Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየሕዝብ የመብት ጥያቄ እንደ አመጽ መታየት የለበትም

የሕዝብ የመብት ጥያቄ እንደ አመጽ መታየት የለበትም

ቀን:

 በዕለተ እሑድ ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በወጣው ጋዜጣችሁ የፊት ገጽ ላይ ‹‹መሪ የሌለው አመጽ ኢትዮጵያን ወዴት ይወስዳታል?›› በሚል ርዕስ ባወጣችሁት ዘገባ ላይ አስተያየቴን ለመስጠት ፈለግኩ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ መቼም ቢሆን አንቱ የተባሉ የእውቀት ባለቤት ፕሮፌሰሮች፣ ዶክተሮች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ ፖለቲከኞችና ወዘተ ካልሆኑ በቀር አስተያየት መስጠትም፣ መቀበልም አይቻልም ተብሎ በሕግ ወይም በአዋጅ አልተከለከለም፡፡

ስለሆነም ዘገባው እንደሚያስነብበው በእውነት ጋዜጣውም ሆነ ብዙዎች እንደሚሉት ይኼ የሰሞኑ ነገር ሕዝባዊ አመጽ ነውን? ወይስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያነሳው ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ? ደግሞስ በአመጽና በዲሞክራሰያዊ የመብት ጥያቄ መካከል ልዩነት የለም እንዴ? እኔ ግን ይህ የሕዝቡ ጥያቄ የኢሕአዴግ አገዛዝ ሰልችቶኛል የሚል ብቻ ሳይሆን የመብት ጥያቄ ነው እላለሁ፡፡ የመብት ጥያቄ ከሆነ ደግሞ የግድ አመጽ ተብሎ መጠራትና መፈረጅ የለበትም ብዬ አምናለሁ፡፡

ሕዝቦች መብታችን ይከበር ብለው ለመነሳት መንግሥትን ፈቃድ መጠየቅም ሆነ ለሚያነሱት ጥያቄ ተወካይ ወይም አስተባበሪ ወይም መሪ ሊኖራቸው ይገባል ብዬም አላስብም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት የሚባል ተቋም ስላለ፡፡ መንግሥት ካለ ደግሞ የሕዝብ ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡

የሪፖርተሩ ዘጋቢ ሆነ ጋዜጣው ተጠሪነቱም ሆነ ውክልናው ለሕዝብ ይመስለኛል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ሕዝብን የመምራት፣ የማስተማር፣ የማሳወቅ እንዲሁም ሕዝብንና አገርን የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ታዲያ ሕዝብ እኔ የምፈልገው አስተዳደር ይኼን አይደለም ሲል ጥያቄውን አግባብ ባለው መንገድ ማስተናገድ የማን ፈንታ ነው? ይኼን ጥያቄ ለማስተናገድ የተሰየመ፣ ወይም የሚቃወም የፖለቲካ ፓርቲ የለህምና አላስተናግድም እንዴት ይባላል? ሕዝብ በቀጥታ ያልተጠየቀባቸው፣ ነገር ግን ሕዝብን የሚመለከቱ ጉዳዮች የተወሰኑበትን መንገድ መመልከት ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡  

በምሳሌ ላስረዳ፡-

  1. የሰንደቅ ዓላማ፣ የክልል ወሰን፣ የአገር ድንበር ክለላ ከመከናወናቸው በፊት ለሕዝብ ውይይት ቀርበው ሕዝብ ተወያይቶ አፅድቋቸዋል ወይ?
  2. የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች ስለመኖራቸው መንግሥት ቢያምንም፣ ከሕዝብ ጋር ተወያይቶ የማያዳግም መፍትሔ ወስዷል ወይ?
  3. በሙስና የተዘፈቁ የአገር መሪዎችንና አመራሮችን ሳይፈራና ሳይደራደር ተዋግቷቸዋል? መዋቅራቸውንስ አፈራርሷል?
  4. የአንድ ብሔር የበላይነትን አስወግዶ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ያማከለ የሥልጣን ክፍፍል አድርጓል?

ጋዜጣው እንደዘገበው ሳይሆን አመጽ ማለት ለእኔ እስከሚገባኝ መንግሥት በግድና በኃይክ ይውረድ ይቀየር ሲባል ብቻ ነው፡፡ በኢሕአዴግ አገዛዝ አልመራም ብሎ ሲያምጽ ነው፡፡ እኔ ያየሁት ይኼን አይደለም፡፡ መንግሥት በጥቂት ቦታ፣ ጥቂት አመጸኞች፣ ሕገ መንግሥቱን ለመናድ ሲሉ የወጡ ሥራ አጥ ‹‹ቦዘኔዎች››፣ የቀድሞ ሥልጣን ናፋቂዎች ወዘተ እያለ ስም ከመስጠትና በአጓጉል ከማጣጣል ይልቅ ወደ መፍትሔው ማምራቱ ይሻለዋል፡፡

ጋዜጣው ለእውነት ብሎ ከቆመ አድርባይነትና እወደድ ባይነት ወይም ብሔርተኝነት ካላጠቃው የአመጽና የመብት ጥያቄ ልዩነትን በአግባቡ ሊያሳይ ይገባዋል፡፡ ለነገሩ በእኔ አመለካከት ከጀምሩም በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እንዳለን ስለማላምን፣ ዛሬ የምናያቸው ችግሮች የተፈጠሩት በዚያ ምክንያት ነው ብዬ ለመናገር እደፍራለሁ፡፡

ኢሕአዴግ አፋዊ ሕዝባዊነት ስለሚያጠቃው ሕዝባዊ ጥያቄዎች ሲነሱበት ይደናበራል፡፡ ሕዝባዊ መሠረት የሌለው መንግሥት ሕዝባዊ ጥያቄዎችን ከመመለስ ይልቅ ለሚነሱ ጥያቄዎች የማይገባ ስም መስጠት ይቀለዋል፡፡

እውነቴን ነው በአሁኑ ወቅት ከምርጫ 97 ብዙ በመማር መስተካከል ሲገባው፣ በመዋቅሩ በርካታ መሠረታዊ ለውጦች ማድረግ ሲገባው፣ ‹‹ለፉገራ›› ብቻ ‹‹ሕዝብ አስተምሮናል፣ ችግሮቻችን እንፈትሻለን›› ባለፈበት አንደበቱ የሠራውን ሥራ ምን እንደሆነ ኢሕአዴግ ያውቀዋል፡፡ እናም ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ፣ በአረም ይመለሱ፤›› እንደሚባለው ሆነና ይኼው ዛሬ ላይ ለምናየው ነገር በቃን፡፡

የዜናው ዘጋቢ በሬዲዮ ፕሮግራም ላይ የወቅቱ የሕዝብ ንቅናቄ (የመብት ጥያቄ) ከምን የመነጨ እንደሆነ ሲወያዩ መስማቱን እንጃ እንጂ፣ ነገሩ እየተባ ያለው ኢሕአዴግ የችግር ምንጮቹን በደንብ ስላልተቆጣጠረ ነው ይህ የተፈጠረው፡፡ ‹‹እነ ግንቦት ሰባትንና አባሎቹን ባለመቆጣጠራችን ነው ችግሩ የተፈጠረው፡፡ ጥቂት ትምክህተኞች በአንዳንድ ቦታ ሕገ መንግሥቱን ለመናድ በመጮኻቸው አንደናገጥም፤›› በማለት ሲናገሩ ያደምጥናቸው የኢሕአዴግ ሰውዬ ምስክር ናቸው፡፡ ሌላይቱ ግን ‹‹ስድስት መቶም ይውጣ ስድስት ሺሕ ሰው፣ የተካሄድ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሠልፍ ነው ነገር ግን ፈቃድ ማግኘት ነበረበት፤›› በማለት ሐሳብ የሰጠችም ነበረች፡፡ እዚህ ላይ የተንጸባረቀውን ልዩነት ልብ ማለት ይገባል፡፡ ለመሆኑ የትኛው ወታደራዊ አገዛዝ ነው በሕዝብ ማዕበል ያልተወሰደው? ብዙ ወታደር፣ መሣሪያና ደጋፊ ቢኖረውም ሕዝባዊ ማዕበል የተነሳበት መንግሥት፣ ከሕዝብ ሞገድ የሚድንበት ሥልጣን የሚኖረው አይመስለኝም፡፡

በመሆኑም ጋዜጣው ሲዘግብ፣ ጋዜጠኛውም ሲከትብ ከእውነት ጋር ይቁም ከሕዝብ ጋር ይወግን፣ የመንግሥትንም ሆነ የሕዝብን ክፍተቶች ይጠቁም፡፡  ሕዝባዊ አመጽ ማለትና ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ የመብት ጥያቄ ልዩነት እንዳላቸው አምናለሁ፡፡ ጋዜጣውም ሆነ ዘጋቢዎቹ ይህንን ልዩነት አውቀው ያሳውቁን፡፡

(ኢያሱ አበበ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...