Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየእንቁጣጣሽ አስቤዛ

የእንቁጣጣሽ አስቤዛ

ቀን:

በኦሮሚያና አማራ ክልል የተደረገውን ተቃውሞ ተከትሎ በተጠቀሱት አካባቢዎች ባንድም ይሁን በሌላ መንገድ የሰዎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ እንዲሁም ማኅበራዊ መስተጋብር ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ሁነቶች ተከስተዋል፡፡ ሠራተኞች ለቀናት ከሥራ ገበታቸው ሲቀሩ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩም ከእቅንስቃሴ ራሳቸውን የመገደባቸው ነገር በማኅበራዊ ድረ ገጾችና በሌሎች መገናኛ ብዙኃን ሲገለጽ ከርሟል፡፡

በሌላ በኩል ከቦታ ቦታ የሚደረግ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ የሆነባቸው አካባቢዎችም ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ የፖለቲካ አለመረጋጋቱ በተለያየ መልኩ ማኅበራዊ መስተጋብር ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ እንደ ዕቁብ፣ ዕድር ያሉ የማኅበራዊ ድጋፍ መንገዶች ሲስተጓጐሉ፤ የዘመድ የወዳጅን ደስታና ሐዘን ሌላ አካባቢ ወይም ከተማ ሄዶ የመካፈል ነገርም በትራንስፖርት ችግር የማይታሰብ የሆነበት አጋጣሚም ነበር፡፡

አለመረጋጋቱ ቢቀጥል በሚል ሥጋት አስቤዛ የሚያደርጉትን ነገር በርከት አድርጐ መሸመት ዓይነት አዝማማያዎችም በስፋት ተስተውለዋል፡፡ ሁኔታዎች በዚህ መልኩ ቢቀጥሉም ብዙ ቦታዎች ላይ እንደ ሁልጊዜው የአዲስ ዓመት ገበያዎች ለሸማች ክፍት ሆነዋል፡፡ አንዳንዶቹ ገበያዎች ‘ሁሉ ሙሉ ዝግጁ’ እንደሚባለው ለአዲስ ዓመት ክብረ በዓል ያስፈልጋሉ የሚባሉ ነገሮችን በሙሉ ለማለት በሚያስችል ደረጃ ሁሉን አሟልተው የተገኙ ቢሆንም የሚጐበኛቸው ሰው እስከዚህም ሊባል የሚችል ነው፡፡ በተቃራኒው በአገሪቱ ምንም ዓይነት የፖለቲካ አለመረጋጋት ያለ ሳይመስል እንደ ሁልጊዜው ዓውደ ዓመት ዓውደ ዓመት በሚል ድባብ የደመቁ የገበያ ሥፍራዎችም ጥቂት ላይባሉ ይችላሉ፡፡ በማኅበራዊ ድረ ገጽ የበዓል ገበያን በማቀዝቀዝና በመዝጋት ጭምር ተቃውሞን የመግለጽ ጥሪን በመከተል በሚመስል መልኩም ፀጥ ረጭ ያሉ ገበያዎች እንዳሉም የሚገልጹ አሉ፡፡

ሐሙስ ጳጉሜን 3 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ ከተማ በሚገኘው እህል በረንዳ አካባቢ ገና በጠዋቱ በበርካታ ገበያተኞች ተሞልቷል፡፡ መተላላፊያው እህል በጫኑ ተሽከርካሪዎች ተይዟል፡፡ ደላሎች በፌስታል የያዙትን ጤፍ እየቆነጠሩ ለገበያተኛው በመስጠት እንዲገዙ ያግባባሉ፡፡ ገበያተኛውም በእፍኝ እጁ የያዘውን ጤፍ ከአንድ እጁ ወደ ሌላው እያደረገ ጥራቱን ይመለከታል፡፡ እዚህም እዚያም ሁለት ሦስት ሆነው ይህን እንግዛ ያን እያሉ የሚነጋገሩ አሉ፡፡

የተወሰኑ ሸማቾችን አነጋግረን እንደተረዳነው የደረጃ ልዩነት እንዳለ ሆኖ በሁሉም የጤፍ ዓይነቶች በኩንታል ከ25 እስከ 200 ብር የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ በዚህም የተነሳ 2,300 ብር የነበረው አንድ ኩንታል መለስተኛ ነጭ ጤፍ በአንድ ጊዜ 200 ብር በመጨመር ወደ 2,500 ብር ከፍ ብሏል፡፡ 2,000 ብር ያወጣ የነበረው አንድ ኩንታል ጤፍ 2,150 ብር፣ 1,800 ብር የነበረው 1,950 ዋጋ ተጠይቆባቸዋል፡፡ በሁሉም የጤፍ ዓይነቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ የተደረገው ከሦስት ቀናት በፊት እንደሆነ እህል በረንዳ በተገኘንበት ዕለት ተገልጾልናል፡፡ ይህም ጤፍ ጠፍቶ ሳይሆን ካለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ሥጋት ሳቢያ የማጓጓዙ ሥራ ቀዝቀዝ በማለቱ እንደሆነ ያነጋገርናቸው ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ነጋዴዎች ይገልጻሉ፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ከሚገኝ አንድ የእህል ወፍጮ ቤት ጤፍ በወንፊት ሲያጣሩ ያገኘናቸምው ወይዘሮ ነሐሴ መጨረሻ ላይ 50 ኪሎ ጤፍ በ1,120 ብር እንደገዙ ከአራት ቀናት በኋላ በድጋሚ ሲመለሱ ግን 30 ብር ጨምሮ እንዳገኙ ነግረውናል፡፡ በቀናት ልዩነት ጤፍ ለመሸመት ከወፍጮ ቤት የተገኙት ‹‹ክፉ ቀን ቢመጣ ይሆነኛል ብዬ ነው›› በማለት ይናገራሉ፡፡

የወፍጮው ቤት ባለቤት ጤፍ የሚያስመጡት ከወሊሶ እንደነበር፣ አሁን ስልክ ደውለው እንዲመጣላቸው ቢጠይቁ በተከሰተው ችግር ሳቢያ እንዳልተሳካላቸው አጫውተውናል፡፡ በመጋዘናቸው ያለውም ጤፍ ተሟጥጦ መሸጡንና የማጓጓዙ ሥራ ካልተጀመረ በስተቀር መጋዘናቸው ኦና እንደሚሆን ይገልጻሉ፡፡  

ከመርካቶ በመቀጠል ትልቅ ወደ ሆነው ሾላ ገበያ አመራን፡፡ በዚያ ያለው ድባብ የደመቀ ነው፡፡ ገበያው ለዓውደ ዓመት በተዘጋጁ ልዩ ልዩ ምርቶችና የእርድ እንስሳት የተሞላ ነው፡፡ ሽንኩርት፣ ቅቤና በርበሬው ሁሉም ቦታውን ይዟል፡፡ የዶሮው ጩኸት የበዓሉ መቅረብ ልዩ ምልክት ዓይነት ሆኗል፡፡ በሾላ ገበያ አንድ ዶሮ ከ250 እስከ 350 ብር ይሸጣል፡፡ ከዶሮ ነጋዴዎቹ መካከል ስሙን ያልገለጸ አንድ ወጣት ‹‹የአርባ ምንጭ ዶሮዎች ሥጋቸው በጣም ጣፋጭ ነው፡፡ ሁሉንም ዶሮዎች ያመጣሁት ከዚያው ነው፡፡ ነገር ግን ሰሞኑን በተፈጠረው ግርግር ሳቢያ ዶሮዎቹን ወደ ከተማ ለማስገባት በጣም ተቸግረናል፡፡ አቋራጭ መንገድ እየተጠቀምን እየተንገላታን ነው ምናስገባው፤›› ብሏል፡፡

ለአንድ ዶሮ የሚጠየቀው ዋጋ ከሌላው ጊዜ ከፍ ያለ ቢሆንም የተለመደ የዓውደ ዓመት ገበያ ነው የሚሉ ሸማቾች አጋጥመውናል፡፡ ‹‹በአዘቦት ቀን ቢበዛ እስከ 150 ብር ድረስ ይሸጡ የነበሩ ዶሮዎች ናቸው በ350 ብር እየተሸጡ ያሉት፡፡ ነገር ግን ይሄ የተለመደ የዓውደ ዓመት ገበያ የዋጋ ጭማሪ ነው፤›› ያሉት ወ/ሮ ገነት ተሰማ የተለየ ነገር አለማስተዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

በገበያው ሽንኩርት በኪሎ ከ20 እስከ 25 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ዛላ በርበሬም ላይ እንዲሁ በኪሎ 60 ብር የሚሸጥ ሲሆን ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ አለማሳየቱን ነጋዴዎችና ሸማቾቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከቀናት በፊት ረቡዕ ዕለት ከደብረ ብርሃንና ከሌሎች አጐራባች ከተሞች ጥራጥሬ ያስገቡ ነጋዴዎች እንደሚሉት ደግሞ በየትኛውም እህል ላይ የዋጋ ጭማሪ አልተስተዋለም፡፡ በግብይት ሒደቱም ያጋጠማቸው የተለየ ነገር የለም፡፡

የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ሰዎች ስለበዓል አከባበር ያላቸውን ስሜት ለየቅል ያደረገው ይመስላል፡፡ አንዳንዶች ጨርሶ በዓል በዓል የሚላቸው ነገር ያለ አይመስልም፡፡ ሌሎች ደግሞ እንደ ሁል ጊዜው አዲስ ዓመትን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ሽርጉዱን ተያይዘውታል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በዓሉን ከናካቴው ባይተዉትም ቀለል አድርገው ለማሳለፍ ያሰቡ እንደ ሁልጊዜአቸው ሰፋ አድርገው ለማክበር እየተዘጋጁ የነበሩም አጋጥመውናል፡፡ ወቅታዊው የገቢያቸው ሁኔታም ብዙዎችን በዓሉን በተለያየ መንገድ እንዲያሳልፉ እንደሚያደርግ አያጠራጥርም፡፡

ኑሮዋን ካለፉት ሰባት ዓመታት ጀምሮ ልብስ በማጠብ ለምትገፋው ዓለሜ (ስም ተቀይሯል)፣ የዘመን መለወጫ በዓልም ሆነ ሌሎች በዓላት አሳስበዋት አያውቁም፡፡ ‹‹ባለቤቴ ከሞተ ጀምሮ በዓልን እንደነገሩ አልፈዋለሁ፤›› የምትለው ዓለሜ፣ ከዘመን መለወጫ በዓሉ ይልቅ ለአንድ ልጇ የምትከፍለው የትምህርት ወጪ ያሳስባታል፡፡ ከዚህ ቀደም ልጇን በግል ትምህርት ቤት እርዳታ አግኝታ ስታስተምር የከረመች ቢሆንም፣ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ ትምህርት ቤቱ ሙሉ ለሙሉ ሊረዳት ስለማይችል፣ እሷ በወር 300 ብር እንድትከፍል፣ ትምህርት ቤቱ 200 ብር እንደሚከፍል በመወሰኑ፣ ዘንድሮ አራተኛ ክፍል የምትገባውን ልጇን መንግሥት ትምህርት ቤት ልታስገባ ተገዳለች፡፡ ለዚህም ልጇን ስታስመዘግብ 400 ብር እንደከፈለች፣ ዓመቱን ሙሉ ግን እንደማትከፍል ትገልጻለች፡፡

ዓለሜ እንደምትለው፣ ስድስት የተለያዩ ቤቶች ውስጥ ልብስ የምታጥብ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ቤትም በሳምንት አንዴ በወር አራቴ ታጥባለች፡፡ በዚህም ከአንዳንዶቹ 200 ብር በወር ስታገኝ፣ ከዚህ በታች የሚከፍሏትም አሉ፡፡ በወር ከምታገኘው 1,000 ብር ገደማ ውስጥ 400 ብር ለቤት ኪራይ በወር ስትከፍል፣ ቀሪው ለቀለብ፣ ለልጇ ትምህርት ቤት ግብዓት ማሟያ ነው፡፡ በመሆኑም ኑሮን በትግል እንደምትገፋ ትናገራለች፡፡

‹‹ዘመን መለወጫን ግማሽ ኪሎ ሥጋ ከቀበሌ ገዝቼ አሳልፋለሁ፤›› የምትለው ዓለሜ፣ የሚያሳስባት የልጇ ወጪ እንጂ የበዓል እንዳልሆነ ትናገራለች፡፡ በዓሉን ዶሮ አርዳ፣ ጠላ ጠምቃ ማክበር ብትፈልግም፣ ከዳቦ የዘለለ የበዓል ድግስ ማድረግ ባለቤቷ ሲሞት አብሮ እንደተቀበረ ታክላለች፡፡ በአገሪቱ አንዳንድ ሥፍራዎች አለመረጋጋት መከሰቱን ተከተሎ የተለያዩ የምታውቃቸው ሰዎች እህል ሲሸምቱ፣ ወፍጮ ቤት በኩንታል ሲያስፈጩ መመልከቷን የምትገልጸው ዓለሜ፣ ‹‹አገር ሰላም ካልሆነ ድስቱ በወጥ፣ መሶቡ በእንጀራ ቢሞላ በምን ዓይነት ጉሮሮ ያልፋል›› በማለት ሰላም እንዲወርድ ትመኛለች፡፡

ወ/ሮ አበዛሽ ፈለቀ የሦስት ልጆች እናት ሲሆኑ፣ የአዲስ ዓመት ወጪ ከሚበዛባቸው የቤት እመቤቶች አንዷ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ እሳቸው እህቶቻቸው በዓመት ውስጥ ያሉ በዓላትን በመከፋፈል በየተራ ቤታቸው እየደገሱ ቤተዘመድ ይጠራራሉ፡፡ እሳቸው የደረሳቸው አዲስ ዓመት ሲሆን፣ ቤተሰቦቻቸውንና ጎሬቤቶቻቸውን በየዓመቱ ይጋብዛሉ፡፡ የአዲስ ዓመት ግብዣቸው ከልጆቻው የትምህርት ቤት መሰናዶ ወጪ ጋር ተደማምሮ ከበድ እንደሚል ይናገራሉ፡፡ ለበዓላት ዋና ዋና የሚባሉ ነገሮች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መወደድ ደግሞ ሁኔታውን ያባብሰዋል፡፡

ሦስት ዶሮ እያንዳንዱ ከ250 እስከ 300 ብር በግ ከ1,500 እስከ 2,000 ብር የበሬ ሥጋ ከ200 ብር የክትፎና ወጥ ጥብስ 160 ብር 1 ኪሎ ቅቤ የወጥ 175 ብርና የክትፎ 200 ብር ይገዛል፡፡

‹‹አይብ፣ ዕንቁላል፣ ውስኪ፣ ቢራ፣ ኬክ፣ ቡና ቀላል የሚባለው ፈንድሻና ፌጦ ሳይቀር ተደማምሮ ወጪዬ እስከ 7,000 ሊሄድ ይችላል፤›› ይላሉ፡፡ በአራት ዓመት አንዴ ለቤታቸው አስፈላጊ የሆኑ ምንጣፍ፣ መጋረጃና ቀለም የመሳሰሉትን ማሟላት ሲኖርባቸው ወጪያቸው ከተቀረው በዓላት ወጪአቸው አንፃር ቢበዛም እንኳን ከዘመድ አዝማድ ጋር መገናኘቱን ቦታ ስለሚሰጡት ቅር አይሰኙም፡፡

ብዙ ጊዜ ወጪያቸውን ለመቀነስ በዓል ከመቃረቡ በፊት የሚፈልጉትን ይሸምታሉ፡፡ ተወደደብኝ ብለው የሚተዉት ነገር ግን የለም፡፡ ‹‹አዲስ ዓመት ቤተሰብና ጎረቤት መልካም ዓመት ይሁን ብሎ የሚመራረቅበት ነውና የቻልኩትን ሁሉ አሟላለሁ፤›› ይላሉ፡፡   

ቦሌ አካባቢ በሚኖሩት በእነ ሐያት አስማማው ቤት ደግሞ በየሁለት ዓመቱ የአዲስ ዓመት በዓል ወጪ ይጨምራል፡፡ ምክንያቱም በየሁለት ዓመቱ እንደ ምንጣፍ፣ መጋረጃ ያሉ ዕቃዎች ስለሚገዙ ይህ ወጪ ከልጆች (ሦስት ልጆች) የትምህርት ቤት ወጪ ጋር ተዳምሮ የቤተሰቡን አዲስ ዓመት ወጪ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ወጪ በሚበዛበት አዲስ ዓመት እስከ ሰላሳ ሺሕ ብር እንደሚያወጡ ሐያት ትናገራለች፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...