Friday, December 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የአደጋ ጠርዝ ላይ የጣሉን የኢኮኖሚ ጉዳዮች

በጌታቸው አስፋው

ኢትዮጵያን የለውጥ ፍላጎት እየናጣት ነው፡፡ የለውጡ ዋና ምክንያት ገና ባይለይም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ጉዳዮች ጎን ለጎን እየተነሱ ነው፡፡ የትኛው ዋና ጥያቄ ነው? የትኛው ተሳቦ የቀረበ ነው? ገና ያልለየለት ጉዳይ ነው? ሦስቱም ተደበላልቀው እየቀረቡ ነው፡፡ የሦስቱም ችግሮችና መፍትሔዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ ሦስቱም በችግርም በመፍትሔም ተወራራሽና ተደራራቢ ቢሆኑም የራሳቸው የተናጠል  ልዩ ባህሪም አላቸው፡፡ ቀዳሚው የብጥብጡ መንስዔ ባይለይም የኢኮኖሚ ቀውሱ ገና ስላልበሰለ የብጥብጥ ግንባር ቀደም አልሆነም፡፡ ፖለቲካውና ማኅበራዊው ቀድመውታል፣ ቢሆንም እየበሰለ ነው፡፡ ነገር ግን እጅ መቆረጣጠም የጀመረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ በፖለቲካዊና ማኅበራዊ መንስዔዎች ብጥብጡ ተቀጣጥሎ ራሱን የቻለ የኢኮኖሚ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ የኢኮኖሚ ብጥብጥ በስፋት ዓይነት ክልላዊ ሳይሆን አገር አቀፋዊ ስለሚሆን አደገኝነቱ የከፋ ነው፡፡

በየተራ ከመምጣት ይልቅ ተደራርበውና ተጋግዘው መምጣታቸው ከታሰበበትና በሰላም ለመጨረስ መልካም ፍላጎት ካለ፣ ለሦስቱም የሰከነና የማያዳግም የችግሮች ሁሉን አቀፍ መፍትሔ ለመሻት ይጠቅማል፡፡ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት የመጨረሻ ተስፋ የተጣለባቸው ቱሪዝምና የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ በሰላም መደፍረስ ምክንያት እንዳይስተጓጎሉ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይበጃል፡፡ በዚህ ዘመን አገር ለመገንባትና ለማፍረስ ከጦር ኃይል አቅም ይልቅ የኢኮኖሚ ብርታትና መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን ከደርግ ምርጫ ትምህርት መውሰድ ይጠቅማል፡፡ ወደ ኢኮኖሚው የሚያደሉትን የብጥብጥ መንስዔዎች ለይቶ ማወቅ ቢያስፈልግ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ፣ ሥራ አጥነቱ፣ የዋጋ ንረቱ፣ የመሬት ይዞታ ፖሊሲው፣ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲው፣ የሀብትና የገቢ ክፍፍሉ፣ ወዘተ የመሳሰሉ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ፖለቲካውና ማኅበራዊው በዜግነት እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚሰማኝ ቢሆንም፣ ሙያው ስለሌለኝ ሙያዊ ትንታኔ ልሰጥበት አልችልም፣ ልቀባጥርም አልፈልግም፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዩን ግን ሙያዬ ስለሆነ ሳልዋሽ ሳልቀባጥር ስሜታዊ ሳልሆን መተርጎምና መተንተን እችላለሁ፡፡ ከሙያው ውጪ ብዙ የሚያወራ ሰው ቀባጣሪ እንደሚሆን እገነዘባለሁ፡፡ የቀባጣሪዎች መብዛትም ኢትዮጵያን ክፉኛ እየተፈታተናት ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊው ጉዳይ በችግር መጠንና ዓይነትም ሆነ በመፍትሔ አፈላለግ ከሌሎቹ ከፖለቲካውና ከማኅበራዊው ይለያል፡፡ የሚለይባቸውን ጥቂት ነጥቦች ለማንሳት ያህል፣

 1. የመልካም አስተዳደር ችግር ሳይሆን የፖሊሲ ችግር ነው፣
 2. የሚያሳስበው የትናንትናውና የዛሬው ጉዳይ ሳይሆን የነገው ነው፣
 3. የችሎታ ጥያቄ ስለሆነ ሥልጣን በመጋራት ድርድር አይፈታም፣
 4. ክልላዊ ጉዳይ ሳይሆን አገር አቀፋዊ ነው፣
 5. የኑሮ መደባዊ ባህሪ ስላላቸው በኢኮኖሚ ተጎጂውን ብቻ ይመለከታሉ፣

የአንድን አገር ኢኮኖሚ በጥቂት ገጾች ጽሑፍ አጠቃሎ መግለጽ ከባድ ነው፡፡ ቢሆንም ግን አጠቃሎ ለመግለጽ የሚያስችሉ ጥቂት የብሔራዊ ኢኮኖሚ መለኪያዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱና ዋናው የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ሒሳብ ነው፡፡ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ሒሳብ የውስጡ ነፀብራቅ ነው፡፡ የውጭው ስኬት የውስጡን ስኬት ያንፀባርቃል፡፡ የውጭው ጉድለትም የውስጡን ጉድለት ያንፀባርቃል፡፡ የተሠሩትን የመኪና መንገዶች፣ የባቡር መንገዶች፣ የኃይል ማመንጫዎች፣ የስልክ መስመሮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት፣ ወዘተ አላየም እንዴ ብላችሁ የምትጠይቁ ሰዎች ካላችሁ፣ እኔ የምናገረው ስለ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አስተዳደር ነው እንጂ ስለልማት አይደለም፡፡ ልማት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አጋዥ እንጂ ምትክ አይደለም፡፡ ዋናው የኢኮኖሚ ችግር የሚመነጨውም ልማት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አጋዥ እንጂ ምትክ አለመሆኑን ካለመረዳት ነው፡፡

የቁጥሮች ቀጥተኛ ትርጉምና ንፅፅራዊ ትንታኔ

በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በቀረበ አገር አቀፍ ጥናት ስልሳ በመቶ የሚሆነው ገበሬ የመሬት ይዞታ ከአንድ ሔክታር በታች ነው፡፡ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቀረበ ጥናት በአማራ ክልል አሥራ አራት በመቶ የሚሆነው ገበሬ ተከራይቶ አራሽ ወይም የእኩል አራሽ ነው፡፡ በሌላ አንድ ጥናት ኢትዮጵያ የግብርና ግብዓተ ምርት በመጠቀም ከብዙ አገሮች በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነች፡፡ እርፍ ጨብጦ ለማረስ የሚዳዳቸው የግብርና ፖሊሲ አውጪዎችና የአፈጻጸም ባለሥልጣናት መሬት ወድቀው ቢንከባለሉ እንኳ፣ የኢትዮጵያውያን ሕዝብ በግብርና ምርት አያጠግቡም፡፡

በአንድ ወቅት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ባህር ዳር ለጉብኝት ሄደው የዓባይ ፏፏቴና ጣና ዳር ላይ ቁጭ ያሉት ባለሥልጣናት ችግራችሁ ምንድን ነው ተብለው ቢጠየቁ የውኃ እጥረት ነው ስላሏቸው፣ ኮሎኔሉ ቆይ ከጎዴ እንስብላችኋለን ብለው አሾፉባቸው ይባላል፡፡ ለም አፈርና ድንግል መሬት ያላት ኢትዮጵያ ባለፉት አሥር ዓመታት በግብርና መር ፖሊሲ መርህ በዓመት አሥራ አንድ በመቶ አድጋለች የተባለች ኢትዮጵያ፣ ከጎረቤት ሱዳን ሽንኩርት ኢምፖርት ታደርጋለች ጤፉ ነው የቀረን፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ሥራ ፈጠራና የኮብልስቶን ንጣፍ ወሬ ሞቶ ተቀብሯል፡፡ ወጣቱ ለሥራ ተነሳሽነት ዝቅተኛ ነው እየተባለ ተወቃሽ ሆኗል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አልገባ ማለት ከምክር አልፎ ወደ ዝልፊያና ማንቋሸሽ አምርቷል፡፡ በውጭ ባለሀብቶች ላይ ከመጠን ያለፈ እምነት ተጥሏል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መፍትሔ ያጣ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ዛሬ በመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ብዛት ከዚህ ቀጥሎ በሚቀርበው በቁጥሮች መረጃ ተደግፎ የተተነተነ የኑሮ ሁኔታ ላይ ነን፡፡ ከአንድ ትውልድ በኋላ በሁለት መቶ ሚሊዮን የሕዝብ ብዛት ምን እንሆናለን? መልሱን አንባቢ ለራሱ ይናገር፡፡ ከብሔራዊ ኢኮኖሚ ዋና ዋና ቁጥራዊ መረጃዎች ውስጥ አንዱ የሆነውንና የጠቅላላ ኢኮኖሚውን ገጽታ የሚወክለውን በብሔራዊ ባንክ የተዘጋጀ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት የክፍያ ሚዛን ሠንጠረዥ (Balance of Payment Table) ቁጥሮችን በመተርጎምና በመተንተን የሁኔታ ዳሰሳ ካደረግን በኋላ፣ የችግሮችን መንስዔ ከነመፍትሔያቸው እንመለከታለን፡፡

የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ክፍያ ሚዛን መረጃ (በሚሊዮን ብር)

ዝርዝር

2006

2007

የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለት

-4,352.3

-8,012.6

 • ቁሳዊ ሸቀጥ ኤክስፖርት

3,300.1

3,019.3

 • ቁሳዊ ሸቀጥ ኢምፖርት

13,712.3

16,458.6

 • የቁሳዊ ሸቀጦች ንግድ ሒሳብ ጉድለት

-10,412.2

-13,439.3

 • የአገልግሎት ንግድ ሒሳብ /የተጣራ/

559.5

-341.4

 • የግል ዕርዳታ/የተጣራ/

4,039.4

4,881.6

 • የመንግሥት ዕሰርዳታ /የተጣራ/

1,461.0

886.5

የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ካፒታል ሒሳብ

4,134.6

7,030.6

 • ብድር የተጣራ

2,667.6

4,828.3

 • ውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ

1467.0

2202.2

 • የምዝገባ ስህተት

120.8

460.6

 • አጠቃላይ ሚዛን /ጉድለት/

-96.9

-521.4

የጉድለት አሸፋፈን

96.9

521.4

 • ከመጠባበቂያ ክምችት በመቀነስ

96.9

521.4

 • ከብሔራዊ ባንክ

+0.04

+0.09

 • ከንግድ ባንክ

-0.1

-0.6

 • ከዕዳ ስረዛ /ማስተላለፍ/

-0.004

0.0

በአገሪቱ የተቆለለ የውጭ ዕዳ /በቢሊዮን ዶላር/

13.9

18.2

 • ከመንግሥታትና ከአገሮች

8.4

8.9

 • ከግል የንግድ አበዳሪዎች

5.5

9.3

 

ሠንጠረዡ ውስጥ በቀረቡት የሁለት ዓመት መረጃዎች በ2006 እና በ2007 ዓ.ም. በሁለቱም ዓመታት ከቁሳዊ ሸቀጥ ኤክስፖርት ገቢያችን ያገኘነው ሦስት ሦስት ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ለቁሳዊ ሸቀጥ ኢምፖርት ወጪያችን ያወጣነው በ2006 ዓ.ም. አሥራ ሦስትና በ2007 ዓ.ም. አሥራ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ የኤክስፖርት ገቢና የኢምፖርት ወጪ ተቀናንሶ የቁሳዊ ሸቀጦች ንግድ ጉድለት (Trade Deficit) በ2006 ዓ.ም. አሥር ቢሊዮንና በ2007 ዓ.ም. አሥራ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ሆኗል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ከገቢ ወጪ የተጣራ የአገልግሎት ሸቀጥ ሽያጭ የአምስት መቶ ስልሳ ሚሊዮን ዶላር ትርፍ ያስገኘ ቢሆንም፣ በ2007 ዓ.ም. ግን የሦስት መቶ አርባ አንድ ሚሊዮን ዶላር ከገቢ ወጪ የተጣራ ኪሳራ ደርሶብናል፡፡ የአገልግሎት ሸቀጥ ንግድ የሚባሉት ቱሪዝምን፣ ትራንስፖርትን፣ የባንክ አገልግሎትን፣ የመንግሥት አገልግሎትን፣ ወዘተ የመሳሰሉ የአገልግሎት ሸቀጦች ማለት ነው፡፡ በቱሪዝም ላይ ብዙ እንደሚሠራ እየተነገረ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፍ በትርፍ ሆነ እየተባለ፣ በኮንፈረንስ ቱሪዝም እየተንበሸበሽን በአገልግሎት የውጭ ግንኙነት ጉድለት ውስጥ መግባታችን ወደድንም ጠላንም ተስፋ የሚያጨልም ነው፡፡

በቁሳዊ ሸቀጦች ንግድና በአገልግሎት ሸቀጦች ንግድ የደረሰብንን ኪሳራ በከፊል የሸፈንነው ለግልና ለመንግሥት ከውጭ በሚመጣው ዕርዳታ ነው፡፡ በሠንጠረዡ ላይ እንደምንመለከተው የግሉ ዕርዳታ ከመንግሥት ዕርዳታ አራት እጥፍ ያህል ስለሚበልጥ፣ ወደፊት ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ ወይም ከማንኛውም የውጭ ለጋሽ አገር ይበልጥ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖሊሲ ለውጥ እንዲደረግ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉት የግል ዕርዳታ ላኪዎች ስደተኛ (ዳያስፖራ) ዜጎች ናቸው፡፡ በ2006ም ሆነ በ2007 ዓ.ም. በእያንዳንዱ ዓመት የንግድ እንቅስቃሴውና ዕርዳታው ተደማምረው በውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንቀሳቃሽ ሒሳብ (Current Account) አሁንም በ2006 ዓ.ም. የአራት ቢሊዮን ሦስት መቶ ሃምሳ ሁለት ሺሕ ዶላርና በ2007 ዓ.ም. የስምንት ቢሊዮን አሥራ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ኪሳራዎች ውስጥ እንደተዘፈቅን ነው፡፡ ስለዚህም ጉድለቱን በከፊል የተቋቋምነው የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት የካፒታልና ገንዘብ ፍሰት (Capital and Financial Inflow) ሒሳብ ውስጥ በሚገኙት የካፒታል ገቢዎች ነው፡፡ ከእነኚህ ሁለት ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ የረጅም ጊዜ ወጪ አገልግሎት የሚውሉ የተጣራ ካፒታል ወደ ውስጥ ፍሰት ሒሳቦች ውስጥ ከመጀመሪያው ቀጥታ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ወደ ውስጥ ፍሰት ይልቅ፣ ሁለተኛው የወደፊት ዕዳ የሆነው የውጭ ብድር ፍሰት ሁለት እጥፍ ያህል ይበልጣል፡፡

ዓመታዊው የቁሳዊና የአገልግሎት ሸቀጦች ንግድ ጉድለት በዓመታዊ የውጭ ዕርዳታው መሸፈን አቅቶት በውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለት ሆኖ ተመዝግቦ፣ በረጅም ጊዜ የተጣራ ካፒታል ወደ ውስጥ ፍሰት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ተደጉሞም ሙሉ በሙሉ ሊሸፈን አልቻለም፡፡ ስለሆነም በተንቀሳቃሽ ሒሳብ የውጭ ዕርዳታውም በካፒታል ወደ ውስጥ ፍሰትም ሊሸፈን ያልበቃው ዘጠና ሰባት ሚሊዮን ዶላር የ2006 ዓ.ም. አጠቃላይ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ጉድለትና አምስት መቶ ሃያ አንድ ሚሊዮን ዶላር የ2007 ዓ.ም. አጠቃላይ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ጉድለት ክፍያ የተሸፈነው ባለፉት ዓመታት ከተጠራቀመው የውጭ ምንዛሪ ሀብት መጠባበቂያ ክምችት ሒሳብ ተቀንሶ ነው፡፡ ኪሳራ በኪሳራ ሆነናል፡፡ የግል ድርጅት ቢሆን ኖሮ ተዘግቶ ያርፈው ነበር፡፡ አገር ግን አስይዛ የምትበደረው ሀብት አታጣም፡፡

ከላይ የቀረበው የክፍያ ሚዛን ሒሳብ እንደሚያመለክተው አጠቃላይ ጉድለቱ የተሸፈነው ከንግድ ባንኮች ሒሳብና ከዕዳ ስረዛ (ማስተላለፍ) ሲሆን፣ ከመጠን በላይ የጎደለው የብሔራዊ ባንኩ መጠባበቂያ ተቀማጭ የውጭ ምንዛሪ ሀብት ግን ዕዳ በመክፈል ፋንታ፣ ከብድርና ከውጭ መዋዕለ ንዋይ በተገኘው የተጣራ የካፒታል ሒሳብ ተደጉሟል፡፡ ይህ የሚያመለክተው በንግድ ባንኮች እጅ ያለው የውጭ ምንዛሪም በብሔራዊ ባንኩ ቁጥጥር ሥር መሆኑን ነው፡፡ ከአንዳንድ አገሮች በቀር የሁሉም አገሮች ብሔራዊ ባንኮች በንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ላይ የማዘዝ ሥልጣን የላቸውም፡፡

በሌላ በኩል የብሔራዊ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ሀብት በብድር ቢደጎምም የውጭ ዕዳም እየተቆለለ ነው፡፡ በሦስት ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርትና በአሥራ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ኢምፖርት ወደፊትም ቢሆን ዕዳ የባሰ ይቆለላል እንጂ፣ መቼም ቢሆን አይቃለልም፡፡ ከዚህም በላይ የካፒታል ወደ ውስጥ ፍሰት ገቢን በመጨመር የውስጥ ጊዜያዊ የፍጆታ መስፋፋትን ፈጥሮ በኋላ ግን የተጠራቀመ ዕዳ በመክፈያ ወቅት ፍጆታው እንደገና ይኮማተራል፡፡ የኢኮኖሚው ዕድገትም እንደዚሁ፡፡ በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ከመንግሥት በጀት እስከ ሰላሳ አምስት ቢሊዮን ብር በውጭ ምንዛሪ ተመንዝሮ ለዕዳ ክፍያ እንደሚውል የመንግሥት በጀት ድልድል ያመለክታል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ከጠቅላላው አሥራ አራት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ አርባ በመቶ ድርሻ ይዞ የነበረው አምስት ተኩል ቢሊዮን ዶላር ከግል የንግድ አበዳሪዎች የብድር ዕዳ በ2007 ዓ.ም. ከጠቅላላው አሥራ ስምንት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ ውስጥ፣ ዘጠኝ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ድርሻውም ከሃምሳ በመቶ በላይ ሆኗል፡፡

ከመንግሥታትና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚወሰድ ብድር በጊዜ ብዛት ክፍያው ለወደፊት ይተላለፋል ወይም ዕዳው ይሰረዛል፣ የወለድ መጣኙም ዝቅተኛ ነው፡፡ ከግል ነጋዴዎች መበደር ግን ይኼ ሁሉ ዕድል የለውም፡፡ ጊዜውን ጠብቆ በግድም በውድም ይከፈላል፡፡ እጅ ጠምዝዘው አንገት አንቀው ያስከፍላሉ፡፡ የወለድ ወለዱም ቀላል አይደለም፡፡ አገራዊው የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጭ ሀብት ሲቀንስ አገራዊው የውጭ ምንዛሪ ዕዳ እየጨመረ ነው፡፡ ሁላችንም በዕዳ ተጠያቂዎችና ዕዳ ከፋዮች ነንና ምን እየመጣ እንደሆነ ጠርጥሩ፡፡ ያልጠረጠረ ተመነጠረ ነው፡፡

ዓይን ጆሮ አይደለም

አዲስ አበባን ጨምሮ በብዙ ከተሞች ተዘዋውሮ የተመለከተ ሰው በሥራ ቀንና በሥራ ሰዓት እጅግ በጣም ብዙ ሰው ሥራ ፈትቶ ሲንቀዋለል ይመለከታል፡፡ በመንግሥትና በግል መሥሪያ ቤቶች ጥናት ቢደረግ ለስምንት ሰዓት ሥራ የተቀጠረ ሰው በቀን አራት ሰዓትም አይሠራም፡፡ ከግልጽ ሥራ አጥነቱ ሥውር ሥራ አጥነቱ ተባብሷል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ተደራጅተው ሥራ ከጀመሩት አብዛኞቹ ገበያ አጥተው ድርጅታቸውን ዘግተው የተበደሩትንም ሳይከፍሉ ወደ ዓረብ አገር ኮብልለዋል፡፡ የቀሩትም የሞት ሽረት ዕድሜ እየገፉ ነው፡፡ አዲስ ማደራጀቱ ቀዝቅዟል፣ ወጣቱም ግራ ተጋብቷል፡፡ ዓይን ጆሮን አይደለም የነገሩትን በሞኝነት አይሰማም፡፡ ራሱ ያያል ባየውም ይፈርዳል፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ በወጣ አንድ ዘገባ ታማሚ በመምሰል መንገድ ላይ ተኝቶ ሲለምን የነበረ ወጣት በልመና ካገኘው ሦስት መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር ጋር በፖሊስ ተያዘ ተብሎ አነበብን፡፡ ወጣቱ ለአገሩና ለሕዝብ ምንም ሳይሠራ ከአገሪቱ ምርት ውስጥ የሦስት መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር ሸቀጥ መግዛት ይችላል፡፡ ኅብረተሰቡም ወጣቱ ሠርቶ ሊያቀርብለት የሚገባውን ሦስት መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር የሚያወጣ ምርት አጥቷል፡፡ በውስጥ እርስ በርሳችን፣ በውጭም ከግለሰቦችና ከመንግሥታት እየለመንና እየተበደርን ልጆቻችንን ለውጭ አገር ቀጣሪዎች ግርድናና አሽከርነት አገልግላችሁ ከምታገኙት ላኩልን ብለን አደጋ ውስጥ እየጣልናቸው እንኖራለን፡፡

ሳይሠሩም ሳይለምኑም ከሚሠራ ዘመድ ተቀብለው ገበያውን የሚያጣብቡና እንደሚሠራ ሰው ወር ቆጥረው ደመወዝ በመቀበል ገበያ ውስጥ የሚጋፉትን ሳይቆጥሩም ሳይጽፉም በዓይን ብቻ ዓይቶ መለየትና መገመት ይቻላል፡፡ ዓይን ራሱ ዓይቶ ስለሚለካ እንደ ጆሮ ሌላ ሰው (የመንግሥት የኢኮኖሚ ባለሟል ወይም በሁለት ቀን ቆይታው ለተደረገለት ቀይ ሥጋጃ የተነጠፈበት አቀባበል ውለታ በሚቀባጥር ፈረንጅ) ተለክቶ በተነገረ ቁጥር አይታለልም፡፡ በአንድ ወቅት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሲናገሩ ‘በሕይወቴ ትልቅ ጥፋት አጠፋሁ የምለው የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተርን ቀይ ሥጋጃ አንጥፌ መቀበሌ ነው ብለው ነበር፡፡ ቀይ ሥጋጃ ላይ በተረማመደ ቀባጣሪ ፈረንጅ ምስክርነት ስለኢኮኖሚው የተባለው ሁሉ ውሸት ሆኖ ሊቆጨን እየጀመረ ነው፡፡ በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ እንዳለው ልጅ መንግሥትም ቀድሞ በቀጣችሁኝ ኖሮ የሚልበት ጊዜ ላይ ደርሷል፡፡ ምርት የሚያመርተው ሰው ጥቂት ሆኖ የሚበላው ሰው ግን ብዙ መሆን የአገሪቱን ኢኮኖሚ እየገዘገዘው ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በየዓመቱ አሥራ አንድ በመቶ እንደሚያድግ በሚነገርበት ጊዜ ይህ ሁሉ ሥራ አጥ መኖሩ፣ ከውጭም ከውስጥም በዕርዳታና በልመና ካልተደጋገፉ መኖር አለመቻሉ፣ በዋጋ ንረት እየተማረሩ መኖሩ ምንን ያመለክታል? የምናየው ሌላ የምንሰማው ሌላ ከዓይናችንን በላይ ጆሯችንን ልናምን አንችልምና የምትዋሹ አትዋሹ፡፡

የሚሸጡት ቢያጡ ራሳቸውን ሸጡ

በደላላ ተሳበበ እንጂ ባለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት ኢትዮጵያ ልጆችዋን ቪዛና ፓስፖርት ሰጥታ በሎሌነት እንዲያገለግሉ እንጀራ ፍለጋ ወደ ውጭ አገሮች አፍልሳ በሚልኩላት ዕርዳታ ጉልበታቸውን ሸቀጥ አድርጋ ለንግድ አቅርባለች፡፡ ስደተኛ ልጆችዋን ‘ዳያስፖራ’ በሚል የቁልምጫ ቃል እያባበለች ወተታቸውን ለማለብ አንዳንዱን አገር ወዳድ ነው ብሎ በማሞካሸት፣ አንዳንዱን በመሬት እሰጥሃለሁ በመደለል እያግባባች ትኖራለች፡፡ ሰላሳ ዓመት አገሩንና መንግሥቱን ያገለገለ የመንግሥትና የግል ሠራተኛ አንድ ክፍል ስቱድዮ የኮንዶሚንየም ቤት ዕጣ እስከሚደርሰው እየጠበቀ፣ ስደተኛው መጥተህ መሬት በነፃ ውሰድ ደረጃውን የጠበቀ ኮንዶሚንየም ተሠርቶልሀል ይባላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጠቀሰው አባት ቤት ያለውን ልጁን ትቶ የጠፋው ልጁን ፍሪዳ አርዶ ተቀበለው እንደተባለው ይሆን? ወይስ ከሎሌነት ጉልበቱ ዋጋ መረቅ ጨመር አድርጎ እንዲልክ ማግባቢያ ነው፡፡

መንግሥትን ከስደተኛ ሎሌዎች እስከመለመን ያዋረደው ጉዳይ ምን ይሆን? በቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ተቀምጠው የሚለምኑ ምንዱባን እንኳ ቀና ብለው የሰው ዓይን ለማየት እያሳፈራቸው ለመንግሥት ይህን ያህል የልመና ድፍረት የሰጠው ማን ነው? የሰው አገር ሎሌነትን እየካበ ወጣቶች በምድርም በባህርም እንዲኮበልሉስ ለምን ይገፋፋቸዋል? በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ላይ ቆመን የምንሸጠው ብናጣ ራሳችንን እየሸጥን አይደለምን? ስደተኛም እንበለው ዳያስፖራ እዚህ ካለነው ብዙ እጥፍ ስለሚሻል በሎሌነት ሥራ ባገኘው ገንዘብ ኢንቬስትር እንዲሆን ጠርተን ስብሰባ ተቀምጦ ባለበት ሰዓት፣ የውስጥ ችግራችን ፈንቅሎ ወጥቶ አሳፈረን፡፡ ዘንድሮስ በዳያስፖራ እንግዶች ፊት ያዋረደን ከድርቅ የከፋ ዝናብና ክረምት ነው የገጠመን፡፡

የማህፀን ኪራይ ጋብቻ ገቢ

አንድ ሰሞን ደግሞ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽኑም የዓባይ ግድቡም ወሬ ቀዝቀዝ ብሎ የጋዜጦችን ዓምድ ያጣበበው የኢንዱስትሪዎች ፓርክ ዜና ነው፡፡ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከእስያ፣ ከአፍሪካም ኢንቨስተሮች እንደመጡም ይነገራል፡፡ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ሠርቶ ያላለፈልን መቶ ፈረንጅ ሠርቶ ያሳልፍልናል የሚል ተስፋ ተጥሏል፡፡ ሕዝባችንን ውጭ አውጥተን መሸጡ አልበቃ ብሎን መሬታችንን በኪራይ ለመሸጥ እየተዋዋልን ነው፡፡ ከቅርብ ወራት ወዲህ ኢሕአዴግ ሰማንያ አምስት በመቶ ከሚሆነው በግብርና ከሚተዳደረው የገጠሩ ገበሬ፣ በሚሊዮን ከሚቆጠረው በጥቃቅንና አነስተኛ ከተደራጀው የከተማ ወጣት፣ በሺዎች ከሚቆጠሩት ከአገር ውስጥ ባለፀጎች ድጋፍ ላይ የተመሠረተ የኢኮኖሚ ዕድገት የአቅርቦት ጎን ፖሊሲው ትኩረቱን ወደ የውጭ ኢንቨስተሮች ቀይሯል፡፡ በአምራቾች ድጋፍ የአቅርቦት ጎን ፖሊሲ በዚህም በዚያም ብሎ አልሆን ቢለው፣ የምድሪቱን ማህፀን ለውጭ ኢንቨስተር ከማከራየት በሚገኝ ገንዘብ ላይ ተማምኗል፡፡

ሐዋሳ ከትመው መሬታችንን በኪራይ ለማግባት የጥሎሽ ቆጠራ ሥነ ሥርዓቱን የተካፈሉ ኢንቨስተሮች ለአገሪቱ ምን እንደሚያመጡ በመገናኛ ብዙኃን ብዙ ተወርቶላቸዋል፡፡ ተቆነጃጅተን አማምረን እንጠብቃቸዋለን ጥሎሹንም በየጊዜው እየጨመርንላቸው ነው፡፡

ከቀረጥ ነፃ ዕቃ ማስገባቱ፣ የግብር ዕረፍቱ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታው፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ ዝግጅቱ፣ ከአገር ውስጥ ባንክ ብድር ማግኘቱ ምድሪቱን ከውጭ ኢንቨስተሮች በኪራይ ለማጋባት የምንሰጣው ጥሎሾች ሆነዋል፡፡ በውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ጨለምተኛ አመለካከት ባይኖረኝም፣ ጥቅምና ጉዳትን ማመዛዘኛ መረጃም ባይኖረኝም፣ ሃያ ዓመት ሙሉ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ሲመላለሱ ለነበሩ የውጭ ኢንቨስተሮች ሥራቸው ሚዜነት የሆነ የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች እንደ አዲስ ሙሽራ  ኃይሎጋ ጭፈራ ገርሞኛል፡፡

የውጭ ኢንቨስተሮች ከ1985 እስከ 2007 ዓ.ም. በነበሩት 22 ዓመታት በ10,229 ፕሮጀክቶች 520.7 ቢሊዮን ብር መዋዕለ ንዋይ አፍስሰው በገበያችን ውስጥ ልንሸምተው የቻልነው እዚሁ የተመረተ በቂ የፋብሪካ ሸቀጥ አላገኘንም፡፡ በዕዳ ከመዘፈቅም አልዳንም፣ መሠረተ ልማቶች ተሟልተው የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተገነቡላቸው አዲሶቹ ኢንቨስተሮችም ምርታቸውን የሚሸጡት በውጭ ገበያ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ስልሳ ሺሕ ተቀጣሪዎች የደመወዝ ገቢ የሚያገኙ ሲሆን ያመረቱት ምርት ግን በአገር ውስጥ ገበያ አይቀርብም፡፡ ወደ ውጭ ተልኮ ለኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሪ የኤክስፖርት ገቢም አያመጣም፣ የሽያጭ ገቢው ለኢንቬስተሮቹ ነው፡፡ የምናገኘው ገቢ የምድራችንን ማህፀን ለውጭ ኢንቨስተሮች ከማከራየትና ከአንዳንድ የመንግሥት ግብርን ከመሳሰሉ ሌሎች የገቢ ዓይነቶች ነው፡፡ 

ከኢንቨስተሮቹ ጋር የሚሠሩት ሠራተኞች ግን በተከፈላቸው ደመወዝ በገበሬው፣ በወዛደሩ፣ በአገልግሎት ሰጪው በአገር ውስጥ የተመረቱትን ሸቀጦች የመግዛት አቅም ያገኛሉ፡፡ በዚህም ለአገር ውስጥ የሚመረቱ ሸቀጦች የጤፉ፣ የዘይቱ፣ የምስሩ፣ የሽንኩርቱ፣ የቲማቲሙ፣ የቃሪያው፣ የሎሚው ዋጋ ይጨምራል፡፡ ተጠቃለን የግብርና ምርት ውስጥ ገብተን እነኚህን የምግብ ምርቶች ልቁጠር እንጂ ገቢያችንን የምንደለድልበት ሌላ ምን ፍጆታ አለን፡፡ የእኛ ሥራ ከስደተኛ ልጆቻችን ላብና ከምድራችን ማህፀን ኪራይ ጋብቻ የሚመጣውን ሀብት ቁጭ ብሎ መብላት ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡ በወጣትነቷ በሴተኛ አዳሪነት የኖረች ውብ ኮረዳ በስተርጅና ኑሮዋ ቆነጃጅት ሴተኛ አዳሪዎችን መመልመል ነውና እኛም የመሬታችንን ማህፀን የሚያገባ ኢንቬስተር እየመለመልን እንኖራለን፡፡

ከዚህ በላይ የቀረበው የመረጃ ትንታኔና የባለሙያ ሐሳብ የአደጋ ጠርዝ ላይ ከጣሉን የኢኮኖሚ ችግሮች ጥቂቶቹን ብቻ የሚያብራራ ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጭ መሟጠጥ ችላ የማይሉት የአደጋ ምልክት መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ መንግሥት በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የሚያጋጥም ነው እያለ የመዘናጋት ስሜት እያንፀባረቀ ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል የችግሮች ምክንያትና መፍትሔዎች ላይ እናተኩራለን፡፡

ጥንዳዊ አፈጣጠርና ጥንዳዊ ፖሊሲ

እግዚአብሔር ብዙ ነገሮችን ሙሉ እንዲሆኑ ጥንድ አድርጎ ፈጠራቸው፡፡ ሁለት ዓይን፣ ሁለት ጆሮ፣ ሁለት እጅ፣ ሁለት እግር አድርጎ ሠራቸው፡፡ በግራም በቀኝም እንዲያዩ፣ በግራም በቀኝም እንዲሰሙ፣ በግራም በቀኝም እንዲሠሩ፣ በግራም በቀኝም እንዲራመዱ አደረጋቸው፡፡ አንድ ዓይን ብቻውን አስተውሎ አያይም፣ አንድ ጆሮ ብቻውን አጥርቶ አይሰማም፣ አንድ እጅ ብቻውን አሳምሮ አይሠራም፣ አንድ እግር ብቻውን አስተካክሎ አይራመድም፡፡ ሰውና እንሰሳትንም ወንድና ሴት ጥንዶች አድርጎ ፈጠራቸው፡፡ በትዳር ውስጥ አንዱ ብቻ ያለው ጎደሎ ሲሆን ሁለቱም ያለው ሙሉ ነው፡፡ በፈረሰ ትዳር ውስጥ ነዋሪው አንድ ብቻ ሲሆን ቤቱ በሀብት ቢበለፅግም አንዱ ከጎኑ ስለሌለ ሌላው ጎደሎ ነው ከቶ ምንም ቢሆን ሙሉ ሊሆን አይችልም፡፡ አንድ አይነድ አንድ አይፈርድ፣ አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብ ብለን በጥንድነት ላይ እምነት እንጥላለን፡፡

ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም በጥንድነት የተገነባ ነው፡፡ እንደ ጥንድነታቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችም ጥንድ ባህሪይ አላቸው፡፡ ፖሊሲዎች ከቀጣሪው፣ ከአሠሪው፣ ከአምራቹ፣ ከመዋዕለ ንዋይ አፍሳሹ በአጠቃላይ አጠራር ከአቅርቦት ጎንና ከተቀጣሪው፣ ከሠራተኛው፣ ከሸማቹ፣ ከቆጣቢው፣ በአጠቃላይ አጠራር ከፍላጎት ጎን ታይተው እንደሚደጋገፉም ተደርገው በጥንድነት ይነደፋሉ፡፡ በአንድ ዓይን ሳይሆን በሁለት ዓይን ይታያሉ፡፡ በአቅርቦት ጎን ፖሊሲ ኢሕአዴግ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም፡፡ ግን በየቀኑ በየዓመቱ ከድጡ ወደ ማጡ ነው የሄደው፡፡ ከዚህ በፊት ዓመቱን ሙሉ በተደጋጋሚ ስለዚህ ጉዳይ የጻፍኩ ቢሆንም፣ አሁን ላለንበት ሁኔታ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ከጊዜው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዛምጄ ደግሜ ለመናገርና ለመጻፍ እፈልጋለሁ፡፡ መፍትሔው አንድ ብቻ ነው ይኸውም የአቅርቦት ጎን ፖሊሲንና የፍላጎት ጎን ፖሊሲን ማጣመር ነው፡፡ ፍላጎትን በፈለገው መንገድ የሚያሽከረክረውና የፍላጎት ጎን መሠረት የገቢ መጠን ሲሆን፣ አቅርቦትን በፈለገው መንገድ የሚያሽከረክረውና የአቅርቦት ጎን መሠረት የትርፍ መጠን ነው፡፡ ስለሆነም የፍላጎት ጎን ፖሊሲ የገቢ መጠን ፖሊሲ ሲሆን፣ የአቅርቦት ጎን ፖሊሲ የትርፋማነት ፖሊሲ ነው፡፡ የገቢ ምንጭ ሥራና ሀብት ሲሆን፣ የትርፋማነት ምንጭም ምርታማነት ነው፡፡ የአንድ አገር ፖሊሲ በሥራና በሀብት ገቢ እና በምርታማነት ላይ ማትኮር አለበት፡፡

የኢሕአዴግ የሃያ አምስት ዓመት ፖሊሲ ያተኮረው ከምርታማነት ውጪ በሚገኝ ትርፋማነት ላይ ሲሆን ይህም ወልጋዳ የአቅርቦት ጎን ፖሊሲ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ለአምራቹ ትርፋማነትን ለማሳደግ የተጠቀማቸው ፖሊሲዎች አንዱ ለአምራቹ በቀጥታ ድጋፍ መስጠት ሲሆን፣ ሌላው የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲው ነው፡፡ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲን ለአምራቹም ለሸማቹም እንደሚመች አድርጎ መመጠን ሲቻል፣ ኢሕአዴግ ያተኮረው በአምራቹ ትርፋማነት ላይ ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ ከስልሳ ብር ተነስቶ ሁለት ሺሕ ብር ገባ፡፡ ሐሰተኛ የፖሊሲ ባለሟሎች የጤፉን መወደድ ግብር ገብሮ ደመወዝ በሚከፍላቸው ነጋዴ እንደሚያሳብቡት ሳይሆን፣ በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መብዛት ምክንያት የመጣ ነው፡፡ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ የኩንታል ጤፍ ዋጋ አራት ሺሕም ስምንት ሺሕም ለመግባት የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ አምራችም ሸማች፣ ሸማችም አምራች ናቸውና የጤፉ መወደድ እንዳይጎዳቸው የተወሰኑ አምራቾች የወር ደመወዛቸው ከሁለትና ሦስት ሺሕ ብር ተነስቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላሳ፣ አርባ፣ መቶ ሺሕ ብር ገባ፡፡ በዋጋ ውድነቱ የተጎዱት የሕዝቡን ግማሽ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ለሥራ ያልበቃ ልጆችና ወላጆቻቸው፣ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች፣ የአዋቂዎችን ግማሽ የሚሆኑት የቤት እመቤቶች፣ ታማሚዎች፣ ሥራ አጥ ወጣቶች፣ በደመወዝ መደራደር የማይችሉት የመንግሥት ሠራተኞች፣ ጡረተኞችና አቅመ ደካሞች ናቸው፡፡ የተጎዱት ሲደማመሩ ከጠቅላላው ሕዝብ ዘጠና አምስት በመቶ ይሆናሉ፡፡

የፍላጎትና የአቅርቦት አዋቂነትና አላዋቂነት

በገቢያቸው መጠን ላይ ተመሥርቶ ሸማቾች በሸመታቸው አምራቾችም በምርታቸው አላዋቂ (Irrational) ከሆኑ የግል ኢኮኖሚውና የብሔራዊ ኢኮኖሚው ጤናማ ግንኙነት ይፋለሳል፡፡ አላዋቂነት ማለት ሸማቾች በገቢያቸው ላይ ተመርኩዞ በሚሸምቱት የፍጆታ ሸቀጥና አምራቾች በትርፍ ላይ ተመርኩዞ በሚያመርቱት ምርት ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጣቸውን ለመምረጥ አለመቻል ማለት ነው፡፡ በሸማቾች በኩልም ይምጣ ወይም በአቅራቢዎች በኩል አላዋቂነት ካለ የግል ኢኮኖሚው ለብሔራዊ ኢኮኖሚው የመሠረት ድንጋይ መሆን ይሳነዋል፡፡ በተለይም ሸማቾች በሸቀጥ ጣዕማቸው አምራቹን ምን እንደሚያመርት አዛዦች ስለሆኑ፣ የእነሱ አላዋቂ መሆን አምራቹንም አላዋቂ ያደርገዋል፡፡ በሸማቾች ትዕዛዝ አምራቾች ለኑሮ ከሚበጅ ሸቀጥ ይልቅ ትርኪ ምርኪ ሸቀጥ በማምረት ሥራ ላይ ይሰማራሉ፡፡ ሸማቾች አዋቂ ሸማች እንዲሆኑ የመንግሥት ፖሊሲ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የገቢ መጠን ግብና የገቢ ድልድል ግብ መንግሥት ሸማቹን የሚመራባቸው መንገዶች ሲሆኑ፣ የገቢ መጠንና የገቢ ድልድል ግቦች የሚወሰኑት በመንግሥት በጀትና በጥሬ ገንዘብ መጠን ፖሊሲዎች ነው፡፡ መንግሥት በበጀትና በጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ ኢኮኖሚውን መምራት አለመቻሉን ከፍ ብለን የተመለከትነው የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት የመረጃዎች ትንታኔ ያመለክተናል፡፡

ለገቢ ድልድል ፍትሐዊነትም ዝቅተኛው የሠራተኛው ደመወዝ ወለል መጠንንና የካፒታል ትርፋማነት ጣሪያ መጠንን በሕግ መወሰንም ይቻላል፡፡ በሞኖፖል ንግድ አምራቾች የሸማቾችን ገንዘብ ያላግባብ እንዳይዘርፉም ውድድርን የሚፈጥሩ ፖሊሲዎች መንደፍ ይቻላል፡፡ አምራቾች አዋቂ አምራች እንዲሆኑ ዛሬ በኢትዮጵያ እንደሚታየው ለአንዱ እንዲያመርት መሬትና ገንዘብ መስጠት ለሌላው መከልከል ሳይሆን፣ በነፃ ገበያ ሕግ መሠረት ሁሉም ሰው እኩል ዕድል አግኝቶ ውድድር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡ ድጋፍ ከውድድር በኋላ ሊመጣ የሚችል እንጂ ውድድርን የሚተካ መሆን አልነበረበትም፡፡ መሬትና ገንዘብ በፍላጎትና አቅርቦት መስተጋብር ዋጋቸው በገበያ ውስጥ የሚተመን የነፃ ገበያ ሸቀጦች እንጂ፣ መንግሥት ለፈለገው የሚሰጠውና ለሌላው የሚነሳው የመንግሥት ንብረቶች አልነበሩም፡፡

ምርት ለማምረት ከሚያስፈልጉት አራት የምርት ግብረ ኃይሎች መሬት፣ ካፒታል፣ የሰው ኃይልና ከሰው ጋር ከተዋሀደው ሥራ ፈጠራ ችሎታ (Entrepreneurship Skill) መንግሥት ከነፃ ገበያው ያልነጠቀው የኋለኞቹን ሁለቱን ብቻ ነው፡፡ እስከ መቼ ድረስ ከሰው የሥራ መሣሪያውን ነጥቆ ባዶ እጅህን ሥራ ፍጠርና ሥራ ይባላል? መሬትና ካፒታል የሌለው ሰው ወይም ቀጥሮ የሚያሠራው ድርጅት ያላገኘ ሰው ምን ሠርቶ ይኖራል? እስከ መቼስ ነው የሥራ መሣሪያ ሀብት ለሕዝብ በራሽን የሚከፋፈለው? ሕዝቡ የሥራ መሣሪያውን ተነጥቆ ባዶ እጅህን ሥራ ፈጥረህ ሠርተህ ብላ በመባሉ የተፈጠረውን ችግርና መፍትሔ ቀጥለን የአቅርቦት ፖሊሲንና የፍላጎት ጎን ፖሊሲን በየተራ በመተንተን እንመልከት፡፡

ምርትና አቅርቦትን የተመለከቱ ፖሊሲዎች

የበጀትና የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲዎች በአቅርቦት ላይም በፍላጎት ላይም ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ ስለዚህም ሁለቱንም ወገኖች በሚጠቅም መልኩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአቅርቦት ላይ ያሳደሩትን ተፅዕኖ እንመልከት፡፡ የበጀት ፖሊሲ በአቅርቦት ላይ ያደረሰው ተፅዕኖ መንግሥት ለገበያ የሚቀርቡ ሸቀጦችን እኔ ላምርት ብሎ በሚያደርገው የሀብት ሽሚያ የግሉን አምራች ከገበያ በማስወጣት ነው፡፡ መንግሥት ኢኮኖሚና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን፣ መሠረተ ልማቶችን፣ እንዲሁም እጅግ ወሳኝ የሆኑ መሠረታዊ የፍጆታና የካፒታል ምርቶችን ማምረት ቢገባውም፣ የገበያ ሸቀጦችን ለገበያው መተው ሲኖርበት ከነፃ ገበያ መርህ ውጪ እያመረተ ይገኛል፡፡ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ የቁጠባና የማበደርያ ወለድ መጣኝ የሚወሰነው በጥሬ ገንዘብ አቅርቦትና ፍላጎት መስተጋብር ቢሆንም፣ መንግሥት የወለድ መጣኙ ላይ በፖሊሲ አማካይነት ተፅዕኖ ለማድረግ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠንን መቀያየር ይችላል፡፡ ይህም በመዋዕለ ንዋይ አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ የምርት መጠንን የመቀነስ፣ የመጨመርና የመለወጥ አቅም ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ውጪ መንግሥት ራሱ በቀጥታ የወለድ መጣኝን በመወሰን በቁጠባና በመዋዕለ ንዋይ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር ግን የነፃ ገበያ መርህ አይደለም፡፡

 

የኢሕአዴግ ወልጋዳ የአቅርቦት ጎን ፖሊሲ ለአምራቾች የሚሰጠው ድጋፍ ነው፡፡ ድጋፍ ሰጪ ድጋፍ ሲሰጥ የራሱን ንብረት መሆን አለበት፡፡ አምራቾች ድጋፍ እንደሚስፈልጋቸውም አይካድም፡፡ ኢሕአዴግ የሚሰጠው የራሱን ንብረት ሳይሆን የሕዝብ የሆነውን መሬትና በሶሻሊዝም ሥርዓት ተወርሶ፣ የሕዝብ ንብረት የሆነውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የልማት ባንክ ገንዘብ ነው፡፡ የድጋፍ ዓይነት የተዥጎደጎደላቸውና ኢሕአዴግ የተማመነባቸው ብልጣብልጥ አምራቾች ነን ባይ ራስን አንጋሾች ባገኙት የማይገባ የአቅርቦት ጎን ድጋፍ ፖሊሲ፣ እውነተኛ አምራቾች በእኩል ሜዳ እኩል ዕድል አግኝተው እንዳይወዳደሩ ስላደረጋቸው ለኢኮኖሚው ፍትሐዊ ዕድገት ጠንቅ ሆኗል፡፡ አምራቹ የሚታዘዘው በቅርቡ ላለው ገንዘብ ለሚሰጠው ለሸማቹ እንጂ በሩቅ ሆኖ በድጋፍ ብዛት ለሚያግባባውና ለሚለምነው መንግሥት አይደለም፡፡ አምራች ነጋዴ ከፈጣሪውና ከአምላኩ ቀጥሎ የሚፈራውና የሚያከብረው የህልውናው ጌታ አድርጎ የሚያየውም ሸማቹን እንጂ፣ ከሩቅ እየተማፀነ የሚለምነውንና በቁጣ የሚያስፈራራውን መንግሥት አይደለም፡፡ የአገር ሀብት ጥቅሙ ወደ ተሻለ ምርት ዘርፍ አዙሮ መጠቀምና የኢኮኖሚውን የማምረት አቅም ማሳደግ ከሰው ሳይመፀወቱና ሳይበደሩ ወይም የውጭ ኢንቨስተርም ሳይለምኑ፣ በራስ አቅም አቅርቦትን ከፍላጎት እኩል ማድረግ የሚቻለው ሸማቹና አምራቹ እንዲናበቡ በማድረግ ነው፡፡

ሸማቹንና ፍላጎትን የተመለከቱ ፖሊሲዎች

በሸማቹ ላይ ተፅዕኖ አድርጎ የሸመታ ዓይነትና መጠኑን ለመቀያየር፣ ለመጨመር፣ ለመቀነስ ወይም ለመለወጥ የገቢ መጠንን የመቀነስ የመጨመርና የመለወጥ ግብ ወይም የገቢ ክፍፍሉን የማመጣጠን ግብ በመንግሥት በጀትና በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲዎች ይገራል፡፡ የፍላጎት ጎን ፖሊሲ ሰዎችን መርጦ ስለማያበላልጥ አድልኦ የሌለበት ፖሊሲ ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ መጣኝ የብርን ዋጋ በማርከስ (Devaluation) ከአገር ውስጥ ምርት ጋር ሲነፃፀር የውጪውን ሸቀጥ ውድ በማድረግ ሸማቹ ከውጭ አገር ምርት ይልቅ፣ የአገር ውስጥ ምርትን እንዲመርጥ ዓለም አቀፍ የንግድ ስምምነቶችን ሳይጥሱ በፖሊሲ ተፅዕኖ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከውጭ ሸቀጥ ጋር የሚወዳደር ሸቀጥ በአገር ውስጥ መቼ ተመረተና ነው ብላችሁ አትጠይቁኝ፡፡ እኔ በመስማት ደረጃ የማውቀው ኢኮኖሚያችን ለአሥራ አምስት ዓመታት በተከታታይ በአሥራ አንድ በመቶ ማደጉን ነው፡፡

ሸማቾች የሚበሉት ምግብ፣ የሚጠጡት ውኃ፣ የሚለብሱት ልብስ፣ የሚኖሩበት ቤት፣ ምግብ ማብሰያቸው፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች፣ የሚጓጓዙበት የሞተር ትራንስፖርት፣ የሚታከሙበት ሐኪም ቤት፣ ለልጆቻቸው ትምህርት ቤት፣ እንዴትና በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚያገኙ የግላቸው ጥረት ቢወስነውም፣ እነዚህ መሠረታዊ የኑሮ ሸቀጦችና ሌሎችም ሸቀጦች ለሕዝቡ እንዴት እንደሚዳረሱ ለዕድልና ለዕጣ ፈንታ የሚተው ጉዳይ አይደለም፡፡ የሸመታ አቅምንና የሸቀጥ ጣዕምን የሚገራ የመንግሥት ፖሊሲም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ኢኮኖሚው በራሽን ይከፋፈል ማለት አይደለም፡፡ ፍላጎትን የመቆጣጠርና ካስፈለገም የመግራትና የመግታት ፖሊሲ የሚነደፈው የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለትን ወይም የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማቃለልና ከዕርዳታና ከብድር ተፅዕኖ ለመላቀቅም ነው፡፡ ወይም በውስጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሸማቹን ከዋጋ ግሽበት ለመከላከል ነው፡፡

በገቢ ድልድል ግብ ብዙ አገሮች ዝቅተኛውን የደመወዝ መጠን በሕግ በመደንገግ ሠራተኛውን ከብዝበዛና ከአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ይከላከላሉ፡፡ የሠራተኛው ገቢና የሸመታ አቅሙ ሲጨምርም አስተማማኝ ሸማች ሆኖ አምራቾችን ያበረታታል፡፡ በሺሕ አምስት መቶ ብር ደመወዝ ከከተማ ወጣ ያለ ደሳሳ ጎጆ በሺሕ ብር ተከራይቶ ከነቤተሰቡ አምስትና ስድስት ሆኖ የሚኖር ሸማች፣ በምንም መልኩ አምራቾችን ሊያበረታታ አይችልም፡፡ የገቢ መጠንና የገቢ ክፍፍል ለውጥ በሰዎች የሸቀጥ ሸመታ ዓይነት ጣዕም ላይ ብርቱ ተፅዕኖ ስለሚኖረው ገቢ ሲቀንስ በቅድሚያ ከገበያ የሚወጡት ትርኪምርኪ ሸቀጦች ናቸው፡፡ ገቢ ሲጨምርም ወደ ገበያ የሚገቡት እነኚሁ ሸቀጦች ናቸው፡፡ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የጥቂቶች ገቢ ሰማይ ደርሶ እንደ ዕርቃን ዳንስ ምሽቶች፣ የመዝናኛና ስፖርት ወሬዎችና ተረቶች የመሳሰሉ ትርኪምርኪ ሸቀጦችን እንዳግበሰበሰች የማያውቅ የለም፡፡ በመረጃ ላይ የተደገፈ የገበያ ጥናት ቢደረግ በገቢና በዋጋ ለውጥ የሸቀጥ ፍላጎት ልጠት (Income and Price Elasticity of Demand) ልኬቶች ገቢ ሲጨምርና ሲቀንስ፣ ወይም ዋጋ ሲጨምርና ሲቀንስ የትኞቹ ሸቀጦች በቅድሚያ ከገበያ እንደሚወጡና ወደ ገበያ እንደሚገቡ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

የፖሊሲ አቀንቃኞች ትምህርትና ጤና ለሁሉም እንዲዳረስ በመደረጉ የኑሮ እኩልነቱና መመጣጠኑ ተረጋግጧል፡፡ በዓለም አቀፍ የእኩልነት ኑሮ መለኪያ  (Gini Coefficient) መሠረት የኑሮ እኩልነቱ የተመጣጠነ የኑሮ ደረጃ ካላቸው (Welfare States) በመባል ከሚታወቁት ስዊድንን ከመሳሰሉ የስካንዲኔቪያን አገሮች ጋር የሚመሳሰል ነው ይላሉ፡፡ ለማስላትና ለመናገር ባይፈልጉም ሁላችንም እኩል ደሃ በነበርንበት የደርግ ዘመን በሀብት ፍትሐዊ ድልድል የስካንድኔቪያን አገሮችን እናስከነዳ ነበር ማለት ነው፡፡ ራሳቸው የኢኮኖሚ ባለሟሎቹንም ጨምሮ ብዙ የመንግሥት ሠራተኞች ከሃያና ሰላሳ ዓመት አገልግሎት በኋላም አራትና አምስት ሺሕ ብር የተጣራ የወር ደመወዝ እያገኙ፣ በድጋፍ በሚያብጡት የግል ንግድ ተቋማት ግን የእነሱን ያህል የሥራ ልምድ የሌላቸው ከሃምሳ እስከ መቶ ሺሕ ብር የወር ደመወዝ እንደሚያገኙ ሳያውቁ ቀርቶ ይሆንን? የእነሱን የወር ደመወዝ ያህል ሌሎች በሰዓታት የቦርድ ስብሰባ ተሳትፎ እንደሚያገኙስ አያውቁምን?

በቀድሞ ጊዜ በውጭ አገር የኑሮ ደረጃ ለሠራተኞቻቸው ይከፍሉ የነበሩትን የተባበሩት መንግሥታት አካል ድርጅቶች የሚያህል ክፍያ፣ ዛሬ የሠራተኛውን ምርታማነት ያላገናዘበ የወር ደመወዝ የአገር ውስጥ የግል ድርጅት ከሸማቹ ከሚመዘብረው ትርፍ ለሠራተኛው ይከፍላል፡፡ ምንም እንኳ ባለመታደላችን በቃላት ምስክርነት የመንግሥት ፖሊሲ አቀንቃኝ ምሁር ከመሆን አልፎ ተርፎ የደመወዝ ዕድገት የሥራ ቅጥርን ቀንሶ ሥራ አጥነትን እንደሚያስፋፋ በሒሳብ ለክቶ የሚያሳየን የኢኮኖሚ ባለሙያ ባይኖረንም፣ ጽንሰ ሐሳብን በተግባር ፈትሸው ከሚያረጋግጡት የፈረንጆቹ ምሁራን የሚሉትን በሰማነው ልክ ማመን እንችላለን፡፡

ፈረንጆቹ ከዚህም ባሻገር የደመወዝ ዕድገት ከምርታማነት ዕድገት በላይ ከፈጠነ ክስረት መሆኑንም ያረጋግጡልናል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የጥቂቶች የገቢ ዕድገት ከምርታማነት ዕድገት በመብለጥ ስትከስር ኖራለች፡፡ ይኼ ክስረትና ከሚያመርቱት በላይ ሸቀጦችን ለመሸመት መቻል ነው ዛሬ ልትፈነዳ አድርሶ አደጋ ላይ የጣላት፡፡ ሰው በማግኘቱ የሚጠላ ሰው የለም፡፡ በተለይም ኢኮኖሚስት ዋናው ሥራው ስለማግኘት እንጂ ስለማጣት አይደለም፡፡ ለመጨመር እንጂ ለመቀነስ ኢኮኖሚስት አያስብም፡፡ ነገር ግን ለአንዱ መጨመር ለሌላው መቀነስ ከሆነና የአንዱ ከልክ በላይ መጥገብ ሌላውን የሚያስርብ ከሆነ፣ የጠገበው ጥጋቡ እስከ ዕርቃን ዳንስ የሚያዋርደው ከሆነ ኢኮኖሚስትም ስለመቀነስ ያስባል፡፡

የውጭ ምንዛሪ መጣኝ መስተካከል አንድምታ

የገጠመንን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡ የኤክስፖርቱና የኢምፖርቱን ንግድ ስንገመግመው ከዓመት ዓመት ክፍተቱ እየሰፋ እንጂ እየጠበበ አልመጣም፡፡ ብድሩም ስለተቆለለ ዕዳው ሳይከፈል በፊት ሌላ ብድር ማግኘት ሊቸግር ይችላል፡፡ የምንዛሪ መጣኙ ቢስተካከል የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ችግር ይቀረፍ ይሆን? የዓለም የገንዘብ ድርጅትም መንግሥትን የምንዛሪ መጣኙን አርክሱ (Devalue) እያለ እየወተወተ ስለሆነ ማርከሱ ይጠቅማል፡፡ የብድር ከፋይነት አቅም ገማች ድርጅቶችም መንግሥት በቀጥታ ከወሰደው ይልቅ፣ ባለበጀት ያልሆኑ የመንግሥት ድርጅቶች የወሰዱት ብድር አሳሳቢ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የምንዛሪ መጣኙ መለወጥ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ይቀርፍ እንደሆን ለመረዳት ስለባንኮች ጥሬ ገንዘብ ሀብት (Monetary Assets of Banks) ዓይነትና መጠን፣ ስለጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠን (Money supply) እና ስለየውጭ ምንዛሪ መጣኝ አወሳሰን ሥርዓቶች (Exchange Rate Regimes) አንዱ በሌላው ላይ ስለሚያሳድረው ተፅዕኖና በገበያ ውስጥ ስለሚያደርጉት መስተጋብር ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ምንጮች የባንኮች ገንዘባዊ ሀብቶች ሲሆኑ፣ እነርሱም ከዕዳ ቀሪ የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ሀብት (Net Foreign Asset) እና የአገር ውስጥ ብድር ሀብት (Domestic Credit) ተብለው በሁለት ይከፈላሉ፡፡ አንዱን በሌላው በመሸጥና በመግዛት ግብይት ምክንያት አንዱ ሲጨምር ሌላው ይቀንሳል፡፡ ወይም በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠን ፖሊሲ ምክንያት ሁለቱም ሊጨምሩም ይችላሉ፡፡ የሁለቱም መጨመር የሸቀጦችን ዋጋ ያንራል፡፡ በሌላ የብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት ውስጥ ባለ የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ መረጃ መሠረት፣ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ምንጭ ከሆኑት ሁለት የባንኮች (የብሔራዊ ባንክና የንግድ ባንኮች በአንድነት) ጥሬ ገንዘብ ሀብቶች ውስጥ ከዕዳ ቀሪ የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ሀብት እየቀነሰ፣ በምትኩ የአገር ውስጥ ብድር ሀብት እየጨመረ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

ለምሳሌም በ2006 ዓ.ም. አርባ ስድስት ቢሊዮን ብር በብር የተመነዘረ ከዕዳ ቀሪ የተጣራ የውጭ ምንዛሪና ሦስት መቶ ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ብድር የባንኮች ጥሬ ገንዘብ ሀብት፣ በ2007 ዓ.ም. ሰላሳ ስምንት ቢሊዮን ብር በብር የተመነዘረ ከዕዳ ቀሪ የተጣራ የውጭ ምንዛሪና ሦስት መቶ ዘጠና ሦስት ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ብድር የባንኮች ጥሬ ገንዘብ ሀብት በመሆን በቅንብሩ በ2007 ዓ.ም. የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ሀብት ድርሻ ቀንሶ የውስጥ ብድር ሀብት ድርሻ ጨምሯል፡፡ ወደኋላ ሄደን ስንመለከትም በ2003 ከነበረው ጠቅላላ የባንኮች ጥሬ ገንዘብ ሀብት ውስጥ ሃምሳ አምስት ቢሊዮን ብር በብር የተመነዘረ ከዕዳ ቀሪ የውጭ ምንዛሪ ሀብት ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ብድር ሀብት አንድ መቶ ሰላሳ ስድስት ቢሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ መረጃዎቹ በየዓመቱ የተጣራ የውጭ ምንዛሪ የባንኮች ሀብት እየቀነሰ የአገር ውስጥ ብድር ሀብት መጨመሩን ያሳያሉ፡፡

ስለጥሬ ገንዘብ ምንጮች ይህን ያህል ካወቅን ስለውጭ ምንዛሪ መጣኝ አወሳሰን ሥርዓቶች ደግሞ አንዳንድ ነጥቦችን እንመልከት፡፡ ሦስት ዓይነት የውጭ ምንዛሪ መጣኝ አወሳሰን ሥርዓቶች አሉ፡፡ እያንዳንዱም የየራሱ ጥቅምና ጉዳት አለው፡፡ በተንሳፋፊ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ አወሳሰን ሥርዓት (Floating Exchange Rate Regime) የውጭ ምንዛሪ መጣኙ በገበያ ዋጋ ስለሚወሰን፣ ብሔራዊ ባንክ በገበያ ውስጥ ተሳትፎ ለማድረግ ጣልቃ አይገባም፡፡ በአገር ውስጥ ብድር የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠን ላይ ብቻ አትኩሮ በሸቀጦች ዋጋ ውጣ ውረድ አማካይነት የውጭ ምንዛሪ መጣኝን በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲው ተቆጣጥሮ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና አቅርቦት እንዲጣጣሙ ያደርጋል፡፡ በተንሳፋፊ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ አወሳሰን ሥርዓት የአገር ውስጥ ምርት ሸቀጦች የገበያ ዋጋ ከውጭ ከሚገቡ የኢምፖርት ሸቀጦች የገበያ ዋጋ ጋር በሚደረግ ንፅፅር የውጭ ምንዛሪ ተፈላጊነትና አቅርቦት በራሱ የውስጥ ሒደት ተስተካክሎ፣ ዋጋውም በገበያ ኃይላት መስተጋብር ይወሰናል፡፡ መንግሥት በቀጥታ የውጭ ምንዛሪ ገበያው ውስጥ ሳይገባ የሸቀጦችን ዋጋ በጥሬ ገንዘብ አቅርቦቱ እየተቆጣጠረ የውጭ ምንዛሪ መጣኙ ላይ በተዘዋዋሪ መንገድ ተፅዕኖ ያደርጋል ማለት ነው፡፡

ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ግብይት ተፅዕኖ አሳድሮ በአገር ውስጥ ብድር ጥሬ ገንዘብ መብዛትና ማነስ የሸቀጦች ዋጋን በማስወደድና በማርከስ፣ በእርግጠኛ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ (Effective Real Exchange Rate) የብር ዋጋ እንዲቀንስ ወይም እንዲጨምርም ያደርጋል፡፡ እርግጠኛ መመነዛዘሪያ መጣኝ የአንድ አገር ምንዛሪ ሸቀጦችን በመግዛት አቅሙ ከሌላው ተገበያይ አገር ምንዛሪ ሸቀጦችን ከመግዛት አቅም ጋር ሲወዳደር፣ ወይም በተመናዛሪዎቹ አገሮች ውስጥ ያለውን የዋጋ ንረት ልዩነት ከግምት ያስገባ የመመነዛዘሪያ መጣኝ ማለት ነው፡፡ ይህም ኤክስፖርትን ለማሳደግና ኢምፖርትን ለመግታት አገሮች የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው፡፡ ለምሳሌ ሃያ ብር በአንድ የአሜሪካ ዶላር ይመነዘር ከነበረና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የአሥር በመቶ የዋጋ ንረት ተከስቶ በአሜሪካ ግን የአምስት በመቶ ብቻ የዋጋ ንረት ከተከሰተ፣ የዋጋ ንረቱ ተቀናንሶ ከዶላር ዋጋ አንፃር የብር ዋጋ በአምስት በመቶ ዝቅ ስለሚል የብርና የዶላር መመነዛዘሪያ አንድ ዶላር በሃያ አንድ ብር ይሆናል፡፡ በዚህም አንድ ዶላር የሚያወጣ የአሜሪካ ሸቀጥ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በአንድ ብር ተወዶ ሃያ አንድ ብር ሲሆን፣ ሃያ ብር የሚያወጣ የኢትዮጵያ ሸቀጥ ወደ አሜሪካ ሲገባ ግን ዋጋው ዘጠና አምስት የአሜሪካ ሣንቲም ብቻ በመሆን በአምስት የአሜሪካ ሣንቲም ይረክሳል፡፡ ለኢትዮጵያ ሁኔታው ኤክስፖርት በመርከስ በአሜሪካ ገበያ ተወዳዳሪ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ገበያ የአሜሪካ ኢምፖርት ውድ ስለሚሆን ተወዳዳሪ አይሆንም፡፡  

በቅድሚያ በሚወሰን ቋሚ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ አወሳሰን ሥርዓት (Fixed Exchange Rate Regime) በፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ምክንያት የውጭ ምንዛሪው መጣኝ ከተወሰነው እንዳይቀያየር፣ ብሔራዊ ባንኩ በገበያው ውስጥ በቀጥታ ተሳትፎ አድርጎ የውጭ ምንዛሪ በመግዛትና በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ በማድረግ ይከላከላል፡፡ በቋሚ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ ሥርዓት ብሔራዊ ባንክ የምንዛሪ መጣኙ እንዳይለወጥ የውጭ ምንዛሪ ሲገዛና ሲሸጥ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ጥሬ ገንዘብ ሀብቱን መጠን (Foreign Reserve)፣ የእርሾ ጥሬ ገንዘብን መጠን (Reserve Money) እና በአጠቃላይ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትን መጠን (Money Supply) የመቆጣጠር አቅሙን ያጣል፡፡ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠን በፖሊሲ የሚወሰን በመሆን ፈንታ በኢኮኖሚው ውስጣዊ መስተጋብር ኃይል የሚወሰን ይሆናል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ለመግዛት በሚወጣው የአገር ውስጥ ብድር ጥሬ ገንዘብ መብዛት የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በውጭ ምንዛሪ ግዢ ምክንያት የተፈጠረውን ተጨማሪ የአገር ውስጥ ብድር ጥሬ ገንዘብ ለማምከን (Neutralization)፣ በአገር ውስጥ የሰነድ ገበያ ሰነዶችን ሸጦ ጥሬ ገንዘብ ከገበያ ውስጥ በማስወጣት መጠኑን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ግን የተደራጀ የሰነዶች ገበያ ስለሌላትና ለማምከን ብላ ብዙ የመንግሥት ሰነዶችን ከሸጠች ከጊዜ በኋላ የወለድ መጣኙን ለመክፈል ከባድ የበጀት ጫና ስለሚፈጥርባት ማምከን የምትችለው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እርሾ ጥሬ ገንዘቧ በውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀመቀጯ ያልተደገፈ መሆኑን የመጠን ልዩነታቸው ስለሚገልጽ ግን የማምከን ዕድሉ አላት፡፡ አንዳንድ አገሮች ምንም እንኳ የገንዘብ አቅርቦት መጠንን መወሰን አቅም ቢያሳጣቸውም የውጭ ምንዛሪ መጣኛቸውን ዝቅተኛ የዋጋ ንረት ካለው አገር ምንዛሪ ጋር ተለጣፊ (Pegged) ያደርጋሉ፡፡ በዚህም የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲያቸው የሚወሰነው ተለጣፊ በሆኑበት አገር የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ ሲሆን፣ በውጭ ምንዛሪ መጣኝ ገበያ ሙሉ ተሳትፎ አድርገው የውጭ ምንዛሪ በመግዛትና በመሸጥ የክፍያ ሚዛን ሒሳባቸውን ጉድለት ማስተካከል አይችሉም፡፡ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ መጣኟን ከአሜሪካ ዶላር ጋር አስተሳስራ ተለጣፊ ስላደረገች፣ በውጭ ምንዛሪ ገበያ ሙሉ በሙሉ ያልሆነ በምንዛሪ ቦርድ የሚወሰን ከፊል ተሳትፎ ስለምታደርግ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጭ ሀብቷን የመደጎም አቅሟ በምንዛሪ ገበያ ተሳትፎዋ ልክ የተገደበ ነው፡፡ ስለሆነም ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ ግብይት በሚያደርጉ አገሮች ምንዛሪና በአሜሪካ ዶላር የምንዛሪ መጣኝ ለውጥ ሲደረግ በተመነዛዛሪ አገሮቹ የእርግጠኛ የምንዛሪ መጣኝ ለውጥ ምክንያት፣ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸውና ወደ ውስጥ የምታስገባቸው ሸቀጦች ዋጋዎች ተለውጠው ከለውጡ ተጠቃሚም ተጎጂም የምትሆንበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡

በየትኛው ምርትና ሸቀጧ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ፈልጋ እንደሆነ ባይታወቅም፣ አገሪቱ በውጭ ንግድ ፖሊሲዋ ኤክስፖርት ተኮር ፖሊሲ እንደምትከተል ትለፍፋለች፡፡ ይልቁንስ ጧት ማታ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ግቡ የምትላቸው ባለሀብቶች ከቻይና ኢምፖርት ሸቀጥ ወረራ ጥበቃ ካልተደረገላቸው፣ ለሕዝባቸው የኢምፖርት ሸቀጥ ምትክ የሚሆን የፍጆታ ምርት ማምረት እንደማይችሉ ብታስብበት ይበጃት ነበር፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ ቢወጣ ቢወርድ በግለሰብ ደረጃ ለሰፊው የኢትዮጵ ሕዝብ አይበርደው አይሞቀው፡፡ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው ገቢው በአገር ውስጥ ለሚመረት የግብርናና አገልግሎት ምርት፣ ቀሪው አሥር በመቶም ለልባሽ (ሳልቫጅ) ጨርቅና ጫማ ለሆነ ሕዝብ የውጭ ምንዛሪ መጣኝ መውጣት መውረድ ምን ትርጉም አለው? ኑሮው ከዓለም ሕዝብ የኑሮ ዓይነት ጋር ለመዋሀድ ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ አገር አይጎበኝ፣ አውሮፕላን አይሳፈር፣ የአውሮፓና የአሜሪካ ሸቀጦች አይሸምት፡፡ ቻይና በምታራግፍበት ትርኪምርኪ ሸቀጥ ምናልባት መጠነኛ ጉዳት ሊደርስበት ይችል ይሆናል፡፡ የድህነት ቅነሳውን ለክተው ከሌሎች አገሮች ጋር የሚያነፃፅሩትና ቀነሰ የሚሉ ሰዎች ስህተት እዚህ ላይ ነው፡፡ የፍጆታ ሸቀጦች ቅርጫታችን ከዓለም ሕዝብ የፍጆታ ሸቀጦች ቅርጫት ጋር የሚነፃፅረው በንጥረ ነገር (ኒዩትሪሽን) መጠን ብቻ እንጂ፣ ጥራቱ በሚሰጠን ደስታና እርካታም ጭምር አይደለም፡፡ አሰስ ገሰስ ሰብሳቢዎች ሆነናል፡፡

በውጭ ምንዛሪ መጣኙ መውጣት መውረድ ተጠቃሚና ተጎጂ የሚሆኑት የመንግሥት ሜጋ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ እንደ አገር ስናስብ ግን የመንግሥትም ሆነ የግል ልማት ሲደናቀፍ የሚጎዳው ሁሉም ኅብረተሰብ ነው፡፡ በግለሰቦች ደረጃ ግን የውጭ ምንዛሪ መጣኙ መውጣትና መውረድ የሚጎዳውና የሚጠቅመው ጥቂት የውጭ ሸቀጦች ተጠቃሚ ሀብታሞችን ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ነዋሪዎች ይልቅ የስደተኛ (ዳያስፖራ) ዜጎች በውጭ ምንዛሪ መጣኙ መውረድና መውጣት ተጎጂና ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ምክንያቱም በሚኖሩበት አገር የኑሮ ደረጃ ልክ የሚከፈላቸው የውጭ ምንዛሪ ወደ ኢትዮጵያ ብር ተቀይሮ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገዛላቸው ቋሚ ንብረት ኑሯቸውን ስለሚለውጠው ነው፡፡ ወደ አገር ቤት ሲመጡ ከውጭ ዜጎች እኩል የትልልቅ ሆቴሎች ተጠቃሚ የሚሆኑትም እነሱ ናቸው እንጂ፣ የአገር ውስጥ ነዋሪ ዜጋማ በምን አቅሙ በደጃፋቸው ቢያልፍ ይበቃዋል፡፡ ውጭ እየኖሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ቤት ገዝቶ ወይም ሠርቶ በጥበቃ ሠራተኛ ማስጠበቅ ተለምዷል፡፡ አብዛኞቹ የሚኒባስ ታክሲዎች ባለቤቶች ዓረብ አገር በግርድና ሁለትና ሦስት ዓመት የሠሩ ናቸው፡፡ እኔም አንድ ሁለት ዓመት ዱባይ ወይም ደቡብ አፍሪካ ሄጄ ጉልበቴን ሸቅዬ (ሸቅጬ) ብመጣ ሳይሻለኝ አይቀርም፡፡

በውጭ ምንዛሪ ተጠቃሚው ሰው ማነስ ምክንያትም ነው ባለፉት ሃያ ዓመታት የአገር ውስጥ ሸቀጦች ዋጋ እስከ ሃያ እጥፍ ሲያድግ፣ የዶላር ምንዛሪ ዋጋ ግን በሦስት እጥፍ ብቻ ያደገው፡፡ ሌላው የምንዛሪ መጣኙ ቢወድቅ ቢነሳ ሕዝቡ በግል ደረጃ እንደማይሞቀውና እንደማይበርደው አመላካች የጥቁር ገበያውና የኦፊሴል መመነዛዘሪያ ዋጋው ተመጣጣኝ መሆን ነው፡፡ የጥቁር ገበያው ተገበያዮች ሻጩም ገዢውም ቁጥር እጅግ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ፣ በኦፊሴል የመገበያያ ዋጋው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድርና በፍጥነት ሊቀያይረው አልቻለም፡፡ ይህ ያልገባቸው ወይም ማደናገር የሚፈልጉ የኢኮኖሚ ባለሟሎች የፖሊሲያቸው ትክክለኛነት በጥቁር ገበያው ዋጋ የተረጋገጠ ይመስላቸዋል፣ ወይም ያስመስላሉ፡፡

ማጠቃለያ

ሃያ አምስት ዓመት ሙሉ በአንድ በአቅርቦት ዓይን ብቻ ሲያይ የኖረው የኢሕአዴግ መንግሥት ማጣፊያው ጠፍቶታል፡፡ በውጭ ምንዛሪ ዕጦት ምክንያት ኢምፖርቱን ቢገድብ የካፒታል ዕቃዎችን ማስገባት አቅቶት ኢኮኖሚው አሥራ አንድ በመቶ ላያድግ ነው፡፡ ገና ከጅምሩ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መኖሩ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶቹ ተንጠልጥለዋል፡፡ የካፒታል ፕሮጀክቶች መንጠልጠል  ወዲያው ችግሩ ወደ ኅብረተሰቡ በፍጆታ ሸቀጦች እጥረት መልክ አይሸጋገርም፣ ቀን ይጠብቃል፡፡ በዚህ ሁኔታ እያለ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋን ጨምሮ የቀድሞው ቦታ ቢመለስ እንኳ የሚገባበት ቀዳዳ ያጣል፡፡ የጥሬ ገንዘብ አስፋፊ ፖሊሲ ተጠቅሞ ኤክስፖርትን ርካሽ፣ ኢምፖርትን ውድ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጩን ሊያሳድግ ቢሞክር የሸቀጦች ዋጋ ግሽበት የውስጥ ኢኮኖሚ ቀውስ ስለሚፈጠር ግራ ገብቶታል፡፡

 የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት አሥጊነት ደረጃን ለመወሰን ሌሎች ወሳኝ ጉዳዮችም ከግምት ውስጥ ይገባሉ፡፡ እነሱም በቅርብ ጊዜ መከፈል የሚገባቸው የውጭ ዕዳዎች ክምችት፣ የአገሪቱ አዲስ የውጭ ምንዛሪ የመበደር አቅም፣ ኤክስፖርትና ኢምፖርት የውጭ ንግድ ከአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ድርሻ እንደ አብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጭ ብዙም ይሁን ጥቂት አንዲት አገር ባላት የውጭ ምንዛሪ ክምችት መጠን ላይ መተማመኗ፣ ከውጭ አገሮች ጋር በሚኖራት ግንኙነትና በድርድር ሊገኙ ከሚችሉ አጋጣሚዎች አንፃር ሊታይም ይችላል፡፡ የዕዳ ስረዛና ልዩ ድጋፍ ማግኘት፣ የዕዳ ክፍያ ጊዜን የማስተላለፍ፣ የውጭ ዕዳን ከነወለዱ ሳይከፍሉ ማከማቸት፣ የመሳሰሉት ሁኔታዎች የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረትን ሥጋት የሚቀንሱ ናቸው፡፡ ‘ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል’ ይባላል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎች መንግሥት የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጭ እጥረት እንዳለበት ደብቆ ሊያቆይ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ናቸው፡፡ ሆኖም እንደ ፀጉራሙ ውሻ አንድ ቀን ሞት መጥቶ ይወስደዋል፡፡ የዚህ ሞት ዓይነት ድባብ በኢኮኖሚያችን ውስጥ እየተስተዋለ ነው፡፡

የኢሕአዴግ መንግሥት እስከዛሬ አገሪቱ ያላትን ጂኦ ፖለቲካ በመጠቀም ከውጭ መንግሥታት ጋር በመወዳጀትና ዕርዳታና ድጋፍ በማግኘትና ደርግ የወረሳቸውን የሕዝብ ንብረቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች በመሸጥ፣ የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾችን በመጋበዝ፣ የአገሪቱ ሕዝቦች ወደ ውጭ ሄደው ጉልበታቸውን ሸጠው የውጭ ምንዛሪ ለዘመዶቻቸው እንዲልኩ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን በከፊል ተቋቁሞታል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ለሁልጊዜው አይቀጥልም፡፡ በአንድ እጅ የሚያጨበጭቡ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካሪዎች ፍላጎትን ትተው ስለአቅርቦት ብቻ እያሰቡና እያወሩ ገደል ሊከቱን ነው፡፡ ስለኑሮአችን ከእኛ በላይ ሊያስብ የሚችል ሰው የለም፡፡ ዝምታም ሁላችንንም ገደል ውስጥ ይከተናል፡፡ ኢኮኖሚው ወደ መውደቅ ያዘነበለ መሆኑ የሚታያቸው ሁሉ ደመናውን ለመግፈፍ አስተያየታቸውን ቢለግሱ ጥቅሙ ለሁላችንም ነው፡፡ የፖሊሲ ስህተት እንደ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ሰውን በመቆጣትና በማስፈራራት በአጭር ጊዜ ውስጥ አይታረምም፡፡ መንግሥት ግን የፖሊሲ ድክመት የሌለ ለማስመሰል ጉዳዩን በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት እያሳበበ ጊዜ መግዛቱን መርጧል፡፡ ሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነትም ቢሆኑ የሚፈሩት ተቆጪ ሰው ሲኖር ነው የሚታረሙት፡፡ ከላይ ያለው ሙሰኛ ከታች ያለውን ሙሰኛ ሲቆጣው፣ ከታች ያለውም የበታቹን ሲያስፈራራ እኛ ቴአትር ቤት ያለን ይመስል ቁጭ ብለን እንመለከታለን፡፡ ጎርፉ ሲመጣ የላይኛውንና የታችኞቹን ሙሰኞች ብቻ ሳይሆን እኛንም ይወስደናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles