Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አዲሱ ዓመት የግሉ ዘርፍ ከማጥ ወደ ለውጥ የሚያቀናበት ይሁን

አገራዊ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል፣ በሥራቸው ያሉ አባሎቻቸውን መብትና ጥቅም ያስከብራሉ እንዲሁም ለኢኮኖሚያዊ ግስጋሴ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ተብለው ከተቋቋሙ ማኅበራት መካከል የንግድ ምክር ቤቶች ይጠቀሳሉ፡፡

በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ቀርቶ በቀደሙት አስቸጋሪ ወቅቶችም ቢሆን የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ያላደረገበት ወይም ደግሞ የግሉን ዘርፍ የሚወክሉ ተቋማት አሻራ የማያርፍበት አገራዊ ዕድገት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፤ አይኖርምም፡፡ ተግባር ላይ ስለመዋሉ ወይም ትርጉም በሚሰጥ መልኩ አስተዋጽኦው ስለመታየቱ መከራከር ቢቻልም፣ ሁሉንም ሊያስማማ የሚችለው እውነታ ግን የግሉ ዘርፍ ሚናን የሚተካው የሌለ መሆኑ ነው፡፡

የግሉ ዘርፍ የሚጠበቅበትንና የሚባልለትን ያህል አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄን በሚዛን ለመለካት ሲታሰብ፣ ብዥታ ውስጥ የሚከቱ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ለሁሉም እኩል የውድድር ሜዳ ያለመኖርና ጫና ፈጣሪ ፖሊሲዎች ሊያሳርፉበት የሚችሉት ተፅዕኖዎች እንዳሉ ሆነው፣ ባለው አሠራርም ቢሆን ጠንካራ የግል ዘርፍ መፍጠር ተችሏል ማለት ከባድ ይሆናል፡፡

በተለይ ጠንካራና ሞጋች የንግዱ ኅብረተሰብን የሚወክሉ ተቋማት አለመኖራቸው ለግሉ ዘርፍ ደካማነት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ጠንካራ ንግድ ምክር ቤቶች ቢኖሩ ኑሮ፣ የተደራጀና ጠንካራ የንግድ ማኅበረሰብ ሊፈጠር ይችል ስለነበር ነው፡፡ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ወቅታዊ ተክለሰውነት ሲታይ ግን እንኳንና ለግሉ ዘርፍ ተከላካይና ተወካይ ሆነው ሊቆሙ ቀርቶ ተቋማዊ ድርጅታቸው ሲታይ እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም፡፡ ትልልቅ የሚባሉቱ የንግድ ኩባንያዎችና የዘርፉ ተፅዕኖ ፈጣሪ  ግለሰቦች በሩቁ ይመለከቷቸዋል፡፡ እርግጥ ይህ የሆነው በምክር ቤቶቹ ደካማነት ብቻ ነው ብሎ መደምደም ሞኝነት ቢሆንም፣ ከላይ እስከታች በተለያዩ ደረጃዎች የተዋቀሩ ንግድ ምክር ቤቶች የሚጠበቅባቸውን ያህል እንደማያከናውኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ውስጣቸውም ጤናማ አይደለም፡፡ ብዙውን ጊዜ ተቋማቱን ለመምራት ሲባል የተፈጠሩ ሽኩቻዎች ጎልተው የመውጣታቸውን ያህል ለችግሮቹ ተጨባጭና ውጤታማ መፍትሔ ሲቀርብ አለመታየቱ፣ ምክር ቤቶቹ የሚታይባቸውን ችግር ሥር እንዲሰድ አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡ ካለባቸው ኃላፊነት አለያም ያከናውናሉ ተብሎ ከሚጠበቀው አኳያ ያን ያህል እንዳይጓዙ አድርጓቸዋል፡፡ ተቋማቱ ከውጭ ያላቸው ስም ትልቅ ነው፡፡ የተሰጣቸውም ኃላፊነት የገዘፈ ነው፡፡ ይህ የመሆኑን ያህል በአጋጣሚው ያገኙትን ዕድል ተጠቅመው የግሉን ዘርፍ ለማጎልበት የሚያስችል ቁመና ላይ አይገኙም፡፡ የአቅም ውስንነት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ጠንካራ የሚባል የግል ዘርፍ እንዳይፈጠር ምክንያት በመሆናቸው ቢጠየቁ ስህተት አይሆንም፡፡ የንግድ ምክር ቤት አባል የሚኮነው በፈቃደኝነት በመሆኑም ጭምር ከሚታይባቸው ዝለት የተነሳ አብዛኛውን የግሉን ዘርፍ ተዋናይ ማቀፍ ያልቻሉ ናቸው፡፡ ብዙዎች አባል ያልሆኑት የተቋሞቹን ደካማ እንቅስቃሴ በመመልከትም ሊሆን ይችላል፡፡

የውጭ አቻ ተቋማትን የሚያገናኙ አገርንም የሚወክሉ ተቋማት የመሆናቸውን ያህል በዕድሉ ተጠቅመው ለውጥ አምጥተዋል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ሁሌም ግን በተቋማቱ አባላትና በአገር ስም የውጭ ጉዞዎች ይደረጋሉ፡፡ ከአቻ ማኅበራት ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነቶችን ሲፈርሙ እናያለን፡፡ ነገር ግን ስምምነቶቹ ምን አስገኙ፣ ምንስ አመጡ ብለን ስንፈትሽ ምንም ነገር የማይገኝባቸው አጋጣሚዎች ይበረክታሉ፡፡ አንዳንዴም ለቻምበሮች የሚወጡ ንግድና ኢንቨስትመንት ተኮር የጉዞ ወጪዎች የዘመድ አዝማድ መጠቃቀሚያ ሆነዋል የሚል ሐሜትም እየተደመጠ ነው፡፡ ነጋዴ የሚለውን ስም ይዘው ለሥራ እየተንቀሳቀሱ የሚታሰብልን አበል አነሰን ብለው የሚጮሁ የንግዱ ኅብረተሰብ ተወካዮች ስለመኖራቸው መስማትም ያስተዛዝባል፡፡ ለነጋዴው የዕውቀት ሽግግር ያስገኛሉ የተባሉ የውጭ ጉዞዎች፣ ከትክክለኛው ነጋዴ ይልቅ ውጭ ለመውጣት ያሰፈሰፉ፣ ያልተገቡ ሰዎች እሄዱ በዚያው የሚቀሩባቸው ጊዜያት አሉ የሚሉ ሹክሹክታዎች ሲደመጡ ተቋማቱ በእርግጥም ውስጣዊ ችግራቸው አሳሳቢ መሆኑን ያሳያል፡፡  ወደ አመራር የሚወጡት ብዙዎቹ የንግድ ኅብረተሰቡ ተወካዮች ዕውን የንግዱ ኅብረተሰቡን ይገልጻሉ፣ ይወክላሉ ወይ? የሚለውን ጥያቄ ደጋግመን እንድንጠይቅም ያስገድዱናል፡፡

ከንግድና ከአገልግሎት ዘርፍ ጋር እንዲሠሩ በራሳቸውም አምራች ኢንዱስትሪዎችን አሰባስበው የተቋቋሙ የዘርፍ ማኅበራትም ሆኑ የንግድ ምክር ቤቶችን   እንፈትሽ ካልን ብርካታ ሕፀፆች እናገኛለን፡፡ የግሉን ዘርፍ የሚወክሉት እነዚህ ተቋማት ብዙውን ጊዜ ሲዋከቡና ሲጣደፉ ለማየት የምንበቃው የምርጫ ሰሞን እየሆነ ሲመጣ ማዘናችን አይቀርም፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ከተግባራቸው ይልቅ ሽኩቻቸው ይጎላል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በቅርቡ የሚያካሂደውን ጠቅላላ ጉባዔ በመንተራስ፣ በዋዜማው የአመራሩን ቦታ ለመያዝ ውስጥ ውስጡን የሚሸርበውን ሴራና ጥንስስ መተንበይ ነብይ መሆንን አይጠይቅም፡፡ ደፈር ያሉ ተወዳዳሪዎችማ በአደባባይ የሚሠሩት ሥራ የግሉን ዘርፍ የሚያንኳሰስና አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡

የንግዱን ኅብረተሰብ ከማገልገል ይልቅ ራሳቸው የሚጠቀሙበትን መንገድ ለማመቻቸት ጥረው ግረው፣ ደክመው የሚኖሩ ስንትና ስንንቶች እንዳሉ ማየት ቀላል ነው፡፡ ዛሬም በአዋጅ ከተፈቀደላቸው፣ በተግባር ከተሰጣቸው ኃላፊነት ይልቅ የምርጫ ዘመን በደረሰ ቁጥር ራሳቸውን ለመምረጥና ለማስመረጥ የሚያደርጉት ፉክቻ ተቋሞቹን ጠንካራ አመራር እያሳጣቸው፣ ይልቁንም ጥቂቶች  ብቻ በመፈራረቅ የሚገቡና የሚወጡባቸው የግል ማኅበራት አድርጓቸዋል፡፡ ይህ አንድ ቦታ መቆም ያለበት ነው፡፡ በመልካም ተግባራቸውና ሠርተው ሊያሠሩ የሚችሉ መሪዎች እንዳይመጡም በሩን የሚዘጋ አካሄድ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ጥሩ ይሠራሉ የተባሉ አመራሮች ለራስ ጥቅም ባደሩና ባደሉ ተመራጮች ያሰቡትን እንዳይሠሩ በመግፋት፣ በመተናኮል ከአካባቢው ተንገሽግሸው እንዲርቁ ተደርጓል መባሉም ቻምበሩን ጎድቶታል፡፡

ከጊዜ ወዲህም የቻምበሩን የአመራር ወንበር ለመቆናጠጥ የንግድ ምክር ቤቶች የሌላቸውን አባላት ቁጥር በእጅጉ በማሳደግ ድምፅ መሰብሰቢያ ለማድረግ ሲሞክሩ መመልከትም ያሳዝናል፡፡ ይህ ሁሉ ጉዞና አበል ለመቀራመት መሆኑ ቸገረ እንጂ የበለጠ ለመሥራትና የተሻለ ሆኖ ለመገኘት ቢሆን እንኳ ባልከፋ ነበር፡፡

እንዲህ ባሉ ተቋማት ውስጥ መንግሥት በቀጥታ እጁን ማስገባት ባይችልም ቢያንስ አገሪቱ የደረሰችበትን፣ ወደፊት ልትደርስበት የምትችለውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚመጥኑ፣ የበሰሉ፣ ለመንግሥትም ምክረ ሐሳብና ተግሳጽ የሚያቀርቡ አመራሮች እንዲኖሩ መደረግ አለበት፡፡

በአገሪቱ የንግድ ምክር ቤቶች ላይ የሚሰነዘርባቸው ትችት ጠንካራና ቆራጥ አመራር ማጣታቸው ነው፡፡ ጥቂቶች ግን አሁንም መኖራቸው አይዘነጋም፡፡ ከሦስት ሳምንት በኋላ የሚካሄደው ምርጫም እንደ ቀድሞው ጊዜ በቲፎዞ ተቦዳድኖ በመምጣት ግርግር ከመፍጠር ይልቅ የተሻለ አመራር እንዲመጣ መጣር ይኖርባቸዋል፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብ የእኔ የሚላቸው ተቋማት እንዲሆኑ፣ መብቱንና ጥቅሙን እንዲያስከብሩ ለማድረግ መነሳት አለበት፡፡ የማይበጁትን፣ በነጋዴ ጭምብል የሚንፈላሰሱበትን ወዲያ ሊያደርጋቸው፣ ሊያባርራቸው ይገባዋል፡፡ መንግሥትም የሚደግፉትንና የሚያንቆለጳጵሱትን ሳይሆን በዕውቀት ላይ ተመሥርተው ሲያበላሽ የሚያቃኑትን፣ ሲሳሳት የሚያርሙትን የነጋዴውን ራሶች ከማሳቀቅ ከማራቅ መቆጠብ አለበት፡፡ 

ዛሬ የአገራችን የግብይት ሥርዓት ቅጥ ያጣበት አንዱ ምክንያት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የንግድ ኅብረተሰቡን የሚወክሉት ሰዎችና ተቋማት በአግባቡ ባለመሥራታቸው ነው፡፡ ነጋዴዎችን በአግባቡ አደራጅተው በአግባቡ እንዲሠሩ ከተፈለገ የንግድ ኅብረተሰቡን የሚያነቃቁ የነቁ አመራሮች ያሻሉ፡፡ ተቋማቱ እንዲህ ያለውን ወሳኝ ኃላፊነት መወጣት ባለመቻላቸው ግን ብዙዎች በውድድር ሳይሆን ከገበያ ሕግጋት ውጭ  እንዲከብሩ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ነጋዴዎች ያላግባብ ዋጋ ሲሰቅሉና ሲያወጡ ሃይ የሚሉ፣ ሥነ ምግባርን የሚያርቁ ንግድ ምክር ቤቶች ስለመኖራቸው እጠራጠራለሁ፡፡ አርዓያ የሚባሉ ነጋዴዎችን ሲያወድሱና ዕውቅና ሲሰጡም አይታዩም፡፡ ይህ ግን መገለጫቸው ሊሆን ይገባ ነበር፡፡ ነጋዴው ግብር በዛበት፣ ሕግ ተጫነበት ከማለት ባሻገር በአግባቡ ሕዝብን ሳይጎዳ እንዲሠራ ለማድረግ ከእነሱ ውጭ ኃላፊነት ሊሰጠው የሚችል አልነበረም፡፡ የንግዱን ኅብረተሰብ ውክልና ይዘው ለጤናማ የግብይት ሥርዓት ካልሠሩ ሥራቸው ምን ሊሆን ነው?

እውነት እንነጋገር ከተባለ መንግሥት ስኳርና ዘይት ችርቻሮ ውስጥ የገባው በንግድ ምክር ቤቶቹ ደካማነትና በተወሰኑ አባሎቻቸው ሥነ ምግባር አልባነት መሆኑን መናገር ማጋነን አይሆንም፡፡

የሚገባውን የትርፍ ህዳግ ይዞ የሚሸጥ ነጋዴ ቢኖረን ኑሮ ወይም በትክክለኛ የገበያ ሥርዓት የሚመራ ነጋዴና አስተዳደር እንዲፈጠሩ ንግድ ምክር ቤቶች ጥረት ቢያደርጉ ኑሮ መንግሥት ዘይት፣ ዱቄትና ስኳር ቸርቻሪነት ባልገባ ነበር፡፡ እርግጥ ይህ ብቻውን መንግሥትን ቸርቻሪ አድርጎታል ማለትም አይቻልም፡፡ ይህንን ሊሠሩ የሚችሉ የግል ድርጅቶችም በሚያገኙት ትርፍ ስንት ኢንዱስትሪዎችን በገነቡ ነበር፡፡

መንግሥትም ቢሆን ለንግድ ምክር ቤቶች መልፈልፈስ እንደ ምክንያት የሚታየውንና የንግድ ምክር ቤቶችን ለማደራጀት የወጣውን አዋጅ ወቅታዊ የአገሪቱንና የንግድ ኅብረተሰቡን ሁኔታዎች ግንዛቤ ውስጥ ባስገባ ቅኝነት እንዲሻሻል ማድረግ አለበት፡፡ በእርግጥ አዋጁን ለማሻሻል እንቅስቃሴ ቢኖርም ማሻሻያውን በማፋጠን ጠንካራ የንግዱ ኅብረተሰብ ተቋማት እንዲፈጠሩ ካልተደረገ፣ የግሉ ዘርፍ ሚና የማይተካ ነው  ማለቱ በወሬ ብቻ ይቀራል፡፡

የንግድ ምክር ቤቶች በውስጣቸው ያለውን ያልተገባ አሠራር ይዘው መንግሥትን መሞገት እንደማይችሉ እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ሳያሰፍኑ፣ በመልካም አስተዳደር ግድፈት እየታሙ የመንግሥትን መልካም አስተዳደር ለመተቸት መሞከር  ስለሚያሳልቅባቸው ይለወጡ፡፡ በአዲሱ ዓመት የመጀመርያው ወር አጋማሽ ላይ የሚካሄው የአገር አቀፍ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫም ይሁንኑ ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባል፡፡

አዲሱ ዓመት ተቋሙን ለማጠናከር ለጉዞ ሳይሆን፣ በሥራ የሚተጋ አመራር እንዲመጣ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት