Thursday, February 22, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

አዲሱ ዓመት አዲስ ምዕራፍ ይሁን!

የተጠናቀቀው 2008 ዓ.ም. የሰቀቀን ዓመት ነበር ቢባል የተጋነነ አይሆንም፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተቀሰቀሱ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ሳቢያ በተፈጠሩ ግጭቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሞተዋል፣ በርካቶች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የአገሪቱ ንብረት ወድሟል፡፡ ከወርኃ ኅዳር ጀምሮ በመናጥ ላይ ያለችው አገር ለህልውናዋ አደገኛ የሆኑ ሥጋቶች ተጋርጠውባታል፡፡ በመላ አገሪቱ የሚኖሩ ዜጎችም ነጋ ጠባ በሚሰሙ አስፈሪ በሆኑ ዜናዎች ሳቢያ ሥጋት ውስጥ ወድቀዋል፡፡ አሮጌውን ዓመት በእንዲህ ዓይነቱ ሥጋት ውስጥ ሆና የሸኘች አገር፣ የአዲሱ ዓመት ዕጣ ፈንታ ቢያሳስባት አይገርምም፡፡ የአገርና የሕዝብ ህልውና ጉዳይ ሲያሳስብ ቁጭ ብሎ በሐሳብ ከመብሰልሰል ይልቅ፣ የመፍትሔ አካል ሆኖ አገርን መታደግ የዜጎች ሁሉ ግዴታ ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት ተስፋ ሰንቆ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን መነሳት የግድ ይላል፡፡ አዲሱ ዓመት አዲስ ምዕራፍ ይሁን፡፡

አዲሱ ዓመት አዲስ ምዕራፍ ይሆን ዘንድ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ጨምሮ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሁሉም ወገኖች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት የሚመራው ኢሕአዴግ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጥልቀት መታደስ አለብኝ ብሏል፡፡ ይኼ መታደስ ለአገር ሰላም ያመጣ ዘንድ፣ ለብጥብጥና ለግጭት መንስዔ የሆኑ ችግሮችን አስወግዶ በጋራ የሚያስማማ መፍትሔ ማስገኘት አለበት፡፡ በ2007 ዓ.ም. ክረምት ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት በኋላ የኢሕአዴግ ምክር ቤት የዴሞክራሲ ተቋማትንና ማኅበራትን ለማጠናከር ስለመወሰኑ ተሰምቶ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በየቦታው ተቃውሞው ሲጋጋል የኢሕአዴግ በጥልቀት መታደስ ጉዳይ ዋነኛው የአገር ወሬ ነበር፡፡ ሁለቱ የድርጅቱ የሥልጣን አካላት (ሥራ አስፈጻሚና ምክር ቤት) መግለጫ ሰጥተው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋዜጣዊ መግለጫ አብራርተው፣ አራት የግንባሩ አንጋፋ አባላት በቴሌቪዥን ለአራት ተከታታይ ቀናት ማብራሪያ ሰጥተውም የዚህ ትርጉም አንድምታ ገና በዝርዝርና በነቂስ አልታወቀም፡፡ በተገባው ቃል ኪዳንና በተሰጠው ተስፋ ብቻ የሕዝብን ልብ መርታት፣ ተዓማኒነትም ማግኘት ይቸግራል፡፡

በመሆኑም ያለመረጋጋት ምንጮች እንዲደርቁና አዲሱ ዓመት በአዲስ ምዕራፍ እንዲጀመር፣ በሕዝብ ውስጥ የሚብላሉ ብሶቶች ወደ ጠመንጃ አማራጭ እንዳይሄዱ፣ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የተወጠረ የፖለቲካ አየርና ትግሉ ወደ ሰከነ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊ ግብግብ መሸጋገር ይኖርበታል፡፡ ለዚህም መጀመሪያ ኢሕአዴግ ራሱ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት መለወጥ ሲኖርበት፣ ይህም የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር ይዞ መገኘት አለበት፡፡ በፓርቲና በመንግሥት መካከል መኖር ያለበት ልዩነት በግልጽ መሰመር ይኖርበታል፡፡ በመንግሥት ተቋማት፣ በማኅበራት፣ በሃይማኖትና በሌሎችም ድርጅቶች በመሠረጫጨት ድርጅቱ ሥርና ጅማት መሆኑን ማቋረጥ ይኖርበታል፡፡ ለእውነተኛና ሁሉንም ለሚያስማማ ለውጥ መነሳት ያስፈልጋል፡፡

ተቃውሞን የመግለጽ መብትና ጨዋነት በተግባር ተግባብተው የሚከናወኑበት፣ በፖለቲካዊ ጉዳዮችና በሕዝብ ጥያቄዎች ላይ እየተነጋገሩ፣ እየተደማመጡ፣ እየተደራደሩ፣ እየተስማሙ፣ ልዩነትን እያከበሩና ዴሞክራሲያዊ መፍትሔ እየሰጡ አገራዊ መግባባት የሚፈጥሩበት አዲስ ዓመትና አዲስ ምዕራፍ ውስጥ መግባት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ኢሕአዴግ የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መንደርደሪያዎች ይጠበቁበታል፡፡ ከእነዚህም መካከል ፖለቲካዊ ፋይዳ ያለውና የኢትዮጵያ የሁለት ወገን የጥላቻ ፖለቲካ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችል የምሕረትና የይቅርታ ዕርምጃ መውሰድ አንዱ የመፍትሔ አካል ነው፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነቱን የማወቅና ፍትሕ የማግኘት መብት እንዳለው አስረግጦ መረዳት ነው፡፡ ለዚህም እስረኞች የተያዙበትንና የሞቱበትን ሁኔታ የሚያጣራ በግልጽና በአደባባይ የሚሠራ ልዩ መርማሪ ኮሚሽን ማቋቋም ተገቢ ነው፡፡

