Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በተጓዙበት ርቀት ልክ የሚያስከፍሉ 836 ሜትር ታክሲዎች ወደ አገር ውስጥ ገቡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር እንዲገቡ ከተፈቀደላቸው 1,163 ሜትር ታክሲዎች መካከል 836ቱ እንደገቡ፣ የተቀሩትም በመስከረም ወር ተጠቃለው እንደሚገቡና በአዲሱ ዓመት ሁሉም ሥራ እንደሚጀምሩ ታውቋል፡፡

ታክሲዎቹ የተዘጋጀላቸውን ታርጋ እየወሰዱ እንደሚገኙ፣ ትራንስፖርት ሚኒስቴርም በተጓዙበት ርቀት ልክ ሊያስከፍሉ የሚገባቸውን ታሪፍ እያዘጋጀ እንደሚገኝ ዓርብ፣ ጳጉሜን 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በተዘጋጀው  ፕሮግራም ወቅት ተገልጿል፡፡

‹‹መንግሥት በተሽከርካሪ ሊያገኝ ከሚችለው 165 ከመቶ በላይ የሆነውን የጉምሩክ ቀረጥ ገቢ ሙሉ ለሙሉ በመተው ዘርፉ እንዲዘምን፣ ኅብረተሰቡም በአገልግሎቱ እንዲረካና የከተማዋ ገጽታ እንዲገነባ ሲባል ታክሲዎቹ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ፈቅዷል፤›› ያሉት የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያም፣ ሒደቱ በኮሚቴ ክትትል ሲደረግበት መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ታክሲዎቹን ተደራጅተው ያስመጡት 26 ድርጅቶች ሲሆኑ ዘሉሲ፣ ዳናስና አዲስ ሜትር ታክሲ ተብለው በአክሲዮን ኩባንያነት ተዋቅረው መሥራት የጀመሩ ማኅበራት  ቀዳሚዎቹ ሆነዋል፡፡ ወደ አገር ውስጥ የገቡት የቶዮታና የሊፋን ተሽከርካሪዎች ሲሆኑ፣ የሊፋን 530 ሞዴል መኪኖች ዋጋ 513,000 ብር እንደነበር ነገር ግን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በመደረጉ የአንዱ መኪና ዋጋ ከ228,000 ብር ባልበለጠ ሒሳብ መግዛት መቻላቸውን የማኅበራቱ አባላት ገልጸዋል፡፡ የዘሉሲ ማኅበር አስተባባሪ ከሆኑት መካከል አቶ ዓለምሸት ከበደ እንደሚሉት፣ ባለንብረቶቹ 30 ከመቶውን የመኪኖቹን ክፍያ በራሳቸው የፈጸሙ ሲሆን፣ 70 በመቶውን ገንዘብ ያበደራቸው ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ ነው፡፡ ብርሃን ባንክ 21 ማኅበራትን ተጠቃሚ ያደረገና 800 መኪኖችን ለማስመጣት ያስቻለ ከ131 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በብድር ሰጥቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የታክሲ ማኅበራቱ ባስመጧቸው ተሽከርካሪዎች በሙሉ በቻይና ባንክ በኩል ኤልሲ በመክፈት ዝቅተኛ የአገልግሎት ክፍያ ህዳግ በማመቻቸት ተሽከርካሪዎቹ ከተመረቱበት ቦታ ቀጥታ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ድጋፍ አድርጓል፡፡

ሁሉም የማኅበራቱ አባላት እስካሁን በእያንዳንዱ በገዙት መኪና 89,000 ብር አዋጥዋል፡፡ የሚቀርባቸውን 159,000 ብር በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከፍለው እንዲያጠናቅቁ ይጠበቃል፡፡

 መኪኖቹ የተገጠመላቸው የአቅጣጫ መጠቆሚያ ወይም ጂፒኤስ አገልግሎታቸው በሚፈለግበት በማንኛውም ጊዜ በስልክ አልያም በሬዲዮ በሚደረግ ግንኙነትና ትዕዛዝ የተፈለጉበት ቦታ እንዲደርሱ ያስቸላቸዋል፡፡

አዲስ ከገቡት 751 ታክሲዎች ጋር አብሮ የሚሠራው ራይድ የተሰኘው ቴክኖሎጂ ሃይብሪድ በተባለው ኩባንያ ዲዛይን ተደርጎ የተሰናዳው ይህ ቴክሎጂ አገልግሎት አሰጣጣቸውን ቀልጣፋና ዘመናዊ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ያዘጋጀው የጥሪ ማዕከልና የስልክ አፕሊኬሽን አማካይነት ደንበኞች በቀላሉ ከአሽከርካሪዎች ጋር እንዲገናኙ ያስችላል፡፡ በተጨማሪም አንድ ደንበኛን ከፈለገው ቦታ ካደረሱ በኋላ ሌላ ደንበኛ ይዘው ወደ ጣቢያቸው እንዲመለሱ በደርሶ መልስ እንዲከፈላቸው የሚያስችል ነው፡፡ አገልግሎቱ ገበያው ውስጥ በስፋት እስኪተዋወቅ እስከ ስድስት ወር ጊዜ ያህል ምንም ዓይነት የአገልግሎት ክፍያ አይጠይቅም፡፡ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ወ/ት ሳምራዊት ፍቅሩ አገልግሎቱ የትራንስፖርትን ዋጋ ተመጣጣኝ እንደሚያደርገው ገልጻለች፡፡   

ከጥቂት ሳምንታት ፊት አዲስ ሜትር ታክሲ የተባለው ኩባንያ በግዮን ሆቴል ባካሄደው ሥነ ሥርዓት 50 የቶዮታ ሥሪት አቫንዛ ሞዴል መኪኖች እንዲያስገባ ተፈቅደውለት በማስገባት ሥራ ለማስጀመር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ኩባንያው ከ26ቱ ማኅበራት አንዱ ሲሆን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መኪኖችን በ400 ሺሕ ብር በላይ በሆነ ዋጋ ከቀረጥ ነፃ ማስመጣቱ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች