ጎርጎርዮሳዊውን የዘመን አቆጣጠር በሚከተሉት አገሮች የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል (ገና) ሰኞ ታኅሣሥ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. (ዲሴምበር 25 ቀን 2017) አክበረዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በዳኢሽ (አይኤስ) ቀንበር ወድቃ የነበረችው የኢራቅዋ ሞሱል ከተማ ዳኢሽ በአገሪቷ ሠራዊት ተጠራርጎ ከወጣ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅዱስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ለማክበር ታድላለች፡፡
የእስላማዊው መንግሥት ‹‹ካሌፋት›› መቀመጫ የነበረችው ሞሱል ነፃ ከወጣች በኋላ ገናን ያከበረችው የአርመን፣ የአሶርያ፣ የካላዲየንና የሶሪያ ማኅበረሰቦችን በእቅፏ በመያዝ ነው፡፡ የገና ዛፎች በየገበያው ከመታየታቸውም ላይ ምግብ ቤቶችና መደብሮች በገና ዛፍና በሳንታ ክላውስ ምስሎች ተጊጠዋል፡፡ በየጎዳናው ስጦታ ሲታደል የታየው ባልተለመደ ሁኔታ ሳንታ ክላውስን ሆና በየጎዳናው በታየችው ጌንዋ ጋህሳን አማካይነት ነው፡፡ በመዲናዪቱ ታግዶ የነበረውን የገና በዓል ሕይወት ለመዝራት ቀላል የሚባሉ ስጦታዎችን ለማበርከት ነው በማለት ተናግራለች፡፡ አሻንጉሊቶችንና የትምህርት መሣሪያዎችን ለክርስቲያንና ለሙስሊም ልጆች በጥንታዊቷ ሞሱል ጎዳናዎች አድላለች፡፡ በነነዌ ከተማ የሚኖሩት የካልዳያን፣ አሶርያና የሶርያ ክርስቲያኖችም የልደቱን ብርሃን ጧፍ በመለኮስ በዓሉን አድምቀውታል፡፡ በሞሱል ለመጨረሻ ጊዜ የገና በዓል ቅዳሴ የተከናወነው ከአራት ዓመት በፊት በ2006 ዓ.ም. እንደነበር ዘ ሚዲያ ላይን ዘግቧል፡፡
***
የበጎች እረኛ
ሙሴ ባህር ከፍሎ ሕዝቡን አሻገረ፣
በታላቁ መጽሐፍ ይኼ ቃል ነበረ፤
የእኛ ሙሴ መርቶን፣
የአርነትን መንገድ በሩቅ አመላክቶን፣
በበረሃ ጉዞ ወንዙ ፊት አድርሶን፤
ይከፍለዋል ስንል ባህሩን በእጆቹ፣
መርከቡን ተሳፍሮ ከእነዘመዶቹ፣
በተስፋ ስናየው እንሳፈር ብለን፣
‹‹ዋና የምትችሉ ተከተሉኝ!›› አለን፡፡
ከነዓን ምድር ላይ ያሰበው ቢሞላም፣
ሙሴ ሕዝቡን መርቶ እሱ ግን አልገባም፤
እኛ መሪ ብለን ታምነነው ወጥተናል፣
እሱ እስራኤል ገብቶ እኛ ግን ቀርተናል፡፡
- ሰሎሞን ሞገስ ‹‹የተገለጡ ዓይኖች›› (2009)
***
‹‹ላሙን ለኛ በረቱን ለእረኛ››
‹‹ተረት ተረት›› ሲል ተራቹ መላሹ ‹‹የላም በረት›› ‹‹የመሠረት›› እያለ መመለሱ፣ አድማጭ ተረቱን ለማዳመጥ መስማማቱን መግለጹ ነው፡፡ ተራቹ በዚህ ብቻ አይቆምም፣ ወደ ተረቱ የሚዘልቀው ‹‹ላሙን ለኛ በረቱን ለእረኛ›› በማለት ነው፡፡
