Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም

ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም

ቀን:

በሀብተሥላሴ ለይኩን (ዶ/ር)

በአዲሱ ዓመት መግቢያ ላይ ቆሜ እንደ አንድ የአገር ተቆርቋሪ ዜጋ ይህን መልዕክት ለማድረስ የወደድኩት ወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ አሳሳቢ ስለሆነብኝ ነው፡፡ እንደ አቅሜ መንግሥት በሚፈጥራቸው ብዙዎቹ የምክክር መድረኮች እየተገኘሁ ያመንኩበትና የመሰለኝን ከመግለጽ ወደኋላ ባልልም፣ ‹‹ኢሕአዴግ አፍ እንጂ ጆሮ የለውም›› እንዲሉ እምብዛም ሰሚ ማግኘት አልቻልኩም፡፡

በመሆኑም ቢያንስ ለታሪክ መመዝገብ ስላለበትና ለክቡርነትዎ በተጨማሪ ሪፖርተር ጋዜጣን የሚያነብ ‹‹ወዳጅ››፣ ‹‹ጠላትም›› ሆነ መሀል ሠፋሪ ስለሚመለከተው ሐሳቤን ለመግለጽ ወድጃሁ፡፡ ማስተናገድ ያለማስተናገድ የሪፖርተር ጋዜጣ ፈንታ ሆኖ በግሌ ግን ያለንበት ሁኔታም ሆነ መደረግ ስላለበት ከአቻ የሥራ ጓደኞቼ፣ ከኢመደበኛ ወዳጆቼና በተለያየ አጋጣሚ ከማገኛቸው ሰዎች ጭምር የተረዳሁትን አጠናቅሬ ላቀርብልዎት ሞክሬያለሁ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!

በቅርቡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የኢሕአዴግ ምክር ቤቶች ያደረጉዋቸውን ግምገማዎች አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ከመላው አገሪቱ ‹‹የተውጣጡ ናቸው›› ከተባሉ ሦስት ሺሕ ገደማ የሚደርሱ ወጣቶች ጋር ያደረጉትን ውይይትም አይቻለሁ፡፡ በእነዚህ ንግግሮች በልበ ሙሉነት ስለአገሪቱ ቀጣይነት እያሰቡ፣ በነባሮቹ የኢሕአዴግ ፖሊሲዎች ሕዝቡን መልሰው ለመምራት እንደተዘጋጁም ሁኔታዎች ያሳብቃሉ፡፡

በእኔ እምነት ግን አሁን አገሪቱ ክፉኛ ታማለች፡፡ እርስዎ ‹‹ግምገማ›› ባሉት መድረክና በወጣቶች ውይይት ላይ እያሉ እንኳን በተለይ በጎጃም፣ በጎንደርና በምሥራቅ ሐረርጌ ዞኖች ከ100 በላይ ንፁኃን ወጣቶች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው ተሰምቷል፡፡ በእነዚሁ ቀናት የወደመው ንብረትም በደሃ አገር ኢኮኖሚ ሲሰላ እጅግ የሚያስቆጭ ነው፡፡

አሁን ባለው ግርድፍ የፖሊስ መረጃ መሠረት በባህር ዳር፣ ዳንግላ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ደምበጫ፣ ቡራዩና መሰል ከተሞች በርካታ የአበባ እርሻ ልማቶችን ጨምሮ የግል ኢንቨስትመንቶች፣ የሕዝብ መገልገያ ተቋማት፣ የግለሰቦች ቤቶችና ተሽከርካሪዎች ውድመት እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ሊደርስ ይችላሉ መባሉን ሰምተናል፡፡ ይህ ጉዳት ከጎንደርና ለወራት ከዘለቀው የኦሮሚያ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ሲታይ ምንኛ አገሪቷን እንዳከሰረ መገመት አያዳግትም፡፡

እንደ አገር ፈጣን ልማት ያመጣች፣ በርካታ ስደተኞች ተቀባይ፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋነኛ አፍሪካዊት ሰላም አስከባሪ የተባልን ነን፡፡ ይሁንና ዘንድሮ ከዳር እስከ ዳር በታየው ቀውስ፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ዕጦት ተምሳሌት ሆነናል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ጎሳ ተኮርነትም እንኳን አንድነትን ሊያመጣ በቀበሌና በወረዳ ድንበር አገር ሊበትን የሚችል ውዝግብ ውስጥ የምንገባ መሆናችን ታይቷል፡፡ ይህንን አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተማጋቾች፣ ዋና ዋና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያዎችና ምዕራባውያን እየገለጹት ነው፡፡ (አንዳንድ መንግሥታትም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ለዜጐቻቸው ማስጠንቀቂያ እስከ መስጠት ደርሰዋል) ይህን ያፈጠጠ ሀቅ ደግሞ ሻዕቢያና ግብፅ የሠሩት ሴራ ነው እያልን ራሳችንን ልናታግልበት አንችልም፣ አይገባምም፡፡

ክቡርነትዎ!

