Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበታሪክ ነገራ ላይ ያተኮረው የፊልም ፌስቲቫል

በታሪክ ነገራ ላይ ያተኮረው የፊልም ፌስቲቫል

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር 12ኛውን የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል (ኢትዮ ፌስት) መክፈቻ ለማስተናገድ መዘጋጀቱን ከሩቅ የሚታዩት ባነሮች ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሳንኮፋ፣ የታሪክ አተራረክ ጥበብ›› በሚል የሚከናወነውን ፌስቲቫል የሚያስተዋውቁ ፖስተሮች በብሔራዊ አካባቢ በሚገኙ ምሰሶዎች ላይም ተለጥፈዋል፡፡ ከታኅሣሥ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሰባት ቀናት የሚቆየው ፌስቲቫሉ በብሔራዊ ቴአትር የተከፈተው አመሻሽ ላይ ነበር፡፡

በመክፈቻ መርሐ ግብሩ፣ በፌስቲቫሉ ለውድድር የቀረቡ ፊልሞች ተዋውቀዋል፡፡ በዘንድሮው ፌስቲቫል የፊልም ባለሙያዎች እንዲወያዩበት የተመረጠው ርዕሰ ጉዳይም ተገልጿል፡፡ በ12ኛው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል 17 ፊልሞች ተወዳድረው በፌስቲቫሉ መዝጊያ አሸናፊዎቹ ይሸለማሉ፡፡

በመክፈቻው ዕለት አንድ አጭር ፊልምና ከተወዳዳሪዎቹ ፊልሞች አንዱ ‹‹ቀያይ ቀምበጦች›› ታይተዋል፡፡ አጭር ፊልሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢነቱ እየጨመረ የመጣው የአዲስ አበባ መቆሸሽ ጉዳይ ላይ ያጠነጥናል፡፡ ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት ኃላፊነት የተሰጣቸው የመንግሥት ባለሥልጣኖች የችግሩ አካል ሲሆኑም ያሳያል፡፡

በፊልሙ፣ በአንድ ክፍለ ከተማ የፅዳት ክፍል ኃላፊ የሆነ ሰው ወረቀት፣ የሙዝ ልጣጭ፣ የሞባይል ካርድና ሌላም ቆሻሻ በየመንገዱ እየጣለ ወደ ሥራ ገበታው ሲያመራ ይታያል፡፡ ከቤቱ ወደ መሥሪያ ቤቱ ባለው መንገድ በርካታ ቆሻሻ መጣያዎች ቢኖሩም፣ አንዳቸውንም አይጠቀምባቸውም፡፡ እያንዳንዱ የማኅበረሰቡ አካል ከተማዋን ንፁህ በማድረግ ረገድ ምን ያህል ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው? የሚል ጥያቄም ያጭራል፡፡

‹‹ቀያይ ቀምበጦች›› በኢትዮ እስራኤላዊ ፊልም ሠሪ ባዚ ጌቴ የተሠራ ሲሆን፣ መሪ ተዋናዩ ደበበ እሸቱ ነው፡፡ በእሥራኤል የሚኖር ኢትዮጵያዊ አባት ከልጆቹ አመለካከት በተፃራሪው ያለው ምልከታ ከልጆቹ አላግባባ ሲለው የሚያሳይ የቤተሰብ ድራማ ነው፡፡   

ከዚህ ፊልም በተጨማሪ በፌስቲቫሉ የሚወዳደሩት ፊልሞች ‹‹እምቢ››፣ ‹‹የልጅ ሀብታም››፣ ‹‹የእግዜር ድልድይ››፣ ‹‹ጊዜ ቤት››፣ ‹‹እንደ እናት››፣ ‹‹ደስ እንዳለሽ››፣ ‹‹ያምራል ሀገሬ››፣ ‹‹ታዛ››፣ ‹‹አብ ሳላት››፣ ‹‹FBI 3››፣ ‹‹አፄ ማንዴላ››፣ ‹‹እስከ መቼ››፣ ‹‹ከደመና በላይ››፣ ‹‹የት ነበርሽ››፣ ‹‹ኮከባችን›› እና ‹‹ማያ›› ናቸው፡፡

የፌስቲቫሉ አዘጋጅ ይርጋሸዋ ተሾመ እንደሚናገረው፣ ውድድር በሚካሄድባቸው ዘርፎች የሚያሸንፉ ባለሙያዎች አገርኛ የክብር ስም ይሰጣቸዋል፡፡ ውድድሩን ለሚያሸንፍ ምርጥ ተራኪ ፊልም ‹‹ጥቁር አንበሳ››፣ ለምርጥ አዘጋጅ ‹‹ሳባ (ኢትዮጵያዊ) ዓይን››፣ ለምርጥ የፊልም ጽሑፍ ‹‹ግዕዞፒያ››፣ ለምርጥ የሲኒማ ቀርፃ ጥበብ ‹‹ቀስተ ደመና››፣ ለምርጥ ተዋናይት ‹‹ድንቅነሽ›› እና ለምርጥ ተዋናይ ‹‹ድንቅነህ›› የሚሉ ስያሜዎች ይሰጣሉ፡፡ ፊልሞቹ የሚዳኙት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር በተውጣጡ ዳኞች መሆኑም ተመልክቷል፡፡

በፌስቲቫሉ ከተካተቱ ፊቸር ፊልሞች በተጨማሪ አምስት አጭር ፊልሞች ይታያሉ፡፡ በኢትዮጵያውያን ፊልም ሠሪዎች የተዘጋጁት አጭር ፊልሞች ‹‹ስህተታችን››፣ ‹‹ሌላ ሕጋዊ››፣ ‹‹ጣቶቼ››፣ ‹‹እሰጥ አገባ›› እና ‹‹የለውጥ መንገድ›› ናቸው፡፡

በፌስቲቫሉ በተለያዩ የባህል ማዕከሎች የሚቀርቡ ፊልሞችም ይታያሉ፡፡ በናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ፎር ታለንትድ ዩዝ ከሚቀርቡ 12 ፊልሞች መካከል ‹‹ኦገስት ቢች››፣ ‹‹አኮማ››፣ ‹‹ቨርቹዋላይዝድ››፣ ‹‹ቴክ ማይ ኸርት አዌይ›› እና ‹‹ፊሽ ሁክ ኤንድ አይ›› ይገኙበታል፡፡

በፌስቲቫሉ ዘጋቢ፣ አኒሜሽንና ሌሎችም የፊልም ዘውጎች መካተታቸውን አዘጋጁ ይገልጻል፡፡ ከዘጋቢ ፊልሞቹ መካከል ‹‹ሁ አር ዩ ኦክቶበር››፣ ‹‹ላይፍ ኢዝ አዌቲንግ››፣ ‹‹አፍሪካ›› እና ‹‹ዘ ፕሮሚስ›› ይጠቀሳሉ፡፡ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ፊቸርና አጭር ፊልሞችም ይታያሉ፡፡

የሩሲያ ባህል ማዕከል ያቀረበው፣ ‹‹ዋር››፣ የታገቱ እንግሊዛዊ ጥንዶችና ሁለት የሩሲያ ወታደሮችን ታሪክ ያወሳል፡፡ በህንድ ኤምባሲ የቀረበው ‹‹ሜሪ ኮም›› በህንዳዊቷ ቦክሰኛ ሜሪ ኮም ታሪክ ላይ ያጠነጥናል፡፡ በፌስቲቫሉ የተካተቱት 70 ፊልሞች በቫድማስ ሲኒማ፣ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴ፣ በፑሽኪንና ሌሎችም ቴአትር ቤቶች ይታያሉ፡፡

በየዓመቱ የተለያዩ ፊልም ተኮር ርዕሰ ጉዳዮች በፌስቲቫሉ እየተነሱ ውይይት ይደረጋል፡፡ ይርጋሸዋ እንደሚናገረው፣ ዘንድሮ የታሪክ አጻጻፍ ዘዬ የውይይት መነሻ ይሆናል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የፊልም ዘርፍ ከተቀዛቀዘበት ምክንያት መካከል የሚጠቅሰው አብዛኞቹ ፊልሞች ተመሳሳይ ይዘትና አቀራረብ ያላቸው መሆኑን ነው፡፡ ‹‹ብዙዎቹ ፊልሞች አስቂኝ የፍቅር ፊልም ሲሆኑ፣ የታሪክ ነገራቸው የምዕራባውያንን (ዌስተርን ኦርየንትድ) መንገድ የተከተለ ነው፤›› ይላል፡፡  

‹‹የራሳችንን ታሪክ በፊልማችን መንገር ብንጀምር ወደፊት መራመድ እንችላለን፤›› ሲል ይገልጻል፡፡ የአፍሪካዊቷን የወፍ ዝርያ ሳንኮፋ፣ ወደ ኋላ እየተመለከቱ ወደፊት የመብረር ባህሪን በምሳሌነትም ይገልጻል፡፡ የዘንድሮው የፌስቲቫሉ ምልክት የሆነችው ሳንኮፍ ወፍ ወደ ቀደመ ታሪክ በመመልከት የሚሠሩ አገርኛ ፊልሞች እንዲበራከቱ ለማሳሰብ እንደሆነ ያስረዳል፡፡

አብዛኞቹ ፊልም ሠሪዎች ትርፋማነትን በማሰብ ከተደጋገመና ከተሰለቸ የፊልም ይዘትና አቀራረብ ውጪ እንደማይሞክሩ ይገልጻል፡፡ በተለያዩ ማኅበራዊ ርዕሰ ጉዳዮች የሚያተኩሩ ፊልሞችን የተመለከተ ውይይት የሚደረገው አካሄዱን ለማረም መሆኑንም ያክላል፡፡   

‹‹ከቦሊውድ ፊልሞች ምን እንማራለን?›› ከመወያያ ነጥቦቹ አንዱ ነው፡፡ በዓለም ገናና ከሆኑ የፊልም ኢንዱስትሪዎች ተሞክሮ ለመቅሰም ያለመ ነው፡፡ በፌስቲቫሉ ከተካተቱ ፊልሞች መካከል ሳይንስ ፊክሽን፣ ድራማ፣ አክሽንና ሌሎችም ዘውጎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዓለም አቀፍ ፊልሞቹን ለፊልም ሠሪዎች በማሳየት ለውይይት መነሻ ለማድረግና በሌሎች አገሮች ያለውን የፊልም ኢንዱስትሪ የመዳሰስ ዓላማ እንዳለው ዳይሬክተሩ ይናገራል፡፡

‹‹ፊልም ሠሪዎቹ በፊልም ዓለም ያሉበትን ቦታ እንዲጠይቁ ያስችላሉ፤›› ሲል ከተለያዩ አገሮች ተውጣጥተው በፌስቲቫሉ የተካተቱ ፊልሞችን ይገልጻል፡፡ በፊልም ሠሪዎችና በተመልካቾች መካከል የውይይት መድረክ መፍጠር ታሳቢ መደረጉንም ያክላል፡፡ ‹‹ፊልም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ሚና የሚፈትሹ ማለትም ኅብረተሰቡንና አገርንም የሚያነቃንቁ ፊልሞች መሥራት ስላለው ሚና ውይይት ይደረጋል፤›› ይላል፡፡

የፊልም ዘርፍ እየሄደበት ያለውን አቅጣጫ የሚያመላክት መምርያ በማስቀመጥ ረገድ መንግሥትና መገናኛ ብዙኃንም ኃላፊነት እንዳለባቸው ያምናል፡፡ አንዳች የጥራት ደረጃ (ስታንዳርድ) ሲኖር ዘርፉን የሚቀላቀሉ ባለሙያዎች የተሻለ ሥራ ለማኅበረሰቡ ይዘው እንደሚመጡም ተስፋ ያደርጋል፡፡ አሁን ከሚታዩት ገበያ ተኮር ሥራዎች በተቃራኒው፣ ስለአገርና ታሪክ የሚያወሱ ፊልሞች መበራከት እንዳለባቸው አያይዞ ያነሳል፡፡

‹‹ከሌሎች የአፍሪካና የአውሮፓ አገሮች የተለየ የአገሩን ፊልም የሚመለከት ሕዝብ አለ፡፡ ልንበዘብዘው አይገባም፤›› ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ ያላት አገር እንደመሆኗ  ፊልሞች የሚያጠነጥኑበት ታሪክ በብዛት እንደሚገኝ ያክላል፡፡ የፊልም ተመልካቹ በተደጋጋመ የፊልም ታሪክና አቀራረብ ተሰላችቶ ፊልም መመልከት ከማቆሙ አስቀድሞ፣ ባለሙያዎች የተሻለ ታሪክ ይዘው መቅረብ እንዳለባቸውም ያስረዳል፡፡

ለዘርፉ ጠቃሚ የሆኑ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማመላከትና የውይይት መድረክ በመፍጠር ፌስቲቫሎች ጉልህ ሚና እንዳላቸው ይርጋሸዋ ይናገራል፡፡ ሆኖም ፌስቲቫሎች ተመሳሳይ ይዘት ካላቸው ብዙም እንደማይጠቅሙ ይገልጻል፡፡ በፊቸር ፊልሞች ዙሪያ የሚያተኩር ፌስቲቫል ካለ፣ ሌላ ተመሳሳይ ፌስቲቫል ከመጀመር በዘጋቢ ፊልም፣ በአጭር ፊልም ወይም በሌሎች ዘውጎች ማተኮር እንደሚያስፈልግም ያክላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