ሰላም! ሰላም! እነሆ እዚህ ደረስን። በእምብርክክ፣ በዕርምጃ በሩጫ ከርመን ከራርመን አይቀየር የለ ዘመን ቀይረናል። እንግዲህ ምን ያህሎቻችን ተቀይረናል? ምን ያህሎቻችን ተቀያይሮብናል? የሚለውን ቤት ይቁጠረው። አንዳንዱ ዘመን እንደ ማልያ ተቀምጦ ይቀያየራል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ እንደ ንግርተ ‘ትራንስፎርመር’ በልማትና በልማታዊነት ራሱን ይቀያይራል። ዛሬ የሆድ የሆዴን የማጫውታችሁ ከቤቴ ሳልወጣ ነው። ‘ትራንስፈር ዊንዶ’ እና ‘ትራንስፎርሜሽን’ ዕቅድ ያልደረሳቸው ወገኖቼን እያሰብኩ፣ ማንጠግቦሽ ቤቱን ሞቅ ሞቅ ስታደርገው አያታለሁ። ቡና ቀራርቧል። ዳቦ ተዘጋጅቷል፡፡ መብራት የለም። ጠላ ቀርቧል፡፡ ውኃ ሄዳለች። “በተገኘው መጠቀም ነው ይኼንንስ ማን አየብን?” ትለኛለች ወዲህ ወዲያ ሽር ብትን የምትለው ውዷ ባለቤቴ። እኔ እንደ አቀማመጤ ሳይሆን እንደ መቀመጤ ብዛት በዚህ ሰዓት ምንም የሌላቸውንና ያጡትን የተቸገሩትን አስባለሁ። በአገር ላይ የደረሰውን መከራ እያሰብኩም እተክዛለሁ፡፡ በሌላ በኩል ጉቦ ካላመጣችሁ፣ ጥቅማ ጥቅም ካላቀረባችሁ፣ ተራራውን ሜዳ ሸለቆውን አቀበት ካላደረጋችሁ እያሉ ወገኔን ቀንበር የሚጭኑበትን አስባለሁ።
ታዲያ ከማሰብ ሌላ ምን ተረፈን? ምንም! ሐሳብ ገንዘብ ቢሆን ኖሮ ይኼኔ በደካማ የቁጠባ ባህላችን ባልታማን ነበር። እውነቴን እኮ ነው። ዳሩ በአደላቸው አገሮች (የታደለም ቢሆን ሠርቶ ነው) ችግር የሆነው የሐሳብ እጥረት ሆኗል። ይኼው ለአንድ ወሳኝ ቢዝነስ ከአንድ ወዳጄ ጋር አውሮፓ ድረስ መለስ ቀለስ ማለት ጀምሬላችሁ ብዙ ነገር እየታዘብኩ ነው። ጊዜና ዕድሉን ለጠበቀ የበረሃ ብቻ ሳይሆን የውኃም መንገድ አለ። ምን ታዘብክ ብትሉኝ? እዚያ ሁሉ ነገር ሞልቶ ሐሳብ አጥሯል። ሐሳብ ከማጠሩ የተነሳ ሲገኝ በገንዘብ ይተመናል። የሐሳብ ባንክም ደህና ጆሮም አላቸው። ሰምቼ ሳይሆን ዓይቼ ነው የማወራችሁ። መንገድ እንግዲህ የማያሳየን የለም! ዘንድሮ በዓይናቸው ሳያዩ በጆሮ ብቻ እየሰሙ የሚናገሩ በዝተዋልና አደራ ጠንቀቅ በሉ።
‹‹በል ተነሳ እንጂ ዳቦውን ቁረሰው። ፈረንጅ አገር ደርሼ መጣሁ ብለህ ባህሉን ልተወው ነው?›› ትለኛለች ማንጠግቦሽ። እግዜር ይስጣት ማንጠግቦሽ የእኩልነት አስተሳሰቧ ምኅዳር ሰፊ ነው። ከመስፋቱ የተነሳ አንዳንዴ ጨቋኝ ባል እያስመሰለችኝ የባሻዬን ልጅ አማክረው ነበር። እሱም፣ ‹‹እሱ መርቆ ሰጥቶሃል እጅ ነስተህ ኑር፤›› ብሎኝ ዝም ይላል። ከዘመናት የምድር ቆይታየ በኋላ እንዳልኳችሁ መንገዱን ጨርቅ አድርጎልኝ አውሮፓን በጨረፍታ ስቃኝ ምን አየሁ? ቆራሽና አስቆራሽ ብሎ ነገር መረሳቱን አየሁ። ታናሽና ታላቅ፣ አጭርና ረዥም አላይ ብዬ ገርሞኝ ነበር። ካለመነካካት ጥጋቸው፣ ካለመደራረስ ችሎታቸው፣ ከመከባበር ሥልጣኔያቸው ብዛት እያንዳንዱ ሰው በራሱና በኑሮው ዙሪያ የሚሽከረከር ፕላኔት ሆኗል። እናም ማንጠግቦሽ እኔ ተነስቼ ዳቦውን እስክባርክ ስትጠብቅ በመብት የተቃኘና በፍቅር የተቃኘ እኩልነት ለውጡ ኩልል ብሎ ታየኝ።
ዘመንና ቁጥር ታሪክ ተናጋሪውን አድማጭ፣ አድማጩን ተናጋሪ ማድረጉ ሳያንስ ቁልቁልና ሽቅብ እያስተያየን ሄዶ የሚመጣው መስከረም ራሱ መቼ ይታክት ይሆን? እያልኩ ተነስቼ፣ ‹‹በስመአብ. . .›› አልኩ። ‹‹በወልድ. . .›› ብዬ ስቀጥል፣ ‹‹ሂድ ውጣ፣ ውጣ . . .›› ብላ ጮኸች። ማንን ነው? ብዬ ስዞር የበግ ደም መፍሰሱን ዓይቶ የሠፈራችን ውሻ አንገቱን ብቅ አድርጎ ዓይን ላይን ተያየን። ‹‹ኢትዮጵያ መፈጠርሽ በጀሽ እንጂ ይኼኔ ሆላንድ ብትሆኝ ኖሮ ምናልባት አሁን የጮህሺው በሠርጉ ዕለት ሊጠራሽ የሚያስብሽ ውሻ ላይ ይሆን ነበር፤›› አልኳት። ‹‹ምንድነው የምታወራው? በል ቁረሰው. . .›› ብላ ወደ ሥራዋ ተመለሰች። በአጭር ቀናት ሆላንድ አገር ቆይታዬ አንድ ቀን ባረፍኩበት የደንበኛዬ ቤት ፖስታ ይመጣል። ተንቀልቅዬ ፖስታውን ስከፍተው የጥሪ ካርድ ነው። ‹ዴዚና ሱዚ በሠርጋችን ላይ እንዲገኙ ይጋብዟችኋል› ብሎ አረፈው። ዓይኔ ኩል የተኳለች ጉደኛ ውሻና ይኼን የሠፈሬን ጎፈሬያም የመሰለ ባለካባ ውሻ ላይ አረፈ። የሦስተኛው ዓለም ሰው ብቻ ሳይሆን ውሻም ነው ከአንደኛው ዓለሜ የሚለየው ለማለት ነው!
