ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ለሁለት ወራት ያህል አገር ውስጥ አልነበሩም፡፡ በካናዳና በአሜሪካ በሥራ ጉብኝት ላይ የነበሩት ኢንጂነር ይልቃል ሰሞኑን ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ በወቅታዊው የአገር አጠቃላይ ጉዳዮችና በፓርቲው ውስጣዊ ችግሮች ላይ ነአምን አሸናፊ ኢንጂነር ይልቃልን አነጋግሮአቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያና በአማራ ክልል ከተሞች አለመረጋጋት ይስተዋላል፡፡ ይህን አለመረጋጋት ተከትሎም የሰዎች ሕይወት የጠፋ ሲሆን የንብረት ውድመትም ደርሷል፡፡ ከዚህ አንፃር ወቅታዊውን የአገሪቱን ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል? የዚህ ሁሉ ችግር መንስዔስ ምንድነው? መፍትሔውስ ምን ሊሆን ይችላል?
ኢንጂነር ይልቃል፡- እውነቱን ለመናገር ይህ ነገር ሰፋ ያለና ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው፡፡ አሁን ምልክቱ መታየት ጀመረ እንጂ የተከማቸ ችግር ነው፡፡ ችግሩ ተከማችቶ ተከማችቶ መገለጫዎቹ መታየት ጀመሩ፡፡ በአጠቃላይ በአገራችን ባለፉት 25 ዓመታት ለተከታታይ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊውና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሕዝቡ የነበሩት ጥያቄዎች በሙሉ በአግባቡ ባለመያዛቸው አሁን እንደሚታየው የሰው ሕይወት እየጠፋ ነው፡፡ ሕዝቡም ተስፋ የመቁረጥ ዕርምጃ እየወሰደ ነው፡፡ በአጠቃላይ አሳሳቢና አስደንጋጭ ነገር ነው፡፡ የችግሩ መሠረት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዳይኖር መደረጉ፣ የሲቪክ ማኅበራት አለመኖር፣ ዜጎች የፈለጉትን አመለካከትና አስተያየት በነፃነት ያለማራመድ፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአታላይ አገዛዝ ወጥቶ የአገሩና የሥልጣን ባለቤት ባለመሆኑ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜ ወጣቶች ሥራ ይጠይቃሉ፣ የተለያዩ የአስተዳደር ክልሎች የማንነት ጥያቄ ይጠይቃሉ፣ እንደዚሁም ደግሞ ነፃና የተለያየ አስተሳሰብ እንዲራመድ የሚፈልጉ ሰዎች የሃይማኖት ነፃነታቸውን ይጠይቃሉ፡፡ እናም ሁሉም በያለበት ጥያቄዎቹ አልተመለሱለትም፡፡ እንደየአካባቢውና እንደየነባራዊ ሁኔታው በተለያዩ ምክንያቶች የሕዝብ መከፋት፣ በመንግሥት ላይ ያለው ቅሬታና በአጠቃላይ ለመንግሥት ይሁንታ ባለመስጠት በሚመስል መልኩ ነገሮች እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከፓርቲያችሁ መሠረታዊ መርሆዎችና ስትራቴጂዎች አንፃር አሁን የተከሰተው ችግር ምክንያት ምንድነው? ፓርቲያችሁ የሚያስቀምጠው የመፍትሔ ሐሳብስ ምንድነው?
ኢንጂነር ይልቃል፡- ይህ ችግር የብዙ ነገሮች ውጤት ነው፡፡ አንደኛ ዜጎች በጋራ የሚያደርጉትና የሚግባቡባቸው የጋራ የሆኑ መሠረታዊያን ተሸርሽረዋል፡፡ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ምናልባት ዜግነትና የብሔረሰብ ማንነት የተደበላለቀ እስከሚመስል ድረስ ባለፉት 25 ዓመታት ለአገር፣ ለዜግነት፣ ለክብር፣ ለማኅበራዊ አገልግሎት የሚያገለግሉ ነገሮች በሙሉ ተሰባብረዋል፡፡ ከዚያ ይልቅ ግለኝነት፣ ሚስጥራዊነትና ራስ ወዳድነት የመሳሰሉት ነገሮች እየተስፋፉ ከመብት ጥያቄዎች ባለፈ አጠቃላይ የማኅበራዊ ዝቅጠት ተከስቷል፡፡ ለዚህም ነው በሥልጣን አካባቢ ሙስናው ያለ ገደብ የሚያድገው፣ ማኅበራዊ አገልግሎትና የፖለቲካ ውድቀት የሚፈጠረው፣ የመንግሥት ቅቡልነት ማጣት የሚመጣው፡፡ ዋናው መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ የሥልጣንና የአገሩ ባለቤት በሆነ ጊዜ የፖሊሲዎች ልዩነት ብዙ አሻሚ አይደለም፡፡ የፖሊሲ አማራጭ መኖርን በተመለከተ የተለያየ አገር በተለያየ ቃል የፖሊሲ አማራጮችን ሊጠቀም ይችላል፡፡ ነገር ግን መሠረታዊ የተባሉት ነገሮች፣ ሁሉም የተማመኑበት ሕገ መንግሥት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፈለገውን በፈለገው ጊዜ የሚያወርድበትና የሚያወጣበት የሥልጣን ባለቤት መሆን፣ ጠንካራ የሲቪክ ማኅበር መኖር፣ ነፃ አካዴሚ መኖር፣ ነፃ ሚዲያ መኖር ለዴሞክራሲ ምሰሶዎች ናቸው፡፡ ያ ግን አሁን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የለም፡፡ ማስመሰል ካልሆነ በስተቀር፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሥልጣንም የአገሩም ባለቤት አልሆነም፡፡ የፖለቲካ ቡድኖች በተለያየ ምክንያት እየተቧደኑ ከላይ ወደታች እንጂ፣ ከታች ወደላይ የሆነ የፖለቲካ ሥልጣን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አልተሰጠውም፡፡
ሪፖርተር፡- ከምርጫ 2007 ቀደም ባሉት ጊዜያትና የምርጫው መጠናቀቅን ተከትሎ ሰማያዊ ፓርቲ የተለያዩ ሰላማዊ ሠልፎች የማካሄድ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ እንደነበርና ፈቃድ እንዳልተሰጠው በተለያዩ መግለጫዎቻችሁ ስትገልጹ ቆይታችኋል፡፡ እነዚያ ሠልፎች ፈቃድ አግኝተው ቢሆን ኖሮ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ፓርቲያችሁ ምን ዓይነት ሚና ይጫወት ነበር?
ኢንጂነር ይልቃል፡- ያ ቢሆን ኖሮ ሁለት ዓይነት ምርጫ ይኖረን ነበር፡፡ አንደኛ ጥያቄዎች ጠቅለል ጠቅለል ይሉና አንኳር አንኳር ሆነው አጀንዳዎች በሚገባ ተቀርፀው፣ የኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅምና የሕዝቡም አጠቃላይ መሠረታዊ ጥያቄዎችና አጀንዳዎች ሰብሰብ ባለ መልኩ አቅርቦ የትኛው ተመልሷል የትኛው አልተመለሰም? መሠረታዊ ጥያቄው የትኛው ነው? ዝርዝር ጥያቄ የትኛው ነው? የሚሉትን ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች በጋራ የሚቆሙባትና የጋራ አጀንዳዎች ሰፋ ብለው የሚመጡበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር፡፡ ሕዝቡም መነሻና መድረሻውን በግልጽ እንዲያየው ያደርጋል፡፡ መንግሥትም እነዚያን ጥያቄዎች በመመለስና ባለመመለስ የጠራ ነገር ኖሮ በሐሳብ ላይ የተመሠረተ ውይይት ለማድረግ ያስችላል፡፡ አለመግባባትም ቢኖር እንኳን በዚያ ደረጃ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ መፍጠር ይቻል ነበር፡፡ አሁን የኢሕአዴግ በጣም መጥፎ በሽታው ሁሉንም ነገር አድቅቆ፣ ችግሩን ሁሉ ራሱ ተሸክሞ፣ መፍትሔውንም ለማምጣት ተቸግሮ ሁላችንም ተዘግቶብን እንደቆምን ዓይነት አደረገው፡፡ ያ ምንም ዓይነት መተንፈሻ እንዳይኖርና ይኼው አብዮት በሚባለው በሒደቱ ቀርፋፋነትና ተስፋ በመቁረጥ፣ ሁሉም የራሱን አጀንዳዎች እየቀረፀ ጥያቄዎችን እንኳን በአግባቡ ለመመለስ ሊመች የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደረሰ፡፡
ሪፖርተር፡- በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተነሱ ጥያቄዎችን አንግቦ ለመደራደር የቻለ የፖለቲካ ተቋም ወይም ድርጅት የለም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጉዳዩን ሸሽተውታል የሚባል አስተያየት ይሰነዘራል፡፡ ፓርቲዎቹ ለምን የሸሹ ይመስልዎታል? እንደሚባለውም እንቅስቃሴዎቹ መሪ አልባ ናቸውና መሪ አልባ የሆነ እንቅስቃሴስ መጨረሻው ምን ይሆናል?
ኢንጂነር ይልቃል፡- አብዮት ሲባል በመሠረቱ ከፓርቲው አለፈ ማለት ነው ትርጉሙ፡፡ ፓርቲ ቀስቅሶ አብዮት አያስነሳም፡፡ አብዮት ማለት በድንገት የሚነሳና ጥያቄዎች ተከማችተው ተከማችተው ሰው ደመነፍሳዊ በሆነ ሁኔታ የሚያደርገው ነገር ማለት ነው፡፡ ተጠንቶ በየደረጃው እየተመራና እየሄደ ከሆነማ አብዮት አይደለም፣ አዝጋሚ ለውጥ ነው፡፡ አብዮት ቅፅበታዊ ነው፡፡ የታፈነ ጥያቄ ምላሸ የሚፈለግበት ነው፡፡ ምናልባትም ስትራቴጂ ተነድፎ ላይቀረፅ ይችላል፡፡ ነገር ግን ባለው አጠቃላይ ሁኔታ ካለመርካት የሚመነጭ ነው፡፡ አሁን እኮ ሕዝቡ በእኛም ሆነ በኢሕአዴግ ተስፋ ቆርጧል፡፡ በተለምዷዊው ሒደት የሚፈልገውን ውጤት እንደማያገኝ ተረዳና የራሱን ውሳኔ ወሰደ፡፡ ጥያቄው መሪ አልባ ነው የሚለው የአብዮትን ትርጉም አንድ ሰው ከተረዳ አብዮት ዛሬ እኔና አንተ እናስነሳ፣ ይህን ሕዝብ እናስነሳ ካልን አብዮት አይደለም፡፡ ተጠንቶ የተደረገ ነገር ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሕዝብ መንግሥት ይቋቋማል፣ ባለአደራ መንግሥት ይቋቋማል፣ ጊዜያዊ የሆኑ ነገሮች ይሆናሉ፣ የሃይማኖት መሪዎችና ሽማግሌዎች ተሰባስበው ነገሮችን መልክ ለማስያዝ ጥረት ሊደረግ ይችላል፡፡ ስለዚህ እነዚህ የተደራጁ ኃይሎች የሚያመጡት ውጤት ባመሳካቱ ነው አብዮት የሚፈጠረው፡፡
እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሰማያዊ እያሸነፈ 30 ወይም 40 በመቶ መቀመጫዎችን በፓርላማ አሸንፎ ቢሆን እኮ አብዮት ላይነሳ ይችላል፡፡ ምክንያቱም በሚቀጥለው ምርጫ 55 በመቶ ድምፅ ያገኝና መንግሥት ይሆናል፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች ይንፀባረቃሉ፣ ሕዝቡ እርካታ ይሰማዋል፡፡ ጥያቄዎቹን የሚያቀርብበት፣ መረጃዎች የሚያገኝበትና ያላቸው ነገሮች የሚስተካከሉበት መንገድ ይፈጠሩለታል፡፡ አሁን ግን ኢሕአዴግ መቶ በመቶ ወሰደ፡፡ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮናሚያዊ ችግሮች እንደታመቁ ናቸው፡፡ ለሃይማኖት ጥያቄዎች መልስ አይሰጥም፡፡ በዚህ አገር ላይ የሚከበርና የሚቆጣ እንኳን የሃይማኖት መሪና ሽማግሌ የለም፣ የአደባባይ ምሁር የለም፣ ሚዲያ የለም፣ ሲቪክ ማኅበረሰብ የለም፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ ከድሮም ጀምሮ መሪ እንዳይኖር ነው የሚፈልገው፡፡ አሁንም ደግሞ ይህንን ነገር የሕዝብ ጥያቄም ሆኖ ቀርቶ የቡድኖች ነው ብሎ ለማጥፋት ነው፡፡ የወልቃይት ኮሚቴ ላይ የሚደርሰውን ነገር ለምን አንመለከትም? እነዚያ ሰዎች እኮ በቅጡ የተደራጁ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም የኢሕአዴግ አባልም አመራርም የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ጥያቄውን እንዴት እንደሚያቀርቡት፣ የክልሉ መንግሥት ጋ እንዴት እንደሄዱና ወደ ፌዴራል እንዴት እንደመጡ የሚታወቅ ነው፡፡ መጨረሻ ላይ አፈራረሳቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚሁ ጋር በተያያዘ አገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መንግሥት ለመዳከማችን ዋነኛው ተጠያቂ ነው ሲሉ ይደመጣል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሉም ወይም ተዳክመዋል የሚል አስተያየት ይሰነዘራል፡፡ በእርስዎ አተያይ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ? ወይስ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሉ ይላሉ?
