›› ብለዋል፡፡

የሁለቱን ክልሎች ሕዝቦች የሚያራርቁና የሚለያዩ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ወገኖች ተገቢ እንዳልሆኑ ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ አንድ የሆነን ሕዝብ መለያየት ቢፈልጉ እንኳን እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

አሁን እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም በፌዴራል መንግሥት አማካይነት የወጣውን ዕቅድ የክልሉ መንግሥት ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በጊዜያዊነት ችግሩን ለመቅረፍ እየተወሰደ ያለውን ዕርምጃ ከመደገፍ በተጨማሪ፣ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ አሁን ተግባራዊ እየሆነ ያለውን የትጥቅ ማስፈታትና የታጠቁ ኃይሎች ወደ ድንበር አካባቢ እንዳይሄዱ ማድረግን ክልሉ እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር አማካይነት የወጣውን ዕቅድ ሥራ ላይ በማዋልና በመተግበር፣ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል በተከሰተው ግጭት ከ600 ሺሕ በላይ የኦሮሞ ተወላጆች ከሶማሌ ክልል መፈናቀላቸው ይታወቃል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...