- ከ114 ቢሊዮን ኪዩብ ሜትር በላይ ውኃ ቢያስፈልገኝም የማገኘው ከ60 ቢሊዮን አይበለጥም ብላለች
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሻኩሪ በናይል ጉዳይ ለመነጋገር ሰኞ፣ ታኅሳስ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ፣ የመስኖ ሚኒስትር ሞሐመድ አብደል አቲ ለግብፅ ፓርላማ የ20 ዓመታት የመንግሥታቸውን የውኃና የመስኖ አጠቃቀም ዕቅድን አሰምተዋል፡፡
ሚኒስትሩ ለግብፅ ፓርላማ አባላት ባሰሙት ዕቅድ መሠረት፣ እ.ኤ.አ. ከ2017 እስከ 2037 ባሉት 20 ዓመታት ውስጥ አገራቸው ለምታካሂዳቸው የውኃ ሀብትና የመስኖ ሥራዎች የነደፈችው የ900 ቢሊዮን የግብፅ ፓውንድ ወይም የ50.5 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ የተተመነለት ስትራቴጂ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ይህን ያህል ወጪ የሚጠይቅ የውኃ ልማት ሥራዎች ግብፅ ለማካሄድ መነሳቷን ያስታወቁት አብደል አቲ፣ ይህም አገራቸው እ.ኤ.አ. በ2050 የውኃ ደኅንነቷን በማስከበር በጊዜው 170 ሚሊዮን እንደሚደርስ የሚጠበቀውን የሕዝብ ቁጥሯ ችግር እንዳይገጥመው የሚያስችሉ በርካታ ፕሮጀክቶችን የምታከናውንባቸው አካሄዶችን ለመከተል መነሳቷን የመስኖ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት እንዳስታወቁ የዘገበው የግብፁ አልሐራም ኦንላን ዜና አውታር ነው፡፡
ይህም ሆኖ ግብፅ በግብርና መስክ ራሷን ለመቻልና ብሎም ለልዩ ልዩ ፍላጎቶቿ መሟላት በየዓመቱ የሚያስፈልጋት የውኃ መጠን 114 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስትር አቲ፣ በተቃራኒው 60 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ብቻ እያገኘች እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡ ይኼም መጠን ከናይል የሚመጣውንና ከከርሰ ምድር የምታገኘውን አካቶ ስለመሆኑም ለግብፅ የግብርና ንዑስ ኮሚቴ የፓርላማ አባላት መናገራቸው ታውቋል፡፡ ከ97 በመቶ በላይ ለግብፅ የመጠጥ ውኃ ምንጭ እንደሆነ የሚጠቀሰው የናይል ውኃ (አብዛኛው ጥቁር ዓባይ) እንደሆነ በመግለጽ፣ ይህ የውኃ መጠን እንዳይነካባት በማስጠንቀቂያም በድርድርም ስትሞግት የቆየችው ግብፅ በኢትዮጵያ እየተገነባ የሚገኘውን የህዳሴው ግድብ ላይ በተደጋጋሚ ሥጋት እንዳደረባት ስታስታውቅ ከርማለች፡፡
በግድቡ ጉዳይ ላይ አንዴ ሲጀመር ሌላ ጊዜ ሲቋረጥ የቆየው የድርድር ሒደትም፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሻኩሪ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትና ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቻቸው ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር መነጋገር ሔድ መለስ የሆነውን የሦስትዮሽ ድርድር ለማስጀመር እንደሚያስችል ይጠበቃል፡፡ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል በተደረሰ ስምምነት መሠረት፣ በሦስቱ አገሮች የተሾመ የቴክኒክ ኮሚቴ ጥናት ማድረግ መጀመሩ ይታወቃል፡፡
