Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርይድረስ “ለሚመለከታችሁ” የፍትሕ አካላት!

ይድረስ “ለሚመለከታችሁ” የፍትሕ አካላት!

ቀን:

በእስማኤል አደም

ዕለተ ማክሰኞ ነሐሴ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. በወጣው ዕለታዊው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የቀድሞውን የፍትሕ ሚኒስቴርን በማፍረስ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ እንዲሁም የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣንን የመክሰስ ሥልጣን አንስቶና የሁሉንም ከሳሽነት በሥሩ አካቶ የተቋቋመው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት አዳዲስ ዓቃቢያንን ለመቅጠር እንደሚፈልግ ገልጾ ማስታወቂያ አስነግሮ ነበር፡፡

በዚህ ከረዳት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እስከ ዓቃቤ ሕግ ደረጃ ሦስት ድረስ መመዝገብና መወዳደር እንደሚቻል በተነገረበት ማስታወቂያ ላይ የአካል ጉዳተኞች፣ የሴቶችና የ“ብሔር ብሔረሰቦች” ተዋፅኦና ኮታ ከግምት እንደሚገባ ተነግሮም ስለነበር፣ በማግሥቱ በርካታ ሰዎች ከክልል ሳይቀር መጥተው ካዛንችስ አካባቢ ባለው ዋና መሥሪያ ቤት በር ላይ የተሠለፉት በጠዋት ነበር፡፡

ተቋሙ ግን ጋዜጣው ላይ በተለይ ለዓቃቤ ሕግ ደረጃ ሦስት ካስቀመጠው የዜሮ ዓመት የሥራ ልምድ በተጨማሪ ማስታወቂያው ላይ ያልተጠቀሰውን ከ“ፍትሕ አካላት ባለሙያዎች ሥልጠና ማዕከላት” ሥልጠና የወሰዱበትን የትምህርት ማስረጃ ይዘው እንዲመጡ በመጠየቅ ነበር፣ የደረጃ ሦስት “ተስፈኛ” የሆኑ የ2008 ዓ.ም. ተመራቂዎችን ሳይመዘግብ የመለሰው፡፡

እንደ አሠራር ከዩኒቨርሲቲ የአምስት ዓመታት ቆያታ በኋላ ወደ የፍትሕ አካላት ማሠልጠኛ ማዕከላት በፈተናና ማጣሪያ የሚገቡ የሕግ ተማሪዎች ከማዕከላቱ የወራት ሥልጠናቸውን ጨርሰው ሲወጡ፣ በዳኝነትና ዓቃቤ ሕግነት የሚሾሙና የሚመደቡበት የግዴታ አገልግሎትም የሚሰጡበት ሥርዓት እንዳለ ሕጉ አካባቢ ቅርበት ያለን ሰዎች የምናውቀው እውነታ ነው፡፡

ታዲያ በምን መሥፈርት፣ ሥርዓትና አሠራር ነው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እነዚህን ሰዎች ለማወዳደር ማስታወቂያ ሊያስነግር የቻለው? ሥልጠናውን ከወሰዱ በኋላ አገልግሎቱን ለመስጠት ፈቃደኛ የማይሆኑ ሰዎች አሉ ማለት ነው? ይህስ አግባብ ነው? ካልሆነስ ተቋሙ ለምን እንዲህ ዓይነቱን አሠራር ፈለገው? … የሚሉ ጥያቄዎች የብዙዎች ሆነዋልና ተቋሙ መልስ ቢሰጥበት የፍትሕ ማዕከላቱም ይህንን ቢያውቁት መልካም ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡

የ “አዲስ አበባውያን” ነገር!

የኢትዮጵያችን ፌዴራሊዝም በዘጠኙ የፌዴራል መንግሥቱ አካላት ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለምና ሁለት የከተማ መስተዳድሮችን ያውቃል፡፡ የድሬዳዋና የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድሮችን፡፡ ድሬ በመስተዳደር ደረጃ ያለች ብትሆንም ከአዲስ አበባ በተነፃፃሪ የአንድ ክልልን (ኦሮሚያን) ባህልና ማንነት በመጠኑም ቢሆን የምታንፀባርቅ ከተማ ስለሆነች፣ ነዋሪዎቿ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትን መታወቂያ ማግኘት አይከብዳቸውም፡፡ ለድሬዳዋ የሕግ ተማሪዎችም ይኸው ጉዳይ አስቸጋሪ ላይሆን ይችላል፡፡

የኦሮሚኛን ቋንቋ እስከቻሉ ድረስም በኦሮሚያ ክልል የፍትሕ አካላት ማሠልጠኛ ተቋማት በኩል ተወዳድሮ ገብቶ መሠልጠኑም ሆነ ከሥልጠናው በኋላ በተመደቡበት አካባቢ መሥራቱ ለድሬዎች እንግዳና ያልተለመደ አዲስ ነገር አይደለም፡፡

ለእኛ ለአዲስ አበባውያኑስ?

ከወራት በፊት በሸገር ሬዲዮ ላይ ይፋ የተደረገ አንድ የጥናት ውጤት በመዲናችን አዲስ አበባ ብቻ ከሃያ ሺሕ የሚልቁ ሥራ አጥ፣ ግን ደግሞ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች እንዳሉ ተገልጾ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲ እያለሁ ከጓደኞቼ በተለይም ከሕግ ተማሪ ጓደኞቼ ጋር አብዝተን ከምንከራከርባቸው ጉዳዮች አንዱ ፌዴራሊዝማችን የ“አዲስ አበባውያን”ን ማንነትና ፍላጎት ፍፁም የዘነጋ የመሆን አለመሆኑ ነገር አንዱ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

እንደ እኔው ሁሉ በርካታ አዲስ አበቤዎች የተለያዩ ብሔሮች ድቅል ነን፡፡ ይህ ባይሆንና ከተመሳሳይ ብሔር ብንወለድ እንኳን ከብሔር ማንነታችን ይልቅ የሸገር ልጅነታችን፣ አለፍ ሲልም ኢትዮጵያዊ ዜግነታችንን ነው የምናጎላውም የሚጎላብንም፡፡ አዲስ አበቤዎች የእናታችን ወይም የአባታችን ክልል ሄደን የምናገኘው “የብሔር” መታወቂያ የለንም፡፡ የእናት ወይም የአባታችን ክልል ሄደን ልናገኝ የምንችለው የ“ፍትሕ አካላት” የሚሰጡት ሥልጠናም የለም፡፡ የፌዴራል ሥርዓታችን የሚያውቀን “ለየብቻ” ነውና ለእኛ ለጅምላዎቹ ቦታ የለውም ወይም ሆን ተብሎ ችላ ተብለናል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ በዘረዘረው መሥፈርት መሠረትም ሆነ አልፎ አልፎ ብቻ ተማሪዎችን የሚቀበለው “የፌዴራል” የሚባለው የፍትሕ አካላት ማሠልጠኛ ማዕከልም ይህንኑ “የብሔር” መሥፈርት የሚጠቀም ተቋም ስለሆነ፣ ለእንደዚህ ዓይነቶቹ የሥራ ማስታወቂያ ውድድሮችና ዕድሎች ተገቢ (Eligible) የሆኑ አመልካቾች የሚመጡት ከክልል የሕግ ተማሪዎች ብቻ ይሆናልና ሸገሮች እንደተለመደው (Business as Usual እንዲሉ!) የበይ ተመልካች ሆንን ማለት ነው፡፡ ብሶት ነውና ይለይለት አይደል?… ሌላ ከዚህም ጠንከር ያለ እውነትን እንደ ምሳሌ ልጨምር፡፡ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ማስታወቂያ ሲወጣ ከተለያዩ ክልሎች ለመወዳደር የመጡ ተማሪዎች እንደነበሩ ከላይ ጠቅሻለሁ፡፡ ከአዲስ አበባውያኑ የሕግ ተማሪዎች በተለየ ለእነዚህ የክልል ተማሪዎች ይህ ተቋምም ሆነ ሌሎች በመዲናዋ የሚገኙ የፌዴራል መንግሥቱ ተቋማት “የዕድላቸው መጨረሻ” አይደሉምና ከተሳካ ተሳካ፣ ካልተሳካም ሥራ አያጡም… ሁለት ጉድጓድ ያላት አይጥ አትሞትም እንዲሉ!

ይህን ጽሑፍ እያሰናዳሁ ባለሁበት ወቅት እንኩዋ እነዚህ የክልል በተለይም የኦሮሚያ፣ የአማራና የትግራይ ክልል ወንድምና እህቶቻችን ወደ ክልላቸው ተመልሰው የየክልሉን የፍትሕ አካላት ሥልጠና ማዕከላት ተቀባይነትን አግኝተዋል፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያዎቹም ቢሆኑ የሚጠብቁት የነሐሴን መጋመስና የክልሉን የፍትሕ አካላት ማሠልጠኛ ማዕከል ማስታወቂያ ነው፡፡ እዚህ ላይ ሳልጠቅሰው የማላልፈው አንድ እውነት ደግሞ የአዲስ አበባ ተወላጆች ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ “አባል” የሚሆኑበት የኢሕአዴግ አደረጃጀት ደኢሕዴን (ብዙ ብሔረሰቦችን ያቅፋል ተብሎ ስለሚታሰብ!) ቢሆንም፣ ተማሪዎቹ ተመርቀው ሲወጡ በዚህ ክልል እንኩዋ ሥልጠናም ሆነ ሥራ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ምንም ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ክልሎች ቅድሚያ የሚሰጡትና እንዲሰጡም የሚገደዱት ለተወላጃቸው ነውና፡፡

ብሶት ነውና ይለይለት አይደል?… በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ላሉ ቀውሶች የተማረው ወጣት ሥራ አጥ መሆኑ ተደጋግሞ በመንግሥታችን ሲጠቀስ አድምጫለሁ፡፡ የእኛስ የአዲስ አበቤዎቹ በከንቱ መባዘንስ ምነው ተዘነጋ? አደባባይ ካልወጣን አንደመጥም ማለት ነው!? ውይይቱ “ውይይት” ስለማይሆን የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል ብዬ ባላምንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በነሐሴ አጋማሽ ከከተማዋ ወጣቶች ጋር ሊያደርጉት የነበረው ውይይት ቢራዘምም ባለፈው ሳምንት ተደርጓል፡፡ እነማንን በምን መሥፈርት፣ የትና መቼ ጠርቶ እንደሰበሰበ ባላውቅም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ በየክፍለ ከተማው ወጣቶችን ሰብስቤ አወያይቻለሁ ሁከቱንም እንዲያወግዙ አድርጌያለሁ ሲልም ተደምጧል፡፡

ለመሆኑ ይኼን ያህል ሥራ ፈላጊ ያለባትን ከተማ የሚያስተዳድሩ ሰዎች ለአዲስ አበቤዎች ቅድሚያ የሚሰጡበት የሥራ ዘርፍ ይኖር ይሆን? አዲስ አበባ ምንም እንኳን የፌዴራሉ መንግሥት ማዕከል ብትሆንም፣ ለእኛ ለአዲስ አበባውያን እንደ ክልል ናትና ሌሎች ክልሎች ለተወላጆቻቸው የሚሰጡት ዓይነት ቅድሚያ ሊሰጠን ይገባል ብንልስ ጠባብነት ይሆንብን ይሆን እንዴ?

በነገራችሁ ላይ የሕግ ተማሪዎችን ጉዳይ እንደ ምሳሌ አነሳሁ እንጂ ነገርየው ብዙዎችን የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ አሁን አሁንማ የግል ድርጅቶችም ሆኑ አክሲዮን ማኅበራት የፖለቲካችንን ጤና ማጣት አሳባቂ ሆነዋልና በግልጽ የማያስቀምጡት፣ ግና እንደ መሥፈርት የሚጠቀሙበት “የብሔር ተኮር” ፉክክራዊ ቅጥር ስለመኖሩ ከአዲስ አበባውያን የተሰወረ አይደለም፡፡ በመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች በንጉሡ ጊዜ ቀርቶ የነበረው የዘመድ አዝማዳ ቅጥር አሁን ስምና መልኩን ቀይሮ በብሔር ብሔረሰብ የፉክክርና የሃይማኖታዊ ዝምድና መግነን በኩል እየመጣ መሆኑን ሰምተናልም፣ አይተን ታዝበናልም፡፡

አዲስ አበባውያን ታዲያ ተስፋችን ምንድነው? አደገኛ ቦዘኔ ተብሎ መሰደብ አይደለምን? በአዲስ አበባችን ያሉና የሸገሩ ጥናት የጠቆማቸውን ሃያ ሺሕ ሥራ ፈላጊዎች ቁጥር ሃያ ምናምን ሺሕ ገፋ ሲልም ሰላሳ ሺሕ ማድረስ አይደለምን… ታድያ ተመርቆ እንኳን ከቤተሰብ እጅና ድጎማ መውጣት ያልቻለ ወጣት ራዕዩን ቢጥልና ሱሱን ቢያጠናክር ለምን ይፈረድበትና ይተቻል? ብሶት ነውና ይለይለት አይደል?… በርካቶች በኢትዮጵያችን የፍትሕ በተለይ የወንጀል ፍትሕ የማግኘቱ ነገር መጓተት ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው ግልጽ ነው፡፡ በተለይ ከፍርድ ቤቶቻችን የወንጀል ፍትሕን፣ ከፖሊስ መከላከያና ደኅንነት ተቋማት የሰብዓዊነት ፍትሕን ማግኘት እየከበደ እንደመጣ መንግሥታችንም አምኖበታል፡፡

የሕግ ተማሪዎች ለሥራ ላይ ልምምድና ለትምህርታዊ ጉዳዮች ወደ ፍትሕ ተቋማት ስንሄድ የምንታዘበው ነገር ቢበረክትም፣ ጥቂቱን እዚህ መጥቀስ ይኖርብኛል፡፡ የመጀመሪያው ነገር ፍርድ ቤቶችን የሚመለከት ነው፡፡ ሌሎች ጉዳዮችን ለጊዜው ትተን በአዲስ አበባችንም ሆነ በክልሎች ለፍርድ መጓተት አንዱ ምክንያት፣ የዳኞች እጥረት እንደሆነና አንድ ዳኛ የበርካታ ሰዎችን ጉዳይ የሚያይ መሆኑ ነው፡፡ በአንፃሩ ሥራ አጥተው ሥራ ፍለጋ የሚንከራተቱና ይህንን ክፍተት መሙላት የሚችሉ ብሎም ራሳቸው ተጠቅመው አገራቸውንና ሕዝባቸውን መጥቀም የሚችሉ የሕግ ምሩቃንን በየቦታው እናያለንና ሊታሰብበት ይገባ ይመስለኛል፡፡

ከዚህም ባሻገር በአገራችን ያለው ሌላው ችግር የሙያና ሙያተኛ መተጣጣትም ጭምር ነው፡፡ በፌዴራል ፍርድ ቤት በአካውንቲንግ ተመርቃ የሕፃናትና ሴቶችን ጉዳይ የምትከታተል “የሕግ ባለሙያ” አውቃለሁ፡፡ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለተደራራቢ ጥቃት የተጋለጡና የሕግ ባለሙያን ድጋፍ የሚሹ መሆናቸው ሲታሰብ ነገሩን ከገረሜታ ከፍ ያደርገዋል፡፡ በአማርኛና ሥነ ጽሑፍ ተመርቆ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የምርመራ ክፍል ይሠራ የነበረ ሰውም አውቃለሁ፡፡ ይህንን ስል ግን ሙያዎችን እያጣጣልኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡ ሙግቴ ለእነሱም፣ ለአገሬና ለአገራቸውም መልካም ነገ ነውና፡፡ በሁለተኝነት የማነሳው ጉዳይ በተለይ የሕግ ተማሪዎችን ብቻ የሚመለከት ሲሆን፣ ይኸውም በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ወቅት የኢሕአዴግ አባል እንዲሆኑ የሚደረግባቸው ጫና እንዲቆም የሚል ነው፡፡

ለምሳሌ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በአንድ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት በነበርኩበት ወቅት፣ ከክፍላችን ሃምሳ ሁለት ተማሪዎች የኢሕአዴግ አባል አንሆንም ብለን እንጀራችን ላይ የቆረጥን ተማሪዎች አራት ብቻ ነበርን፡፡ የዚህ ቀላሉ ምክንያት የሕግ ባለሙያዎችም እንደ ሌሎች ተማሪዎችና ዜጎች የፈለጉት ፓርቲ አባል ሊሆኑ የሚችሉበትን መብት ማክበር ቢገባም፣ ዳተኛ በሆንበት የዳኝነት ነፃነት ላይ ሌላ ሸክም ስለሚሆንና ፍርድ ቤቶቻችንን ፍትሕ አልባ ተቋማት ስለሚያደርግ ነው፡፡ በዋነኝነት ዳኞችንና ዓቃብያነ ሕጎችን የሚያሠለጥኑ የፍትሕ አካላት ማሠልጠኛ ማዕከላትም ተማሪዎችን ሲመዘግቡም ሆነ ሲፈትኑ፣ ከ10 እስከ 15 በመቶ ለአባልነት እየተሰጠ መሆኑ ሊቀርና ዕውቀትን ብቻ መሥፈርት ሊያደርጉ ይገባል፡፡

በተመሳሳይ አመክንዮ (Logic) አባልነት የሌሎችንም የፍትሕና የዴሞክራሲ ተቋማትን ሙያዊ ነፃነት እያሳጣ እንደሆነ መግለጽ ይኖርብኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምሳሌ ከተባልኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንን፣ እንዲሁም እስካሁን ከጠቀስኳቸው የተሻለ እንቅስቃሴ ላይ ቢሆንም የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ምናልባት በቅርቡ ሜጄር ጄነራል ጻድቃን ገብረ ትንሳዔ እንዳሉት መልሶ በነፃነት መቋቋም የሚያስፈልጋቸውም ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ተቋማት የእውነትና በእውነት የሚሠሩ ነፃ የሕግ ባለሙያዎችን የሚሹ ቢሆንም፣ መንግሥታችን ይህን ባለማድረጉና ማድረግም ባለመፈለጉ የሕዝብን ተዓማኒነት ማግኘትና የቆሙለትንም ዓላማ ማሳካት ሲሳናቸው ተመልክተናል፡፡

ብሶት ነውና ይለይለት አይደል?…… በአገራችን ተቋማት እንደ አዲስ ሲዋቀሩ ወይም የሆነ ዓይነት “አዲስ” አደረጃጀት ሲፈጠርና መዋቅር ሲሠራ፣ ነባር ሠራተኞችን የማንሳፈፍና ውስጣዊ መንገራገጭ የመኖሩ ነገር ተለምዶአዊ ነው፡፡ በቅርቡ እንኳን የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ባለሥልጣን ሠራሁት ባለው አዲስ መዋቅር ሳቢያ በርካታ ሠራተኞቹን ከመሥፈርት በታች ናችሁና አብረን አንቀጥልም ማለቱ አይረሳም፡፡ 

በነሐሴ 8 ቀን 2008 የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ፣ ተቋሙ ሲመሠረት በአፈጻጸማቸው ከፍተኛ ውጤት ያላቸው ዓቃቢያንን ብቻ መርጦና ተቋሙ ሊያስተናግድ የሚችለውን ያህል ብቻ ወስዶ በአዲሱ ተቋም ውስጥ እንደመደባቸው ተገልጾ ነበር፡፡ ታዲያ ለምን ለአዲስ ተቀጣሪዎች ማስታወቂያ ማውጣት አስፈለገ ለሚለው ጥያቄም፣ ዳይሬክተሩ አቶ ፋንታው አምባው ሲመልሱ “በየተቋሙ የነበሩትን ዓቃቢያንን ሁሉ እንድንወስድ የሚያስገድደን ሁኔታ የለም፤” ነበር ያሉት፡፡

እርግጥ ነው ሕጋችን ለእንደነዚህ ዓይነት አሠራሮች ግልጽ ምላሽ የለውም፡፡ ቢሆንም እንደ ፍትሕ ተቋም ተስፋ ስንጥልበት ገና ከመነሻው እንዲህ ዓይነት ግድፈት ውስጥ መግባቱ ይህ እምነታችንን የሚንድ ይሆናል፡፡ ነግ በእኔ ነውና የሙያ ጓደኞቻችን ጉዳይም ያሳስበናል፡፡ ይህ በሌላ አገላለጽ “የተንሳፈፉ” ወይም ሊንሳፈፉ የሚችሉ ሠራተኞች መኖራቸውን ቢነግረንም የ“ጥሩ አፈጻጸም” መለኪያው ብዙ ክሶችን ማቅረብ መቻል መሆኑን እንደሚያምነው የ“ፍትሕ ሚኒስቴር” ዓይነት አረዳድ፣ በፌዴራሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ውስጥ ከቀጠለ የተለወጠ ምንም ነገር አለመኖሩን የሚያስረዳ ነው የሚሆነው፡፡

ከዚህም ባሻገር የነባሮቹ ዓቃቢያን “ብቃት ማነስ” ጉዳይ እውነት ከሆነ ከፍተኛ የሕዝብ ተልዕኮና አደራ የተጣለባቸው፣ ግን ደግሞ ይህንን ሕዝባዊ አደራ ቀርጥፈው የበሉትን ሁለቱን ተቋማት (የኢፌዴሪ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንንና የጉምሩክ ባለሥልጣንን) ብቃት የማጣት ገመና የሚገልጽና ተያያዥ ጥያቄዎችንም የሚያስነሳ ይሆናል፡፡ በመጨረሻም ይህን ልበልና ብሶት መር መልዕክቴን ላብቃ… የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 29 ሥር ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን ቢደነግግም፣ ይህንን በመጻፌ ሥራ የማጣት ሥጋት አይኖርብኝም ማለት ግን አይደለም፡፡ የተጻፈ ሁሉ ቢተገበር ለዚህች አገር ሕገ መንግሥቱ ብቻ በቂዋ ነበር፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...