Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየፀጥታ መደፍረስ ያጠላባቸው የበዓላት ዋዜማ ጉዞዎች ሥጋት ፈጥረው ሰነበቱ

የፀጥታ መደፍረስ ያጠላባቸው የበዓላት ዋዜማ ጉዞዎች ሥጋት ፈጥረው ሰነበቱ

ቀን:

በአገሪቱ የተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ በዘመን መለወጫ ዋዜማ ከቦታ ቦታ የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ ጥላውን አጥልቶ ሰንብቷል፡፡ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ወቅቱ በዓል እንደመሆኑ የስምሪት ዝግጅት ቢያደርግም፣ በተወሰኑ  አካባቢዎች የፀጥታ ሥጋት በመኖሩ የታዩ ምልክቶች በመኖራቸው መስተጓጎል መፈጠሩ እየተነገረ ነው፡፡

በኦሮሚያ ክልል በተለይ ከጳጉሜን 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በምዕራብ አርሲ ከበቆጂ አሰላ ከዚያም ወደ ዶዶላና አዳባ ከተሞች የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መገታቱን ከሥፍራው የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በአካባቢዎቹ በሁለት ሚኒባስ ታክሲዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

ለእነዚህ ጉዳቶች መነሻ የሆነው በኦሮሚያ ክልል ከጳጉሜን 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በቤት ውስጥ የመቆየት የተቃውሞ ስልት በማኅበራዊ ሚዲያዎች በመጠራቱ ሲሆን፣ የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ለመግታት በአካባቢው ነዋሪዎች በተወሰዱ ጥቃቶች መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ከእነዚህ አካባቢዎች በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ከተሞች በተጠራው የቤት ውስጥ ተቃውሞ በርካታ የንግድ መደብሮች ሲዘጉ፣ ገበያዎችም የወትሮ እንቅስቃሴያቸውን ማቆማቸው ተገልጿል፡፡ ተቃውሞዎቹን ገሸሽ በማድረግ በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት መሰንዘሩም ታውቋል፡፡

በአገሪቱ አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ የትራንስፖርት ኩባንያዎች መካከል ሰላም ባስ አክሲዮን ማኅበርና ስካይ ባስ ትራንስፖርት ሲስተም አክሲዮን ማኅበር ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሰላም ባስ ወደ ጎንደር ከተማ ጉዞ ካቋረጠ ሰንብቷል፡፡ የሰላም ባስ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ አያሌው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎንደር አንድ አውቶቡስ ተቃጥሎባቸዋል፡፡ በየጊዜውም በሚነሱ ግጭቶች የመስታወቶች መሰባበር እያጋጠማቸው ነው፡፡

‹‹በመስታወቶች መሰባበር መስተጓጎል ሳይፈጠር ወዲያውኑ ጥገና እያደረግን አገልግሎት እየሰጠን ነው፤›› ሲሉ አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን አንድ አውቶቡስ ከተቃጠለ በኋላ የጎንደር ጉዞ ሙሉ በሙሉ ማቋረጣቸውን አመልክተዋል፡፡

ሰላም ባስ በዓመት 650 ሺሕ ሰዎች እንደሚያጓጉዝ፣ በዚህ ጉዞ ውስጥም አውቶቡሶቻቸው 8.29 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር እንደተጓዙ አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡ ሰላም ባስ በሚቀጥለው ዓመት በአጠቃላይ 800 ሺሕ ተጓዦችን ለማጓጓዝ ያቀደ ሲሆን፣ በኪሎ ሜትር ደረጃም አሥር ሚሊዮን ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ጉዞ ለማድረግ ውጥን መያዙን አስረድተዋል፡፡  

በሚቀጥለው ዓመት ከአሥር እስከ 15 አዳዲስ አውቶቡሶችን ወደ መስመር ለማስገባት መታቀዱን አቶ አበበ አመልክተዋል፡፡ ‹‹የተሟላ ኢንሹራንስ አለን፣ በተፈጠሩት ክስተቶች የደረሰብን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የለም፤›› በማለት አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር ባደረገው ዳሰሳ የሰላም ባስ ከአዲስ አበባ ጎንደር ወይም ከጎንደር አዲስ አበባ በሚያደርገው ጉዞ በአንድ መኪና ከ174 ሺሕ ብር በላይ ገቢ የሚያስገባ ሲሆን፣ ይህ ስሌት በወር ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል፡፡

ሌላው የትራንስፖርት ድርጅት ስካይ ባስ ትራንስፖርት ሲስተም አክሲዮን ማኅበር ነው፡፡ ስካይ ባስ ባሉት 11 አውቶቡሶች በአምስት መስመሮች ማለትም ድሬድዋ፣ መቐለ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳርና ሐዋሳ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

የስካይ ባስ ትራንስፖርት ሲስተም አክሲዮን ማኅበር ኦፕሬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምሰው ወርቁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያቸው ሌሎች አዳዲስ መስመሮችን ለመክፈት ጥናት እያጠና ነው፡፡

በአገሪቱ በተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ በድሬዳዋ የጉዞ መስመር ሦስት አውቶቡሶች ላይ የመስታወት መሰባበር እንደደረሰበት አቶ ደምሰው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን በተፈጠረው ችግር ያቋረጥነው መስመር የለም፤›› ሲሉ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌሎችም የትራንስፖርት ድርጅቶችና ግለሰቦች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ማወቅ ተችሏል፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች በሚደረጉ ጉዞዎች ሥጋት የፈጠረባቸው አሽከርካሪዎች ሰላም የሰፈነባቸውን መስመሮች የመምረጥ አዝማሚያ እያሳዩ መሆኑ ታይቷል፡፡ ወቅቱ የሁለቱ ታላላቅ እምነቶች ሃይማኖታዊ በዓል ከመሆኑ በተጨማሪ የዘመን መለወጫም ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወደ ትምህርት ተቋማት የሚንቀሳቀሱ ተማሪዎችም በዚሁ ወቅት የሚጓጓዙ በመሆናቸው ጉዞው ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያም ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...