Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኮንሶ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀረበ

የኮንሶ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀረበ

ቀን:

–  አካባቢው መረጋጋት ተስኖታል

የደቡብ ክልል መንግሥት የኮንሶ ሕዝብ በኮሚቴው አማካይነት በዞን ደረጃ ለመተዳደር ያቀረበውን ጥያቄ ባለመቀበሉ፣ ጥያቄውን ለፌዴሽን ምክር ቤት አቀረበ፡፡

የደቡብ ክልል መንግሥት ብሔረሰቦች ምክር ቤት ሰኔ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ለኮንሶ አካባቢ በዞን የመደራጀት ጥያቄ አቅራቢዎች በጻፈው ደብዳቤ፣ ጥያቄው ተገቢነት የለውም የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ለኮንሶ ሕዝብ ጥያቄ በመሸኛ ደብዳቤ ዘጠኝ ገጽ ያለው ትንታኔ በመስጠት ክልሉ በፍፁም የኮንሶ ሕዝብን በዞን የመደራጀት ጥያቄ እንደማይቀበል አስታውቋል፡፡

የኮንሶ አካባቢ በዞን የመደራጀት ጥያቄ አቅራቢ ኮሚቴ አባል አቶ ገመቹ ገምሴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ክልሉ ከ11 ዓመታት ጥያቄና ትግል በኋላ በጽሑፍ ጥያቄያችንን እንደማይቀበል ገልጾልናል ብለዋል፡፡

በዚህ መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጠየቀው መስፈርት መሠረት የኮንሶ ሕዝብ ጥያቄውን ሰሞኑን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቧል ሲሉ አቶ ገመቹ ገልጸዋል፡፡

‹‹የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክረምት ወራት ዕረፍት በመውጣቱ፣ በአዲሱ ዓመት መጀመርያ ጥያቄዎቻችን እንደሚመለከት ተነግሮናል፤›› በማለት አቶ ገመቹ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኮንሶ ወረዳ መረጋጋት የተሳነውና የግጭት ቀጣና የሆነ ሲሆን፣ ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በሁለት መንደሮች መካከል በተነሳ ግጭት በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን፣ በሰዎች ላይም ጉዳት መድረሱንና ሕፃናትና ሴቶች ወደ አጎራባች ቀበሌዎች መሰደዳቸውን አቶ ገመቹ ተናግረዋል፡፡

ባለፉው አምስት ወራቶችም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ ደመወዝም አይከፈልም ተብሏል፡፡ የሴፍቲኔት ፕሮግራም እየተካሄደ ባለመሆኑ፣ እንዲሁም የጤና ተቋማት በተሟላ መንገድ አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው ነዋሪዎች ለችግር መዳረጋቸውን አቶ ገመቹ ተናግረዋል፡፡

የኮንሶ ሕዝብ በዞን ደረጃ ለመተዳደር ጳጉሜን 2007 ዓ.ም. ለደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ ነገር ግን የደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት የኮንሶ ሕዝብ ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡ የክልሉ ምክር ቤት ሰኔ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹የኮንሶ ሕዝብ መሠረታዊና ቀጥተኛ ጥቅሞችንና ሌሎች ሕገ መንግሥታዊ ዓላማዎችን ለማሳካት እንዲቻል ሕዝቡ አሁን ባለበት በሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን እንዲቀጥልና ለብቻው በዞን ለመደራጀት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት የለውም፤›› ብሏል፡፡

የደቡብ ክልል ምክር ቤት የብሔረሰቦች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የኮንሶ ሕዝቦች ጥያቄ መርምሮ ባቀረበው ሪፖርት፣ በዞን ደረጃ ለመተዳደር ጥያቄ ከቀረበ ማግሥት ጀምሮ በርካታ ሕገወጥ ተግባራት ተፈጥረዋል፡፡ ከተፈጸሙት ሕገወጥ ተግባራት መካከል ሕገ መንግሥቱ እንዲያስከብር የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ከጥቃት እንዲከላከል ተጠሪነቱም ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሆነውን የኮንሶ ወረዳ ፖሊስ ኃይል ከክልል ጀምሮ ከተዘረጉ መዋቅሮች  የሚሰጠውን ትዕዛዝ እንዳይቀበል ተደርጓል፡፡

‹‹ለወረዳው ከተመደቡ 160 የፖሊስ አባላት 17ቱ ብቻ ሲቀሩ ሌሎች 143ቱ መደበኛ ሥራቸውን እንዲለቁ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኮንሶ ወረዳ መቀመጫ ከሆነው ካራት ከተማ በወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው እንዲሁም ተፈርዶባቸው ጭምር በቁጥጥር ሥር የሚገኙ 60 ሰዎች ከታሰሩበት ፖሊስ ጣቢያ በኃይል እንዲለቀቁ ተደርጓል፤›› ሲል የክልሉ ምክር ቤት ሪፖርት አቅርቧል፡፡

‹‹ከዚህ በተጨማሪም የግብርና ባለሙያዎችና መምህራን ሥራ እንዲያቆሙ ተደርጓል፡፡ ለሴፍቲኔት ፕሮግራም የተመደበው በጀት ሥራ ላይ እንዳይውል ተደርጓል፤›› ሲል የሚገልጸው የክልሉ ምክር ቤት፣ ጥያቄያቸው በኃይል ምላሽ ለማግኘት የተደራጁ መኖራቸውንና ለዚህም ሕገወጥ ተግባር የብሔረሰብን ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት በአሉታዊ መንገድ እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጿል፡፡

‹‹መዋቅር መፍጠር ወይም አደረጃጀት በራሱ ግብ ሳይሆን የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተወጠኑ የልማትና መልካም አስተዳደር አጀንዳዎች ማስፈጸሚያ መሣሪያ ነው፡፡ በክልሎችና በተለያየ ጊዜ የሚነሱ በመዋቅር የመተርተር ጥያቄዎች የሕዝቡን ቀጥተኛ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ በሚችሉ አቅጣጫዎች ላይ ተመሥርተው መታየት አለባቸው፤›› ሲል የክልሉ ምክር ቤት የዞን ጥያቄው በፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት ብቻ ሳይሆን የደቡብ ክልል ፀጥታና አስተዳደር ቢሮም የዞን ጥያቄውን በበጎ አልተመለከተውም፣ ቢሮው በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት እንደገለጸው በኮንሶ ወረዳ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው፡፡ በተለይም የመዋቅር መተርተር ጥያቄ ማለትም ኮንሶ ራሱን ችሎ በዞን መደራጀት አለበት የሚል ፈጽሞ ልማታዊ ያልሆነ አስተሳሰብ የተሸከሙ ጥገኛ ቡድኖች አካባቢውን ለማተራመስና ዞኑን ለመበተን የማይሠሩት ሥራ የለም ሲል ጉዳዩን በአሉታዊነት ተመልክቷል፡፡

‹‹ቡድኑ ዕቅድና ሐሳቡን ለማሳካት ባህላዊ የጎሳ አደረጃጀትን ሽፋን በማድረግ እስከ ቀበሌ ድረስ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በመጣስ በሰዎች ላይ የገንዘብ ቅጣት መጣልና ማኅበራዊ ግንኙነቶች እየጎዱ ነው፤›› ሲል የገለጸው የፀጥታ ቢሮው፣ ለዚህ ሕገወጥ ተግባር አጀንዳ አዘጋጅ የእኛው አመራር (ደኢሕዴን) ነው፤›› ሲል ይደመድማል፡፡

የፀጥታ ቢሮው ከዚህ በተጨማሪ በተለይ አመራሩ ጭምር ተጠያቂ መሆኑን በወረዳው ያለውን የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴ ያነሳል፡፡

‹‹አካባቢው እንዳይረጋጋ ከሚያደርጉ ጉዳዮች አንዱ ሕገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የኮንትሮባንድ ከሞያሌ ተነስቶ ሀገረ ማርያም በመግባት በቡርጂ ወረዳ አድርጎ ወደ ሀገረ ማርያምና ኮንሶ ወረዳዎች በመግባት ካራት ከተማን ማዕከል በማድረግ በጋሞ ጎፋ ዞን አድርጎ መሀል አገር ይገባል፤›› ይላል ሪፖርቱ፡፡

‹‹በዚህ መስመር ለሚገቡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ዋና አመቻቹ የደኢሕዴን አመራር መዋቅር ነው፡፡ በተለይም በሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን የቡርጂ ወረዳ ፖሊስ አዛዥና የወንጀል መከላከል ኃላፊን ጨምሮ ተጠያቂ እንዲሆኑ የተደረገበት ከመሆኑም በላይ፣ ድርጅታችን ባለፉት ዓመታት ባደረገ ግምገማ የዞኑ አመራሮችን ተጠያቂ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩን ማስታወስ ብቻ በቂ ነው፤›› በማለት የሚተነትነው የፀጥታ ቢሮ ሪፖርት፣ ‹‹የኮንትሮ ባንድ ማዕከል በሆነው ካራት ከተማና አካባቢው በየጊዜው ለሚቀሰቀሰው ግጭት የራሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርቷል፡፡

በደቡብ ክልል ካሉት 14 ዞኖች ውስጥ የሰገን አካባቢ ሕዝቦች አንዱ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በአራት ልዩ ወረዳ ተዋቅሮ የነበሩት ቡርጂ፣ አማሮ፣ ኮንሶና ደራሼ ከአራት ዓመት በፊት አንድ ላይ ሆነው የሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን መሥርተዋል፡፡

ነገር ግን የኮንሶ ወረዳ ራሱን በቻለ ዞን ለመተዳደር ጥያቄ ቢያነሳም፣ ጥያቄው በክልሉ ተቀባይነት በማጣቱ ጥያቄውን ሰሞኑን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረቡን አቶ ገመቹ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለዕረፍት በመበተኑ ከዕረፍት ሲመለስ ምላሽ እንደሚሰጥ ተነግሮናል፤›› በማለት አቶ ገመቹ ገልጸዋል፡፡

የኮንሶ ሕዝብ በዞን ለመተዳደር ያቀረበው ጥያቄ መሠረት የሚያደርገው የኮንሶ ልዩ ወረዳ ሕዝብ መክሮና ፈቅዶ አዎንታውን ባልገለጸበት መንገድ በሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን እንዲዋቀር መደረጉ አግባብ አይደለም በሚል ነው፡፡

ለደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት የቀረበው ጥያቄም የኮንሶ ወረዳ ‹‹በጫና የሰገን ሕዝቦች ዞን ውስጥ እንዲካተት በመደረጉ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ በደሎች ደርሰውብናል፤›› ሲል ይገልጻል፡፡

‹‹የኮንሶ ሕዝብ አንድነት፣ ማንነት፣ ከፋፍሎ ለመበተን የሚደረገው እንቅስቃሴ ይቁም፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 (3) መሠረት ራስን በራስ የማስተዳደር (በዞን የመደራጀት) መብት እንዲከበርልን እንጠይቃለን፤›› ሲል የኮንሶ ተወካዮች በጻፉት ደብዳቤ ክልሉን ጠይቀው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...