Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአዲስ አበባ ሕገወጥ ቦታ ይዘዋል የተባሉ ነዋሪዎች ይዞታቸው ሕጋዊ እንዲደረግ ግፊት እያደረጉ...

በአዲስ አበባ ሕገወጥ ቦታ ይዘዋል የተባሉ ነዋሪዎች ይዞታቸው ሕጋዊ እንዲደረግ ግፊት እያደረጉ ነው

ቀን:

  • የአዲስ አበባ አስተዳደር የተዘጋ ጉዳይ ነው ብሏል

በአዲስ አበባ ከተማ አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ መሬት በወረራ የያዙ ግለሰቦች በመመርያ ተፈቅዶ ሕጋዊ የተደረጉ ቢሆንም፣ ከዚያ በኋላ መሬት በወረራ የያዙ ግለሰቦችም ይዞታቸው ሕጋዊ እንዲደረግ ግፊት እያደረጉ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የማስፋፊያ ቦታ ባላቸው ክፍላተ ከተሞች የሚገኙና በሚመለከተው አካል ሳይፈቀድ ቦታ የያዙ ግለሰቦች፣ በየክፍላተ ከተሞችና ወረዳዎች በመመላለስ መንግሥት ይዞታቸውን ሕጋዊ እንዲያደርግ እየወተወቱ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚያዝያ 1988 እስከ ግንቦት 1997 ዓ.ም. ድረስ በሚመለከተው አካል ሳይፈቀድ መሬት በወረራ የያዙ አካላትን ሕጋዊ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ነገር ግን ከ1997 ዓ.ም. በኋላም እስከ 2004 ዓ.ም. ድረስ በተለይ በስድስቱ ክፍላተ ከተሞች ማለትም ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ የካ፣ ቦሌ፣ ጉለሌና አቃቂ ቃሊቲ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች በሚመለከተው አካል ሳይፈቀድ መሬት በተለያዩ መንገዶች አጥረው የያዙና መኖርያ ቤት የገነቡ በርካታ መሆናቸውን የአስተዳደሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የፌዴራል መንግሥት የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ ያወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 እስከወጣበት ጊዜ ድረስ፣ አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ የተያዙ ቦታዎችን ሕጋዊ ለማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ እስከማርቀቅ ደርሶ ነበር፡፡

ነገር ግን ‹‹ሕገወጦች››ን ‹‹ሕጋዊ›› እያደረጉ መቀጠል አይቻልም በሚል ምክንያት፣ አስተዳደሩ እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ ብቻ መሬት የወረሩ ግለሰቦችን ሕጋዊ ማድረግን መርጧል፡፡

በዚህ ሒደት ግን ከአዲስ አበባ ከተማ ባለአደራ አስተዳደር ጀምሮ በከንቲባ ኩማ ደመቅሳ የሥልጣን ዘመን፣ እንዲሁም አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የከንቲባ ድሪባ ኩማ አስተዳደር አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ የተገነቡ ግንባታዎችን ወጥ ባልሆነ መንገድ ሲያፈርሱ በመቆየታቸው፣ መኖርያ ቤት የፈረሰባቸው እንዳሉ ሁሉ ያልፈረሰባቸውም በብዛት አሉ፡፡

በከተማው ለተፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይህ ፍትሐዊና እኩል አገልግሎት አለማግኘት ጉዳይ አንዱ መገለጫ መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በተለይ አግባብ ባለው አካል ሳይፈቅድ ግንባታ አካሂደው እስካሁን ያልፈረሰባቸው አካላት፣ ይዞታቸው ሕጋዊ እንዲደረግ በተለያዩ መንገዶች ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

የከተማው አስተዳደር ይህንን ጥያቄ ተቀብሎ ምላሽ ለመስጠት ከ1997 ዓ.ም. በኋላ አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ ግንባታ ያካሄዱ ግለሰቦችን መረጃ እንዲሰበሰብ አድርጓል፡፡

ይህ መረጃ ከስድስቱም የማስፋፊያ ቦታ ካላቸው ክፍላተ ከተሞች በመሰብሰቡ፣ በነዋሪዎች ዘንድ የከተማው አስተዳደር እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ ያላግባብ ቦታ የያዙ ግለሰቦችን ‹‹ሕጋዊ›› ሊያደርግ ነው የሚል መረጃ እየተናፈሰ ነው፡፡ ይህ መረጃም በሰፊው እየተናፈሰ በመሆኑ ‹‹ሕገወጥ›› ተብሎ መኖርያ ቤት የፈረሰባቸው ግለሰቦች ጉዳያቸው በድጋሚ እንዲታይ እየጠየቁ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርጋሞ ሀማሞ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ መሬት በወረራ የያዙ አካላት ይዞታቸው ‹‹ሕጋዊ›› እንዲሆን ይጠይቃሉ፡፡

‹‹ፍላጎቱ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስከ 1997 ዓ.ም. ብቻ ያሉትን ለማስተናገድ ወስኖ በሩን ዘግቷል፤›› ሲሉ አቶ ሀርጋሞ አስረድተዋል፡፡

‹‹በእርግጥ አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ መሬት በወረራ የያዙ አካላትን ለማስተናገድ በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ አሠራር የለም፡፡ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ በማስተናገድ ጉዳዩን ዘግተዋል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ‹‹ሕገወጦችን›› ሕጋዊ ያደረገበትን ምክንያት በወቅቱ እንደገለጸው፣ በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች በስፋት የመኖርያ ቤት ግንባታዎች ባለመካሄዳቸው ከችግር አንፃር ያደረገው ነው፡፡

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የቤቶች ልማት በሰፊው እየተካሄደ በመሆኑ፣ ይህንን አሠራር መከተል አግባብ አይደለም በሚል በሩን መዝጋቱ ነው የሚነገረው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...