ከተመሠረተች ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠረችው አዳማ (ናዝሬት) ከተማ በለውጥ ሒደት ውስጥ ትገኛለች፡፡ የምሥራቁን ክፍል ከመሀልና ከምዕራብ ጋር የምታገናኘው የንግድና ኢኮኖሚ ማዕከሏ አዳማ ከዓመት በፊት በአንድ አስተዳደር ብቻ ትመራበት የነበረው አካሄድን በስድስት ክፍላተ ከተማ መለወጧ አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡
በዘመናዊት ኢትዮጵያ ከተሞች ታሪክ ብቸኛው ሴት ከንቲባ ሆነው የተመዘገቡት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ መንበሩን ከተረከቡበት ኅዳር 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ወዲህ ከተሠሩት ተግባሮች መካከል የከተማዋ አውራና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ ድልድዮች፣ እንዲሁም ባለሦስት ፎቅ የጽሕፈት ቤት ሕንፃ ግንባታ መከናወን ይገኙበታል፡፡ እነዚሁኑ በ168 ሚሊዮን ብር የተገነቡ አዳዲስ ግንባታዎች የከተማው አስተዳደር ታኅሣሥ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. አስመርቋል፡፡
ከንቲባዋ በምረቃው ዕለት እንደተናገሩት፣ አዳማን የንግድና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ሲንከባለሉ የቆዩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ረገድ መሠራቱንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
የከተማዋ ነዋሪ አቶ አማቾ ማሆጋኖ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከንቲባ አዳነችና ካቢኔያቸው በሥራ ዘመናቸው ትልቅ ሥራ ተብሎ ሊነገርላቸው በሚችል መልኩ ያስገነቡት ባለ 20 ሜትር ስፋት የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ በመስተዳደሩ የግንባታ ታሪክ የመጀመርያው እንደሆነ ይነገራል፡፡ ‹‹የመንገዱ መገንባት ቁጥራቸው ከአምስት በላይ ለሆኑ ተጎራባች ቀበሌዎች በማሳለጫነት ለመጠቀም ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፤›› ብለዋል አቶ አማቾ፡፡
ከግንባታዎች ምረቃ በተጓዳኝም በአዳማ ከተማ የሚገኙ ዋና ዋና አደባባዮችና ጎዳናዎች በታዋቂ ባለታሪኮች መሰየማቸው ይፋ ተደርጓል፡፡ በአገሪቱም ሆነ በክልሉ ታሪክ ሁነኛ ሥፍራ የተሰጣቸው ኮሎኔል አብዲሳ አጋ፣ ብርጋዲየር ጄኔራል ታደሰ ብሩ፣ ጄኔራል ዋቆ ጉቶ፣ ታጋዮቹ ኤሌም ቂልጡና ማሞ መዘምር፣ አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ፣ ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱና ድምፃዊው አሊ ብራ መንገድና አደባባይ በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡
ከእነዚህም መካከል የከተማዋ አውራ ጎዳና ‹‹አባ ገዳ ጎዳና››፣ ከገልማ አባ ገዳ (ትልቁ አዳራሽ) ዝቅ ብሎ የሚገኘው አደባባይ ‹‹ጄኔራል ታደሰ ብሩ›› ሲባሉ፤ ከቦሌ ገዳ መናፈሻ የሚወስደው አዲስ የአስፋልት መንገድ በቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ፣ ወንጂ ማዞሪያ ተብሎ የሚጠራው አዲስ መንገድም በዋሚ ቢራቱ ስም እንዲጠሩ ተደርጓል፡፡
በተያያዘም በቁጥር ይጠሩ የነበሩት የከተማዋ 14 ቀበሌዎች የኦሮሞ ባህልና ታሪክ የሚያንፀባርቁ ስያሜዎች እንደተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