Wednesday, February 28, 2024

የደቡብ ሱዳን አዲሱ የተኩስ አቁም ስምምነትና የተደቀነው ሥጋት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ እርስ በርስ ጦርነት ካመሩ አራት ዓመታት አለፉ፡፡ ይህ ግጭት ቆሞ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ በተለይ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) ሁለቱ ኃይሎች ያነገቡትን መሣሪያ በመጣል፣ ወደ ጠረጴዛ ውይይት እንዲመጡ ተደጋጋሚ ጥረት በማድረግ ተጠቃሽ ነው፡፡

ሐሙስ ታኅሳስ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ሁለቱ ኃይሎችና ሌሎች በርካታ የታጠቁ ተቃዋሚ ኃይሎች በአዲስ አበባ ያደረጉት የተኩስ አቁም ስምምነትም የተከናወነው በዚሁ በኢጋድ አማካይነት ነው፡፡ ይህ ስምምነት በተለይ ሁለቱ ኃይሎች ከሁለት ዓመት በፊት አድርገውት የነበረውን ስምምነት የሚከልስ ነው፡፡ ስምምነቱ ባለፈው ዓመት በተነሳው ግጭት መጣሱ ይታወሳል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ዋነኛው ተቃዋሚያቸውን ዶ/ር ሪክ ማቻርን ከምክትል ፕሬዚዳንትነት ማባረራቸው የግጭቱ ዋነኛ መነሻ ነበር፡፡ ይህም ግጭት የብሔር መስመር በመያዙና ዲንቃዎች ኪርን በመደገፍ፣ ኑዌሮች ደግሞ ማቻርን በመደገፍ በመሠለፋቸው በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ አንድ-ሦስተኛ የሚሆነው የደቡብ ሱዳን ሕዝብም ለመፈናቀል ተገዷል፡፡ ግጭቱ እየቆየ በመጣ ቁጥር ሌሎች ተሳታፊዎችን እየጋበዘ መምጣቱም አይዘነጋም፡፡

የፕሬዚዳንት ኪርና የዶ/ር ማቻር ተወካዮች በአዲስ አበባው ስምምነት ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ኪርን በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባርናባ ማሪያል ቤንጃሚን ናቸው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶ/ር ሙሳ ፋቂ ማሃማት ስምምነቱን አስመልክተው ሲናገሩ፣ ‹‹ይህንን ስምምነት ስትፈጽሙ ለዚህ አሳዛኝ ምዕራፍ ፍፃሜ እንደምታበጁለት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይህ ሊበረታታ የሚገባው የመጀመርያው ዕርምጃ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በስምምነቱ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበር የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ከአሁን በኋላ ሰብዓዊ መብትን ለመጣስ የሚደረደር ሰበብ የለም፡፡ ሁሉም ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነቱን የማክበር ግዴታ አለባቸው፡፡ ስምምነቱን በሚጥሱ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ እናደርጋለን፤›› በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡

ዶ/ር ሪክ ማቻር ዓርብ ታኅሳስ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ በሥራቸው የሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች ራሳቸውን ለመከላከል ካልሆነ በስተቀር ከማንኛውም ዓይነት ግጭት እንዲርቁ አሳስበዋል፡፡

ተመድም ስምምነት ላይ ካልተደረሰ በሁለቱም ኃይሎች ላይ ማዕቀብ እንደሚጥል በተደጋጋሚ አስጠንቅቆ ነበር:: ይህንኑ ስምምነትም ‹‹በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን የመጨረሻው ዕድል›› ብሎታል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ተፈርሞ በተግባር ላይ መዋል ያልቻለው ስምምነት በድጋሚ ነፍስ እንዲዘራ ለማድረግ የተለያዩ የደቡብ ሱዳን ባለድርሻ አካላት፣ አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጽሕፈት ቤት ከታኅሳስ 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ስብሰባ  ተቀምጠው ነበር፡፡ ከእነዚህ ባለድርሻ አካላት መካከልም የመንግሥት ተወካዮች፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የታጠቁና ያልታጠቁ ቡድኖች፣ ሲቪል ማኅበራት፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የንግድ ሰዎች፣ የሴቶችና የወጣቶች ተወካዮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ስምምነቱ ከተኩስ አቁም በተጨማሪ ለሲቪል ዜጎች ጥበቃ ስለማድረግና የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያደርጉ ቡድኖች እነዚህን ዜጎች እንዲያገኙ ማድረግን ይጨምራል፡፡ በኢጋድ የደቡብ ሱዳን ልዩ መልዕክተኛ እስማኤል ዋይስ ባለድርሻ አካላቱ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ካደነቁ በኋላ፣ ‹‹አንድ ሰነድ ላይ መፈረም በጣም ቀላል ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን ስምምነቱን የፈረማችሁ ወገኖችን የምማፀነው ስምምነቱን እንድታከብሩትና ደጋፊዎቻችሁም እንዲያከብሩት እንድታደርጉ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረትና ትሮይካ በመባል የሚታወቀው የኖርዌይ፣ የእንግሊዝና የአሜሪካ ጥምረት በጋራ ባወጡት መግለጫ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከኢጋድ ጋር በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ መግለጫው ስምምነቱ እንዲፈረም ያለሰለሰ ጥረት ያደረጉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶ/ር ሙሳ ፋቂ ማሃማትንና የኢጋድ አባል አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን አሞግሷል፡፡

የተመድ የደቡብ ሱዳን ሚሽን በተመሳሳይ ባወጣው መግለጫ የአዲስ አበባውን ስምምነት በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን አስፈላጊ የመጀመርያ ዕርምጃ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ ለደቡብ ሱዳን ሕዝቦች ጥቅም ሲባል ሁሉም ወገኖች ስምምነቱን እንዲያከብሩና ዘላቂ ሰላም በአገሪቱ እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እንድያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የሁለቱ ኃይሎች ቀጣይ ድርድር የሥልጣን ክፍፍል ቀመር መቅረፅና ምርጫ ማካሄድ ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል፡፡ አስቀድሞ በተያዘው ዓመት ነሐሴ ላይ ምርጫ ለማድረግ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ይህን ዕውን ማድረግ ስለመቻሉ ብዙዎች ጥርጣሬ አላቸው፡፡ ለዚህ ጥርጣሬ እንደ አብነት የሚጠቀሰው ስምምነቱ በተግባር ላይ የሚውለው እስከ መቼ ነው? ለሚለው ጥያቄ መልሱ በውል አለመታወቁ ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚዎች ስምምነቱ በተፈረመ በቀናት ልዩነት የመንግሥት ወታደሮች ጥቃት ፈጽመውብናል ብለው መክሰሳቸው መዘገቡ፣ የስምምነቱን እርባና ቢስነት ማሳያ ተደርጎም እየተወሰደ ነው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዳዲስ ተቃዋሚ ቡድኖች መቀመጫ ያደረጓት ሴንትራል ኢኳቶርያ ስቴት ውስጥ የምትገኘው ላሱ በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ሥር የነበረች ቢሆንም፣ መንግሥት አካባቢውን የተቆጣጠረው ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላ መሆኑ ተነግሯል፡፡ ተቃዋሚ ኃይሎች ቦታዋን መልሰው ለመቆጣጠር መዛታቸው፣ ስምምነቱ ሥራ ላይ ሳይውል እንደ ከሸፈ ማሳያ ነው በማለት የፖለቲካ ተንታኞች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

በዶ/ር ሪክ ማቻር የሚመራው ተቃዋሚ ኃይል ቃል አቀባይ ላም ፖል ጋብርኤል መንግሥትን ለዚህ ተጠያቂ ቢያደርጉም፣ የደቡብ ሱዳን ጦር ቃል አቀባይ ሳንቶ ዶሚክ ቾል በበኩላቸው ጥቃቱን የጀመረው ተቃዋሚው ኃይል እንደሆነና መንግሥት ጣልቃ የገባው የሲቪል ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

 ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ከሃያ ዓመታት በላይ እርስ በርስ ያደረጉት ጦርነት እንዲቋጭ ያደረገውንና በ1997 ዓ.ም. የተፈረመውን አጠቃላይ የሰላም ስምምነት እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያ የጎላ ሚና ተጫውታለች፡፡ በ1997 ዓ.ም. በሱዳንና በሱዳን ሕዝቦች ነፃ አውጪ ጦር መካከል በተፈረመው አጠቃላይ የሰላም ስምምነት መሠረት በተደረገው ሪፈረንደም፣ 98 በመቶ የሚሆኑ ድምፅ ሰጪዎች ደቡብ ሱዳን እንድትገነጠል ውሳኔ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ ይሁንና የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ዋነኛው ተቃዋሚ ዶ/ር ሪክ ማቻር የሚመሩዋቸው ሁለቱ ኃይሎች ወዲያውኑ ግጭት ውስጥ በመግባታቸው በአካባቢው የደኅንነት ውጥረት እንዲነግሥ አድርገዋል::

ደቡብ ሱዳን እንደ አዲስ ሉዓላዊ አገር የራሷን ዕጣ ፈንታ ከመቅረፅ አኳያ ያሉባትን ፈተናዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ የአገሪቱ ሰላም ከኢትዮጵያ ሰላምና የፖለቲካ መረጋጋት ጋር የሚያገናኙት ብዙ መስመሮች በመኖራቸው ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ዘላቂ እልባት ለመስጠት ጥረት ስታደርግ ይታያል፡፡ የራሷ ሰላምና የፖለቲካ መረጋጋት ጥያቄ ውስጥ በገባበት በዚህ ወቅት ይህ ስምምነት እንዲፈረም በቀዳሚነት መሳተፏም የዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ካላት ሚና አኳያ የሁለቱ ኃይሎች ስምምነት እጅግ የሚያስፈልጋት ነገር ነው::

በሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም. ደቡብ ሱዳኖች የመጀመርያ ዓመት የነፃነት በዓላቸውን ሲያከብሩ፣ የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የዛሬው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንዲህ ብለው ነበር፡፡ ‹‹ይህን የነፃነት መልካም ዕድል ከሕዝቦች ጥቅም አንፃር እንደምታዩት ተስፋ አደርጋለሁ፣ እጠብቃለሁም፡፡ አገራችሁን ለመመሥረት፣ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ሰላም የሰፈነበት ድንበር እንዲኖራችሁ ልትሠሩ ይገባል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የደቡብ ሱዳን አመራር ይህን ለማድረግ እንደሚችል እንተማመናለን፤›› ነበር ያሉት፡፡ በተጨማሪም አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለንን ግንኙነት ከፍተኛ ግምት እንሰጠዋለን፡፡ እኛ ከእናንተ ጋር የምንጋራው ድንበር ብቻ ሳይሆን ታሪክ፣ ባህል፣ እንዲሁም በዋነኛነት ብሩህ መጪ ጊዜያትንም ጭምር ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ከሱዳንም ሆነ ከደቡብ ሱዳን ጋር ባለመስማማትና በጠላትነት በመፈራረጅ ያካሄደችውን የፖሊሲ ውጤት አይታለች፡፡ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ግን ሰላማዊና በመግባባት ላይ ያተኮረ ፖሊሲ ለማራመድ እየሞከረች ትገኛለች፡፡ ከሱዳን ጋር ያላት እየተጠናከረ ያለ ግንኙነት ያሠጋቸው አገሮች ግብፅን ጨምሮ ከደቡብ ሱዳን መንግሥትና ከተለያዩ አንጃዎች ጋር ኢትዮጵያን ለማጣላት ጥረት እያደረጉ መሆኑም መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ከሁለቱ ሱዳኖች ጋር ሰላማዊና የተመጣጠነ ግንኙነት መፍጠር ለኢትዮጵያ ከፖለቲካ፣ ከዲፕሎማሲ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከሰላምና ከደኅንነት አንፃር ካለው ቀጥተኛ ጠቀሜታ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ከግብፅ፣ ከኤርትራ፣ ከኬንያ እንዲሁም አገር በቀል ተቃዋሚዎች በሱዳን በኩል የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቆጣጠር እንደሚረዳት የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡

ነገር ግን ባለድርሻ አካላቱ ቢጨምሩም በየጊዜው የሚጣሱት ስምምነቶች እንዲከበሩ ማድረግ፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሌሎች በአገሪቱ ሰላም ሰፍኖ ማየት ለሚፈልጉ ኃይሎች የተደቀነባቸው ዋነኛ ሥጋት ነው፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -