Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትቁጣን የተጠጋ ጥላቻ ቋያ እሳት ይወልዳል!

ቁጣን የተጠጋ ጥላቻ ቋያ እሳት ይወልዳል!

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

በተናጠል መታገልና በአካባቢያዊ ጥያቄ ላይ ማተኮር ወደ ዴሞክራሲ አያደርስም፡፡ ዴሞክራሲ ተባብሮ መታገልን ይጠይቃል፡፡ በጥላቻ፣ በኩርፊያና በጥርጣሬ ተቦርቡሮ  በምንም ዓይነት የተባበረ ትግል ማድረግ አይቻልም፡፡ ቢሞከርም በቀላሉ አፈትልኮ መከፋፈል አይቀርለትም፡፡ አንደኛው ወገን “እናንተ!. . . እነሱ!. . .” እያለ ጥቃት አድራሽ፣ ሌላው ወገን አደጋ ይደርስብኛል እያለ ሸሺ ከሆነማ፣ የዴሞክራሲና የእኩልነት ጥያቄ በአፍ ጢሙ ተደፍቶ፣ የመጨረሻው “ድል” ራስንም ሌላውንም የሚበላ የመጨራረስ እሳት ውስጥ መግባት ነው፡፡

ንፋስ፣ ደረቅ ጢሻና የሚጋረፍ ሙቀት ባለበት ሥፍራ ምንም ያህል ቢርብ እሳት ለማንደድ አይሞከርም፡፡ የታሰበው ቀርቶ ያልታሰበው ሊሆን ስለሚችል፡፡ “ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው” የሚለው ምሳሌም ይኼንኑ ነው የሚያስገነዝበው፡፡ ሆድ የባሰው ለደግ ሥራ ማጭድ ቢዋስ ለሰው አንገትም ሊያውለው ይችልላልና፡፡

ሆድ መባስና ግልፍታ መሄጃ የጠበበው ማዕበል ማለት ነው፡፡ ይህንን ዓይነት ስሜት እጅግ ጥንቁቅ የሆነ ፖለቲካ እንኳ ከጥፋት አርቆ መምራት እጅግ እንደሚያስቸግረው የብዙ አገሮች ልምድ ያስተምራል፡፡ ዛሬ እየተከሰተ ያለው ስሜትም ሆድ የባሰው የሚባለው መሳይ ነው፡፡ በዚህ ንጠት ውስጥ “ትግሬ አማራ ኦሮሞ ሲዳማ ጉራጌ ወዘተ ወዘተ. አብሬህ አብረኸኝ!” በማለት ፈንታ፣ ፖለቲካ አወቅን ሕዝብ አታገልን ብለው በመንግሥት ውስጥ ያለ የሥልጣን ድርሻን በብሔረሰብ የሚቆጥሩና ሠልፈኛ ላይ የደረሰ ግድያን ከብሔረሰብ ጋር የሚያገናኙ የፖለቲካ ደናቁርት፣ ሆድ ለባሰው ማጭድ እያቀበሉ፣ ደረቅ ጢሻ ላይ እሳት እያያያዙ መሆናቸው አዕምሮ ካላቸው ይግባቸው!! ከዚህ እሳት ለማምለጥና የዴሞክራሲን ነፃነት ለመቀዳጀት የኢትዮጵያ ልጆች የጥላቻንና የኩርፊያን እግር ብረት በጣጥሰው በጋራ ጥያቄዎች ላይ አንድ ቃል አንድ ልብ ሆኖ መግጠም የግድ አስፈላጊያቸው ነው፡፡ መጀመርያ ነገር ጥላቻንና ኩርፊያን ማፈራረስ በራሱ፣ ከእስረኝነት መውጣትና ነፃነት ውስጥ መግባት ነው፡፡

የተባበረችው አሜሪካ ውስጥ የነጭ ዘረኝነት፣ ድህነት፣ የቤተሰብ ውስጣዊ ሰላም ማጣት፣ የቤተሰብ መፍረስ፣ ከትምህርት መሰናከል፣ ወሮበላነትና አምባጓሮኛነት፣ የአደንዛዥ  ዕፅ ሱሰኝነትና አስተላላፊነት፣ የፖሊስ አድሎኛ ጭካኔና እስር ቤቶች ጥቁሮችን ያኝኳቸዋል፡፡ ይህንኑ ብልሹ እውነታ ያንፀባረቀ አሉታዊ ንቃተ ህሊና በቀን ተቀን ተራክቦ በዜና ዘገባዎች፣ በፊልሞች፣ በዘፈኖች ውስጥ ሁሉ ተዘርግቶ ከአዙሪቱ ውስጥ እንዳይወጡ አድርጎ ይልሳቸዋል፡፡ ጥሪት ማበጀት የቻሉና ቡድን ቢጤ የፈጠሩ የፊልም ሰዎች እንኳ አዙሪቱን ለመጣስ የሚያግዝ ፋና መለኮስ አልተቻላቸውም፡፡  የጥቁር መብት ንቃትና ተቆርቋሪነት ራሱ ከባርነት ጀምሮ እስከ ዛሬ በተለያየ መልክ ያለውን በደል እያነሱ ከማፍተልተል ማለፍ አልቻለም፡፡

የጥቁሮች የመብት ትግል የትጥቅ መንገድን ከዚህ በፊት ሞካክሮት ነበር፡፡ ሰላማዊ ትግልን ኖሮበታል፣ ዛሬም ይሟገታል፣ ይጮሃል፣ ያጋልጣል፣ ያወግዛል፡፡ የተወገዱና የተሻሻሉ ነገሮች ቢኖሩም የድቀት ካቴናዎቹ ግን ዛሬም እንደያዙት ናቸው፡፡ አሁን ጭራሽ በተዛባ አመለካከት ላይ የቆመው የፖሊስ ጥቃት፣ ጉዳት መሰንዘር የማይችልን ዜጋ (መሬት ላይ በደረት ተደፍቶ የተያዘን) በስድስት ጥይት እስከ መግደል ሲደርስ የጥቁሮች ቁጣ የአድፍጦ ተኳሽ ተበቃይነትንም ወለደ፡፡ የጥይት በቀሉ አገዛዙን ማስደንገጥና ማሳሰብ ቢችልም፣ እንደ ትግል መንገድ ቢያዝ የከፋ ጥቃት በጥቁሮች ላይ እንዲበዛ ሰበብ የሚሆን ነው፡፡

መንገድ እየወጡ መጮህና መፍትሔን ከመንግሥት መጠበቅም ቢሆን የድቀት ወጥመዶችን ለመስበር አያስችልም፡፡ ወጥመዶቹን መስበር የሚቻለው፣ ጥቁሮች የመብት ንቃታቸውንና የመንፈስ አንድነታቸውን  በሁለገብ ትግግዝ አንቀሳቅሰው አሉታዊ (ከዕፅ፣ ከወንጀል፣ ከአምባጓሮ፣ ከውመና፣ ወዘተ ጋር የተያያዘ) መታወቂያ ካርዳቸውን ለመበጣጠስ ሰፊና ከሰው ወደ ሰው የሚጋባ ትግል መክፈት ከቻሉ፣ ብሎም በልሽቀት መመረዝንና ተስፋ መቁረጥን የሚያራቡ ሁኔታዎችን የሚቀይሩ ማሻሻያዎችን ከመንግሥት  የመጠየቅን እርባና ለራስ በራስ ትግላቸው ማፋጠኛ አድርገው ከተረዱት ብቻ ነው፡፡ ይህ የማይቻል የሚመስለን በጥቁሮቹ ሁኔታ ውስጥ ያሉት ይሁዲዎች ቢሆኑስ ኖሮ እስከ ዛሬ ይማቅቁ ነበር? ብለን ብንጠይቅ መልሱ ጨለማ አይሆንብንም፡፡

በብዙ የኑሮ ጣጣ መተጋገዝን ከሚሻው የጥቁሮች ነፃነት ጋር የእኛን ከፍጅት የማምለጥ ተግባር እናገናዝበው፡፡ ፍጅትን የማክሸፍ ተግባር፣ በአደባባይ ትግል መንግሥትን የመወጠርና ከጥይት ጋር የመገናኘት ቀንበርን የግድ አያሸክመንም፡፡ የመጀመርያው ተግባር በኩርፊያ፣ በመራራ ስሜትና በጥላቻ መሞላት ለጠብ ደጋሾች መጫወቻነትና ለእርስ በርስ መተላለቅ የሚዳርገን መሆኑን ከልብ መቀበል ነው፡፡ ሁለተኛው ተግባር አጎብሮ ከመተያየት እየወጣን አንድ ዓይነት ሐሳብ ላይ ስለመድረስ ሳንጨነቅ፣ ተከባብሮ የተለያየ ሐሳብ መለዋወጥን በመለማመድ የገረሩ ስሜቶችን መበተንና እንዳይጠራቀሙ መከላከል ነው፡፡ ሦስተኛው ለየትኛውም ጥቃትና በደል አጫፋሪና መሣሪያ አለመሆን ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ የሚፈልጉት ራስን ማሳመንና ትንሽ ወኔ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የገረሩ ስሜቶችን የሚፈጥሩና የሚቀሰቅሱ ንግግሮችና ድርጊቶችን  ባጋጠሙን ቦታና ጊዜ ሁሉ ያለወገናዊነት መቃወም፡፡ በተለይ በውይይትና በስብሰባዎች ጊዜ በሕጋዊ ፓርቲዎች ላይ ”የአገር ጠላት”፣ “ከሐዲዎች”፣ “ኢትዮጵያዊነታቸው የሚያጠራጥር”፣ “ፀረ ሕዝብ”፣ “የዜሮ ድምር ፖለቲከኞች”. . . የሚሉ ብከላዎችና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ ቅስቀሳዎች ከየትም አቅጣጫ ሲወረወሩ በቅዋሜ ማሳፈር፤ የትኛውንም ፓርቲ ሕዝቦችን ሳያላትም መብቶችን ወደ ማሟላት በመውሰድ እርባናውን መመዘን፤ ኢሕአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎቹ ሰብስቤ ልስበክ ሲሉ በሕዝቦች ውስጥ የተፈጠሩ መሸካከሮችንና ጥላቻዎችን የሚያሟሽሹ ምን የተግባር መርሐ ግብር አላችሁ ብሎ መጠየቅ የፀረ ፍጅት መልዕክት መጀመርያ ነው፡፡ ልፋቱ ትንሽ፤ ውጤቱ ግን በጣም ከፍተኛ!!

ከፍትሐዊነት ጋር የሚጣላው ወገናዊ የሥልጣንና የሀብት ዋና ዘጋኝነት፣ እንዲሁም በአስተዳደርና በኢኮኖሚ ሕይወት ውስጥ የሚፈጠር የጠባብ ወገናዊነት ሰንሰለት ጤናማ ግንኙነትንና ሰብዕናን በመንታ ስለት ይገዘግዛል፡፡ ጠባብ ስብስብና ሰንሰለት አቋራጭ የጥቅም መንገድ ከመሆን አያመልጥም፡፡ ስብስቡንና መረቡን አለኝታዬ ወገኔ ያለም በአቋራጩ ለመጠቀም መሹለክለኩ አይቀርም፡፡ አልፎም  በተመኪነት ሌላው ላይ  ለመባጠጥም ሆነ፣ ከዚህ በፊት ደቁሶኛል ብሎ የሚያስበውን ወገን ለመበቀል ስሜቱ ይነቃቃል፡፡ ባይተዋር ተደርጌያለሁ ያለም፣ በሀሜትና በጥላቻ ራሱንና ሌላውን ለመመዝመዝ ይጋለጣል፡፡ መጨራረስን የሚደግሱት የዚህ ዓይነቶቹ የአመለካከትና የስሜት ለውጦች (ጉዳቶች) ናቸው፡፡ እናም አደገኛነታቸውን ላለመዘንጋት በህሊና ውስጥ የ”ተጠንቀቅ!” ምልክት መትከልና ዕውናዊና ህሊናዊ ብልሽቶችን ለመቀየር መጣጣር፣ የገዛ ሕሊናን ከመሞገት አንስቶ በባልንጀራነትና በሌሎች ማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ ለስብጥር ቦታ መስጠት፣ በአጠቃላይ ተከፋፍሎ ለመጠቃቃትና ለመባላት የሚያመቹ ጎዳናዎችን እየሸሹ የሚያስተጋግዙ ጎዳናዎችን መጥረግ፣ የመባላት አደጋን ለማራቅ እጅግ የሚበጁ የኑሮ ዘይቤዎች ናቸው፡፡

ለኢትዮጵያ ትልቁ የህልውና ጥያቄ ዛሬ አስፈላጊ ግን አወዛጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ወጣቶች በትዕግሥትና ባለመማረር የመከራከር፣ የመወያየትና የመቀራረብ ልምምድ አለማድረጋቸው የአገራቸውን ጣጣዎችና ፈተናዎች ለመወጣት አለመሰናዳት (ሲከፋም የጥፋት ማገዶ ለመሆን ተመቻችቶ መጠበቅ) ነው፡፡ ይህ ትልቅ የአገር ክስረት ነው፡፡ 

በአንድ ድርጅትና አቋም አምልኮ መሰልቀጥ ምን ያህል ከማስተዋልና ከማሰብ እንደሚያርቅ የ”ታወር ኢን ዘ ስካይ” ደራሲ ሕይወት ተፈራ ራሷን በመማሪያነት ለዛሬው ወጣት አቅርባለች፡፡ ኢሕአፓ ውስጥ ተከስቶ ከነበረው የተቃውሞ አቋም ጋር የመተዋወቅ የተሻለ ዕድል ገጥሟት የነበረችው ይቺ ወጣት፣ ድርጅቱ በእርስ በርስ መበላላትና በመንግሥት ኃይሎች አሳድጅ ግድያና ለቀማ ከተንኮታኮተ፣ እሷም ከታሰረች በኋላ እንኳ ፍቅሯ አልተናወጠም ነበር፡፡ ከፍ ያለ እርከን ላይ የነበረ አንድ የኢሕአፓ አባል በእስረኛነት የ“ንቃት” ጊዜ ኢሕአፓ ደርግን ፋሽስት ማለቱ ስህተት እንደነበር መናገሩ በብዙዎቹ ታሳሪዎች ዘንድ ከክህደት የተሻለ ትርጉም ተነፍጎት፣ እሷም ከእሱ ባለመነጠሏና ከመኢሶን እስረኛ ጋር ተቀራርባ በመታየቷ እንደ ጠላት በተጠመደች ጊዜ ግን፣ አዕምሮዋ ተነዝሮ ጥያቄ በጥያቄ ሙግት በሙግት ሆነ (Hiwot 2012: 344-5፣350)፡፡ አምልኮ ይህን ያህል እሷን ገንዞ ሊገዛት ከቻለ ተራ አባላቱ “ኢሕአፓ አጥፍቷል፤” ሲባል አይኮን ቢሆኑ አይሠራ ቢሠሩ የሚያስደንቅ አይሆንም፡፡

ያለኔ ሐሳብ  – ያለኔ መሪነት – ያለኔ ሥልጣን ባይነት በኃይለ ሥላሴ፣ በደርግና በኢሕአዴግ ዘመን በሌሎች አገሮችም እንደታየው የአምባገነንነት መሰንቆ ነው፡፡ ለዚህ መሰንቆ መማረክ (ዕጣን ከብቸኛ ሐሳብና ገዥነት ጋር አጣብቆ ማየት) ለፈላጭ ቆራጭነት እጅ መስጠት ነው፡፡ በአማራጭ የለሽ ሐሳብ ውስጥ መኖር እስረኝነት ነው፡፡ ሐሳቦችን ብቻ ሳይሆን የሐሳብ ነፃነትን ይነጥቃል፡፡ የአዕምሮ ጠያቂነትን ይሰልባል፡፡ በዝምታና በአጨብጫቢነት ሰብዕናን ያስጨርሳል፡፡

በሐሳብ ብዙነት ውስጥ መኖር ወዲህና ወዲያ ያፈናፍናል – ነፃነት ነው፡፡ የማንኛችንም ሐሳብ እንዲወጣና ከሌሎች ጋር እየተመዛዘነ እንዲኖር ይፈቅዳል፡፡ የሐሳቦች መመዛዘን አዕምሮን ያሠራል፣ ያበለፅጋል፡፡ ለሐሳብ ብዙነት ደጋፊ ማብዛት – በአጠባ የታሰሩ አዕምሮዎችን ብዛት መቀነስ – ነፃነትን ማቅረብ – የአምባገነንነትን ቅጠል መመልመል ነው፡፡

ይህንን ማካሄድ ማለትም ብዙ ሐሳብ በሚንሸራሸርበት ሁኔታ ውስጥ መኖር ያዋጣናል እያሉ መስበክ ሳይሆን ፈላጭ ቆራጮች ከሚወዱት ጠበኝነት፣ ኩርፊያና መፈራራት ወጥተን መነጋገር እንጀምር፡፡ አንዳችን ሌላችንን ለማጥመቅ ሳንከጅል ከየአቋማችን ውስጥ የሚያስማማንን እንፈልግ፡፡ የሚያስማማንን በማጥበቅና ልዩነታችንን በማክበር መቀራረብን እናበራክት ማለት ነው፡፡

የወጣቱ በግልፍታ ብሔረሰብ ነክ አምባጓሮ እያስነሳ ከመከታከትና ማዶ ለማዶ ከመተያየት እየወጣ ወደ ሥልጡን ውይይት መጣ ማለት፣ ቀስት በጭፍን እያስወነጨፉ ራስን ከመጉዳት (ታፍኖ መገዛትን ከማጠንከር) እየወጣ ዒላማ ላይ አነጣጥሮ ቀስት ማስፈንጠር ጀመረ ማለት ነው፡፡ የወንዜ ልጅ፣ የብሔር/የፓርቲ ወገኔ ሳይሉ ማንኛውንም በደልና አድልኦ መቃወም ሥር የያዘ መተሳሰብንና መተማመንን ይገነባል፡፡ የብሔር መብትን የመፍራትና ከግል መብት ጋር የሚቃረን አስተሳሰብ ውኃ ውስጥ የገባ ጨው የሚሆነውም የዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲገጥመው ነው፡፡ የጥላቻና የጥርጣሬ ወጥመዶች ተሰብረው የዚህ ዓይነት መቀራረብ ተፈጠረ ማለት፣ የዴሞክራሲ ጀምበር ጮራዋ በኢትዮጵያ ምድር ላይ መፈንጠቅ ጀመረ፣ የዴሞክራሲ ትግል ትልቅ ጉልበት አገኘ፣ በቅጥፈትና በአብሽቅ ፕሮፓጋንዳ ሕዝብን መዳፈር ውድቀትን ማነፍነፍ ሆነ፣ አንዱን ከአንዱ አጋጭቶ አምባገነንነትን የማጠናከር ቀዳዳ ተዘጋ ማለት ነው፡፡ 

በዕድሜ ሸምግሎ በህሊና ወጣት መሆን እንደሚቻል ሁሉ በዕድሜ ወጣት ሆኖም በእርጅና መያዝ ይኖራል፡፡ የህሊናን እርጅናና ወጣትነት የሚወስነው ከእውነታ ጋር ያለው መቀረረብና መራራቅ ነው፡፡ ህሊና ከተጨባጭ ኑሮ ጋር የሚገናኝበት ገመድ ሲበጠስ ወይም ሲስተጓጎል ሐሳቦች ይሸብታሉ፡፡ ጫት እየቀረጠፉና ድራፍት እየጨለጡ ልቅምቃሚ ወሬ በማባዘት ኑሮ ውስጥ መዋጥና የተወራውን ሁሉ ሳይመርጡ/ሳይፈለፍሉ እያስገቡ ራስን መጎሰር ማርጀት ነው፡፡ እንዲህ ያለ እርጅና ውስጥ የገቡ ወጣቶች እንዳሉ ሁሉ፣ የጋራ መግባቢያ የቸገረው የኢትዮጵያ ታሪክ ጉዳይ አሳስቧቸው መጻሕፍት እየተዋዋሱና ተጋግዘው እየገዙ በማንበብና በመወያየት ታሪክን የሚያጠኑ አንዳንድ የባልንጀራ ቡድኖች ብቅ ብቅ ማለታቸው ይሰማል፡፡ ይህ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ጀምር ነው፡፡ የተስፋው አስኳል ያለው ግን ተመሳሳይ ሐሳብና አመለካከትን ማውራት ላይ ሳይሆን የተለያዩ፣ እንዲያውም የተቃረኑ ግንዛቤዎችንና ትርጓሜዎችን እየተደማመጡ ለመለዋወጥ መቻል ላይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለነበሩም አዲስ ለሚጀመሩም የጥናትም ሆነ የጓደኝነት ስብስቦች የሚጠቅሙ ጥቂት ነጥቦችን እናካፍል፡፡

  • ነትበው የሚንቀዋለሉ ሐሳቦችን፣ የየትኛውንም ፓርቲ ቲፎዞነት፣ የፍጥጫ አቋሞችን፣ የሾኬ ውይይት ሥልቶችን ሁሉ ወደ ጎን ብሎ በክፍት አዕምሮና በአዲስ ሙሽት ነገሮችን በማስረጃ እየመዘኑ ለመቀበል መዘጋጀት፣
  • ውይይቶች ያለቀለት ነገርና ሙሉ መግባባት ላይ የመድረስ የቅርብ ውጤት እንደማይኖራቸው አስቀድሞ መግባባት፣
  • በጥናትም ሆነ በውይይት ጊዜ፣ በብዙ መጻሕፍት ላይ ሰፍሮ መገኘትን፣ ተደጋግሞ በመገናኛ ዘዴዎች መነገርን፣ ብዙ መወደስን የእውነተኛነት ማረጋገጫ አድርጎ በመውሰድ ላለመታለል መጠንቀቅ፣
  • የታሪክ ሰውን፣ የታሪክ ሐተታንም ሆነ ትርጓሜን ስለወደድነው ብቻ የሌለ ማስረጃ ሁሉ እየደረደሩ ሽንጥ ገትሮ ጥብቅና በመቆም ድክመት ላለመጠመድ ዘወትር መጣጣር፣
  • የተረዱትንና ያስተዋሉትን ሳይሰስቱ ቅድሚያ የማጋራትና ለውይይት መነሻ የመሆን ቅንነትን መልመድ፣ ራስን ደብቆ አንተ ምን ትላለህ በማለት ሌላውን ካናዘዙ በኋላ ሐሳብ ዘርፎ እኔም የምለው ይህንን ነው ከሚል አጭበርባሪነት መራቅ፣ የተናጋሪው ሐሳብ አሳምኖን ፊት የነበረንን ሐሳብ ካስለወጠን ስለትዝብት ሳይጨነቁ እውነቱን መግለጽ፣
  • ውይይትንና ክርክርን  አስፋፍቶ ለማስኬድ የመረጃ እጥረት ሲያጋጥም በመላ ከመናወዝ ይልቅ፣ የተሻለ የመረጃ ዝግጀት አድርጎ በሌላ ጊዜ ወደ ርዕሰ ጉዳዩ መመለስ፣
  • በውይይት ጊዜ አዋቂነትን ለማሳየት የመሞከር ግብዝነትን፣ እኔ ብቻ ላውራ የማለትን፣ ጋል ጋል የማለትን፣ ባልንጀራን አጣድፎ መሳቂያ የማድረግን ትርፍ የለሽ ፍላጎቶችን መንገድ አለመስጠት፣
  • “ይህማ አለማወቅ ነው፣ ታሪክን/አገርን መካድ ነው፣ ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው. . .” የሚሉ ችኩልና መግባባትን ከሚያደናቅፉ ድምዳሜዎች መራቅ፣ ሲከሰቱም መገሰጽ፣
  • ከውይይት በኋላ፣ ምን ያህል ለራሴ ሀቀኛና ሚዛናዊ ነበርኩ? ስህተትንና መረታትን መቀበል ምን ያህል ቀሎኝ ነበር? ወዘተ እያሉ ራስን መገምገምና ማረም፡፡

      በጥናትና በውይይት ውስጥ አስተማማኝ መረጃዎችና ማስረጃዎች ሊያጥሩ፣ የማውጠንጠን አቅም ሊያንስና የተደራጀና የነጠረ ግንዛቤ መፍጠር ሊያቅት ይችላል፡፡ ሁሉም ግን በሒደት ከልምምድና ከመጎልበት ጋር መሟላታችው አይቀርም፡፡ ትልቁ ነገር፣ ዓብይ ውዝግቦችን ለመፍታት የሚያስፈልገው ተደማምጦ የመነጋገር ልምምድ መቀራረብን፣ መተማመንን፣Anchor መግባባትን በሚያሳድግ አቅጣጫ መጀመሩ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...