Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያን መርኮቦች በባህር ላይ ነዳጅ የሚሞላው አዲሱ የጂቡቲ ኩባንያ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ሬድ ሲ ባንከሪንግ›› በሚል ሥያሜ ከተቋቋመ ሁለት ዓመታት ያስቆጠረው ኩባንያ፣ በራሱ መርከብ አዲስ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወራት አስቆጥሯል፡፡ ኩባንያው በጂቡቲ መንግሥት የ55 በመቶ ድርሻ እንዲሁም በዱባዩ ዩናይትድ ካፒታል ኢንቨስትመንትስ ግሩፕ የ45 በመቶ ድርሻ የተቋቋመ ነው፡፡

ኩባንያው በባህር ላይ ከመርከብ ለመርከብ የነዳጅ መሙላት ወይም መቅዳት (ባንከሪንግ) አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መርከቦች የዚህ አገልግሎት ዋነኛ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን የሬድ ሲ ባንከሪንግ ኩባንያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አብዲ ኢስማኤል ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ ጂቡቲ ባስተናገደችው ዓለም አቀፍ የንግድ ዓውደ ርዕይና የአፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ፎረም ወቅት፣ ሚስተር ኢስማኤል ስለሚመሩት ኩባንያ እንቅስቃሴ ለሪፖርተርና ለካፒታል ጋዜጦች አብራረተው ነበር፡፡ ኩባንያው ምንም ከተቋቋመ ገና ሁለት ዓመታትን ቢያስቆጥርም ቅሉ፣ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ግን ከ600 በላይ መርከቦችን በባህር ላይ የናፍጣና የከባድ ነዳጅ የመቅዳት አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻሉን ኃላፊው ይናገራሉ፡፡

እንደ ሚስተር ኢስማኤል ማብራሪያ፣ በአሁኑ ወቅት ኩባንያው በገዛው መርከብ አማካይነት የኢትዮጵያ መርከቦች ከዚህ ቀደም ከገልፍ አገሮች ይሞሉ የነበረውን ጥቁር ናፍጣ ወይም ሄቪ ኦይል ሙሉ በሙሉ ማቅረብ ጀምሯል፡፡ በወር ከ14 ሺሕ እስከ 16 ሺሕ ሜትር ኩብ ነዳጅ በባህር ላይ ለሚገኙ መርከቦች የሚሞላው ሬድ ሲ ባንከሪንግ፣ ይህ መጠን በዓመት ሲመነዘር ከ80 እስከ 90 ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሽያጭ እንደሚያስገኝ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መርከቦች መደበኛውን ናፍጣ ብቻ ከኩባንያው ይሞላላቸው እንደነበር የጠቀሱት ሚስተር ኢስማኤል፣ በአሁኑ ወቅት ግን ሁለቱንም ዓይነት የነዳጅ ፍላጎታቸውን ከኩባንያው ማግኘት እንደቻሉ ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ሲባል ሁሉም የኢትዮጵያ መርከቦች በሬድ ሲ ባንከሪንግ ነዳጅ ይሞላላቸዋል ማለት፣ በጂቡቲ በኩል በማድረግ ወደ ደቡባዊ እስያና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚያቀኑትን መርከቦች እንጂ ከእነዚህ መስመሮች ውጭ የሚጓዙት በየሚሔዱባቸው አካባቢዎች በሚገኙ የባህር ላይ ነዳጅ አዳይ መርከቦች አማካይነት አገልግሎቱን ያገኛሉ፡፡

በጥር ወር ሥራ መጀመሯ የተበሠረው ነዳጅ አዳይ መርከብ ‹‹ሬድ ሲ 1›› የሚል ሥያሜ የተሰጣት ስትሆን፣ 4.2 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎባት በጂቡቲ መንግሥት (የወደቦችና የፍሪ ዞን ባለሥልጣን አብላጫ ባለቤትነት) ተገዝታ አገልግሎት መስጠት ጀምራለች፡፡ 9,600 ቶን የምትመዝነው ይህች መርከብ፣ 10 ሺሕ ኩብ ሜትር ነዳጅ መጫን የሚችሉ ሁለት ታንከሮች የተገጠሙላት ሲሆን፣ በሰዓት 500 ሜትር ኩብ ነዳጅ ፓምፕ የሚያደርጉ ሦስት ካርጎ ፓምፖችም አሏት፡፡

እንደ ሚስተር ኢስማኤል ማብራሪያ፣ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ አንድ ተጨማሪ ከባህር ላይ ነዳጅ አዳይ መርከብ የመግዛት ዓላማ ተይዟል፡፡ በዚህም ጂቡቲ በቀይ ባህር አማካይት የሚስተናገደውን የዓለምን 65 በመቶ የመርከቦች እንቅስቃሴን በነዳጅ አገልግሎት ማዳረስ የምትችልበት አካሔድ እንደሚፈጠር ያምናሉ፡፡

ከዚህም ባሻገር በጂቡቲ እንደሚተከል የሚጠበቀው የነዳጅ ማጣሪያም ከአፍሪካ እስከ ደቡብ አፍሪካ ባለው መስመር አልፎም ወደ ባህረ ሰላጤው አገሮች የማዳረስ የኩባንያቸው ትልቁ ዕቅድ እንደሆነ ሚስተር ኢስማኤል አስታውቀዋል፡፡

በጂቡቲ ነዳጅ በማከፋፈል ሥራ የተሰማራው ዩናይትድ ካፒታል ኢንቨስትመንትስ ግሩፕ (ዩሲአይጂ)፣ በአብዛኛው በጂቡቲ ውስጥ የነዳጅ ማደልና የድኅረ ሽያጭ አገልግሎት ሲያቀርብ የቆየ ኩባንያ ነው፡፡ ዋና መሥሪያ ቤቱ በዱባይ የሆነው ዩሲአይጂ፣ ከጂቡቲ ባሻገር በአሜሪካም ጽሕፈት ቤት አለው፡፡ ኩባንያው ከነዳጅ ንግድ ባሻገር በሎጂስቲክስና በሪል ስቴት መስኮች በመካከለኛው ምሥራቅና በሰሜን አፍሪካ አገሮች ውስጥ ኢንቨስትመንቶች ያሉት ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በጂቡቲ የነዳጅ ማደል ቢዝነስ ውስጥ በመግባት እየተስፋፋ የሚገኝ ኩባንያ ነው፡፡ ከአሜሪካው ‹‹ዩኤስ ዲፌንስ ሎጂስቲክስ ኤጀንሲ›› የሚቀርብለትን ናፍጣና የአውሮፕላን ነዳጅ ለስምንት የአፍሪካ አገሮች እያከፋፈለ የሚገኘው ይህ ኩባንያ፣ እስካሁን ከ150 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ አቅርቧል፡፡ በዚህ ኩባንያ ሥር የሚተዳደረው ሌላኛው የነዳጅ ምርቶች አቅራቢ ድርጅት ኤሚር ኦይል የተሰኘው ሲሆን፣ ይኸውም ኩባንያ የሞተር ቅባቶችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የነዳጅ ውጤቶች በጂቡቲ፣ በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በማቅረብ ላይ የሚገኝ ነው፡፡

ዩሲአይጂ ኩባንያ በነዳጅ ማደል ሥራ ለየት ያለ አገልግሎት ማስተዋወቁንም ኃላፊው ይናገራሉ፡፡ ተንቀሳቃሽ የነዳጅ ማደያ አገልግሎት በመስጠት በተለይ በጂቡቲ ወታደራዊ ቤዝ ላላቸው አገሮች አገልግሎት የሚሰጥ ኩባንያ ነው፡፡ በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የአሜሪካ፣ የቻይና፣ የጃፓንና የጣልያን ጦር ሰፈሮች ይጠቀሳሉ፡፡

አገልግለቱ የሚሰጠው ባለ 40 ጫማ ኮንቴይነር ውስጥ በተካተቱ 35 ሺሕ ሊትር ነዳጅ መያዝ በሚችል የነዳጅ ታንከር፣ ፓምፕና ጄነሬተር አማካይነት ሲሆን፣ ወደተፈለገበት አካባቢ በማጓጓዝ የነዳጅ እደላ ሥራ ለመሥራት እንደሚያስችል ተብራርቷል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች