ባለፉት ዓመታት በየዓመቱ ከ100 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ጥጥ ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ሲያቀርብ የቆየው የብራይሌ እርሻ ልማት ድርጅት፣ ለደቡብ ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት እንዲተላለፈ ተወሰነ፡፡
በ1998 ዓ.ም. የተቋቋመው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የተቋቋመው የተንዳሆ እርሻ ልማት ድርጅትን በመጠቅለሉ፣ የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ትልቁን የጥጥ እርሻ ማጣቱ ይታወሳል፡፡
ከአሥር ዓመት በኋላ ደግሞ የአገሪቱ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኘውን የብራይሌ እርሻ ልማት ድርጅትን ለሁለተኛ ጊዜ አጥቷል፡፡ የአገሪቱ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ በመስፋፋት ላይ ቢሆንም፣ ለኢንዱስትሪው ጥሬ ዕቃ የሚያመርቱ እርሻዎች ወደ ሌላ ሥራ እየገቡ መሆናቸው ብዙዎች እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው እየተናገሩ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቀድሞ የብራይሌ እርሻ ልማት ድርጅት ባለቤቶች የሰጠው ብድር ባለመመለሱ፣ 5,490 ሔክታር ስፋት ያለውን ይህንን ግዙፍ እርሻ ተረክቧል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይህንን እርሻ በዘርፉ ለሚታወቀው አሚባራ ቢዝነስ ግሩፕ በኪራይ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን፣ አሚባራ እርሻ ለአሥር ዓመታት ሲያለማው ቆይቶ የኪራዩ ጊዜ በ2007 ዓ.ም. በመጠናቀቁ ንግድ ባንክ እርሻውን መልሶ ይዞታል፡፡
ከዚህ በኋላ ባንኩ ይህንን እርሻ በ137 ሚሊዮን ብር መነሻ ዋጋ ለመሸጥ ተደጋጋሚ ጨረታ ቢያወጣም ገዥ ባለማግኘቱ፣ በኪራይ ለማስተላለፍም ተደጋጋሚ ጨረታ ቢያወጣም ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡
በመጨረሻ ነሐሴ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. የእርሻ ልማት ድርጅቱን የሚፈልጉ ኩባንያዎች የሚጫረቱበትን ዋጋ፣ የአሠራር ሁኔታና የድርጅታቸውን ወቅታዊ ሁኔታ የሚገልጽ መረጃ አቅርበው እንዲወዳደሩ ጋብዟል፡፡
በዚህ ጨረታ ሳግላ ትሬዲንግና አሚባራ ቢዝነስ ግሩፕን ጨምሮ ስድስት የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች ተወዳድረው ለሳግላ ትሬዲንግ ለሦስት ዓመት በኪራይ፣ ከሦስት ዓመት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ግዥ ለመፈጸም ባቀረበው የቢዝነስ ፕሮፖዛል አሸናፊ ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነሐሴ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ለሳግላ ትሬዲንግ በጻፈው ደብዳቤ ሳግላ ትሬዲንግ አሸናፊ መሆኑን በመግለጽ ቀርቦ ውል እንዲፈራረም አስታውቆ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ ሒደት ላይ እያለ የደቡብ ክልል ለቆላማ አካባቢዎች የሚሆኑ ዘሮች ለማባዛት ይህ መሬት እንዲሰጠው ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል፡፡
የደቡብ ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በላይ ሐሮሶ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የክልሉ ምርጥ ዘር ድርጅት የመሬት እጥረት አለበት፡፡ በተለይ ለቆላማ አካባቢዎች በቆሎ፣ ሰሊጥ፣ ማሽላ፣ ቦሎቄና ሽምብራ ለማብዛት ይህ መሬት ያስፈልጋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተነጋግሮ ይህንን መሬት ለመውሰድ በቅርብ ውል እንደሚፈራረም፣ ቀጥሎም ሙሉ ለሙሉ ግዥ እንደሚፈጽም አቶ በላይ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ለአገሪቱ ምርጥ ዘርም ሆነ ጥጥ ያስፈልጋል የሚሉ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ደቡብ ኦሞ የሚገኘው ይህ እርሻ፣ ቀደም ባሉት ዓመታት ሌሎች እህሎችን ለማምረት ተሞክሮ ውጤታማ አልነበረም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አገሪቱ ግዙፍ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች በማስፋፋት ላይ የምትገኝ በመሆኗ የጥጥ ልማት ሊታሰብበት እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡
በ2008 ዓ.ም. ካሉት በተጨማሪ 25 አዳዲስ የጨርቃ ጨርቅ ፕሮጀክቶች ወደ ምርት ተሸጋግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በ2009 ዓ.ም. በማሽን ተከላና ኮሚሽኒንግ ላይ የሚገኙት ቬሎሲቲ ቴክስታይል፣ አርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ማስፋፊያና ኤምኤንኤስ ቴክስታይል ወደ ሥራ ይገባሉ፡፡
ከዚህ ቀደም በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች የጨርቃ ጨርቃ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀሉ በመሆናቸው የአገሪቱ የጥጥ ምርት ፍላጎት እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በአንፃሩ የጥጥ ምርት አቅርቦት ላይ ክፍተት እንዳለ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ነሐሴ አጋማሽ ላይ በመከረበት ወቅት የቀረበው የጥናት ጽሑፍ እንደሚያስረዳው፣ በ2007/2008 ዓ.ም. 90 ሺሕ ሔክታር መሬት በጥጥ እንዲሸፈን አቅዶ ነበር፡፡ ነገር ግን ማሳካት የተቻለው 68 ሺሕ ሔክታር ሲሆን፣ የተቀረው 13,967 ሔክታር በድርቅ ምክንያት ለሌላ ምርት እንዲሆን መደረጉን አመልክቷል፡፡
በምርት በኩልም ጥናቱ እንደሚገልጸው በአፈጻጸሙ 115 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ጥጥ የተገኘ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 42 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የተዳመጠ ጥጥ ተገኝቷል፡፡ ዕቅዱም 72 በመቶ መሆኑ ጥናቱ አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ከደቡብ ክልል ጋር ይነጋገሩበታል፡፡ ‹‹በቂ መረጃ ሳይኖር ለምርጥ ዘር ይሆናል መባሉ አግባብ ስለማይሆን ጉዳዩን እኛ ይዘነው ከክልሉ ጋር ተነጋግረን የጥጥ እርሻ ሆኖ እንዲቀጥል እንሠራለን፤›› በማለት አቶ ስለሺ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ብራይሌ እርሻ ልማት በኪራይ ለመስጠት የወጣውን ጨረታ ያሸነፈው ሳግላ ትሬዲንግ ይህንን የደቡብ ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት ውሳኔ ተቃውሞ፣ ለደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ደሴ ዳልኬ አቤቱታ አቅርቧል፡፡ ሳግላ ትሬዲንግ በጻፈው ደብዳቤ የብራይሌ እርሻን ተጫርቶ ያሸነፈው፣ እርሻው ዋነኛው የጥጥ ምርት የሚገኝበት ስለሆነ መሆኑን ገልጿል፡፡
‹‹ሳግላ ብራይሌን እርሻ ማሸነፉ ሲታወቅ ይህ ሐሳብ እንዴት እንደመጣና ለምን እንዳስፈለገ ግልጽ አይደለም፤›› በማለት ሳግላ ትሬዲንግ ለፕሬዚዳንቱ በጻፈው ደብዳቤ ቅሬታውን ገልጿል፡፡
‹‹ብራይሌ እርሻ ቆላማ በመሆኑ ከምርጥ ዘር ይልቅ ለጥጥ ምርት ውጤታማ በመሆኑ ለሚቋቋሙ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የግብዓት እጥረት የሚያቃልል፣ እንዲሁም ሞዴልና አንጋፋ የጥጥ እርሻ በመሆኑ ጉዳዩ በድጋሚ ታሳቢ ሊደረግ ይገባል፤›› በማለት የሚገልጸው የሳግላ ትሬዲንግ ደብዳቤ፣ ‹‹የጨረታው አሸናፊ በመሆናችን ሕጉ መከበር ስላለበት፣ ከምርጥ ዘር ድርጅት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚቻል በመሆኑ ከግንዛቤ ገብቶ ውሳኔ ይሰጠን፤›› በማለት አመልክቷል፡፡