– የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቅጣት ተጣለበት
በአየር መንገድ የደንበኞች አገልግሎት ሱፐርቫይዘር መሆኑ የተገለጸው አቶ ሀብታሙ አሻግሬ የውጭ ዜጎችን በሕገወጥ መንገድ በመላክ ክስ ተመሠረተበት፡፡ ደሳለኝ አስመላሽ፣ ሜሮን ተሾመ፣ ቢንያም መኮንን፣ ዳንኤል መሓሪና ሩታ ደበሳይ የተባሉ ኤርትራውያንና አንድ ናይጄሪያዊ በሐሰተኛ ሰነድ ካናዳ እንዲሄዱ በማድረጉ መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡
የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ተከሳሹ ሥራው የፈጠረለትን አጋጣሚ በመጠቀም ተጓዦቹ አሟልተው መቅረብ የነበረባቸውን የጉዞ ሰነድ ሳያሟሉ እንዲያልፉ አድርጓል፡፡
አውሮፕላን ላይ መሳፈር የሚያስችላቸውን የይለፍ ወረቀት (Boarding Pass) ይዘው መቅረብ የነበረባቸው ስድስቱ ሰዎች አለመያዛቸውን ሲገልጹለት፣ 23,000 ብር በመቀበል የሌላ የአየር መንገድ ሠራተኛ የይለፍ ቃል (ፓስወርድ) በመጠቀም፣ የተጓዦቹን ስም በቦርዲንግ ፓስ ላይ በመሙላት እንዲያልፉ ማድረጉን ክሱ ይገልጻል፡፡
ተጓዦቹ በተሰጣቸው ሕገወጥ የይለፍ ወረቀት ሕጋዊ ተጓዦች መስለው በመሳፈር ወደ ካናዳ መጓዛቸውንም ክሱ ይገልጻል፡፡ ስድስቱም ተጓዦች ካናዳ እንደገቡ በሕገወጥ መንገድና ሰነድ መጓዛቸው በመረጋገጡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በእያንዳንዳቸው ተጓዦች 3,200 ዶላር በድምሩ 19,200 ዶላር እንዲቀጣ ማድረጉ ተገልጿል፡፡ ተከሳሹ በፈጸመው ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀምና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ሙስናና ወንጀል መክሰሱን የኮሚሽኑ ክስ ያብራራል፡፡