በእነ በቀለ ገርባ የክስ መዝገብ ለተከሰሱ 22 ሰዎች የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ መጥሪያ የደረሳቸው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓቢይ አህመድና (ዶ/ር) የለገዳዲ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በተጠሩበት ቀን ለምስክርነት መቅረብ ስለማይችሉ ተለዋጭ ቀን እንዲሰጣቸው የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ፍርድ ቤቱን በአክብሮት በደብዳቤ ጠየቀ።
ጽሕፈት ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው የጠየቀበት ምክንያት ለምስክርነት የተጠሩት የሥራ ኃላፊዎች በአገራዊ ጉዳይ ላይ ውይይት እያደረጉ ነው በማለት ነው።
በተመሳሳይ ለዚሁ የክስ መዝገብ በምስክርነት የተጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጽሕፈት ቤታቸው በኩል በሥራ መደራረብ ምክንያት መገኘት እንዳልቻሉ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።