በእርግጥ ያሳለፍነው ዓመት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ጥሩ ጊዜ የሚባል አልነበረም፡፡ በአገሪቱ ከ50 ዓመታት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ መታየት፤በጋምቤላ ክልል በደቡብ ሱዳን የጎሳ ታጠቂዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕልፈት፣ የበርካታ ሕፃናት ተጠልፎ መወሰድና ሌሎችም ሥጋቶች ተከሰቱ፡፡ በአገሪቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የፀረ ስደት ግብረ ኃይል ቢቋቋም ሕገወጡ ስደቱ ከመባባስ አልተገታም፡፡ እንዲያውም በደቡብ በኩል በሚደረግ የቡድን ስደት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በየኮንቴነሩ ሞተው ተገኙ፡፡ በኬንያ፣ በሱዳንና በታንዛኒያ እስር ቤቶች የሚማቅቁት ‹‹ሕገወጦችም›› የውድቀት ማሳያ ናቸው፡፡ ታዲያ የአገሪቱ ለውጥና ዕድገት እምኑ ላይ ነው? ያስብላል፡፡

ያጠናቀቀነው ዓመት ከስኬት ይልቅ የችግርና የቀውስ ነው የሚባልበት ሌሎች ማሳያዎችም አሉ፡፡ ቀዳሚው እርስዎ የሚመሩት መንግሥትና አጋሮቻችሁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን ያለምንም ተቀናቃኝ ከያዛችሁ በኋላ የዲሞክራሲ ምኅዳሩ ይበልጥ መጥበቡ ነው፡፡ በተለይ ኢሕአዴግ እምብዛም ሕዝቡ ድጋፍ የማይሰጣቸውን ‹‹ተቃዋሚዎች›› ለጨዋታው ማሟሟቂያ ያህል ይዞ ቢንቀሳቀስም በነፃ መደራጀት፣ ሐሳብን በነፃነት መግለጽ፣ የፖለቲካ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ማድረግ ቅንጦት መሆኑ የውድቀት መጀመሪያ ነበር፡፡

በድርጅትዎ አሥረኛ ጉባዔ ላይም ቢሆን ‹‹ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ይጠናከራል፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦቱም እየተባባሰ ስለሆነ እንገታዋለን፤›› የሚል ቃል ኪዳን ተገባ፡፡ ከዚያ በኋላ በ‹‹ጥናት›› ላይ የተመሠረተ ውይይትም ተካሄደ፡፡ ሕዝቡም አጀንዳውን ከአደባባይ አልፎ በየጓዳው አብላላው፡፡ ይሁንና ከውይይትና ‹‹ግምገማ›› ያለፈ እዚህ ግባ የሚባል ዕርምጃ አልታይ አለ፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባን ጨምሮ በታችኛው የመንግሥት እርከን ላይ ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ‹‹የኢሕአዴግ›› አመራሮች ከሥራቸው ተነሱ ተባለ፡፡

ከእነዚህ ብዙዎቹ ተነሽዎች ወደ ትምህርት ቤት፣ መልሶ ወደ ሌላ ሹመትና የንግድ ሥራ እንደገቡ ይነገራል፡፡ አስገራሚው ነገር በአቅም ማነስና በትምህርት ዝግጅት መጓደል የተነሱት ምንም አይደል፡፡ ‹‹ሙሰኛ›› የተባሉት ግን በሕግ የሚጠየቁበትም ሆነ ያጋበሱት የሕዝብ ሀብት የሚመለስበት ምልክት እንኳን አለመታየቱ ነው፡፡ ጭራሽ የመንግሥትዎ ሙሰኛና ሕገወጥ ካድሬዎች ገንዘብ እየተቀበሉ ከማስተር ፕላን ውጪ የሕዝብ መሬት ሲሸነሽኑ የከረሙበት ቦታ ላይ የሠፈሩ ዜጎች በግፍ ተፈናቀሉ፡፡ ከነልጆቻቸውም ወደ ጎዳና ተበተኑ፡፡

‹‹ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ለመታገል ኢሕአዴግ ወኔ የለውም፤›› የሚሉ ተቺዎች ለመብዛታቸው ማረጋገጫው የክራሞቱ ሁኔታ ነው፡፡ በትልልቅ ባለሥልጣናት ደረጃ በየብሔራዊ ድርጀቱ የሚነሳው ሐሜት፣ በተለይ በዋና ዋና ከተሞች በአንድ ጀንበር የበለፀጉ ጥቂት የሥርዓቱ ነቀዞች ጉዳይ በቸልታ መታለፉ ሕዝቡን ተስፋ አስቆርጦታል፡፡ ሊሸሽግ ያልቻለው የዋና ኦዲተር ሪፖርት፣ የሜጋ ፕሮጀክቶች መጓተት፣ እንደ ‹‹ሜቴክ›› ባሉ የመንግሥት ካምፓኒዎች ላይ የሚነሳ ቅሬታ ሁሉ መንግሥት ሊለወጥ አይችልም የሚል ድምዳሜ እያስያዘ መጥቷል፡፡

በዚህ መሀል እርስዎም ሆኑ የካቢኔ አባላትዎ ‹‹የመልካም አስተዳደርና የሪፎርም ሥራዎ ውጤት እያጣ ነው፤›› ወደሚል ያልተጨበጠ ፕሮፓጋንዳ ገባችሁ፡፡ በምክር ቤት ሪፖርት ሳይቀር ይኼው ተገለጸ፡፡ ግን አሁንም ያለብቃት፣ በትውውቅና በዝምድና መሾሙ ቀጥሏል፡፡ በአገራቸው ጉዳይ ተቆርቋሪ የሆኑና ሊያገለግሉ የሚችሉ ዜጎች በማንነታቸው ብቻ ይጠረጠራሉ፡፡ ይገፋሉም፡፡ ታዲያ ይህ ምንን ያሳያል? መታበይና እብሪትን ካልሆነ፡፡

በአዲስ አበባ የመሬት ካርታ ማውጣት፣ ማሳደስ፣ ውኃና መብራት ማስቀጠል፣ በትራንስፖርት መስክ ሊብሬ፣ ታርጋ ወይም የተሽከርካሪና የአሽከርካሪ ብቃት ማውጣት መሠለፍንና የቀጠሮ ርዝማኔን ብቻ አይደለም የሚጠይቁት፡፡ ጉቦ የሚያስገፈግፉም ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ዜጎች ግዴታቸውን ለመወጣት አስበው ለግብርና ለታክስ ጉዳይ ሲሄዱ ጉቦና ሙስና የሚጠየቁበት አሳዛኝ አገር እየተፈጠረች ነው፡፡

በየአካባቢው ያሉ የቀበሌ አስተዳደር አካላትና ደንብ አስከባሪ ተብዬዎች የየመንደሩ ሽፍቶች ሆነዋል፡፡ ‹‹ሕገወጥ›› በሚሉት ግንባታ፣ የቤት እድሳት፣ ገበያ፣ ንግድ… ስም ወደ ሕጋዊነት እንዲሄዱ ከማድረግ ይልቅ ጉቦ እየተዋጣ እንዲሰጣቸው መድፈር ጀምረዋል፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ ጉቦኛን የሚያፋፋው ሕዝብም ሥርዓቱን እያገዘው ባለመሆኑ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ በትራፊክ ፖሊሶችና ሌሎች ፖሊሶች አካባቢ የሚታየው የሥነ ምግባር መጓደልም በሥርዓት ደረጃ ያለው ብልሽት ውጤት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ጉድ ታዲያ ሕዝብን አያስቆጣም?

በ2008 ዓ.ም. ሌላኛው አሳዛኝ ሁኔታ የተከሰተው በአገሪቱ ሕዝባዊ እምቢተኝነትና ይህን ተከትሎ የተስተዋለው የንፁኃን ሕልፈትና የንብረት ውድመት ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ለወራት በዘለቀው ሠልፍና ግጭት ከ450 በላይ ንፁኃን ዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡ በአማራ ክልልም ቀስ በቀስ እየተስፋፋ በሄደ ግምት ተመሳሳይ የሚባል ቁጥር ያለው ሕይወት አልፏል፡፡ የአካል መጉደሉና የጅምላ እስሩም ቢሆን ሕዝብና መንግሥትን የሚያቃቅር ነው፡፡

ክቡርነትዎ!

በሁለቱ ትልልቅ ክልሎች የተነሳው ግጭት ‹‹ሕዝባዊ እምቢተኝነት ነው›› የሚባልበት ግልጽ መገለጫ አለው፡፡ የተለያዩ የአገሪቱ የፖለቲካ ተንታኞችና ምሁራን እንደሚሉት በኦሮሚያ መነሻው ‹‹የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ የጋራ ማስተር ፕላን›› በአማራ ክልልም ‹‹የወልቃይትና አካባቢው የማንነት ጥያቄ›› ይሁኑ እንጂ፣ የተጠራቀሙ የሥርዓቱ ድክመቶች ድምር ውጤት የፈነቀለው ቀውስ መሆኑን ነው፡፡

ቀዳሚው ጉዳይ ከሁለቱ ሰፋፊ ክልሎች የወጡና በማንነታቸው የተደራጁ የተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ከሌሎችም በባሰ ደረጃ ተገፍተዋል (Marginalized ሆነዋል)፡፡ በዚህም ብዙዎቹ ፓርቲዎቻቸውን በትነው ተሰደዋል፡፡ አሊያም በእስር ቤት የመማቀቅ ዕጣ ገጥሟቸዋል፡፡ ይህ በሌሎች አናሳ ብሔረሰቦች ውክልና ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ያልታየ ግፉአንነት መሠረቱ መንግሥት ጽንፈኛ ከሚላቸው ኦነግና ግንቦት ሰባት ጋር ሊያያዝ ቢችልም፣ በአገር ውስጥ ያሉትም ከመድቀቅና ከመበታተን አልዳኑም (መኢአድ፣ አንድነት፣ ኦፌኮን፣ ወዘተ ያሉበትን ሁኔታ ይመለከቷል)፡፡

እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች ደግሞ መጠኑ ይብዛም ይነስ ደጋፊ የላቸውም ሊባሉ አይችሉም፡፡ አሁን አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት ማንነትን ዋነኛ ጉዳዩ እያደረገ በመጣ ማኅበረሰብ ውስጥ ብሔር ተኮር ድርጅቶችን ማዳከም፣ ተወላጁን ቅር ማሰኘት እንደሆነ መንግሥት ያለመጠርጠሩ ውጤት ነው፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!

ሌላኛው ጉዳይ በእርስዎ ካቢኔ ብቻ ሳይሆን ባለፉት ሩብ ክፍለ ዘመናትም ያልታዩና እንደ ዋዛ ሥር እየሰደዱ የመጡ የፓርቲዎና የመንግሥት ችግሮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ እርስዎ በቅርቡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ በ‹‹ጥልቀት›› ገምግሞታል ያሉት የወልቃይት የማንነት ጥያቄና ግጨው አካባቢ ያለ የሁለቱ ክልሎች ድንበር ጉዳይ እስካሁን ለምን ከረመ?! ቢባል መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ሕዝብን ያለማዳመጥና አድርባይነት (ፍርኃት) ይመስለኛል፡፡

ሰሞኑን በአንድ ታዋቂ ድረ ገጽ ላይ ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ሳይቀሩ፣ ‹‹ጉዳዩን ገፍተን ሄደን በሕዝበ ውሳኔ አንፍታው እንጃ ድርጅቶቹ በትጥቅ ትግል ላይ ከነበሩበት ከ1976 ዓ.ም. ጀምሮ ይነሳል፡፡ አወዛግቦንም ያውቃል፤›› ብለዋል፡፡ እንግዲህ ዛሬ ለዓባይ ወልዱና ለገዱ አንዳርጋቸው ካቢኔ ጦስ ለአገሪቱም መዘዝ ያስከተለ ጣጣ እዚህ ደረጃ የደረሰው መቶ በመቶ በመንግሥትዎ ድክመት ነው፡፡

በተመሳሳይ በኦሮሚያና በፊንፊኔ ዙሪያ የጋራ ማስተር ፕላን፣ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ስለምታገኘው ሕገ መንግሥታዊ ጥቅምና የአርሶ አደሩ ካሳ ጉዳይ መንግሥት ሕዝቡን ያሳመነ ዕርምጃ አለመውሰዱ እምነት ያልጣለባቸውን ካድሬዎች ብቻ ይዞ እየወሰነ፣ ትልልቅ ጉዳዮችንም ሕዝብን ሳያሳምን ይቅርና ሳይገልጽ እንኳ እንዳሻው እያደረገ ‹‹ልማት›› ለማምጣት ይፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ሰፊው የሕዝብ መሬትም ሆነ ለተነሽ ካሳ የሚባለው ገንዘብ በሥልጣን ላይ ባሉና ግብረ አበሮቻቸው እንደሚዘረፍ በግላጭ እየታየ ነው፡፡ ታዲያ ነገሩ እንዴት ቀላል ሊሆን ይችላል?!

ክቡርነትዎ!

በእኔ እምነት ኢሕአዴግን በተለይ ከእነዚህ ሁለት ትልልቅ ሕዝቦች (Majority) ጋር እያቃቃረው የመጣው ሌላኛው ጉዳይ በድርጅትዎ ውስጥ ካላቸው የሥልጣን ውክልና ማዘቅዘቅ አንፃር ነው፡፡ ዛሬ ኢሕአዴግና መንግሥት ይህቺ አገር ከገባችበት ቀውስ ውስጥ የእኩልነትና የውስጠ ዲሞክራሲ ሥርዓትን አጠናክሮ መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ ግድም ይለዋል፡፡

በአገሪቱ ያሉ ሁሉም ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩም በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ብዙኃኑ ያላቸው ሚና እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ አንዳንዶች ይህን የተዛባ አካሄድ ኢሕአዴግ ‹‹ብዙኃኑ በመጠኑ ልክ ሥልጣን ከወሰደ አናሳውን (Minority Group) ይጨቁናል›› የሚል የስታሊን ፍልስፍና ስለሚከተል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ብሔርና ማንነት የሁሉ ጉዳይ ጫፍ እየሆነ በመጣበት የአሁኒቷ ኢትዮጵያ ግን፣ የሥልጣን ብሔራዊ ምጥጥን መዘንጋት ያውም ብዙኃኑን ማግለል የትም ሊያደርስ የሚችል አይደለም፡፡

ከዚህ አንፃር ቀዳሚው ተጠቃሽ የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት፣ የብሔራዊ መረጃ ደኅንነትና የመሳሰሉ ተቋማት ናቸው፡፡ ይኼ በትግል የተገኘ ልምድን ለመጠቀም ሲባል የቆየ መከራከሪያ ዛሬም ድረስ አገራዊ ገጽታ አለመላበሱ ያለጥርጥር ለመተማመን ችግር ነው፡፡ በተመሳሳይ በብዙዎቹ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች (በተለይ ኤጀንሲዎችና ቢሮዎች የብዙኃን ወካይ መሪዎችን ማግኘት ይከብዳል) እዚህ ግባ የሚባል ብቃትና ዕውቀት ሳይኖር የፓርቲ አባል በመሆኑ ብቻ ቁልፍ ቦታዎችን ማስያዝስ የት ያደርሳል?

ሌላ አብነትን ለመጠቆም ለምሳሌ አዲስ አበባ በአዲስ አበቤዎች እንድትመራ ማድረግ አልተቻለም፡፡ እንዲያውም በቀበሌና በወረዳ ደረጃ በአብዛኛው በአንደኛው ድርጅት ካድሬዎች መመራቷ ነው የሚታየው፡፡ ይህ ሁኔታም ሥርዓቱ ምንም ያህል የተጠያቂነት ዘዴ ቢዘረጋ ለሙስና፣ ለመድልኦም ሆነ ለሐሜት መጋለጡ አይቀርም፡፡ በመሠረቱ በተጨባጭም እየታየ ያለው የተደራጀ ሥርዓት አልበኝነት ከዚህ እንዳይመነጭ ያስጠረጥራል፡፡ ስለዚህ አንዱ የትኩረት ነጥብ መሆን ያለበት ይህ የሥልጣን ድልድል ጉዳይ ነው፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር

የትግራይ ሕዝብና ሕወሓት ለአሁኒቷ ኢትዮጵያ መፈጠር (በተለይ ፊውዳላዊና አምባገነን ሥርዓቶችን በማስወገድ) ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ይህን አገራዊ ውለታ በሌሎች ዘንድ ቅቡል ማድረግ የሚቻለውም ሆነ አብሮነታችን ተከባብሮ ለዘመናት የሚዘልቀው ግን፣ በአገሪቱ የሚታይ እኩልነትና ፍትሕ ሲረጋገጥ ነው፡፡

አሁን እየታየ እንዳለው ‹‹የትግራይ ሕዝብ በከፈለው መስዋዕትነት ልክ ሕወሓት የጠቅላይነት ሚና ይኑረው›› የሚል አስተሳሰብ ግን መታረም ያለበት ነው፡፡ ይህን የተዛባ የኢፍትሐዊነት አካሄድም በቀዳሚነት ራሱ ሕወሓትና ኢሕአዴግ ካላረሙት ሌላውም ወገን ታግዬ ካልመጣሁ ሥልጣን አላገኝም ወደሚል ጀብደኝነት እንደሚያማትር የሚያደርግ ነው፡፡ በመሠረቱ የባለታሪኩንና የሃይማኖተኛውን የሰሜኑ ሕዝብን የሚመጥን ተግባርም ሊሆን አይችልም፡፡

ዛሬ ዛሬ በአገሪቱ ሥልጣን የመጨረሻው ደረጃ ላይ ያሉትን እርስዎን እንኳን ‹‹መወሰን አይችሉም!›› የሚሉ ታዛቢዎች እየበዙ ነው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ቢሆንም ባይሆንም የእኩልነት መልክ ያለው ስብጥር ባለመኖሩ ነው፡፡ ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ስመለስም አማራና ኦሮሚያን በመሰሉ ሰፊ ክልሎች ውስጥ ያሉ ተወካዮችን እኮ ከማንነትም በላይ የአውራጃና የክፍለ አገር አጥር በማበጀት ዕውቅና የማይሰጡም ትንሽ አይደሉም፡፡

ከዚህ አንፃር የአማራ ክልልን እየመራ ያለው ብአዴን (ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ድርጅት ውስጥም ሆነ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ያሉ ዘጠና በመቶና ከዚያ በላይ የሚሆኑት ‹‹የአማራ ተወካዮች›› የወሎና የሰቆጣ አካባቢዎች ተወላጆች ናቸው፡፡ ይህ አኳኋን ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከነበራቸው ልምድና ከሥርዓቱ አጋርነት አንፃር የመጣ ነው ቢባል እንኳን፣ እንዴት ኢሕአዴግ 25 ዓመታት ሙሉ ከጎጃም፣ ከጎንደርና ከሸዋ አካባቢዎች አመራሮችን መፍጠር አልቻለም ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ እንግዲህ ይህን ሁሉ የዘርና የመንደር አጀንዳ እየመዘዝን ጎራ እንድንሸነሽን ያደረገንን መሠረታዊ ምክንያትም መለየት ያስፈልጋል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!

አገራችን ፌዴራላዊ ሥርዓት ማራመዷ እኔን ጨምሮ ብዙዎቹ የአገሪቱ ዜጎች ተቀብለውታል፡፡ ነገር ግን ሥርዓቱ በቋንቋ ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆኑ፣ ለማንነትና ለቡድን መብት እጅግ የተለጠጠ ዕውቅና መስጠቱና አገራዊ ማንነትን እየቀበረ ለመሆኑ አልጠራጠርም፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ መሪዎቻችንን ከብሔር ማንነትም ወርደን የተወለዱበትን አውራጃና መንደር ወደ መጠየቅ የደረስነው፡፡ እንዲያው ለነገሩ አገራዊ ስሜቱ የጎላ ‹‹ናሽናሊስት›› የሚባል መሪስ አለን እንዴ?!

እንዲያው ድፍረት ካልሆነብኝ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ይህን የጎሳ ፌዴራሊዝም ቀስ በቀስ እያዳከሙ ወደ ጠንካራ ዲሞክራሲያዊ አንድነት እየመጡ እንደነበረ ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡ በተለይ ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም መባቻ አንስቶ በንግግራቸው የሦስት ሺውን ዓመት ድምር የአገሪቱ ታሪክ ዕውቅና ሰጥተው ነበር፡፡

የባንዲራ ቀን፣ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን፣ የአርብቶ አደር ቀን፣ የአርሶ አደር ቀን፣ የመከላከያ ቀን… በሚል አገራዊ በዓላትና ኢትዮጵያዊ መልክ ያላቸውን ሁነቶችም መፍጠር ተጀምሮ ነበር፡፡ ከሁሉ በላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎችን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተገኙ ሕዝቡን በማነጋገር፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ጎልተው በመታየት በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን በመጋበዝና በማወያየት ‹‹ናሽናሊስት›› ወደመሆን መጥተው ነበር፡፡ ለዚህም ነው በሰውዬው ሕልፈት ወቅት ዜጎች ከጫፍ ጫፍ በአንድ ዓይነት ስሜት (የሚቃወሟቸው ጭምር) ያዘኑት፡፡

ክቡርነትዎ!

እንዳለመታደል ሆኖ ግን እርስዎና የእርስዎ ካቢኔ ይህንን ጅምር ማስቀጠል አልቻላችሁም፡፡ እንዲያውም አቶ መለስ ቀስ በቀስ እያጠበቡት የመጡትን የብሔር ፖለቲካ በማስፋት ዜጎች በመንደርተኝነት ኔትወርክ እንዲተሳሰሩ ተደርጓል፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝና በአሁኒቷ ኢትዮጵያ እኮ አክሲዮንና ማኅበር ብቻ ሳይሆን ዕቁብና የሰንበቴ ትስስር በተወላጅነት ሆኗል፡፡ ለሙስናው መባባስም ሆነ ለዴሞክራሲው አለመጎልበት ጠባብነቱ የፈጠረው ደንቃራም ቀላል የሚባል አልሆነም፡፡

አሁን በአገሪቱ እየታየ ላለው ትርምስም ቀደም ሲል በኅብረ ብሔራዊነትና በጠቅላይ አስተሳሰብ (ትምክህተኝነት) ሲታማ የነበረው ትግል ላይ ነኝ የሚለው ኃይል ሁሉ ጠባብነትና ዘረኝነትን ማራመዱ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ‹‹ውሻ በቀደደው…›› እንዲሉ ጽንፈኛው ተቃዋሚ የአገሪቱን መዳከም በሚሹ ኃይሎች ጭምር እየታገዘ በዘረኝነት ላይ ተመሥርቶ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ያራመደው የጥላቻ ዘመቻ አገር የሚበትን ነው፡፡ ወትሮም ሕዝቡ ወደ አንድነት የሚያመጣው የተጠናከረ ሥራ ባለመሠራቱም ፍጥጫው ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ አድርጓል፡፡

አሁን ባለችው ዓለም ከየትኛውም ጫፍ ይምጣ የሰው ልጅ ሕጋዊ ይሁን እንጂ የትም አገር ሠርቶ መኖር ይችላል፡፡ ለዚህ አባባል ጥሩ ምሳሌ የምትሆነው አሜሪካ ነች፡፡ በእኛ አገር ግን አሁን አሁን እየታየ እንዳለው አማራው በኦሮሚያ ወይም በደቡብ፣ የትግራይ ተወላጅም በኦሮሚያ ወይም በአማራ ክልል በነፃነት ሠርቶ መኖር የሚችልበት ልበ ሙሉነት ጠፍቷል፡፡ ያለሥጋት ለመንቀሳቀስም ዋስትና ያለው አይመስልም፡፡ ታዲያ ይህ ‹‹አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የተፈጠረበት አገር›› ለማለት ይቻላልን?! በእኔ እምነት ይህ ክስተት ከድህነትም በላይ የከፋ ውርደትና ውድቀት ነው፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!

እንግዲህ ሐሳቤን ባጠቃልለው ሳይሻል አይቀርም፡፡ ይህቺ አገር ያለጥርጥር የልማትና ዕድገት ለውጥ እያመጣች ነው፡፡ ነገር ግን ውስብስብ ችግሮች የተበተቧትና የሕዝቡን ግንዛቤና ብልህነት ያላገናዘበ ፖለቲካዊ ሥሪት የቀፈደዳት መሆኗን ማጤን ይገባል፡፡ ለሌላው ዓለም ለይስሙላ ‹‹ዴሞክራት›› ወይም ‹‹ትልቅ መንግሥት›› ነን ማለቱ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ይህን ሰፊና ውስብስብ አገር እንደሚመራ መንግሥት ከሕዝቡ ጋርም መተማመን የሚያስፈልግበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንዳላችሁ ልትመዝኑ ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር እነዚህን ምክረ ሐሳቦች ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡

መንግሥትም ይበልጥ ሕዝባዊ ሆኖ አገሪቱን ለአጭርም ሆነ ረጅም ጊዜ ለመምራት ሙስናን በርትታችሁ ታገሉ፡፡ በተለይ በሕገወጥ ኔትወርክና በብሔር መሳሳብ እየበለፀጉ ያሉ ካድሬዎችዎን አደብ አስገዙ፡፡ ለዚህ ደግሞ ካቢኔዎንም ሆነ በደረጃው ያለውን መዋቅር አሁን እንዳላችሁት ብዙዎችን የሚያሳትፍ ማድረግ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ይልቁንም በስም ብቻ ተቋቁመው፣ በጀት ተመድቦላቸው ሙት የሆኑ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት (ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ እንባ ጠባቂ ኮሚሽን፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን…) ከእስር ቤት ነፃ አውጥቶ ሕይወት እንዲኖራቸው ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ‹‹ልማት አምጥቻለሁ›› በሚል አጉል ጀብደኝነት ዲሞክራሲያዊ ምኅዳሩን ማዳከም ብቻ ሳይሆን ገድሎታል፡፡ በአገሪቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ተገዳዳሪ የለም፡፡ ነፃ ፕሬስ ብልጭ ብሎ እየጠፋ ነው፡፡ በነፃነት መሰብሰብና ሠልፍ ማድረግ ‹‹ወንጀል›› ሆኗል፡፡ የመንግሥትም (የሕዝብ) ሚዲያዎችና የኢሕአዴግ የፓርቲው ልሳኖች (አዲስ ራዕይ፣ ህዳሴ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ) የሚለያያቸውን አጥር አፈራርሰዋል፡፡ የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ ሥራ ተደበላልቆ ቅጥ አምባሩ ጠፍቷል፡፡

እነዚህ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አሠራሮች ቀስ በቀስ ሥር እየሰደዱ ባህል የሆኑት በተለይ እርስዎ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ነው፡፡ እንግዲህ ይህን አለመቀየር ውድቀትን ከማፋጠን ውጪ ምንም ትርፍ አይኖረውም፡፡ በር የተዘጋበት ሕዝብ እንኳን በድህነት ውስጥ ሆኖ ፍላጎቱ ቢሟላም ደረማምሶ እንደሚወጣ ሊቢያና ሶሪያን ብቻ ማየት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ እኛም አገር የሚያቆመው እንደሌለ አይተናል፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ በአገሪቱ በተለይ በአናሳ ብሔረሰቦች ላይ የፈጠረው መነሳሳትና የእኩልነት ተሳትፎ ቀላል አይደለም፡፡ ይሁንና ግን የቀደመውን የአንድ ወገን የበላይነት አስወግዶ አሁንም የሌላ ወገን የበላይነት እንዳይነግሥ መደረግ አለበት፡፡ ይህቺ አገር የሁሉም ዜጎች የጋራ ቤት ልትሆን የምትችለው በመተማመን ላይ የተመሠረተ አንድነት መገንባት ሲቻል ነው፡፡ በመሠረቱ ኢሕአዴግ በአገር አንድነትና በሕዝቦች አብሮነት ላይ የሠራው ሥራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ዛሬ በማንነት ስም፣ በመንደርና በወንዝ ልጅነት መፈላለግ የሚብላላው መብዛት አንድነት የሌለው ሕዝብ ምልክት ነው፡፡ በዚህ ላይ የጥላቻ ንግግርና ዘረኝነት ሲጨመርበት ያለጥርጥር የሚጋብዘው ጥፋት ነው፡፡

ክቡርነትዎ ይህን እውነት ክዶ ዓይንን ከመጨፈን፣ ፊት ለፊት ተጋፍጦ ብሔራዊ መግባባትም በሉት ብሔራዊ እርቅን ማሰብ ግድ ይላል፡፡ በመሠረቱ እኮ የትም ይኑሩ የት የዚህች አገር ዜጎች ሁሉ ኢትዮጵያ የጋራ ቤታቸው ነች፡፡ ታዲያ ስለምን አንዱ የሌላውን መጥፋት እየተመኘ ሊኖር ይችላል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደታየው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚነሱ ሁከቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት እየወደመ ነው፡፡ ሰሞኑን በአማራ ክልል በስምንት የአበባ እርሻዎች ላይ 600 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት መውደሙን መገንዘብ ተችሏል፡፡ በኦሮሚያም ተመሳሳይ ነው፡፡ ይኼ ለምን ሆነ ብሎ መጠየቅ የእናንተ ድርሻ ነው፡፡

በእኔ እምነት ግን በአንድ በኩል ሕዝቡ ያላመነበትና ያልተቀበለው ልማት ይመስለኛል፡፡ በሌላ በኩል ለአርሶ አደሩ ለመሬት ይዞታው የተከፈለው ካሳ ዝቀተኛ ነው ወይም ተመዝብሯል፡፡ ምናልባት እንደ ሦስተኛ ምክንያት የሚነሳው ይኼው ለዓመታት የተሠራበት ጠባብነት የፈጠረው ባለሀብቱን የሩቅ ሰው ከማድረግ ይመነጫል፡፡ (ይህ እንግዲህ ዓለም አንድ መንደር በሆነበት የሉላዊነት ዘመን ሊሰሙት የሚቀፍ ውርደት ነው፡፡ ግን ምን ይደረግ እውነቱ እሱ ሆኗል)

የሕዝቡ ቁጣ የተገለጸበት ሌላው መንገድ ከማረሚያ ቤት እስከ ፍርድ ቤቶችና አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች ያሉ የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን ማውደሙ ነው፡፡ እነዚህን የቢሮክራሲው መሣሪያዎች ‹‹የእኔ አይደሉም!›› ብሎ ያወደመበትን ሚስጥር ከሕዝብ ጋር በግልጽ መወያየት መለየት ያስፈልጋል፡፡ ሥርዓቱ መቶ በመቶ ምርጫ አሸነፍኩ እያለ ራሱን ሲደልል ከዳር እስከ ዳር ሕዝብ እየተነሳ እሳት የሚለቅበት ተቃርኖን ፊት ለፊት ተጋፍጦ አለመፍታት ዕረፍት የሚሰጥ ሁኔታን አይፈጥርም፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ያሉበት ሁኔታ የሚያስጨንቅና ከባድ ጊዜ መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ነገር ግን የዚህች አገር ሁኔታ ሁሉ በእርስዎና በባልደረቦችዎ ትከሻ ላይ መውደቁን አውቃችሁ ልትነሱ ይገባል፡፡ ከውሸት ሪፖርትና ከአስመሳዮች ንግግር ወጥቶ ሀቀኛና አብዮተኛ ትውልድን በድርጅትዎ ውስጥ መፍጠርና አገር ሳይፈርስ ለሌሎቹ ዕድል መስጠትም ብልህነት ነው፡፡ ፈጣሪ ይርዳዎት፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር ብዬ ልሰናበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...