Friday, May 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ በማኅተም የተደገፈ የውጭ ምንዛሪ ምዝገባ ቁጥር ለአመልካቾች እንዲሰጥ የሚያሳስብ ማስታወቂያ አወጣ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባንኮች በየሳምንቱ የሚያቀርቡትን የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ሪፖርት በየቀኑ እንዲልኩ ታዘዙ

የውጭ ምንዛሪ ጥያቄን በግልጽነት ለማዳረስና ለማስተዳደር በማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሁለት ዓመት በፊት ያወጣውና በየጊዜው ሲያሻሽለው የቆየውን መመርያ በቅርቡ ከማማሻሉም በላይ፣ ይህንኑ መመርያ መሠረት ያደረገና የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ የሚያቀርቡ ደንበኞች ላቀረቡት ጥያቄ በማኅተም የተደገፈ ተራ ቁጥርን ጨምሮ ሌሎች መብቶችና ግዴታዎቻቸውን የሚገልጽ ማስታወቂያ በየባንኮች መለጠፍ ጀመረ፡፡

ብሔራዊ ባንክ ይህንን ማስታወቂያ ከመለጠፉ ቀደም ብሎ ሲያወጣቸው በቆዩ መመርያዎች አማካይነት፣ ባንኮች ከተጠቃሚዎች የሚቀርቡላቸውን የውጭ ምንዛሪ ጥያቄዎች ያለ አድልኦ በግልጽነት እንዲያስተናግዱ የሚያስገድዱ አሠራሮችን ሲያስተዋውቅ ቆይቷል፡፡ በባንኮች በኩል ተፈጻሚ እንዲደረጉ የተፈለጉት መመርያዎች ግን በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ አልሆኑም፡፡ በርካታ ተጠቃሚዎች ለጠየቁት የውጭ ምንዛሪ ጥቂት በማይባሉ ባንኮች ከአድሏዊነት የተላቀቀ ምላሽ ሊያገኙ እንዳልቻሉ ተረጋግጧል፡፡ 

ብሔራዊ ባንክ በባንኮች በለጠፈው ማስታወቂያ መሠረት ማንኛውም ደንበኛ የባንክ ሒሳብ ቢኖረውም ባይኖረውም ለውጭ ምንዛሪ ጥያቄ የመመዝገብ መብት እንዳለው፣ ጥያቄ አቅራቢዎች በመጡበት በማንኛውም የሥራ ሰዓት መመዝገብን ጨምሮ፣ በምዝገባ ወቅት ምንም ዓይነት ገንዘብ ማስያዝ እንደማይጠበቅባቸውና ለምዝገባም ምንም ዓይነት ፕሮፎርማ ወይም የዋጋ መጠን ክልከላ እንደማይደረግ በማስታወቂያው ከተጠቀሱት መብቶች ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ መብቶች ቀደም ብለው በወጡት መመርያዎች ውስጥ የተካተቱ ቢሆንም፣ ለየት ያለ ሆኖ የመጣው ግን ‹‹ምዝገባው እንዳለቀ የምዝገባውን ተራ ቁጥር የሚያሳይና የባንኩ ማኅተም ያረፈበትን ማስረጃ መቀበል መብታችሁ ነው›› የሚለው የማስታወቂያው ክፍል ነው፡፡

ይህንን በማጠናከርም፣ ‹‹የምዝገባ ቁጥሩን በማቅረብ ባንኩ የፈቀደበትን ተራ ቁጥር ያለበትን ደረጃ ማወቅ መብት ነው፡፡ የባንኩ ኮሚቴ የፈቀደውን የውጭ ምንዛሪ፣ መፈቀዱን ካወቃችሁበት ጀምሮ እስከ 15 ተከታታይ ቀናት ድረስ የመጠቀም መብት አላችሁ፤›› የሚል ማስታወቂያ በየባንኩ እየዞሩ የብሔራዊ ባንክ ባልደረቦች ሲለጥፉ እንደነበር ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡ 

