በዕንቁጣጣሽ ዋዜማ ላይ ሆኜ ዓምና የተባለውን፣ 2008 እያሰብኩት ነበር፡፡ እንዴት ባጀን፣ እንዴትስ ከረምን እያልኩ ሳውጠነጥን ነበረ፡፡ ጊዜ ሲወስድ ለካ እሱም እያሳሳቀ ኖሯል፡፡ ትናንት ላይ ሆኜ የዛሬ 41 ዓመት በኅዳር ወር 14ኛ ቀን ላይ ዓለምን ያስደመመ ኢትዮጵያን የቅድመ ሰው ዘር መገኛነትን ያመላከተ የሉሲ ግኝት በዓለም ዙሪያ ሲነዛ፣ ለኛ ከቁብ ያልቆጠርነው ወይም ያልሰማነው የዓመተ ፍዳው መጀመሪያ ዘመነ ደርግ በቀድሞ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ግድያ መፈጸሙ ነበር፡፡ ከሉሲ ጋርም ሳንተዋወቅ ለዘመናት ዘለቅን፡፡
የተሸኘው ዓምና ላይ ሆነን ስለ ሉሲ አዲስ ዜና የሰማንበት አዲስ ግኝት ከ3.2 ሚሊዮን ዓመት በፊት ስለነበረው አሟሟቷ ‹‹ከዛፍ ላይ ወድቃ›› መሆኑን ሳይንቲስቶች ማረጋገጣቸውን በዓለም ዙሪያ ሲነዛ ኢትዮጵያ ባለድርሻ ሆናም ዜናው ሲበሰር በአገር ውስጥ በተፈጠረው አለመረጋጋት ሳቢያ እንደያኔው ትኩረት አጥቶ ነበር፡፡ የሁከቱ በየፈርጁ መፈጠር፣ አመፁ የሰው ሕይወትን መቅጠፍ ተከትሎ ስለ ሉሲ ደንታ ያልሰጣቸው እንዳልነበሩ ማሳያው በማኅበራዊ ሚዲያው የተሠራጨው ነፀብራቅ ነው፡፡ ማላገጡ፣ መሳለቁ፣ ወዘተ ታይቷል፡፡ ‹‹ፍሬ ማጣት‹‹ ያሉም ነበሩ፡፡
ምስኪን ሉሲ ያኔ ስትገኝ በአገሯ ተገቢውን ክብር ሳታገኝ ቀርታ፣ ዘንድሮም ተመሳሳይ ነገር መፈፀሙ እንዴት ነው ነገሩ? አሰኝቶኛል፡፡
2008 ሐሴትና ብካይ (ደስታና ሐዘን) አፈራርቆብን አልፏል፡፡ ውጣ ውረዱ ግን ከጉዳት እስከ ኅልፈት የዳረገ ሮሮና እንጉርጉሮው የበረከተበት ሆኖ ሳየው ያገሬ ገበሬ ያንጎራጎረው ታወሰኝ፡፡ ‹‹ራቤ ጥማቴ ዕርዛቴ ሦስቱ ይደበድቡኛል ባንድ እየዶለቱ››፡፡
ሉሲን እያወቅናት እንዳላወቅናት የሆነበት መንገድ ቢታይም እኔን ያስገረመኝ ብሎም ያሳዘነኝ እንዲያው ምን ይሻላል? ያሰኘኝ በሪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ከአንድ ወርቅ አልማዛዊቷ ካስገኘችው በቀር በለመደቻቸው ውድድሮች ለድል አለመብቃቷ ያሳዘናቸው የቀድሞ ዕንቁ አትሌቶች፣ ላሰሙት ድምፅ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት ነበር፡፡
በኃይሌ ገብረሥላሴ ፊታውራሪነት የተሰባሰቡት የኦሊምፒክ ባለወርቅ አትሌቶችንና አሠልጣኞችን ሚኒስትር ዴኤታው ‹‹አናውቃቸውም›› ማለታቸው የት እንደደረስን ያሳየን ነበር፡፡ በጅረት ተጠራርተው በስፖርት ሚኒስቴርና በብሔራዊ ፌዴሬሽን ውስጥ ያለዕውቀት በድፍረትና በስህተት እየተሠራ ባለው ሥራ ለአገሪቱ አትሌቲክስ ውድቀት እየታየበት ነው ኧረ ታረሙ፤ ሥልጣኑን ለባለሙያዎች አስረክቡ በማለታቸው ነበር፤ ‹‹እናውቃችሁም›› የተባሉት፡፡ ‹‹የስፖርቱ ባለቤት እኛ መሆናችንን ማመን አለባቸው፤ አሁን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነን፡፡ ከዚያ ወደ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንመጣለን›› በማለት የኦሊምፒኩ ጀግና ኃይሌ ገብረሥላሴ መናገሩ በየሚዲያው ሰምቻለሁ፡፡
ኃይሌ እውነቱን ነው፡፡ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በአመዛኙ መች ከኦሊምፒክ መርሕ ጋር በቅጡ ተዋወቀና፡፡ በወገንተኝነት እንጂ በስፖርቱ ያለፉ ባለሙያዎችን ያሰባሰበ አለመሆኑ የሚያሳየው በየመድረኩ ድምፃቸውን አለመሰማታቸው ነው፡፡ በሪዮ ስለተገኘው ውጤት መግለጫ በጽሕፈት ቤቱ ባለሙያዎች እንዲሰጥ መደረጉ አመራሮቹ የት ሄደው ነው? አሰኝቶኛል፡፡ ለሪዮ ኦሊምፒክ ያሳተሙት መጽሔት አንዱ የባዶነት ነፀብራቅ ነው፡፡ ‹‹ቂጣ የለም እንጂ ወተት በነበረ፤ በዚያ ፉት አርገን እንበላ ነበረ›› ሆኖብኛል፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ እንደጻፈው የተዘበራረቀ ታሪክ፣ የተፋለሰና ለዕውነታ የራቀ ነገርን ይዞ ይኼ ነው ‹‹ታሪኬ›› ብሎ ለሪዮ ኦሊምፒክ መድረክ ማቅረቡ፣ ታሪኩን የማያውቁ እነሱ፣ ታሪኩን በቅጡ ለማያውቁ ጭፍሮቹ ሰጥቶ የአገር መሳለቂያ ያደረገንን ተቋም መበተን እንዴት አልተቻለም?
ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በውስጤ ባለሙያ አለኝ ብሎ አፉን ሞልቶ ለመናገር የሞከረው በ11ኛው ሰዓት ላይ ‹‹በሞተ ከዳ›› ተተክተው የገቡት በርግጥም ባለሙያ የሆኑት የአዲስ አበባው ተወካይ ናቸው፡፡ የአገሪቱ ቁልፍ ክለቦች የተካተቱበት አዲስ አበባ ከተማ፣ ለዘመናት በብሔራዊ ፌዴሬሽን ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ወንበር እንዳያገኝ ተገፍቶ አንድም ክለብ ከሌላቸው አካባቢዎች ለአመራርነት ተካተው ላየ ሳይገረም አይቀርም፡፡
ስፖርታችን፣ ኦሊምፒካችን በተለይም አትሌቲክሳችን ከምንጊዜውም በላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ በስፖርቱ ቤት፣ በየፌዴሬሽኑ፣ በኦሊምፒኩ አብዮት ያስፈልጋል፡፡ ስፖርት ሚኒስቴሩም ሆነ የፌዴሬሽን አመራሮች ‹‹አበረታች›› እያሉ የሚያደላድሉት ነገር፣ ግን የድመቷን ተረት ነው የሚያስታውሰኝ፡፡
ውርዬ ሌሎች ድንጋይ ላይ ተቀምጠው አይታ፣ እሷ ቅቤ ላይ (በገረረ ፀሐይ) ቁጢጥ ብላ ‹‹ተደላድለን ተቀምጠናል›› አለች፡፡ ቅቤው ግን እየቀለጠ ነው፡፡
- (ዓለም ፀሐይ መብራቱ፣ ከሳሪስ)