ኢንጂነር ይልቃል፡- መጀመሪያ እኮ አሁንም ሥልጣን ያለው አገዛዝ በእንቆቅልሽ የተሞላ ነው፡፡ የሚያወራውና ትክክለኛ ግብሩ ተቃራኒዎች ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ አሁን በአናሳ ልሂቃን የሚመራ ድርጀት ነው፡፡ ነገር ግን ጥፍንግ ያለ ማዕከላዊነት ያለው ፓርቲ ነው፡፡ ከዚያ የኅብረት መንግሥት ወይም ፌደራላዊ አወቃቀር እቀበላለሁ ይላል፡፡ በጣም ሥር የሰደደና የታሰረ ማዕከላዊነት ያለው ፓርቲ የኅብረት መንግሥትን ሲቀበል እንዴት ሊሆን ይችላል? ስለዚህ ሁለቱ አይጣጣሙም፡፡ የኅብረት መንግሥት ያልተማከለ አስተዳደርን፣ ሥልጣንን ወደ ሕዝብ ማውረድን፣ ለታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ሥልጣንን እየሰጡ ለሕዝብ ሥልጣንን ማቅረብ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ጠባይ ደግሞ ጥቂት ሰዎችን ይዘው ጥፍንግ ያለ ማዕከላዊነት አሠራር ያለው ነው፡፡ ስለዚህ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ማምጣት አይችልም፡፡ ከዚያ ደግሞ ከግራ ርዕዮተ ዓለም የተቀዳ እኛና እነሱ በሚል ሁለትዮሽ ጠላትና ወዳጅን የሚፈትን ድርጅት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የብዙኃን ፓርቲን እቀበላለሁ ይላል፡፡ ባህሪው ደግሞ ጠላትና ወዳጅን የሚሰብክ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ስለተቃዋሚዎች የሚጠቀሙትን የቃላት አጠቃቀም ተመልከት፡፡ በዚህ የተነሳ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን ከልቡ አያየውም፡፡ በእነኚህ ባህሪዎቹ የተነሳ ጠንካራ ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይል በኢትዮጵያ ሊፈጠር አይችልም፡፡ ለዚህ ነው ምርጫውም የውሸት እየሆነ ነገሮች ወደ አብዮት የተቀየሩት፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሥርዓት የሚያካሂድ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በኢሕአዴግ ዘመን የፖለቲካ ፓርቲ አብቦና አፍርቶ የማይሄደው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢሕአዴግ እስካለ ድረስ የመኖር ተስፋቸው የመነመነ ነው፡፡ አሁንም ያን ያህል ነው፡፡ ቢፈጠሩም ይቀጭጫሉ፣ ይፈርሳሉ፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ ኢሕአዴግ ተሃድሶ አካሂዳለሁ በማለት በተለያዩ መድረኮች እየገለጸ ይገኛል፡፡ ጥቅል ሐሳቡን ወደ ጎን አድርገን ከፖለቲካ ፓርቲዎች የመደራጀትና በነፃነት ከመንቀሳቀስ አንፃር የተባለውን የተሃድሶ ሐሳብ እንዴት ያዩታል?
ኢንጂነር ይልቃል፡- ለእኔ ይህ አስተያየት ማታለል ነው፡፡ ብዙውን ነገር ስለመለከተው ገድላቸውን ማውሳት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ገድልህን ራስህ የምታወራ ከሆነ ደግሞ የሆነ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ገድልህንና ታሪክህን ያገለገልከው፣ የረዳኸው፣ ለውጥ ያመጣህለት ሰው ነው እንዲነግርህ የሚገባው፡፡ እኛ ይህንን ሁሉ ነገር ሰጥተናችሁ ረሳችሁን የሚል የቅሬታ ንግግር ነው የሚመስለው እንጂ፣ የእውነት ለመለወጥ አይመስልም፡፡ ረስታችሁታል እናስታውሳችሁ የሚል ነው ትልልቆቹ ሰዎች ወጥተው ሲናገሩ የምሰማቸው፡፡ አሁን ደግሞ እነርሱ የዘነጉት ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን ነገር ነው፡፡ የሕዝቡ ፍላጎት ኢትዮጵያ ሰፊ አገር ስለሆነች ጥፍንግ አድርጎ የተወሰነ ቡድን ይዞ ቀጭን ትዕዛዝ እየሰጡ መግዛት የማይቻልበት ነባራዊ ሁኔታ መፈጠሩን ነው፡፡ አዳዲስ አስተሳሰቦችና ዕይታዎች እየመጡ መሆኑን ነው፡፡ የነበሩት ነገሮች ሁሉ በነበሩበት መቀጠል እንደማይችሉ ነው፡፡ እነሱ ግን በያዝነው የችግር የአፈታት ዘዴ አሁንም እንቀጥላለን ይላሉ፡፡ የምር አገር ከሥልጣን በላይ ስለሆነ የምንችለውን ነገር አድርገናል፡፡ እንደኛ አገራቸውን የሚወዱ የተለየ ሐሳብ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ይኖሩ ይሆናል፡፡ ይህንንም ለማስተናገድ ዝግጁ ነን የሚል የእውነት የፖለቲካ ቆራጥነት አላየሁበትም፡፡ አሁንም በዚያው ማድበስበስ እንደሚቀጥሉ ነው የሚታየኝ፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ አሜሪካንና ካናዳ ሁለት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ ቆይተው ተመልሰዋል፡፡ በዚህ መሀል የሰማያዊ ፓርቲ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የወሰደው ዕርምጃ አለ፡፡ አሁን ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ምን እየተካሄደ ነው?
ኢንጂነር ይልቃል፡- ይህ ጉዳይ በሁለት መልኩ ሊታይ ይችላል፡፡ ሰፋ አድርገህና በቀናነት ካየኸው ሰማያዊ ገና ለጋ እንደመሆኑ የተለያዩ ተቋማት በፓርቲው ውስጥ በራሳቸው ውሳኔ እየሰጡና የራሳቸውን ሕግ ለማስከበር የሚያደርጉትን ጥረትና ሙከራ እንደ አንድ ቀና ነገር ልታየው ትችላለህ፡፡ እስከ ዛሬ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ እንደዚህ ሰምተን አናውቅም ወይ? ተደባደቡ ወይ ተጣልተው ተከፈሉ፣ አልያም ወደ ምርጫ ቦርድ ሄዱ ሲባል ነው የምናውቀው፡፡ ሊቀመንበር ተከሰሰ፣ ተወቀሰ፣ ሥራ አስፈጻሚ የማስተማመኛ ድምፅ ተሰጠበት፣ ያን ውሳኔ ደግሞ የሆነ የሥራ ክፍል ሰረዘው የሚባሉ ነገሮች በፓርቲዎች ውስጥ አልነበሩም፡፡ እነዚህን ነገሮች ስታያቸው ጤናማ ልምምድ አድርገህ ልትወስዳቸው ትችላለህ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ውሳኔዎች ደግሞ እንዴት ተሰጡ አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ምንድነው የሚያመለክተው? የተወሰኑት ውሳኔዎች ደግሞ ፓርቲውን እንደታሰበው አሳድገውታል ወይ? የሚሉትን ነገሮች ስታያቸው ብዙ ውሱንነቶች ያሉባቸው ነገሮች አሉ፡፡ አሁን አገራችን ካለችበት ሁኔታ አንፃር ጉባዔ መጥራት፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ያለው ችግር ምን ያህል እንደሆነ በሚታወቅበት ሁኔታ የተሰጠው ውሳኔ ጊዜውን የጠበቀና አግባብነት ያለው ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ዋና ዋና የሕዝብ አጀንዳዎችን ይዞ መቅረብ እንጂ የፓርቲ ፖለቲካ አሁን ለሕዝብ የሚቀርብበት ጊዜም አልነበረም፡፡ ከዚያ አንፃር የሥልትም ሆነ ነባራዊ ሁኔታን ያለማጤን ችግር አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አካባቢ ኢሕአዴግ አስርጎ ያስገባቸው ሰዎች ፓርቲያችንን አደጋ ላይ ጣሉት፣ ወይም አፈረሱት የሚል ወቀሳ ይሰነዘራል፡፡ ኢሕአዴግ ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ሰርጎ በመግባት ፓርቲውን የማዳከምና የማፍረስ ሥራ እየሠራ ነው ብለው ያምናሉ?
ኢንጂነር ይልቃል፡- ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ለዚህ በቂ መረጃዎች አሉኝ፡፡ አንደኛ ሚስጥራዊ የተባሉ የፓርቲው ስብሰባዎች በደቂቃ ውስጥ የኢሕአዴግ ወዳጅ በሆኑ ድረ ገጾች ሲጻፉ አያለሁ፡፡ ከዚያ የምንረዳው ነገር የሰማያዊን ጉዳይ ምን ያህል ሌት ተቀን እንደሚከታተለው ነው፡፡ ከዚያ በተጨማሪም የተካሄዱትን ውይይቶች በተሳሳተና ለሕዝብ የተለየ መልዕክት በሚያስተላልፍ ዘይቤ ሲያወሩዋቸው ታገኛቸዋለህ፡፡ እኔ ሳላውቅ እንኳን ኢሕአዴግ የሚያውቅበት መንገድ አለ፡፡ የዲሲፒሊን ኮሚቴ አንድ ውሳኔ ወሰነ ተብሎ መሰብሰባቸውን እንኳን አናውቅም፡፡ ግን በኢሕአዴግ ወዳጆች ተጽፎ አየን፡፡ የድርጅቱን ባህሪ ሲመጣ ጀምሮ ያሰብክ እንደሆነ እንዲያውም ሊገርመን አይገባም፡፡ ባያደርግ ነው የተለየ ነገር አድርገህ ለሥልት ነው ዝም ያለው ልትል ትችል ይሆናል እንጂ ኢሕአዴግ ፓርቲ ሲያፈርስ እኔ አልገረምም፡፡ በባህሪው እንደዚያ ነው ያደገውና፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ አሜሪካና ካናዳ ጉብኝት አድርገው ተመልሰዋል፡፡ የጉዞው ምክንያት ምን ነበር? ከጉብኝትዎስ ምን ይዘው ተመለሱ?
ኢንጂነር ይልቃል፡- መጀመሪያ ስሄድ የሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፌስቲቫል ቶሮንቶ ካናዳ ነበር የሚካሄደውና እዚያ አገር በአንድ የሲቪክ ማኅበር ኢትዮጵያውያን የሚሰባሰቡበት ስለነበር፣ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታና በተለይ በእስረኞች ጉዳይ ላይ ንግግር እንዳደርግ ነበር ተጋብዤ የሄድኩት፡፡ ከዚያ የተረፈ ጊዜ ካለ በተለያዩ ግዛቶች ካሉ ከኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አባላት ጋር መነጋገርና ለዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ማስረዳት ላይ ያለመ ነበር፡፡ በተለይ የአሜሪካና የካናዳ መንግሥታት የኢሕአዴግ የልብ ወዳጅ ስለሆኑ፣ ወዳጃችሁ ችግር ላይ ነው፣ ታሟል፡፡ የወዳጃችሁ ሕመም ለቀጣናው፣ ለአገሪቱም ለራሱም ሞት እንዳያመጣ በጊዜ ብታስቡበት ይሻላል የሚለውን ለእነርሱ ለመንገር ነበር፡፡ በተቻለ መጠን ይህንን ለማስረዳት ችያለሁ፡፡ በካናዳ መንግሥት ውስጥም ያሉ የፓርላማ አባላትን፣ በውጭ ጉዳይ ውስጥ ያሉ የምዕራብና የምሥራቅ አፍሪካ ኃላፊዎችን፣ ከኢትዮጵያ የልማት ተራድኦ ዳይሬክተርን ጭምር አነጋግሬያለሁ፡፡ አሜሪካ በመጣሁም ጊዜ ከሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ አባላት ጋር ውይይት አድርጌያለሁ፡፡ እንዲሁም ከውጭ ጉዳይ ረዳት ሴክሬተሪ ጋርም ተወያይቻለሁ፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ጉዳይ ከሚያውቁ ሰዎች ጋር ተወያይቻለሁ፡፡ እንዲሁም ለየት ባለ መድረክ ከዶ/ር መረራ ጉዲና ጋር ሆነን አትላንቲክ ካውንስል በሚባል የቲንክ ታንክ ቡድን ስብሰባ አዘጋጅነት ከአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከተለያዩ ዘርፎች፣ ከኮንግረስ፣ ከውጭ ጉዳይ፣ ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶችና ኢትዮጵያን የሚያውቁ ምሁራን ባሉበት የኢትዮጵያን ሁኔታ አስመልክቶ የወደፊቱስ ምን ይሆናል? አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች? በሚለው ላይ ተወያይተናል፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ ከአሜሪካና ከካናዳ እንደመመለስዎ የዳያስፖራን ፖለቲካ እንዴት ይመለከቱታል? በዚህ ጉዳይ ላይ ዳያስፖራው በአገሪቱ የፖለቲካ ለውጥ ላይ ምንም አስተዋጽኦ የለውም፣ ሊኖረው አይገባም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በተቃራኒው ድግሞ እነርሱም የአገራቸው ጉዳይ ያገባቸዋል የሚሉ አሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
ኢንጂነር ይልቃል፡- እኔ ፖለቲካን እንደዚህ ቀለል አድርጎ መፈረጅ አልፈልግም፡፡ የኢትዮጵያ ልጆች እስከሆኑና የኢትዮጵያ ጉዳይ ያሳስበናል እስካሉ ድረስ እዚያ መንደር ኖሩ እዚህ መንደር ኖሩ ሁሉም አገሩ ነው፡፡ በአገሩ ጉዳይ የሚመለከተውን ማድረግ ይችላል፡፡ ዳያስፖራ የሚባለው አንድ ፈርጅ ያለው፣ አገር ቤት የሚገኘው ሌላ ፈርጅ ያለው አድርጎ የአገርን ችግር እንደዚህ ከፋፍሎ ማየት ይለምድብንና ሌላ ዓይነት ቅርፅ ይኖረዋል፡፡ ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በመራቃቸው የአገር ናፍቆት ይኖራል፡፡ ከሚኖሩበት አገር አንፃር ደግሞ በአገራቸው የሚያዩት ነገር ይኖራል፡፡ ሌላ አገር ሄደው ተከብረው፣ ሀብት አፍርተው፣ ልጆች ወልደው፣ አስተምረው ትልቅ ደረጃ ሲደርሱ ያያሉ፡፡ በአገራቸው ላይ ደግሞ ያንን ነገር ሳይሆን ያያሉ፡፡ በዚያ ሁኔታ ውስጥ ቁጭትና እልህ ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ነፃ አገርም ስለሆነና እንደኛ በቀጭን መንገድ የማይሄዱ በመሆናቸው ነፃነታቸውን ተጠቅመው ስለአገራቸው ጉዳይ ይጮሁ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የዳያስፖራ ፖለቲካና የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚባለው ነገር ራሱ አስተሳሰቡ ትክክል አይመስለኝም፡፡ እነርሱም አገራቸው ነው፣ እነርሱም እንደኛው ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር ከአሁን በኋላ የሰማያዊ ፓርቲ ሚና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ምን ይሆናል?
ኢንጂነር ይልቃል፡- አሁን ትግሉ የሕዝብ ሆኗል፡፡ ሁሉ ነገር የሚሆነው በሕዝቡ ነው፡፡ ተጎጂውም ተጠቃሚውም ሕዝቡ ነው፡፡ ፖለቲካ የሕዝብ ነው፡፡ ያም በመሆኑ በየአካባቢው እንዳሉት ነባራዊ ሁኔታዎች ሕዝቡ ጥያቄዎችን ማቅረብ ጀምሯል፡፡ የፓርቱ ሚና ሊሆን የሚችለው እነዚህን ጥያቄዎችን አጉልቶና የፍልስፍና ቅርፅ ሰጥቶ አገራችን ሳትበታተን የምንሄድበትን መንገድ ጆሮ ያለው ካለ እንዲሰማ ማሳየት ነው፡፡ በኢሕአዴግ እርካታ አጥቶ በየቦታው የሚጮኸውና ወገኑ የሚሞትበት ሰው ምን ይጠብቃል? ለዚያ የሚሆኑትን የፖሊሲ ዶክመንቶችንና የሐሳብ ዘዴዎችን ማቅረብ ነው፡፡ እነዚያን ነገሮችንም ጀምረናል፡፡ ከዚያ ውጪ ወደ ሕዝብ የሚኬደው ለማደራጀትና ለማስተማር ነበር፡፡ አሁን ነገሮች ሁሉ የፓርቲን መስመር አልፈዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በህር ዳር የተካሄደውን ሠልፍ እንደጠራችሁ ካሳወቃችሁ በኋላ እንዳልጠራችሁ የሚገልጽ መግለጫ በድጋሚ አውጥታችኋል፡፡ በባህር ዳር የተፈጠረው ነገር ምንድነው? ሠልፉን ከጠራችሁ በኋላ አልጠራንም ያላችሁትስ ለምንድነው?
ኢንጂነር ይልቃል፡- የተፈጠረ ውዥንብር አልነበረም፡፡ ሁሉም ነገር ግልጽ ነው፡፡ ሠልፉን የጠራነው የሠልፉ ቀን ከመድረሱ ከአሥራ አምስት ቀናት በፊት ነው፡፡ ምናልባትም ጎንደር ሠልፍ ሳይደረግ በፊት ነው፡፡ እኛ መጀመሪያ ያቀድነው ሕዝባዊ ስብሰባ ነበር፡፡ ሕዝባዊ ስብሰባ ለማድርግ አቅደን ለመቀስቀስ ተፈቅዶልን ሙሉዓለም አዳራሽ ላይ ስብሰባ ለማድረግ አመራሮቻችን ቅስቀሳ ለማድረግ ወደ ባህር ዳር አቀኑ፡፡ እዚያ የሄዱትን ሰዎች በሙሉ አሠሯቸው፡፡ ለመቀስቀሻ የሚያገለግሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ወሰዱ፡፡ በዚህ ምክንያት ሕዝባዊ ስብሰባው ሳይካሄድ ቀረ፡፡ ስለዚህ ሕዝባዊ ስብሰባ ማድረግ እንደማይቻል ሲታወቅ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ መግለጫ ተሰጠ፡፡ ይህ በታቀደበት ሁኔታ በመሀል ጎንደር ላይ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ለመከላከል ባደረጉት ጥረት የተፈጠረው ነገር ተፈጠረ፡፡ ያ እንዳለ ሆኖ መሀል ላይ ሰማያዊ ሠልፍ እንደጠራ ሲታወቅ የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ አስተያየቶች ይሰጡ ነበር፡፡ አንደኛ ሰማያዊ የጎንደርን ሠልፍ መሳካት አይቶ በዚህ ውስጥ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት መሀል ላይ የገባ አድርጎ የሚሰጥ አስተያየት ነበር፡፡ የእኛ ግን ቀደም ብሎ የታቀደና ከሕዝባዊ ስብሰባ ወደ ሰላማዊ ሠልፍ የተቀየረ ነው፡፡ ሰማያዊ ራሱ ነው የጠራው፡፡ ነገር ግን ፖለቲካው የሕዝቡ ሆኗል፡፡
ሰማያዊ የሕዝቡን ጥያቄ ማንሳትና ማስተባበር አስፈላጊ የማይሆንበት ሁኔታ ከተፈጠረና ልክ ጎንደር ከወልቃይት ጋር ቅርብ በመሆኑ ያ ቅርበት ያመጣው ስሜታዊ ግንኙነት ሕዝብ በራሱ ለራሱ ያደረገውን ነገር ባህር ዳር ላይ ላይደረግ ይችላል፡፡ ነገር ግን ባህር ዳር ላይም ሕዝቡ እንደዚያ የሚያደርግበት ሁኔታ ካለ የፓርቲው እንቅስቃሴ አስፈላጊ አይደለም ልንተወው እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡ በራሱ ባደረገው ላይ የፖለቲካ ፓርቲ ሊገባ አይችልም፡፡ ያ በሆነበት ሁኔታ በአጋጣሚ እሑድ እኛ ሠልፍ ስንጠራ ዓርብ ዕለት ኮሎኔል ደመቀ ፍርድ ቤት ይቀርብ ነበር፡፡ ከዚያ ጋር በተያያዘ ጎንደር ላይ ብዙ ሰው ሞተ፡፡ በዚያ ምክንያት የባህር ዳር ሕዝብ በጣም ተቆጣ፡፡ በዚህ መሀል ጠቅላይ ሚኒስትሩም የአማራ ክልል ፕሬዚዳንትም ለማንም የተሰጠ የሠልፍ ፈቃድ የለም ብለው ተናገሩ፡፡ በዚህ መሀል የእኛ ቢሮ ተከበበ፡፡ ወደ ሥፍራው ሲሄዱ የነበሩ ሰዎች ታሰሩ፡፡ በመሆኑም እኛ የሕዝቡን ሠልፍ የማድረግ መብት እናከብራለን፡፡ ነገር ግን የማስተባበር ኃላፊነቱን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ልናደርግ አንችልም ብለን አሳወቅን፡፡
ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ የኢሕአዴግ ግምገማ በኋላ ከነባር የፓርቲው አባላት ከዚህ በኋላ የፓርቲ አባል ባይሆኑም እንኳን ብቃት ላላቸው ሰዎች ሥልጣን ልንሰጥ እንችላለን የሚል ነገር ተደምጧል፡፡ እርስዎ ቢጋበዙ ከኢሕአዴግ ጋር ለመሥራት ፈቃደኛ ነዎት?
ኢንጂነር ይልቃል፡- ይህ እኮ የልጆች ጨዋታ ነው፡፡ ይህ ልዩነቱ ለኢሕአዴግ የአባልነት መዋጮ የመክፈልና ያለመክፈል ጥያቄ ብቻ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ፖሊሲ፣ አመለካከትና አመራር ብቻ እስከሆነ ድረስ ግለሰቡ ብቻውን ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡ በአንድ አገር ነገሮችን ወደግራ ወደቀኝ የሚቀይረው ሥርዓት ነው፡፡ አንድን ሰው በማባረርና በማስቀመጥ የሕዝብ ጥያቄ በዚያ አይመለስም፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ችግር የግለሰቦች የብቃት ማነስ ወይም ልዩ ችሎታ መኖር አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ችግር በአጠቃላይ ተቋማዊ ነው፡፡ የሕዝብ የአገሩና የሥልጣኑ ባለቤት መሆን፣ ተጠያቂነት ያለው መንግሥት መኖር፣ የመሾምና የመሻር ሥልጣን በሕዝቡ እጅ መሆን፣ ያሉት ተቋማት በራሳቸው ብቁ መሆናቸው ነው፡፡ እነዚያ ሁኔታዎች ላይ ሳንሠራ ጥያቄዎቹ ግለሰቦች ላይ ያሉ አይደሉም፡፡ ግለሰብን በመለዋወጥ የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡ እንዲያውም ይኼ ኢሕአዴግ መሠረታዊ ችግሮቹን ፈፅሞ ለመንካት ፈቃደኛ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