ተረት በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ቢኖርም አካሔዱ ግን እንደየብሔረሰቡ ትውፊት ይለያል፡፡ ይህ የተረት መንደርደርያ የተገኘው ከአዲስ አበባ ሰሜን ምሥራቅ 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው አንኮበር ነው፡፡ አንኮበሮች ተረትን እንደ ቁም ነገር ማስተላለፊያ ማስተማሪያ /መማማሪያ፣ ይቅርታን ማስተማሪያ ብልሃት አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡
‹‹ነገር በምሳሌ፣ ጠጅ በብርሌ፣ መዝሙር በሃሌ›› እንዲሉ አንኮበሮች ፍየልን በለፍላፊነት፣ ጦጣን በብልጠት፣ ዝንጀሮን በቂልነት፣ ኤሊን በአዝጋሚነት፣ በግን በየዋህነት፣ ጅብን በሆዳምነት፣ አንበሳን በጀግንነት፣ ዶሮን በረባሽነት በመጠቀም ቤተሰቦቻቸውን ልጆቻቸውን ያስተምሩበታል፡፡
***
የዕፀዋት የሒሳብ ችሎታ
ዕፀዋት ከፀሐይ ብርሃን የሚያገኙትን ኃይል ተጠቅመው ፎቶሲንተሲስ በሚባል ውስብስብ ሂደት አማካይነት ምግብ ያዘጋጃሉ። በአንዳንድ ዝርያዎች ላይ የተደረጉ ጥናቶች፣ ዕፀዋት ሌላም አስደናቂ ነገር እንደሚያከናውኑ ይኸውም ያዘጋጁትን ምግብ በአንድ ምሽት በተሻለ ፍጥነት ጥቅም ላይ የሚያውሉበትን መንገድ እንደሚያሰሉ አረጋግጠዋል።
ዕፀዋት ቀን ላይ በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኘውን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ ስታርችና ወደ ስኳር ይለውጣሉ። አብዛኞቹ ተክሎች ሌሊት የሚጠቀሙት፣ ቀን ላይ ያከማቹትን ስታርች ነው፤ ይህም ተክሉ እንዳይራብና እድገት ማድረጉን እንዲቀጥል ያስችለዋል። በተጨማሪም ያጠራቀሙትን ስታርች ጥቅም ላይ የሚያውሉበት ሂደት በጣም ፈጣን ወይም በጣም አዝጋሚ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የተመጣጠነ ነው። ጎህ እስኪቀድ ማለትም ተጨማሪ ስታርች መሥራት የሚችሉበት ጊዜ እስከሚደርስ ድረስ 95 በመቶ ያህሉን ይጠቀሙበታል።
ጥናቱ የተካሄደው አራቢዶፕሲስ ታሊያና በተባለ የሰናፍጭ ዝርያ ላይ ነው። ሌሊቱ ሊነጋ የቀረው ሰዓት 8ም ሆነ 12 አሊያም 16 ይህ ተክል ያከማቸውን ምግብ እንደ ሌሊቱ ርዝማኔ አመጣጥኖ እንደሚጠቀም ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ተክሉ ሊነጋ የቀረውን ሰዓት ግምት ውስጥ በማስገባት ያለውን ስታርች ያመጣጥናል፤ በዚህ መንገድ ምግቡን ጥቅም ላይ ሊያውል የሚችልበትን ከሁሉ የተሻለ ፍጥነት ያሰላል።
ለመሆኑ ዕፀዋት ምን ያህል የስታርች ክምችት እንዳላቸው የሚያውቁት እንዴት ነው? ጊዜን የሚለኩት እንዴት ነው? ስሌት የሚሠሩትስ ምን ዓይነት ዘዴ ተጠቅመው ነው? ወደፊት የሚደረጉ ተጨማሪ ምርምሮች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ያስገኙ ይሆናል።
‹‹ንቁ!››ኅዳር 2015