አቶ አደራ አብደላ፣ የኤስኤኬ ቢዝነስና ፐርሰናል ዴቨሎፕመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ
አቶ አደራ አብደላ የኤስኤኬ ቢዝነስና ፐርሰናል ዴቨሎፕመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ድርጅቱ ከተቋቋመ 11 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ድርጅቱ በትራንስፎርሜሽናል ሊደርሽፕ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ላይ የሚያተኩሩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ይሰጣል፡፡ አመለካከትና ማንነት ላይ የሚያተኩሩ ሥልጠናዎችን ለወጣቶችና ሕፃናት በነፃና በክፍያ ለማድረስም እየሠራ ይገኛል፡፡ የሚሰጣቸው ሥልጠናዎች በሥርዓተ ትምህርቱ እንዲካተቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ተደራሽ እንዲሆኑ ለማስቻል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የድርጅቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን ሥራ አስኪያጁን አቶ አደራን አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ትኩረት አድርጐ የሚሠራበትን ቢገልጹልን?
አቶ አደራ፡- የድርጅቱ ዋና ትኩረት ክህሎት፣ አመለካከትና ዕውቀትን መገንባት ነው፡፡ በተለይም አመለካከት ላይ በይበልጥ ይሠራል፡፡ ይህም የሆነው በአገራችን ከፍተኛ የአመለካከት ችግር በመኖሩ ነው፡፡ የአመለካከት ክፍተት አለ ማለት ሰዎች ያላቸውን ክህሎት በአግባቡ እንዳይጠቀሙበት ያደርጋቸዋል፡፡ አመለካከታቸው ግን ከተቀየረ ያገኙትን የንድፈ ሐሳብ ዕውቀት ወደ መሬት በማውረድ ችግሮችን ለመፍታት ይችላሉ፡፡
ሪፖርተር፡- የአመለካከት ችግር ከምን ይመነጫል?
አቶ አደራ፡- አመለካከታችንን የሚቀርጹት ብዙ ነገሮች ናቸው፡፡ አመለካከት ከሕፃንነት ጀምሮ የሚዳብር ነው፡፡ በሕፃናቱ ዙሪያ ከሚገኙ ከቤተሰብ፣ ከመምህራን እና አጠቃላይ ከማኅበረሰቡ አመለካከት ይቀረጻል፡፡ ወጐቻችን፣ አባባሎቻችን እና ሃይማኖታችን ማንነታችንን እና አስተሳሰባችንን ይቀርጻሉ፡፡ ሥራ በሚያበረታታ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖር አንድ ሰው ሥራ ለመሥራት ያለው ተነሳሽነት ከፍተኛ ይሆናል፡፡ በሌላውም እንደዚሁ፡፡ ጮክ ብሎ መናገር፣ ፈጠን ብሎ መራመድ፣ መምህርን ጥያቄ መጠየቅ፣ የተገኘን ሥራ መሥራትና የመሳሰሉት ይህንንም ያህል አይበረታቱም፡፡ የአመለካከት ክፍተት አለብን፡፡ ይህንን አገር አቀፍ ሥራ በመሥራት በኢትዮጵያ ውስጥ የአመለካከት ተሀድሶ ለማምጣት ነው የምናስበው፡፡
ሪፖርተር፡- አንድ ሰው የአመለካከት ክፍተት አለበት የሚያስብሉ ነገሮች ምን ምን ናቸው?
አቶ አደራ፡- አመለካከት ማለት ዓለምን የምናይበት ዕይታ ነው፡፡ አገርን ብንመራ፣ ድርጅት ብናስተዳድር እና በሌሎችም ሥራዎች ብንሰማራ እያንዳንዱ ሥራችን የሚወሰነው በአመለካከታችን ነው፡፡ ሰዎች አመለካከታቸውን ከቀየሩ ሰብዕናቸውም ይቀየራል፡፡ ይህ ደግሞ ነገ ለሚያደርጉት የተግባር እንቅስቃሴ ትልቅ ስንቅ ይሆናቸዋል፡፡ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ በንድፈ ሐሳብ ዕውቀታቸው ከፍተኛ ደረጃ ይደርሳሉ፡፡ ነገር ግን ለነገሮች ያላቸው አመለካከት ውስን በመሆኑ በንድፈ ሐሳብ የሚያውቁትን መሬት አውርዶ ለማስፈጸም ይቸገራሉ፡፡ በዚህም ዕውቀት ሳያንሳቸው ያላቸውን ዕምቅ አቅም ሳይጠቀሙበት ይቀራሉ፡፡ የአመለካከት ክፍተት ማለት እነዚህን ነገሮች የሚያካትት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አብረዋችሁ የሚሠሩ ሌሎች ድርጅቶች አሉ?
አቶ አደራ፡- ከባለፉት 11 ዓመታት ጀምሮ ከተለያዩ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር አብረን ስንሠራ ቆይተናል፡፡ ለመቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና ለጐንደር ዩኒቨርሲቲ የትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺፕ ሥልጠናዎችን ሰጥተናል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝም በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥረን በትምህርት ሥርዓቱ በተለይም በቴክኒክና ሙያ አመራር ላይ ለሚገኙ ከአዲስ አበባ ለተውጣጡ ኃላፊዎች የትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺፕ ሥልጠና ሠጥተናል፡፡ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ለሚገኙትም የሥራ ፈጠራ ሥልጠናዎች ሰጥተናል፡፡ ከዩኒሴፍ ጋርም እንደዚሁ አብረን እንሠራለን፡፡
ሪፖርተር፡- በማኅበረሰቡ ውስጥ በርካታ ችግሮች እያሉ ራስን የማበልጸግ ፕሮግራም ላይ ለመሥራት እንዴት መረጣችሁ?
አቶ አደራ፡- ራስን የማበልጸግ ፕሮግራምን የመረጥነው በሥራ ሒደት ከሚያጋጥሙን ነገሮች በመነሳት ነው፡፡ የአመለካከት ክፍተት በተለይ እላይ ባሉ ሥራ አስፈጻሚዎችና እንደ አጠቃላይ በማኅበረሰቡ ውስጥ አለ፡፡ ራስን የመምራትና የትራንስፎርሜሽን ሊደርሽፕ ሥልጠና የሰጠናቸው ሰዎች ‘ይህን ትምህርት ከልጅነታችን ጀምሮ አግኝተነው ቢሆን’ ይሉናል፡፡ ለምንድነው እንደዚህ የምትሉት ስንላቸውም ‘ባህላችን፣ ልማዳችን በሰው ፊት ቀርበን ራሳችንን እንድንገልጽ አይፈቅድልንም፡፡ ተሸማቀን ነው ያደግነው፡፡ ድምጻችን ዝቅ ያለነው፣ ይህም በስራችን ውጤታማ እንዳንሆን አድርጎናል’ ይሉናል፡፡ እኛም ይሄንን ነገር ለምን አናጠናም ብለን የአገራችንን የሕፃናትና ወጣቶች ፖሊሲ ሪፖርት ማየት ጀመርን፡፡ በሪፖርቱ ላይ አመለካከት እና ሰብዕና ላይ ክፍተት መኖሩን ተመለከትን፡፡ ከሲቪል ሰርቪስ የሚወጡ ሪፖርቶችም እንደዚሁ ማኅበረሰቡ የአመለካከት ችግሮች እንዳሉበት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ የአመለካከት ክፍተቶችን መሙላት የሚችሉ የትምህርት ዓይነቶች በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ተካትተዋል ወይ የሚለውንም ለማየት ሞከረን ነበር፡፡ ከሥነ ዜጋ ትምህርት ባለፈ ማንነት እና ማኅበራዊ ሕይወት ያተኮሩ ትምህርቶች የሚማሩበት ሁኔታ አለመኖሩን ተረዳን፡፡ በአቅማችን የበኩላችንን ለማድረግም አገራችን ውስጥ ያሉ ወደኋላ የሚያስቀሩን ጐታች አመለካከቶች ምንድናቸው ብለን ነቅሰን አወጣን፡፡ ይሉኝታ፣ አልችልም፣ ረፍዶብኛል፣ የሀበሻ ቀጠሮ የመሳሰሉት ማኅበረሰቡን ወደኋላ የሚያስቀሩ ችግሮች ለይተን አወጣን፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቀነስም በሥርዓተ ትምህርት መልክ በማዘጋጀት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሥልጠናዎች እየሰጠን እንገኛለን፡፡ በአገሪቱ 42 በመቶ የሚሆኑት የኅብረተሰቡ ክፍሎች ወጣትና ሕፃናት ናቸው፡፡ ይህንን ያህል ድርሻ የሚይዘውን የኅብረተሰቡን ክፍል ለብቻችን መድረስ ግን አንችልም፡፡ ስለዚህም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር አብረን ለመሥራት ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡
ሪፖርተር፡- ፕሮግራሙ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ይሆናል? ወይስ በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰነ ነው? ሥልጠናውን የምትሰጡትስ በትምህርት ክፍለ ጊዜ ነው?
አቶ አደራ፡- በበጋው ወቅት መደበኛ የትምህርት ሥርዓቱ ካበቃ በኋላ፣ አልያም ቅዳሜና እሑድ ለመስጠት አስበናል፡፡ ለጊዜው ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ ላይ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በቅርቡ ፕሮጀክቱን ለማስተዋወቅ ባዘጋጀነው ፕሮግራም ላይ የነበሩ ታዳሚዎች ፕሮግራሙ በክልሎችም ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቀውናል፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ ይህን የምንሠራውም እንደ ማኅበራዊ ኃላፊነት ሲሆን፣ የተለያዩ አጋር ድርጅቶችም እገዛ ያደርጉልናል፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላም ፕሮጀክቱ ለመንግሥት ተላልፎ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን የስረአተ ትምህርቱ አካል እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ይህም ልጆቻችን ከንድፈ ሐሳብ ክህሎት ባሻገር ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ተምረው ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡ ራዕያችን ጥበብ ያለው አገር መምራት የሚችል ትውልድን መፍጠር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ለፕሮግራሙ ምን ያህል በጀት መድባችኋል?
አቶ አደራ፡- ፕሮግራሙን ያዘጋጀነው በማኅበራዊ ኃላፊነት ቢሆንም በነፃ ለመስጠት አላሰብንም፡፡ የተለያዩ ግብዓቶች እንገዛለን፣ አዳራሾች እንከራያለን፣ ሌሎች የተለያዩ ወጪዎችም አሉ፡፡ ይህንን ለመሸፈን እና ፕሮግራሙም ቀጣይነት እንዲኖረው መክፈል የሚችሉ ከፍለው ሥልጠናውን እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ መክፈል የማይችሉ ደግሞ ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች በምናገኘው ድጋፍ ወጪያቸውን በመሸፈን ሥልጠናውን በነፃ እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- የምታዘጋጇቸውን ሥልጠናዎች በኅብረተሰቡ ምን ያህል ተቀባይነት አግኝተዋል?
አቶ አደራ፡- በእኛ ዕይታ ያልታየ የማንነት ቀውስ አለ፡፡ ለምሳሌ ተነጋግሮ መፍታት እየተቻለ ትዳሮች፣ የንግድ ተቋማት ይፈርሳሉ፣ እርስ በርስ አለመተማመን አለ፣ የሃይማኖት ተቋማትም የተለያዩ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ወጣቶችም ስለ አገር ደንታ የላቸውም፣ ራስ ወዳድ ናቸው ይባላል፡፡ ይህ ሁሉ ቀውስ የሚፈጠረው በአመለካከት ችግር ነው፡፡ ከቀለም ትምህርት ባሻገር ባህሪ ተኮር ዕውቀት ከሌለ አዋቂ አጥፊ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ወላጆች ልጆቻቸው የችግሩ ሰለባ እንዳይሆኑ ይጨነቃሉ፡፡ በሠራናቸው ጥቂት ማስታወቂያዎችም በርካታ ሰዎች አገልግሎቱን ፈልገው ወደኛ እየመጡ ይገኛሉ፡፡ የኅብረተሰቡ ተቀባይነት ጥሩ ነው፡፡ ከጊዜ ወደጊዜም እያደገ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ያለው የአመለካከት ችግር አገሪቱን ምን ያህል ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል?
አቶ አደራ፡- የግል ተቋም እንደመሆናችን አገር አቀፍ ጥናት አላደረግንም፡፡ ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያዊ የምናውቃቸውን የማኅበረሰቡን ችግሮች ነቅሰን አውጥተናል፡፡ ለምሳሌ የሥራ ተነሳሽነታችን ምን ያህል ነው የሚለውን ብናይ ከዓለም አቀፍ ደረጃው ዝቅ ያለ ነው፡፡ ሥራን አፍቅረን እንደ ፀጋ ቆጥረን ነው ወይ የምንሠራው? ወይም እንደ ግዴታ እንደ ዕዳ አስበነው የሚለውን ነገር ስናይ በጣም ወደኋላ የቀረንበት ነገር ነው፡፡ ሌላው የጊዜ አጠቃቀማችንን ብንመለከት ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ የሀበሻ ቀጠሮ ይባላል፡፡ በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ ጊዜ አይከበርም፡፡ ይህንንም እንደ ባህል ይዘነዋል፡፡ ሀበሻ አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መሥራት አይችልም የሚባል ነገርም አለ፡፡ ይህ ደግሞ ባለመነጋገር ሐሳብን ባለመጋራት የተፈጠረ ወደኋላ የቀረንበት ነው፡፡ የማድነቅ ባህላችንም ሌላው ችግር ነው፡፡ ለአመራር የምንሰጠው ዋጋም ችግር አለበት፡፡ መሪዎችን ለመቀበል እንቸገራለን፡፡ አመራራቸውን ከመቀበል ይልቅ የመጠራጠር፣ ከእነሱ እንከን የማውጣት ነገር ይታያል፡፡ እንደዚህ ያሉትን ችግሮች አመለካከት ተኮር ሥራዎችን ከታች ጀምሮ በመሥራት የሚቀረፉ ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ አገራችን ወደኋላ አስቀርቷታል፡፡
ሪፖርተር፡- ሥልጠና ከሰጣችሁ በኋላ ውጤታማነቱን የምትገመግሙበት አሠራር አላችሁ?
አቶ አደራ፡- ሥልጠናው ሲያልቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደኋላ የሚያስቀሩ አመለካከቶች ምንድናቸው ብለን ነቅሰን እናወጣለን፡፡ ከዚያም ለሠልጣኞቹ እንገልጻለን፡፡ እነሱ የሚጨምሩበት ነገር ካለ እንዲጨምሩበት እናደርጋለን፡፡ ቀጥሎ የሬሳ ሳጥን እናዘጋጃለን፡፡ ወደኋላ እንዲቀሩ የሚያደርጓቸውን አስተሳሰቦች የሬሳ ሳጥኑ ውስጥ በመክተት እንዲቀበር እናደርጋለን፡፡ ይህንንም አልችልም ቀብር ሥነ ሥርዓት እንለዋለን፡፡ በዚህ ሥልጠናው ይጠናቀቃል፡፡ ከተጠናቀቀ በኋላም በተወሰኑት ላይ ክትትል እናደርጋለን፡፡ አመለካከት በአንድ ሥልጠና የሚቀየር አይደለም፡፡ ረጅም ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን በተወሰኑት ላይ ጥሩ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ በዚህ መሠረትም ሥልጠና ከሰጠናቸው መካከል የተወሰኑትን ተከታትለን ውጤታማ መሆናችንን ማወቅ ችለናል፡፡
ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ያለውን ሥር የሰደደ የአመለካከት ችግር ለማጥፋት ምን ያህል ጊዜ ያስፈልጋል?
አቶ አደራ፡- ቻይናዎች ያደጉት ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ ነው፡፡ ለዚህም የአመለካከት ለውጥ በማምጣታቸው ነው፡፡ ይህም አገርን የማስቀደም አመለካከት፣ የሥራ ተነሳሽነት፣ አብሮ የመሥራት ፍላጐትና ሌሎችም የአመለካከት ለውጦች በመፈጠራቸው የተገኘ ነው፡፡ በእኛም አገር ሕፃናት ላይ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ላይ፣ የግል ድርጅቶች ላይ፣ አጠቃላይ ፖለቲከኞች እና የሃይማኖት ተቋማት ላይ ቢሠራ አመርቂ ውጤት እንድናገኝ ያስችላል፡፡ በሚቀጥሉት 30 እና 40 ዓመታት ውስጥም ተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ ይቻላል፡፡