Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የአካል ጉዳተኞች ድምፅ

  ተስፋዬ ገብረማርያም የቲኤፍቲ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ነው፡፡ የሚንቀሳቀሰው በክራንች በመታገዝ ነው፡፡ ሁለት እግሩን ያለ ድጋፍ እንዳይንቀሳቀስ ያደረገው የአካል ጉዳት የደረሰበት ገና ልጅ ሳለ ነበር፡፡ አጋጣሚው ሮጦ ላልጠገበው ተስፋዬና ቤተሰቦቹ ከባድ ሐዘን ውስጥ የከተታቸው ነበር፡፡ በተለይ እናቱ ዳግመኛ ልጅ ለመውለድ እስኪወስኑ ድረስ አጋጣሚው አስደንግጧቸው እንደነበር ተስፋዬ ይናገራል፡፡ የደረሰበት ጉዳት ያለ ድጋፍ እንዳይንቀሳቀስ ከማድረግ ባለፈ የወደፊት ዕጣ ፈንታውን የመወሰን አቅም እንደሌለው ሲያምን ግን ነገሮች ተቀየሩ፡፡ እንደ ነገሩ የነበረው የትምህርቱ ሁኔታም አብሮ ተቀየረ፣ ብርቱ ሆነ፡፡ ግርማ ሞገስ የተላበሰ ድምፁ ደግሞ ገና በልጅነቱ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ላይ እንዲሳተፍ ዕድል ሰጠው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአካል ጉዳተኞችና በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በናሁ ቲቪ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙን 25 ሚሊዮን አካል ጉዳተኞችን የሚወክል ጉዳይ በሚዲያ ከማቅረብ ጋር ተያይዞ ስላሉ ልዩ ልዩ ፈተናዎች ሻሂዳ ሁሴን ተስፋዬ ገብረማርያምን አነጋግራዋለች፡፡

  ሪፖርተር፡- በጋዜጠኝነት ሙያ ምን ያህል ጊዜ ሠራህ?

  ተስፋዬ፡- ጋዜጠኝነት ከጀመርኩ በጣም ብዙ ዓመት ሆኖኛል፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ቅዳሜ መዝናኛ፣ የወጣቶች ፕሮግራም፣ ለገዳዲ ላይ በድምፅ ተሳትፎ አደርግ ነበር፡፡ በቅጥር መሥራት የጀመርኩት ግን በኤፍኤም አዲስ 97.1 ላይ ነው፡፡ በአካል ጉዳተኞች ላይ ትከረቱን ያደረገ ፕሮግራምም የጀመርኩት በፋና 98.1 ላይ ነበር፡፡ ከዚያም ወደ ዛሚ ገባሁ፡፡ በዛሚ ‹‹ድርሻችን›› የተባለ የአካል ጉዳተኞች ፕሮግራም ወደ አምስት ዓመታት ሠርቻለሁ፡፡ በፋና 98.1 ላይም ‹‹አንድ ድምፅ›› የተሰኘ እንዲሁ አካል ጉዳተኞች ላይ ያተኮረ የአንድ ሰዓት የሬዲዮ ፕሮግራም ነበር የምሠራው፡፡

  ሪፖርተር፡- የአየር ሰዓት ገዝቶ አንድ የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለማቅረብ የተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር ሄዶ ስፖንሰር ማፈላለግ ግድ ይላል፡፡ ይህም የአንድ ፕሮግራም ቀጣይነት በድርጅቶች ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የሚያደርገው ነው፡፡ ለአካል ጉዳተኞች ተገቢው ትኩረት ባልተሰጠበት ሁኔታ ድርጅቶች ለመሰል የሬዲዮ ፕሮግራም ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት ምን ይመስላል?

  ተስፋዬ፡- በማርኬቲንግ በኩል በጣም ከባድ ችግር አለ፡፡  የአካል ጉዳተኛው ጉዳይ የማን ነው ብዬ አንዳንድ ስፖንሰር አድራጊዎችን ስጠይቅ ደግሞ በዚህ መጣቹብን ይሉኛል፡፡ የመንግሥት ተቋማት ስፖንሰር እንዲያደርጉን ስንጠይቅ በጀት የለንም ይላሉ፡፡ እንዴት ተደርጎ ነው ታዲያ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ የሚሠራው? አካል ጉዳተኝነት እኮ እንደ ጥላ ነው የሚከተልሽ፡፡ እንዴትና በምን ቅፅበት አካል ጉዳተኛ እንደምትሆኚ አታውቂውም፡፡ ጉዳዩ የሁላችንም መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡ ከሌሎች ፕሮግራሞች በተለየ የአካል ጉዳተኛው ፕሮግራም እንዴት ድጋፍ ያጣል? እኔኮ ባደጉ አገሮች የምኖር ቢሆን ትልቅ ስኬታማ ሰው እሆን ነበር፡፡ ነገር ግን እዚህ አገር የምሠራው ሥራና ባለሀብቱ ልንገናኝ ስላልቻልን ስኬት ርቆኛል፡፡ በእርግጥ ሀብታም የመሆን ህልም የለኝም፡፡ ነገር ግን አገሬ ላይ አንድ ነገር አበርክቼ ማለፍ ስለምፈልግ እታገላለሁ፡፡ አንድ ስፖንሰር ለማግኘት ግን ያለው ፈተና ከባድ ነው፡፡ ስፖንሰር እንዲያደርጉልኝ ስጠይቃቸው ይህንን የመሰለ የሚያምር ድምፅ ይዘህ ለምን የስፖርት ጋዜጠኛ አትሆንም ይሉኛል፡፡ አካል ጉዳተኛ ሲባል በራሱ የሚቀፋቸው ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን የአካል ጉዳት የሚያስጠላ፣ የሚቀፍ ነገር አይደለም፡፡ ከጉዳት በቀረሽ ላይ አንድ ነገር እንድትጨምሪ ያደርግሻል፡፡ አካል ጉዳተኛው ራዕይና ተልዕኮ አለው፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ሆኑ የግል ድርጅቶች የአካል ጉዳተኛውን ጉዳይ ስፖንሰር ያድርጉትና ይመልከቱት፡፡ በእርግጠኝነት ትልቅ ተፅዕኖ መፍጠር ይችላሉ፡፡ በነገራችን ላይ ስፖንሰር ማድረግ ማስተዋወቅ ብቻ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ስፖንሰር ማድረግ ጉዳዩ የእኔ ነው ብሎ ለአንድ ፕሮግራም ድጋፍ ማድረግ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ነው፡፡ የድርጅቱ ስምም በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍ እንዲልና እንዲታወቅ ይሆናል፡፡ መንግሥት፣ ተቋማትና ሌሎችም ባለድርሻዎች በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን ትኩረት አድርገው መከታተል አለባቸው፡፡ በአካል ጉዳተኞች፣ በጎዳና ተዳዳሪዎች፣ በሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ላይ የሚሠሩ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በልዩ ሁኔታ አቅም እንዲያገኙ ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡ አጋር የሚሆኑ ትልልቅ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ የሚገደዱበት አሠራር ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ ማኅበራዊ ኃላፊነት የሚሰማው ነጋዴ ጥቂት ነው፡፡ እነሱን ማግኘቱ ራሱ ከባድ ነው፤ በሰው በሰው ነው የሚገኙት፡፡ ስለዚህ መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ የአካል ጉዳተኞች በዓል በመጣ ቁጥር በጀታቸውን ከሚለቁ በያገባኛል ስሜት ሁሌም መሳተፍ አለባቸው፡፡

  ሪፖርተር፡- አካል ጉዳተኞች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የሚዘጋጁ ፕሮግራሞችስ ምን ያህል ሳቢ ናቸው? ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶችን የማሳመን አቅማቸውስ ምን ያህል ነው?

  ተስፋዬ፡- የእኛ ፕሮግራም አንዱ ፎርማት በአካል ጉዳተኛው ላይ የሚታዩ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን መለየትና መፍትሔ ማፈላለግ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ስኬታማና ሞዴል የሚሆኑ አካል ጉዳተኞችን ካሉበት በማምጣት ማኅበረሰቡ እንዲያውቃቸውና በስኬታቸው እንዲማር ማድረግ ነው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተደብቀውና ከማኅበረሰቡ ተገልለው የሚኖሩ አካል ጉዳተኞች እንዲወጡ የማድረግ ሥራም ይሠራል፡፡ ክራንችና ዊልቸር የሌላቸው ለመንቀሳቀስ የሚቸገሩ ብዙ አሉ፡፡ የእነሱንም ፈተና የሚያሳይ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ስፖንሰር አድራጊና ማስታወቂያ አስነጋሪዎች የተለመደውን ነገር ነው የሚያስቀድሙት፡፡ ከዚያ ባለፈ ደግሞ በቲፎዞ ነው የሚሠራው፡፡ ነጋዴው ማስታወቂያ የሚሰጥሽ ስለሚያውቅሽ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ፕሮግራሞችን መደገፍ እፈልጋለሁ ብሎ የሚመጣ ድርጅት አለመኖር ትልቅ ፈተና ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ ትኩረት የተሰጠው ዘግይቶ ቢሆንም እስካሁን ሚዛን የሚደፉ ሥራ መሥራት ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን የሚታዩት ለውጦች ብዙም አይደሉም፡፡ በዚህ ላይ ምን ትላለህ?

  ተስፋዬ፡- ድሮ የነበረውን ከአሁኑ ጋር ሳነፃፅር ጥሩ ጅምሮች እንዳሉ ይሰማኛል፡፡ አካል ጉዳተኞች የሰውን እጅ ከመጠበቅ፣ ከመለመን ወጥተው በተዘጋጀላቸው ዕድል በመጠቀም መሥራት እንዲችሉ ሆኗል፡፡ ይህ ግን በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ የአገሪቱ ክፍሎች ችግሩ እንዳለ ነው፡፡ በከተማው ውስጥ ግን ጥሩ ነገር አለ፡፡ ከዚህ ቀደም ታክሲ ለመያዝ በድጋፍ የሚንቀሳቀሰው አካል ጉዳተኛ፣ በኬን (ነጭ በትር) የምትመራ ዓይነስውር የግድ መጋፋት ይጠበቅባት/በት ነበር፡፡ አሁን ግን ቢያንስ ታክሲ ለመያዝ ሠልፍ አለ መጋፋት አይጠበቅብንም፡፡ አካል ጉዳተኞች በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተቀጥረው መሥራትም ጀምረዋል፡፡ በከተማው ውስጥ የሚገነቡ ሕንፃዎች አካል ጉዳተኛውን ያማከሉ እንዲሆኑ ራምፕ ሳይኖራቸው እንዳይገነቡ ተደርጓል፡፡ ይህ ጥሩ የሚባል ጅምር ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ የአመለካከትና የግንዛቤ ችግሮች አሉ፡፡ ብዙ የሚቀሩን ነገሮች አሉ፡፡ በክልሎች ደግሞ ገና ብዙ መሥራት ይጠይቃል፡፡ እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን መቀየር የሚቻለው በሚዲያ ነው፡፡ እኔም ተስፋዬ ሾው የተባለውን ፕሮግራም የምጀምረው ይህንን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡፡

  ሪፖርተር፡- አገሪቱ በፈረመቻቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ለአካል ጉዳተኞች የተሰጡ የተለያዩ መብቶች አሉ፡፡ ድንጋጌዎቹ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጡትን መብት አውቆ የማስከበሩ ነገርስ ምን ይመስላል?

  ተስፋዬ፡- የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ረገድ በትልቁ መሥራት ችሏል፡፡ የአካል ጉዳተኛውን መብት የሚያስጠብቁ የተለያዩ ሕጎችን አውጥቷል፡፡ ነገር ግን አፈፃፀም ላይ ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ አካል ጉዳተኛውም ቢሆን መብትና ግዴታዎቹን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ የለውም፡፡ በወረቀት ላይ የሰፈሩ መብቶችና ግዴታዎችን እንኳን አያውቅም፡፡ ለዚህም ነው መገናኛ ብዙኃን የሚያስፈልገው፡፡ መገናኛ ብዙኃን ይህንን ጉዳይ ያነሳል፡፡ አካል ጉዳተኛውም ለካ ይኼ መብት አለኝ እንዲል ያደርገዋል፡፡

  ሪፖርተር፡- የአካል ድጋፍ መሣሪያዎች አቅርቦት ላይ ችግር እንዳለ ይታወቃል፡፡ የጉዳዩ አሳሳቢነት ምን ያህል ደረጃ ደርሷል?

  አቶ ተስፋዬ፡- አሁንኮ ሁሉም ቢዝነስ ሆነ፡፡ በፊት ሦስት ብር ትሸጥ የነበረችው ክራንች ላይ የምትገጠም ጎማ እንኳ በአሁኑ ወቅት 100 ብር እየተሸጠች ነው፡፡ ለጋሽ ድርጀቶች እንኳ በነፃ እየሰጡ አይደለም፡፡ ሁኔታው አካል ጉዳተኞች ዕድሜ ልካቸውን የሰው እጅ ጠባቂ እንዲሆኑ የሚያደርግ፣ ቤት ውስጥ ተደብቀው ተገልለው እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ የአካል ጉዳተኛውን ሕይወት ያቀልላል፡፡ ለምሳሌ ምርኩዜ ላይ ያለው ጎማ አልቋል፡፡ ስለዚህም መግዛት አለብኝ፤ አለዚያ አንሸራትቶ ይጥለኛል፡፡ እኔስ ገንዘብ ስላለኝ እገዛለሁ፣ ገንዘብ የሌለው አካል ጉዳተኛስ? ስንቱ አካል ጉዳተኛ ነው ገንዘብ ለው? አብዛኛው አካል ጉዳተኛ ገንዘብ የለውም፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ጉዳዩን አገናዝበው ሊሠሩ ይገባል፡፡ አካል ጉዳተኛውም የችግሩ ባለቤት እንደመሆኑ ግፊት ማድረግ አለበት፡፡

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

  የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አለመተማመንና የውጭ ጣልቃ ገብነት የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለማስቆም አስቸጋሪ እንዳደረጉት ተገለጸ

  ‹‹ጦርነቱ በአጭሩ ካልቆመ ማዕቀብ አንዱ አማራጭ ይሆናል›› የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ በአሸናፊ...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ‹‹የንባብ አብዮት ለትውልድ ብለን ተነስተናል›› አቶ ሰለሞን ደርቤ፣  የሕያው ፍቅር ለኢትዮጵያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ

  ሕፃናት በለጋ ዕድሜያቸው አዕምሯቸው እንዲዳብር ማንበብ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ዜጎች ዕውቀት፣ ብልኃት፣ ሥልት፣ ዘዴና ችሎታ እንዲኖራቸው ማንበብ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ይነገራል፡፡ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚያዊ...

  የቤት ፍላጎትንና አቅርቦትን ለማጣጣም የተነሳው ተቋም

  በአዲስ አበባ ከተማ በመኖሪያ ቤት እጥረት የተነሳ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች ሲፈተኑ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አቅሙ ኖሯቸው መኖሪያ ቤት ለመሥራት...

  የአካል ጉዳተኞችን ሕይወት የመቀየር ጉዞ

  ብርሃን ለሕፃናት የማኅበረሰብ ተሃድሶ መርህን መሠረት በማድረግ፣ በዋናነትም አካል ጉዳተኛና ሌሎች ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን ለማገዝ ከ25 ዓመታት በፊት በጥቂት በጎ ፈቃደኞች የተመሠረተ ድርጅት ነው፡፡...