Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምሊቢያ ውስጥ መፈናፈኛ ያጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን የመታደግ አዲስ ጅምር

ሊቢያ ውስጥ መፈናፈኛ ያጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን የመታደግ አዲስ ጅምር

ቀን:

በቅርቡ በሲኤንኤን አማካይነት የተሠራጨው ተንቀሳቃሽ ምሥል ሊቢያን የስደተኞች የምድር ገሃነም አድርጓታል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለማሰብ የሚከብድ የባሪያ ንግድ የሚካሄድባት አገር መሆኗ ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡ በተለይ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች ስደተኞች በሊቢያ ውስጥ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ታግተው መከራ የሚያዩበት፣ በአገሬው ሰዎች ሳይቀር ጉልበታቸው በነፃ የሚበዘበዝበት፣ በተጨናነቁ እስር ቤቶች ስቃይ የሚፈጸምባቸው፣ ከዝርፊያ በተጨማሪ ግድያ ሳይቀር የሚፈጸምባቸው ስደተኞች በመቶ ሺዎች ይቆጠራሉ፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ግን ሰብዓዊ እንቅስቃሴዎች ጀምሯል፡፡

በሊቢያ የስደተኛ መጠለያዎችና እስር ቤቶች የታገቱ አሥር ሺሕ ስደተኞችን ወደ አውሮፓ ለማጓጓዝ መወሰኑን የአውሮፓ ኅብረት ባለፈው ሳምንት አስታውቋል፡፡ የጣሊያን የአገር ውስጥ ሚኒስትር ማርኮ ሚኒቲ ላ ሪፐብሊካ ከሚባለው የጣሊያን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ እ.ኤ.አ. በ2018 አሥር ሺሕ ስደተኞችን ከሊቢያ ለማስወጣት ተወስኗል፡፡ ስደተኞቹ ምንም ዓይነት አደጋ ሳያጋጥማቸው በሰብዓዊ መንገድ ከሊቢያ ለማውጣት የታሰበው፣ የአውሮፓ አገሮች በሊቢያ ያለው አደገኛ ሁኔታ ስላሳሰባቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

ሊቢያ ውስጥ መፈናፈኛ ያጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን የመታደግ አዲስ ጅምር

 

የአውሮፓ ኅብረት ዓርብ ታኅሳስ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ፣ ከሶማሊያና ከየመን ሊቢያ ደርሰው በችግር ውስጥ የነበሩ 162 ስደተኞችን በወታደራዊ አውሮፕላን በማጓጓዝ ሮም እንዲገቡ አድርጓል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አማካይነት ጣሊያን የደረሱት የአራቱ አገሮች ስደተኞች ሕፃናት የያዙ እናቶች፣ ወላጅ አልባ ሕፃናትና አካል ጉዳተኞች መሆናቸው ተዘግቧል፡፡ እነዚህ ስደተኞች በቀጥታ አውሮፓ እንዲገቡ በማድረግ የመጀመርያዎቹ መሆናቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሊቢያ ውስጥ 400 ሺሕ ስደተኞች እንዳሉ የተመድ መረጃ ያመላክታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 36 ሺሕ ያህሉ ሕፃናት ናቸው፡፡ የዓለም የስደተኞች ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2018 30 ሺሕ ያህሉን በፈቃደኝነት መርሐ ግብር ወደ መጡበት ለመመለስ ዕቅድ መያዙን አስታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 ብቻ 15 ሺሕ ያህል ስደተኞች በዚህ መርሐ ግብር መመለሳቸው ተገልጿል፡፡ ሊቢያ ለስደተኞች ወደ አውሮፓ መተላለፊያ በመሆኗ በርካቶች እዚያ ቢደርሱም፣ እ.ኤ.አ. በ2011 በአገሪቱ ቀውስ ከተፈጠረ በኋላ ብዙዎች ለከፍተኛ እንግልትና አደጋ ተጋልጠዋል፡፡

በተለይ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሊቢያን መናኸሪያቸው በማድረጋቸው፣ የባሪያ ንግድ መጀመሩ የተጋለጠው በቅርቡ ነበር፡፡ ሲኤንኤን በቅርቡ በተንቀሳቃሽ ምሥል ያቀረበው አስደንጋጭ የባሪያ ንግድ ይከናወን የነበረው ከዋና ከተማዋ ትሪፖሊ አቅራቢያ ነበር፡፡ ይኼም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል፡፡ ከሊቢያ በሜድትራኒያን ባህር በሚደረገው አደገኛ ጉዞ እ.ኤ.አ. በ2016 180 ሺሕ ስደተኞች ጣሊያን ጠረፍ የደረሱ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2017 ደግሞ 119 ሺሕ ነበሩ፡፡ በዚህ መሀል በብዙ ሺሕ በሚቆጠሩ ስደተኞች ባህር ውስጥ ሰጥመዋል፡፡ ከሁሉ እጅግ በጣም አሳባቢ ነው የተባለው የወላጅ አልባ ሕፃናት ጉዳይ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 ብቻ 15 ሺሕ ወላጅ አልባ ሕፃናትን የጣሊያን ጠረፍ ጠባቂዎች ታድገዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም አደገኛ የሚባለው ስደተኞች የሚጓጓዙበት የሊቢያ መስመር ለብዙዎች አሰቃቂ ነው፡፡ የሜዲትራኒያን ባህር ኃይለኛ ወጀብ አስተማማኝ  ያልሆኑ ጀልባዎችና የዛጉ አሮጌ መርከቦች ተሳፍረው ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ ለመሸጋገር ሙከራ የሚያደርጉ ስደተኞች፣ ለማመን አዳጋች የሆኑ ፈተናዎችን ይቀበላሉ፡፡ ሊቢያ ውስጥ ከሚያጋጥማቸው እስራት፣ ድብደባ፣ አስገድዶ መድፈርና ከመሳሰሉት ጀምሮ የጉልበት ብዝበዛ ሳይቀር ይፈጸምባቸዋል፡፡

ሊቢያ ውስጥ መፈናፈኛ ያጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን የመታደግ አዲስ ጅምር

 

የሲኤንኤን ፍሪደም ፕሮጀክት እንደሚለው፣ በወርኃ ታኅሳስ ለ11 ቀናት ከሊቢያ ወደ አውሮፓ ለመሸጋገር ከ27 አገሮች ከተውጣጡ 659 ስደተኞች ጋር ጉዞ ያደረገው ብቸኛ ሚዲያ ሲኤንኤን ነበር፡፡ የስፔን ግብረ ሰናይ ድርጅት እነዚህን ስደተኞች ለመታደግ ባደረገው እንቅስቃሴ ጣሊያን ጠረፍ የደረሱት አንድ ሦስተኛው ብቻ ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ ስደተኞች ለሲኤንኤን እንደተናገሩት፣ ሊቢያ ውስጥ ታግተው ለቤተሰቦቻቸው እየደወሉ እስከ 3,000 ዶላር ድረስ እየከፈሉ መለቃቀቸውን ተናግረዋል፡፡ መክፈል ያልቻሉ ደግሞ ለብዙ ዓይነት እንግልቶች ሲዳረጉ፣ በተለይ ጥቁር አፍሪካውያን ለባርነት ተዳርገዋል ማለታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡

ናይጄሪያዊው ሴሊስቴን ኢኪ ለሲኤንኤን እንደተናገረው፣ አጋቾቹ በጠየቁት መሠረት ጓደኛው 2,930 ዶላር ልኮለት ተለቋል፡፡ ብዙዎቹ ግን እንደ ባሪያ ነው የሚታዩት ብሏል፡፡ በመዶሻ ምት ከጥቅም ውጭ የሆነውን የግራ እጅ አውራ ጣቱን ብቻ ሳይሆን፣ በጥይት ጉዳት የደረሰበትን እግሩን ያሳየው ናይጄሪያዊ ስደተኛ እስር ቤት ውስጥ ሰዎች ሲገደሉ ማየቱን ይናገራል፡፡ ብዙዎቹ ደግሞ ጥቁሮች እንደሆኑም ያክላል፡፡ ‹‹እስር ቤት ውስጥ ልክ እንደ አንተ ሰብዓዊ ፍጡር የሆኑ ስደተኞች እንደ ዱር አውሬ ይገደሉ ነበር፤›› ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡

ብዙዎቹ ስደተኞች ሊቢያን እንደ ገሃነም ምድር እንደሚመለከቷት ነው ለሲኤንኤን የነገሩት፡፡ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች የሚመጡ ስደተኞች በአገሬው ሰዎችና በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ይዘረፋሉ፡፡ ለጉልበት ብዝበዛ ይዳረጋሉ፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው ሰብራዛ፣ ዘዋራህና ዛውያ የሚባሉት ከተሞች የሕገወጥ አዘዋዋሪዎች መናኸሪያ ናቸው፡፡ ናይጄሪያዊው ስደተኛ እንዳለው፣ በሊቢያ ጎዳናዎች ላይ በነፃነት መንቀሳቀስ ራስን ችግር ውስጥ መክተት ነው፡፡ ሥራ ተገኝቶ ቢሠራ እንኳ ሊቢያውያን አይከፍሉም፡፡ ገንዘቤን ስጡኝ ብሎ መጠየቅ ደግሞ ራሱን የቻለ አደጋ ያመጣል፡፡

አንድ ቤተሰብ ውስጥ አባት ጠመንጃ አለው፣ እናት ጠመንጃ አላት፣ ልጆችም እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ናቸው የሚለው ናይጄሪያዊው ስደተኛ፣ ሁሉም ጥቁር አፍሪካውያንን የሚያስፈራሩበት ጥይት አላቸው ብሏል፡፡ መሐመድ ጉራይ የተባለ የ23 ዓመት የሶማሊያ ስደተኛም፣ ሦስት ጊዜያት ታስሮ በአጠቃላይ ከዘመዶቹ ስምንት ሺሕ ዶላር ለምኖ መክፈሉን ይናገራል፡፡ እሱ እንደሚለው አስደንጋጩ ይኼ አይደለም፡፡ እሱን ያገቱ አሥር ሰዎች አንዲት ሴትን ሲደፍሩ በዓይኑ እንዲያይ ማድረጋቸው በጣም ያሳቅቀዋል፡፡ ዲያሎ አልሃሳኔ የሚባል የ17 ዓመት ጊኒያዊ ደግሞ ለአንድ ሊቢያዊ ገበሬ በግዳጅ በሚያገለግልበት ወቅት፣ ሊያመልጥ ነበር የተባለ ሱዳናዊ ስደተኛ ተገድሎ አስከሬኑ እሱ የሚያድርበት ጠባብ ክፍል ውስጥ መወርወሩን በሰቀቀን ተናግሯል፡፡

በእንዲህ ዓይነቱ ሰብዓዊነት የጎደለው ጭካኔ ሊቢያ ውስጥ ተጠልለው ያሉ ስደተኞችን ለማስወጣት በአውሮፓ ኅብረት ዕቅድ ቢያዝም፣ ከብዛታቸው አንፃር ግን ዕቅዱ የሚሸፍነው አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙ 18 ሺሕ ሰዎች ሲኖሩ፣ በጣም በርካቶች ደግሞ በግዳጅ ሥራ ላይ እንዳሉ ይነገራል፡፡ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች እጅ ውስጥ የሚገኙት ደግሞ በመቶ ሺዎች ይቆጠራሉ፡፡ የጣሊያን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሚኒቲ የአሁኑ ጅምር መሆኑን አመልክተው፣ ወደፊት ሰብዓዊ ኮሪደሮችን በስፋት ለመክፈት ተስፋ ይኖራል ብለዋል፡፡ እስከዚያ ግን ሊቢያ የስደተኞች ገሃነም ሆና ትቀጥላለች፡፡

ሊቢያ ውስጥ መፈናፈኛ ያጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን የመታደግ አዲስ ጅምር

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...