አዲሱ ዓመት ከአሮጌው ዓመት የዞረ ድምር ውስጥ የሚወጣበት፣ ብሩህ ተስፋ የሚሰነቅበት፣ ለጠብና ለግጭት መንስዔ የሆኑ አጓጉል ድርጊቶች የሚወገዱበት፣ ከኃይል ይልቅ በሰላማዊ መንገድ ችግሮች የሚፈቱበት፣ የሕዝብ ጥያቄዎች በአንክሮ ተሰምተው በፍጥነት ምላሽ የሚያገኙበት፣ የአገርንና የሕዝብን ሰላም የሚያናጉ፣ ለዕልቂትና ለውድመት የሚያጋልጡ ፉከራዎች ቆመው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚረዱ መፍትሔዎች የሚመነጩበት፣ በማንነትና በብሔር ጥላቻ ላይ የተመሠረቱ አውዳሚ ሐሳቦች በኢትዮጵያዊነት ጠንካራ የአንድነት ስሜት በፍቅር የሚረቱበት፣ ወዘተ. እንዲሆን ሁሉም ወገኖች በጥልቀት ማሰብ አለባቸው፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎች ወደማይፈለግ አቅጣጫ እንዳይነዱና ለአገር ህልውና ጠንቅ የሚሆኑ አደጋዎች እንዳይፈጠሩ፣ ለዴሞክራሲያዊና ለሰላማዊ እንቅስቃሴዎች የሚበጅ ምኅዳር እንዲፈጠር ዜጎች በሙሉ ተፅዕኖ መፍጠር አለባቸው፡፡ የሰላማዊና የዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች የበላይነት አጥተው የጠቡ መንገድ ከተመረጠ ግን ለማቆም አዳጋች ከመሆኑም በላይ፣ አገሪቱና ሕዝቧ የማይወጡት አዘቅት ውስጥ ይገባሉ፡፡ አገሪቱም ለታሪካዊ ጠላቶቿ በቀላሉ ዒላማ ትሆናለች፡፡ ስለዚህም አዲስ ዓመት የአዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ ይደረግ፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ካሁን በኋላ ደም መፍሰስ የለበትም፡፡ ዜጎችን ለስደትና ለእንግልት የሚዳርጉ ተግባራትም ሊስተናገዱ አይገባም፡፡ የአገሪቱ አንጡራ ሀብትም ለአደጋ መጋለጥ የለበትም፡፡ ይልቁንም ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕ፣ እኩልነትና ሰብዓዊነት ይለመልሙ ዘንድ ከፍተኛ ጥረት መደረግ አለበት፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው አካልም ሆነ ሥልጣን ለመያዝ እንታገላለን የሚሉ ወገኖች ቅድሚያ ለሕዝብ ፍላጎት ይስጡ፡፡ ሥልጣንን ለማጠባበቅም ሆነ ለመንጠቅ ሲባል ብቻ ከሕዝብ ፈቃድ ውጪ መሆን መዘዙ የከፋ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በሕዝብ ፈቃድ ብቻ ነው፡፡ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጠው ፈቃዱን በማሟላት ብቻ ነው፡፡ እስካሁን የታዩት አካሄዶችና አሠራሮች ከሕዝብ ጋር ካጣሉ፣ መፍትሔው ለሕዝብ የሚበጀውን ብቻ በተግባር ማዋል ነው፡፡ ሁሉም ወገን ለሕግ የበላይነት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል፡፡ በተሰናባቹ ዓመት የታዩት ሰቆቃዎች በአዲሱ ዓመት በፍፁም እንዳይደገሙ ከተፈለገ፣ አዲሱ ዓመት የአዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ እንዲሆን መሥራት ብቻ ነው የሚያዋጣው!

መልካም አዲስ ዓመት!

መልካም የአረፋ በዓል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...

ቢሮአቸውን ዘግተው በተገልጋዮች ላይ የቅርብ ሩቅ የሆኑ ሹማምንት ጉዳይ ያሳስባል

በንጉሥ ወዳጅነው  በአሁኑ ወቅት ብቻ ሳይሆን ትናንትም ቢሆን የተመረጡም ሆኑ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...

አፍሪካውያን እንዳይታዘቡን ጥንቃቄ ይደረግ!

የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው የመሪዎች ጉባዔ በኅብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሄደ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ ከዛሬ 61 ዓመት በፊት ከጥንስሱ እስከ ምሥረታው ወሳኝ ሚና የነበራት ኢትዮጵያ...

ታሪክን ከመዘከር ባሻገር የመግባቢያ መንገዱም ይፈለግ!

እሑድ የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ የተመረቀው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ከታላላቅ አገራዊ ክንውኖች ተርታ የሚመደብ ነው፡፡ ይህንን መሰል የታሪክ ማስታወሻ በታላቅ ክብር...