ምንም እንኳ የቴክኒክ ኮሚቴው የሚያቀርበው ጥናት መነሻ እንዲደረግ ኢትዮጵያና ሱዳን ፍላጎታቸውን ቢያሳውቁም፣ ኢትዮጵያ በምትገነባው የህዳሴው ግድብ ሳቢያ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ በግብፅ ላይ እንደማይኖር በተደጋጋሚ አሳውቃለች፡፡ ግብፅ ግን የውኃ ድርሻዬ ይቀንሳል በማለት ስሞታ በማቅረብ ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡ የዜና አውታሩ ሲያትት፣ ኢትዮጵያ ይህ እንደማይሆን በማሳወቅ ውድቅ ብታደርገውም ግብፅ ግን ሥጋቷን በማስተጋባት ጸንታ እየገፋችበት ነው፡፡
ለግብፅ ፓርላማ የቀረበውን የውኃ ሀብት ዕቅድ የሚያስፈጽሙ ዘጠኝ ሚኒስቴሮች ይፋ ተደርገዋል፡፡ የግብርና ሚኒስቴር፣ የጤና፣ የአካባቢና የዕቅድ እንዲሁም የቤቶች ሚኒስቴሮችን ጨምሮ ሌሎችም በውኃ ሀብትና በመስኖ ስትራቴጂው ትግበራ ላይ የሚሳተፉ ተቋማት መሆናቸውን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
ስትራቴጂው የኢንዱስትሪ ፍሳሽን ጨምሮ ውኃን በማጣራት መልሶ የመጠቀም ዕቅድ እንዳካተተ ሲገለጽ፣ ለግብርና ሥራዎች የሚለው የውኃ ፍጆታም በዘመናዊ መስኖ አማካነት በራሽን እንደሚሰራጭ ሚኒስትር አቲ ማበራራታቸው ተዘግቧል፡፡ ከዚህ ባሻገር ጨዋማ የባህር ውኃን በማጣራት ጥቅም ላይ ማዋልም በ20 ዓመቱ ስትራቴጂ ውስጥ የተካተተ ተግባር እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ የዝናብ ውኃን ማቆርም የግብፅ ዕቅድ ሲሆን፣ ከናይል ወንዝ ተፋሰስ አገሮች ጋር በትብብር መሥራትም አማራጭ የውኃ ደኅንነት ማስጠበቂያ ሥልት ከሆኑት ውስጥ ይመደባል፡፡
ይህ ሁሉ ይባል እንጂ ግብፅ ከሚገባት ድርሻ በላይ የናይልን ውኃ እየጠጣች ነው በማለት ባለፈው ወር በሱዳን በኩል ቅሬታ ቀርቦባት እንደነበር ይታወሳል፡፡ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ መሠረት ግብፅ የሱዳንን ድርሻ እየተቀራመተች ትገኛለች፡፡ ይኼንን የሱዳንን ወቀሳ ስህተት እንደሆነ በማስተባበል ምላሽ የሰጡት የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሻኩሪ፣ ግብፅ የድርሻዋን ማለትም 18.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ ሙሉ በሙሉ እያገኘች ነው ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ ይህም ሆኖ ሱዳን ይኼንን ድርሻዋን መጠቀም ያልቻለችው በግብፅ ችግር ሳይሆን፣ ድርሻዋን ማከማቸት የምትችልበት መሠረተ ልማት ስለሌላት ነው በማለት ሻኩሪ ተናግረዋል፡፡
በአንፃሩ ግን ሱዳን በበኩሏ ግብፅ ያለአግባብ ከሚገባት በላይ ውኃ (የግብፅን) ድርሻ ከመውሰድ የሚያግዳት ግብድ በኢትዮጵያ እየተገነባ በመሆኑ ከፍተኛ ሥጋት እንደገባት መናገራቸውን የግብፅ መገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡ ተደምጠዋል፡፡ ይህም ቢባል ግን ግብፅ እርስ በርሱ የተምታታ መረጃ እየሰጠች እንደምትገኝ የሚያሳየው በአንድ በኩል የሚያስፈልገኝን የውኃ መጠን ማግኘት አልቻኩም ብትልም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከሚገባው በላይ ውኃ እየመጣባት የአሰዋን ግድብን ሥጋት ላይ የሚጥል ጎርፍ እንደሚያጋጥማት ስትገልጽ ትደመጣለች፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ለሱዳን አቻቸው የሰጡት ምላሽ ይህንኑ የሚጠቅስ ነው፡፡ ‹‹ሱዳንን አልፎ በራሱ ጊዜ ወደ ግብፅ የሚገባው የናይል ውኃ በአሰዋን ግድብ ላይ አደጋ ደቅኗል፡፡ በተለይም በጎርፍ ወቅት ትልቅ ሥጋት ነው፤›› በማለት ሻኩሪ ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