በስም ቢለያይም እንግዲህ ሰውም የእንስሳ መደብ ነው። ታዲያ የሰው ልጅ ከሌላው እንስሳ የሚለየው ማሰብ በመቻሉ ነው ይባላል። መቁጠር በመቻሉ የሚለው የመጣው በኋላ ነው። እኛ የሦስተኛው ዓለም ሰዎች ቁጥር ከፊት ሐሳብ ወይም ‹አይዲያ› ከኋላ አድርገነው ፍዳችንን እናያለን። ይኼው ዘመን ቆጥረን ቆጥረን የለውጥ ያለህ ስንል ኖረን በቃ ከዚህ ወዲያ መከራና ችግር አሳር ደህና ሰንብት ሲባል ድንገት ሰማን። ምን መጣ? ሚሊኒየም፡፡ ቁጥር፡፡ ሚሊኒየምና ትራንስፎርሜሽን ውኃ የተራጩ አብሮ አደጎች ናቸው ከተባልን ወዲያ አኃዝና አኃዛውያን በዙ። እግዜር ይመስገን ከሚሊኒየም በኋላ ሚሊየን ተናቀ። በዚያው ልክ ሚሊየኖች ሽቅብ ወጡ ቁልቁል ወረዱ።
ምን ለማለት እንደፈለኩ እኔ ራሴ አሁን ግራ ገባኝ። ግን የሚገባኝ አንድ ነገር አለ። በእኛና በአንደኛው የዓለም ሰዎች መሀል ያለው ልዩነት አንድና አንድ ብቻ ነው። እንግዲህ ቁጥር ማስቀደም ለሚቀናው ሰው አንድ ሁሌም መጀመርያው ናት። አንድ ስል ያየሁት እኔ ለምሳሌ በአደጉት አገሮች ማንም ማንንም አይለውጥም። ማንም ከምንም ነገር ጥገኝነት ነፃ ነው። ዓመት ቢመጣ ዓመት ቢሄድ ደንታ የላቸውም። ጊዜን ያሳልፉታል፣ ግን ደግሞ በአግባቡ ይጠቀሙበታል። የሙሉ ወይም የጎደሎ ቁጥር ፎቢያ ኑሯቸው ላይ ለውጥ እንደማያመጣ ያውቃሉ። አንዱ ባለፈው እዚህ ከመጣሁ በኋላ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‹‹ጎዶሎ ቁጥር እኮ ነው ቀን እያበላሸ፣ ረሃብና ግርግር የሚበዛበት አንበርብር። ምን ተሻለን?›› ሲለኝ ጥገኝነት ሳልጠይቅ መቅረቴ ቆጨኝ። አንዳንድ ጠማማና ያልተቃኑ አስተሳሰቦች እንደ ፖለቲካ ጥሩ ማማሃኛ ቢሆኑ እውነቴን ነው የምላችሁ ተለያይተን ነበር!
እናላችሁ ይኼው አዲስ አበባን ጨርሼ ዓለም ማደረስ የጀመርኩበት ሥራዬ ገና በእንጥልጥል ቢሆንም ከአጀማመሩ አጥጋቢ ይመስላል። ደንበኛዬ እዚህ አገር ጭኖ አምጥቶ መሸጥ የፈለገው የመስታወት መቁረጫ ማሽን አየር ላይ ጣጣው በማለቁ ኮሚሽኔ እጄ ገብቷል። ‹‹አንበርብር ብር አላዋጣው ብሎ በዩሮ ማሰብ ጀምሯል ይሉሃል፤›› ሲሉኝ ነበር ባሻዬ። ምቀኛ አታሳጣኝ ብዬ እኔም አደብ ገዝቼላችኋለሁ። እንኳን ለደላላ ለተደላይ አደብ መግዛት ጭንቅ በሆነበት ጊዜ አደብ መግዛቴን በበኩሌ ዱባይ መሬት ከመግዛት ለይቼ አላየውም። የምሬን ነው። ይኼን አስቤ ለብቻዬ ፈገግ አልኩ። ማንጠግቦሽ ጥብስ ትጠብሳለች። ቤት ያፈራውን ቅመሱ ብዬ የጠራኋቸው ጎረቤቶቼ ‹ዩሮ ያፈራውን በለን እንጂ› እያሉ ሲጎርፉ አንድ ብላቴና ሰተተ ብሎ ገባ። ‹ማሙሽ የማን ልጅ ነው ደግሞ?› እያልኩ ሳባብለው ‹ጋሽ አንበርብር እንቁጣጣሽ‹ አለኝ። ‹‹በየዓመቱ ያምጣህ!›› ብዬ ‹‹የታለ የሳልከው ሥዕል?›› ስለው ከኪሱ አንድሮይዱን አንደርድሮ አውጥቶ የቢዮንሴን ፎቶ አሳየኝ።
‹‹ምንድነው እሱ?›› ስለው፣ ‹‹ወረቀት መጨረስ ድሮ ቀረ። እኔ የሳልኩት ነው፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ዓይኔ ደክሞ ነው ብዬ ‹እስቲ እስቲ› እያልኩ ተቀብዬ ለአንድ ጎረቤቴ ሳሳየው ‹‹አዶቤ ፎቶ ሾፕ ነው፤›› አለኝ። የባሰ አታምጣ። ግራ ገባን እኮ እናንተ? እፍረት ደህና ሰንብት ማለት ሕፃናቱን ውስጥ ጭምር ሰርፆ ገባና አረፈው። ሁለቴ ብር አውጥቼ ስሰጠው ዓይን ዓይን እያዬ ‹‹ምን ገዝቼ ልምጣ?›› አለኝ። የምልከው መስሎት ነዋ። ‹ሁለት ብር ምኔ ናት› ነዋ። እንደለመደብኝ ‹በል ጥፋ ከዚህ› እንዳልለው ሳይቸግረኝ አውሮፓ የልጅ አስተዳደግን ዓይቼ መጣሁ። ዕድሜ ለመሰንበት በአዶቤ ፎቶ ሾፕ እንቁጣጣሽን በኮፒ ፔስት ፎቶ አንቆጥቁጠው የሚያውሉን ልጆች ወለድን! አይገርምም?
በሉ እንሰነባበት። ዘመን እንደሆነ ያሰነባብታል እንጂ አይሰናበትም። ቋሚና አላፊም ቢሰነባበቱ አይታክቱም። ቸር ተመኝተን በቸርነቱም እዚህ ደረስን። ስምንትን ሽረን ዘጠኝን ጻፍን። ጻፈብን እንዳልል ለዘመን አድልቼ የጻፉበትን የት አድረጋቸዋለሁ? እኔስ የት ላይ ነኝ? የሚለውም አለ። ፍርድ እንደ ራስ እያሉ ፈራጅ አብዝተውብን ፍትሕና ሚዛኑ ተዛባብን። ውበት እንደተመልካቹ እያሉ ዕይታና አተያይ እንደ አሸን እየጎረፈ እውነትና ሐሰት መለየት ከበደን። ‹‹ያልከበደን ዘመን ሸኝቶ መቀበል ብቻ ነው፤›› ሲሉኝ ነበር ባሻዬ። ‹አበባ ይሆሽ – ለምለም› የዘፈኑ እናቶች በለምለምና በተራቆተ ምድር መሀል ያለውን ልዩነት የሚዘነጉ ልጆች ወለዱ። ‹ባልንጀሮቼ – ለምለም› ብለው ያዜሙ ትውልዶች ባልንጀራውን ከራሱ በላይ የሚወድ ሳይሆን ለራሱ ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ትውልድ ተኩ። ፍርድ እንደራስ ከሆነ፣ ሎጂክ ዓይኑ ይጥፋ ከተባለ እኔም የመፍረድ መብቴ የተጠበቀ ነው። ይብላኝ ለጠባቂዬ።
እናም ስቀጥል አዎ ‹ባልንጀሮቼ – ግቡ በተራ – ለምለም› ያሉ ሰብሳቢዎች የሕይወት ውሉና ግቡ እየተምታታበት አገሩን ትቶ ወደ ሰው አገር የሚገባ ጥገኛ አፈሩ። ‹እንጨት ሰብሬ› ያሉት ማንም ተነስቶ ለገዛ ጥቅሙና ዓላማው የሚማግዳቸው እንደ እንጨት የሚሰበሩ ዜጎች ተኩ። ‹ቤት እስክሠራ› ያሉት ይኼው እስከ ዛሬ የእናት የአባቶቹን ቤት የመሥራት ህልም ያላሳካ ትውልድ በዓይናቸው እያዩ የእርጅና ዘመናቸውን በፀፀት አገባደዱ። በአጠቃላይ ጎበዝ ‹አደይና የብር ሙዳይ› እንደ መስቀል ወፍ በዓመት አንዴ የሚዘፈኑ እንጂ የሚጨበጡ አልሆነም። ይኼም የዕድገቱ ውጤት ይሆናል ብለን እንገምት? እስኪ የከርሞ ሰው ይበለን? ምናልባት ከርሞ ቢለዋወጥ የማይታክተው ዘመን ትተን ራስን ለመለወጥ ራሳችን ላይ ተግተን እንገናኝ ይሆናል። ውጥረቱን አላልተን፣ ኩርፊያውንና ንትርኩን ትተን፣ በአንድነት የጋራ መሶቡን የምንቋደስበት ዓመት ይሆንልን ዘንድ እየተመኘን ብንለያይስ? በአዲሱ ዓመት የላላው ከሚወጠር ውጥሩ ቢላላስ? ለዓላማ ብቻ ሳይሆን ለመርህም እንኑር! መልካም አዲስ ዓመት! መልካም ሰንበት!