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባንክ ባለሙያዎች እንደገለጹት፣ ብሔራዊ ባንክ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች የሚጠየቀው የውጭ ምንዛሪን ያለ አድልኦና ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› ለማስተናገድ በማለት ሲያወጣቸው የቆዩት የግልጽነትና የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር መመርያዎችን በተጨባጭ ተግባራዊ ለማድረግ፣ ጥያቄ ለሚያቀርበው አካል እንዲያውቀው ማስታወቂያ መለጠፉ ለውጥ ሲያመጣ እየታየ ነው፡፡ ሕዝቡ መብቱን በግልጽ እንዲያውቅ የሚያደርግ፣ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄውም ቅድሚያ ለሚሰጣቸው መስኮች ያለ አድልኦ እንዲስተናገዱ ለማድረግ የሚረዳ እንደሆነና በመመርያው መሠረት የሚሠሩ ባንኮችም ከተፅዕኖ የሚያሳርፍ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት ጋር በተያያዘ ጥቂት በማይባሉ ባንኮች ውስጥ ሕገወጥ አሠራሮች ተንሰራፍተው እንደነበር ይነገራል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የተያዙ ወረፋዎችን ማምታታት፣ ወረፋን ለሌሎች አሳልፎ መስጠትና በድርድር መሸጥ፣ ተመዝጋቢው ተራው በቃል ተነግሮት ሲጠባበቅ ቆይቶ ተራ እንደሌለው የሚረዳበት አካሄድ ይታይ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በባንኩ ደንበኛ ካልሆነ በቀር፣ ፕሮፎርማ ካላመጣ፣ የባንኩ ደንበኛ ወይም የሒሳብ ደብተር ያለው ካልሆነ፣ ወዘተ አይስተናገድም የሚሉ አሠራሮች በርካቶችን ሲያስመርሩ የቆዩ ቢሆኑም፣ ብሔራዊ ባንክ ተጠቃሚዎች እንዲህ የሚባል አሠራር እንደሌለ ለሕዝብ ለማሳወቅ በየባንኮቹ ማስታወቂያ መለጠፍ መጀመሩ አግባብ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ይህም ሆኖ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ለሚጠይቁ አካላት ግዴታም አስቀምጧል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሚመዘገቡ ሰዎች የአስመጪነት ፈቃድ፣ ወይም የኢንቨስትመንት ፈቃድ፣ ወይም የኢንዱስትሪ ፈቃድ የማቅረብ ግዴታ አለባቸው፡፡ ከዚህ ባሻገር ለውጭ ባለሀብቶች ትርፍ ለማስተላለፍ፣ ወይም የውጭ አየር መንገዶች ቲኬት ሽያጭ ማስተላለፊያ ለሚጠይቁም በብሔራዊ ባንክ የተፈቀደ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሌላ ባንክ የተመዘገበ ፕሮፎርማ፣ ወይም በሌላ ባንክ ለተመሳሳይ ጥያቄ አለመመዝገባቸውን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ማቅረብን ጨምሮ፣ ምዝገባ ስለማከናወናቸው የሚያረጋግጥ የምዝገባ ቁጥርና የባንክ ማኅተም ያረፈበትን ማስረጃ ማቅረብ የሚሉት በግዴታነት የተቀመጡ መጠይቆች ናቸው፡፡

እነዚህ ሁኔታዎች ተሟልተው ሳለ ጥያቄ አቅራቢዎች መስተናገድ ባይችሉ በአካል፣ በስልክና በጽሑፍ ቅሬታ ማቅረብ የሚቻልባቸውን አሠራሮች እንደዘረጋም ብሔራዊ ባንክ ባሠራጨው ማስታወቂያ አስፍሯል፡፡

ስለማስታወቂያውና ስለውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጡ በብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ክትትልና የመጠባበቂያ ክምችት አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ የኔ ሐሳብ ታደሰን ለማነጋገር ሪፖርተር ሞክሮ በሕዝብ ግንኙነት በኩል ምላሽ ማግኘት እንደሚችል ተገልጾለታል፡፡ ከሕዝብ ግንኙነት ክፍል ማብራሪያ ለማግኘት ተሞክሮ ባይሳካም፣ የባንኩ አዲሱ አካሄድ ለተጠቃሚው እሰየው እንደሆነ ባለሙያዎች ግን ተናግረዋል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ብሔራዊ ባንክ ከሰኞ ታኅሳስ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ባሠራጨው ደብዳቤ፣ ባንኮች በየሳምንቱ ይልኩ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ጠያቂዎች ዝርዝር ሪፖርት፣ በየቀኑ በኢሜይል እንዲልኩ ማዘዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በምክትል የባንኩ ገዥና ዋና የኢኮኖሚ ባለሙያ ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ተፈርሞ ለባንኮች በተሠራጨው ደብዳቤ እንደተገለጸው፣ ባንኮች ስለቀረበላቸው የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ዝርዝር መረጃውን በማጠናቀር በየዕለቱ ለብሔራዊ ባንኩ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም ሆኖ በሰነድ የተጠናቀረ ሪፖርት እንደተመደው በየሳምንቱ መላካቸውን እንዲቀጥሉ ያሳሰበው ብሔራዊ ባንክ፣ በኢሜይል የሚላክለት ሪፖርት ከሐሙስ ታኅሳስ 18  ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በደብዳቤው አስታውቋል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች