በኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበርና በአንጋፋ አትሌቶች በሚመራው ኮሚቴ አማካይነት በወቅታዊ የአትሌቲክሱ አቋም በተመለከተ ከአትሌቶች ጋር ታቅዶ የነበረው ስብሰባ ለመስከረም 5 እና 6 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡
በስለሺ ስህን የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበርና በኃይሌ ገብረሥላሴ የሚመራው ጊዜያዊ የአትሌቶች ኮሚቴ በጋራ በመሆን ለመወያየት የታቀደው ስብሰባው ሁሉም አትሌቶችና አሠልጣኞች እንዲሁም ማናጀሮች በተገኙበት መደረግ አለበት በመባሉ ነው ለሌላ ቀን ቀጠሮ የተያዘለት፡፡
ጳጉሜን 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሆቴል ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ስብሰባው በዕለቱ በተገኙት አሠልጣኞችና አትሌቶች መካከል የተለያዩ ጥያቄዎች ሲሰነዘሩም ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ስብሰባውን ለማካሄድ ዘጠኙም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊ መሆን አለባቸው የሚል አስተያየት ተሰጥቷል፡፡
‹‹አትሌቱን ወደማይገባ አቅጣጫ የሚወስዱ አካላት ተፈጥረዋል፣ ማኅበሩ የአትሌቶች ባለቤት መሆኑና ስብሰባውን ለአትሌቶቹ ቀድሞ በማሳወቅ ኃላፊነቱን መወጣት ነበረበት፤›› በማለት የጊዜያዊ አትሌቶች ኮሚቴ በኩል የተሰጠ አስተያየት ነበር፡፡
ነሐሴ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. በብርሃኔ አደሬ አፍሪካ ሞል አንድ ዓላማ አንግበው እንደተነሱ ያሳወቁት የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበርና ጊዜያዊ የአትሌቶች ኮሚቴ፣ በአትሌቲክሱ ላይ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ለመስጠትና ዘብ ለመሆን በአንደነታቸውን ላይ መተማመን መኖር እንዳለበት ከቤቱ የተነሳ ሐሳብ ነበር፡፡
ከአትሌቶቹና ከሚመለከታቸው አካላት ለመመካከር ያቀደው የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር በስብሰባው ላይ ብዛት ያላቸው አትሌቶች ያልተገኙት፣ የአዲስ ዓመትን በዓል ለማክበር ወደየቤታቸው ማምራታቸውና ማኅበሩ ለአትሌቶቹ በደንብ በሚዲያው ወይም ለአሠልጣኞቻቸው በኩል አለማሳወቁ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
አትሌቶቹ በሁለቱ አካላት የደረሱበትን ስምምነት ዓላማ ለአትሌቶቹ ማሳወቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውና የባለቤትነት ጥያቄን ለመጠየቅም በጋራ መሆኑ ወሳኝ እንደሆነ ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ማኅበሩ ከተመሠረተ በኋላ ከአትሌቶቹ ጋር ተገናኝቶ አለመመካከሩ እንደ ክፍተት የተነሳ ቢሆንም በአንፃሩ የአትሌቶቹ ማኅበር በአትሌቲክሱ ላይ የሚታየውን ክፍተት ለማጥራት በሥራ ተጠምዶ እንደነበር የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ስለሺ ስህን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በተደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የአትሌቲክስ ማኅበሩና ጊዜያዊ ኮሚቴው አንድ መሆናቸውን ሲገልጹ፣ በተለይ ለአትሌቶቹ በደንብ አለማሳወቁ ስህተት እንደነበረ አሠልጣኝ ቶሎሳ ቆቱ አብራርተዋል፡፡ የማኅበሩ አሠራር ግልጽ እንዳልሆነና ከጊዜያዊ ኮሚቴው ጋር የተደረገውን ጥምረት ያልተዋጣላቸው አትሌቶች እንዳሉ የገለጸው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ስለሺ ‹‹እኛ አሁንም አንድ ነን፡፡ ጥያቄያቸው ጥያቄያችን ነው›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
በቀጣይም በአትሌቲክሱ ላይ ለሚነሱት ችግሮች መፍትሔ ለመሻት፣ የቀድሞ አትሌቶች ሙያቸውን ተጠቅሞ ፌዴሬሽን ውስጥ ገብተው የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ማቅረባቸው እንደማይቀር አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ምርጫ ከማድረጉ በፊት፣ ጊዜያዊ ኮሚቴና የአትሌቶች ማኅበሩ መስከረም 5 እና 6 በሚያደርጉት ስብሰባ አንድ ውሳኔ ላይ እንደሚደርሱ ይጠበቃል፡፡