Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርእንወራረድ!... ኢሕአዴግ ከራሱ ጋር ታግሎ ይድናል!

እንወራረድ!… ኢሕአዴግ ከራሱ ጋር ታግሎ ይድናል!

ቀን:

በሰላም ተፈሪ  

‘ኢሕአዴግ አበቃለት፣ በፀና ታሟል፣ የታጋዮች ሳይሆን የሙሰኞች ግንባር ሆኗል፣ ብርሌ ከነቃ አይሆንም ዕቃ …’ ኧረ ሰሞኑ በኢሕአዴግ ላይ ብዙ ተሟረተበት። ይህንን የወቅቱን ወሬና ትንታኔ ተሸክመው መጥተው በስጦታ ላቀረቡልኝ እነ እንትና ኢሕአዴግ ሕመሙን የሚያውቅ ግን መድኃኒት እጁ ላይ ይዞ መጠኑ ሲያጠና ጊዜ እያባከነ ያለ ታማሚ ነው ብዬ ነገሩን ስሞግታቸው፣ የእጁ ነርቭ የሚያዘው የአንጎሉ ክፍል ተጎድቷል መድኃኒትዋን አይውጣትም ሲል ፅኑው ሞጋቼ አሾፈ። እኔም ደግሞ እንወራረድ ኢሕአዴግ ይድናል አልኩኝ። አሪፉ ተሟጓቼ ቂቂቂ… ብሎ ጨዋታችንን በሳቁ አሞቀው። ነገሩ በቃል ከሚቀር በጽሑፍ ይሁን አልኩኝና የጽሑፌ ርዕስ እንዲሆን መረጥኩት። በዚያውም ለሞጋቼና ለመሰሎቹ እንዲደርስ መጻፍ ይበጃል አልኩና እንወራረድ ኢሕአዴግ ይድናል! ብዬ ይኸው ቀረብኩኝ።  

‘ቁም! ማነህ? ስምህን ተናገር፣ መታወቂያ አለህ?’ የሚሉ ጠንካራ ቃላት በየቦታው ወራት ባስቆጠረው ከጥያቄ ወደ ግርግር በተሻገረው አመፅ ምክንያት የሚሰማ ድምፅ ሆኗል። የረሳነው ድምፅ ነበር። ይህ የማንፈልገው ድምፅ የከተማ ጎዳናዎቻችን ድምፅ እንዲሆን እየተመኘና ልከኛውን ጥያቄ እየጠማዘዘና እያቀጣጠለ ያለው ማን ነው? ይህ ነገር ሆድ ይፍጀው ተብሎ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። የአገርና የሕዝብ ህልውና ጉዳይ ነው።

ወቅቱ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ነው። እንኳን አደረሰን! በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ኢትዮጵያውያን በየቀያቸው በሚያነሱት የአዲስ ዓመት መባቻ አብሳሪ የአንድነት ችቦ ባለ ክፉ ምኞትና የሙስና አጋፋሪ ተገፍትረው ይለያሉ። በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥትም ጉንፋንና አተት እየሆኑ ያስቸገሩት ደቃቅና ግዙፍ መዥገሮችን ጠራርጎ ራሱን ያድናል። እንወራረድ ምኞቴ ከንቱ ምኞት አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ በቂ ሕክምና አድርጎ መድኃኒቱን በራሱም በሕዝብ እጅም ተግቶ ይድናል፣ አገሪቱንም ይታደጋል። ኧረ ‘የኢሕአዴግ በሽታ ጉንፋን ብልህ አታቃለው ከጉንፋን በላይ ነው’ አለኝ ሞጋቼ። እሺ ምን ይባል አልኩት? ‘ልብ ድካም ነው’ አለኝ። በሞጋቼ መልስ እኔም፣ እሱም፣ አብረውን የነበሩትም ሁላችንም የምር ሳቅን። ፖለቲካ አዘል ወሬ እንዲህ እየተፎጋገሩ ማውራት የተለመደ ይሁን አይሁን ለአንባቢያን ልተወውና ሁላችንም ግን እስክናነባ ስቀናል። ከሳቅ ከተመለስኩኝ በኋላ እሱንም ቢሆን ቡና፣ ሲጋራ፣ አልኮል … ስታቆም ይድናል ብዬ ሳልጨርስ ሚጢጢዋ የእኔ ቲፎዞ ‘ኢኮኖሚ ይጎዳል’ ብላ ነገሩን ስታጦዘው የመጀመሪያው ሳቅ ተደገመ። ከሳቅ ስንመለስ እንወራረድ ኢሕአዴግ ይድናል! አልኩኝ። እሺ እናስይዝ ተባለ። ምን? ስንት? ስንል እንዲህ ዓይነት ውርርድ በቀነ ገደብ መወሰን ስለሚከብድ አይሆንም ተባለ። እኔ የሁለት ወር ጣሪያ ይቀመጥለት አልኩኝ። ሞጋቼ ሊያበቃለትም ሊድንም ይህ ጊዜ አይበቃም አለ። እሺ የራስህ የጊዜ ሰሌዳ አስቀምጥ ሲባል ‘ምን ይኼ ሥርዓት ሞተ ስትለው ይድናል፣ ዳነ ስትለው ይሞታል’ ብሎ ዝም አለ። እኔ ግን ቀጠልኩኝ።    

ኢሕአዴግ ፖለቲካን በደመወዝና በምንዳ ብሎም በሙስና ቀመር ሳይሆን፣ ከአገራዊ ፍቅር የሚመነጭ ሕይወትን ስለሕዝብ አሳልፈህ በመስጠት አገር የምታቀናበት መሣሪያ መሆኑን የተገነዘቡ  ኢትዮጵያውያን ታጋዮች በውስጥ ስላሉት አዕማድና ችካል ሆነው ያቆሙታል። እንወራረድ!!! የግንባሩ ዋና ዋና አዕማዶች ሦስት ዓይነት መሆናቸው ለሚወራረዱኝ ግልጽ ላድርግ። ኢሕአዴግ ዓምዶቹ እኔ እንደማስቀምጠው አቀማመጥ የሚደለድላቸው ይሁን አይሁን አላውቅም። እኔ ግን ሞጋቼን ማስረዳት ስላለብኝ የእያንዳንዳቸው ስም፣ ይዘት፣ ጠቀሜታና ድርሻ ዘርዝሬ ለሚዛን አቀርባለሁ። የዓምዶቹን ፅናት፣ ታላቅነትና ህያውነት አስረድቼ ሞጋቼ የሚያቀርበውን ፌዝ ይሁን ቁምነገር በእንወራረድ ጽሑፌ ኢሕአዴግ ይድናል እለዋለሁ።    

አንደኛው የኢሕአዴግ ዓምድ የሚታየው ግን የማይታየው አካል መግዛትና ማንቀሳቀስ የሚችል ብርቱው ኃይል “ሐሳብ” (Idea) ነው። ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን ሰላም፣ ፍትሕ፣ ዕድገት፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ … የሚሉ ሐሳቦች ማቆሪያ የመጠሪያ ስም ነው ልንለው እንችላለን። እነዚህ ሐሳቦች ደግሞ በተፈጥሯቸው እየፋፉ ወይም እየቀጨጩ የመሄድ ፀባይ ይኖራቸው ይሆናል። ነገር ግን ዘለዓለማውያን እንጂ ተሰባብረውና ተበታትነው የሚጠፉ ግዑዛን አይደሉም። ስለዚህ ኢሕአዴግን እየሞረዱ ከዝገቱ እንዲነሳ የሚያስችሉት ተፈጥሯዊ የሐሳብ ዓምዶች አሉት ማለት ነው። በመሆኑም  ዘመን ያሻገሩት ግን ደግሞ የደከሙትና የዛጉት ሐሳቦች በዘመናዊ የሐሳብ ሞረድ ይሞርዳቸዋል፣ መልሶ ያንፀባርቃል፣ ይድናል። በህያዋን ዘንድ ከሐሳብ በላይ ብርቱ መሣሪያ የለም። ምክንያቱም እሱ የሁሉም ተፈጣሪዎች መጀመሪያ ነው። ኢሕአዴግም በቀና ሐሳቦች የተፈጠረ በመሆኑ ብርቱ ሆነው የሚታዩትን እያሸነፈ እዚህ ደርሷል ስል ሞጋቼ ነጠቀኝና ‘እውነት ነው ግን? በአዳዲስ ሐሳቦች የተፈጠሩ ብርቱ ጠላቶች ገጥመውታል’ ካለ በኋላ ‘እነሱም አደገኛ ራስን የማበልፀግ ሐሳብ የወለዳቸው የሕዝብ አደራን መርሳት፣ የሕዝብና የአገር ፍቅር መመናመን፣ ፍትሕ በመደለያ መፈጸምና ሌሎችም’ አለኝ። ‘እነዚህም የሐሳብ ልጆች መሆናቸውን አትርሳ’ ብሎ ጨዋታውን ወደኔ ወረወረው።

ጥሩ ያልካቸውም የሐሳብ ልጆች ናቸው። ግን እነዚያ ነገሮች ለኢሕአዴግ ዲቃላ ሆነው የገቡበት ሐሳቦች እንጂ የፈጠሩት ወይም የወለዳቸው አይደሉም ስለው፣ ‘የሁለቱም ሐሳቦች ፍሬ ግን እየታየ ነው’ አለኝ። ሞጋቼ ‘ሳይበዙስ ይቀራሉ ብለህ ነው?’ ብሎ አፌዘ። ‘ደግሞ አትናቀው የእነሱም ሐሳብ ነው አዕምሮና ጊዜ ፈሶበታል’ ብሎ ጨመረ። አስደሳቹ ነገር ሁለቱም በውስጡ መኖራቸውን ኢሕአዴግ ማወቁ አሁንም የሐሳብ ብርታቱ ነው ስለው፣ ‘ማወቅ ብቻ በቂ ነው እንዴ?’ አለኝ። አይደለም ስል ‘በል ተፈጥሮአዊ ሐሳቦቹን በድሪቶ ተሸፍነውበት የመጠቃቀም ሐሳቦች አንፀባራቂ ሆነዋል’ ብሎ ደመደመ። የሞጋቼ የሐሳብ ክብደቱና እውነተኛነቱ ተፈታተነኝ። ግን ዲቃላውን ሐሳብ ለመለየት ሌት ተቀን ሐሳብ እያፈለቀ፣ ሕግ እያረቀቀ፣ በቅጣት እያስተማረ የሚታገል ጤነኛ አካል አለ ብዬ ስጀምር ቀናኝ መሰለኝ፣ እኔና ሞጋቼም ብንሆን እንዲሁ እየተሟገትንም ዲቃላውን ሐሳብ አንደግፍም አይደል? ስለው ‘አዎን’ አለኝ። ስለዚህ ለብርቱ ጨለማ ትንሽ ብርሃን ትቀደዋለች እንደሚባል ሕዝብ የማስደሰት አገር የማቅናት ሐሳብ ያላቸው የኢሕአዴግ ሰዎችም የበለጠ ያንፀባርቃሉ። ስለዚህ ኢሕአዴግ በሐሳብ ይነሳል፣ እያሻሻለ ይገሰግሳል… እንወራረድ! በቀናዎቹ ሐሳቦች ተደግፎ ኢሕአዴግ ይድናል።

ሁለተኛው ዓምዱ የማይታየው ረቂቁን ሐሳብ የሚሸከሙ ታማኝ ታጋዮቹ ናቸው። ‘ኧረ አንተ ሰው ብትሰማኝ ምን አለበት?’ የሚል ዘፈን አቀነቀነብኝ። ቀጥሎም አሁን በዚህ የእንብላ እንብላ ዘመን ኢሕአዴግ ታማኝ ታጋዮች አሉት ብለህ ደፍረህ ትናገራለህ እንዴ? ያለኝ ሰው አውቀዋለሁ። ስሙን አልጠራም እንጂ ድምፁን ሰምቸዋለሁ። አዎ ኢሕአዴግ ታማኝ ባለአደራ ታጋዮች አሉት። እነማን? የምትል በፌዝ ቃና ጣል የተደረገች ድምፅ ሰምቻለሁ። ግን ማን ሞኝ አለ ወዳጁን ለበላተኛ ጥርስ አሳልፎ የሚሰጥ በማለት እኔም ስም አልጠራም አልኩኝ። ይሁን እንጂ እንወራረድ ኢሕአዴግ አደራቸውን ያልበሉ ታጋዮች አሉት ብዬ ቀጠልኩኝ። በቅርብ ያለው ሞጋቼ ‘ስንት ይሆናሉ?’ አለኝ ። የብዛት ሳይሆን የጥራትና የፅናት ኃያልነትን ለሚያምን አሁንም ኢሕአዴግ የሚያድኑት ታጋዮች እንዳሉት ሳብራራ አሪፉ ሞጋቼ፣ ‘ደጋግመህ አስብ’ አለኝ። ወደ ፊት ወደ ኋላ፣ ወደ ግራ ወደ ቀኝ አልኩና በኢሕአዴግ ውስጥ የሕዝብና የአገር ፍቅር የሚያንገላታቸው ታጋዮች እንዳሉት አስረገጥኩኝ። ጠያቂ መሆን እንዴት ቀላል ነው። ገንዘብ … ያላሸነፋቸው እነማን ናቸው? ብሎ አፋጠጠኝ። ግን ለምንድነው ስለግለሰቦች እንድናወራ የምትገፋፋኝ ስለው ‘መገለጫ ለማግኘት ነው’ አለ። ‘ደግሞም እያጠፉም እያለሙም ያሉት ሰዎች ናቸው። በወረቀት ያሉ ቀለማት አይደሉም’ ብሎ ተቀናጣ። የመጀመሪያውን ዓምድ ሳስረዳህ ኢሕአዴግ ሐሳብ ነው ብያለሁ። ስለሆነም እነዚያ አሉት የምልህ ታጋዮች የድርጅቱን መልካም እሴት የደፈነውን ገለባ በመንሽ እየገለጡ የታፈነውን መልካም ዘር እያወጡ መልሰው ቆፎ ይሞላሉ፣ አገር ይሆናሉ አልኩት። ‘አሁን ያልከው ከሽለላና ከቀረርቶ በምን ይለያል?’ እንዳለኝ ውስጤ ደግሞ እንዴት ያሳዝናል አለኝ። ምኑ ብዬ ሳልጠይቀው? ‘የምትወደውን መከላከል ሲያቅትህ’ ብሎኝ ጠፋ።

እኔም ለሞጋቼ እንዲህ አልኩት። አንኳሮቹ የኢሕአዴግ የሙስና አለቆችና የሌብነት መንገዶቻቸው የምትላቸውን ንገረኝና በእያንዳንዱ ላይ ሐሳብ እንስጥ አልኩት። ‘ይሻላል ብለህ ነው?’ አለና ‘ባልከው አቀራረብ ከሄድኩኝ ለአንተ የሚከብድህ ይመስለኛል’ የሚል ንግግር ጠብ አድርጎ ኢሕአዴግ አበቃለት የምልበት ዋና ምክንያት “የፖለቲካ ሙሰኝነቱ” ነው ብሎ ከባድ ሐሳብ ቁጭ አደረገ። ቀጥሎም ‘እንደ ጆሮ ጠቢ ግን ማድረስ የለም’ አለ። አጋጣሚው ከተጠያቂነትና ከተከላካይነት የሚያስወጣ መንገድ ሆነልኝና እንዴት? ብዬ ጠየቅኩኝ። ‘ኢሕአዴግ መሞት የጀመረው ቅድም ያልከውን ብርቱ የሐሳብ ዓምድ መሸከምም ሆነ መደገፍ የማይችሉ በብቃት፣ በንቃት፣ በዕውቀት፣ በሕዝባዊነት፣ በአገራዊ ፍቅር፣ በያገባኛል ባይነት በነፃነት የማይጠይቁ “ሰምቶ አደሮች” በማብዛቱ ነው’ ብሎ ሐሳቡን አጠናከረው። ‘ይህ የተሳሳተ መንገዱ በደም ሥራቸው የዚህች አገርና የድርጅቱ ፍቅር ያነደዳቸው ታጋዮቹ አራት ኪሎ ካደረሱት በኋላ በልቷል’ አለኝ። ‘ምክንያቱም የድርጅቱ አለቆች ሰሚ እንጂ የተለየ ሐሳብ ያለው ተሟጋችና ተተኪ በቀና ማየት አልፈለጉም። ቆንጆዎቹን ታጋዮች በመብላቱ የድርጅቱ እውነተኛ ማንነት ወደ ሕዝብ ሳይዘልቅ ቀርቷል። ይኼ ተግባሩ የራሱ ጉዳይ እልህ እችል ነበር ነገር ግን ከእነዚያ የምር የሕዝብና የአገር ፍቅር ያነደዳቸው በርካታ ታጋዮች መልካም ልምድና ተሞክሮ ማግኘት ይችል የነበረው ዜጋ በተገላቢጦሽ እየተማረ ነው።’ በተገላቢጠሽ? ስትል አልኩት። አየህ አሁን መንግሥት በሠፈራችን፣ በቢሯችን በዩኒቨርሲቲያችን የምናውቀው ሰነፍ ሰው ይሾማል፣ ይሸልማል። ማንም ሰው ደግሞ ተሿሚ ተሸላሚ መሆንን ይፈልጋል። ስለዚህ ሰነፍ መሆን በኢሕአዴግ ለሹመትና ለሽልማት ሲያበቃ ጎበዝና ጠያቂ መሆን ደግሞ ለውርደት ይዳርጋል’ ብሎ ‘ትውልዱ ተፈጥሮ በሰጠችው አዕምሮ ይደመድማል። ምክንያቱም ከአለቃው ጋር ተመሳስሎ አገር ቢፈርስም ዝም ብሎ የአለቃ ቃል እያከበረ ራሱን፣ ቤተሰቡንና ቻይናን እያበለፀገ የሚኖር ሰው ምንም እንደማይሆን ይመለከታሉ። ይህ አቅጣጫ ኢሕአዴግ አገር እያለማ የአገርም የራሱንም እሴት የጎዳበት ታሪኩ ነው።

‘ይኸው እንዲህ ያሉ ሰዎች የአገሩን ገንዘብ ዝቀውታል፣ ፍትሕ አጉድለዋል ኢሕአዴግንም ከሕዝብ ጋር አጣልተውታል። በነገራችን ላይ እነዚህ የኢሕአዴግ ሰዎች ከሁሉም የኢትዮጵያ አከባቢዎች የተገኙ ናቸው። በመሆኑም በሽታ ዘርፈ ብዙ ነው’ ብሎ ዘነጠብኝ። ያበቃል ስል ‘አየህ?’ ብሎ ቀጠለ። ቻይናውያን በቢሊዮን ብር ሊያተርፉ በመቶ ሺዎች ጉቦ ተቀብለው ያለ ደረጃው መንገድ የሚመርቁ፣ የትርፍ ድርድራቸውን እንኳን ከፍ አድርገው የማይወስዱ ሰነፎች የበረከቱባት አገር ሆነች። የሰነፎች ቤት ደግሞ ይፈርሳል ብሎ’ ተስፋ ሊያስቆርጠኝ ሞከረ። ሞጋቼ እመነኝ ታማኝ ታጋዮቹ ያልካቸውን እውነቶች ተቀብለው ለአገርና ለሕዝብ ሲባል የዓሳ ግማቱ በጭንቅላቱ ብለው ያለ ምሕረት በአናት አተኩረው ያጭዳሉ፣ አትሞኝ’ አለኝ። ምን ነው በጌትነት አናት ላይ ያሉ አለቆች ወዛቸውና ልብሳቸው ያስፈራል ብለህ ነው። እመነኝ እነሱ ከአገር በላይ አይደሉም። ከዚያም አልፎ ተያይዞ ለምለሙንና ደረቁን አብሮ ከመጥፋት አደጋውን የፈጠረው ሙሰኛ ማጥፋት ይመርጣሉ። ሕዝቡ ደግሞ ትእምርተ ሙስና የሆኑትን ሲወገዱ ካየ ኢሕአዴግን እንኳን ወደማንነትህ ደህና ተመለስክ ብሎ ይቀበለዋል። ስለዚህ በሁለተኛው ዓምዱም ኢሕአዴግ ይድናል። እንወራረድ! 

ሦስተኛው ዓምድ የልማት፣ የታቀደ ዕድገት፣ የተጻፈ ሕግ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ልምምድና ሌሎች ተስፋዎች የተመለከተ ሕዝብ ነው። ሕዝብ ደግሞ ብርቱ አለንጋ ነው ብዬ ሳልጨርስ ‘ሕዝብማ ኢሕአዴግን እየገረፈ ነው’ አለኝ ሞጋቼ። የሕዝብ ጅራፍ ጤነኛና ለማስተካከል የሚወጣ ነው አልኩኝ። እውነት ነው ለዝርፊያ ታክቲክ ራሱን አብቅቶ ሕዝቡን ያቆሰለ የኢሕአዴግን አካል ቆርጦ ለመጣል የሕዝቡ የጊዜ ጣሪያ ደርሷል። ቢሆንም ሕዝቡ ኢሕአዴግ በሚመራው መንግሥት መሪነት ሊተገብረው ተመኘ እንጂ፣ አገሩን አፍርሶ ቀየውን አውድሞ ሥርዓት አልባ ለመሆን ጅራፉን እንዳላነሳ እርግጠኛ ለመሆን በቅርብ ያለ ሰው መጠየቅ በቂ ነው። ማንም ኢትዮጵያዊ በአገሩ ያየውን ሁለንተናዊ ተስፋ እንዲጨልምበት አይፈልግም። ነገር ግን በታየው ተስፋ ተሸጉጠው ይኸውልህ የእኛ ፍሬ ነው እያሉ መጪውን ዘመን አንቀው የያዙት ታማሚ የኢሕአዴግ አካላት ሸልቶ ለመጣል ሁሉም ኢትዮጵያዊ መቀሱን ይዞ ከጤነኛው የኢሕአዴግ አካል የቆመበት ጊዜ ነው። ምክንያቱም ሕዝብ … እነማን ነበሩ? ትዝ አለኝ እነ ባለሁለት ዜግነት… እንደነሱ ሌላ አገርና ዜግነት የለውም። ስለዚህ ሕዝብ መንግሥት ሆኖ እየመራ ላለው ኢሕአዴግ ከበሽታው እንዲድን ደማካሴና ጤና አዳም በመሆን ያገለግለዋል። በመሆኑም ኢሕአዴግ በሕዝብ ድጋፍ ይጠራል፣ የበለጠ የእውነተኛ ዴሞክራሲ ማዕከል ይሆናል። እንወራረድ ኢሕአዴግ ከራሱ መዥገሮች ነፃ ይወጣል። የነፃነት ሐዋርያት አፍርቶ ከገባበት ማዕበል በሕዝብ ድጋፍ ይድናል። እንወራረድ! ሕዝቡ ኢሕአዴግን ያድናል፤፣በአዲስ ውበት ቀርፆ ያወጣዋል።

የኢሕአዴግ መዳን አለመዳን በኢትዮጵያ ህልውና ወሳኝ ድርሻ ስላለው የኢሕአዴግን መዳን ተመኘሁ። ምኞቴ እውን እንደሚሆን ለማስረገጥ ከኢሕአዴግ የተፈጥሮ ባህርያት ዋና ዋናዎቹን ለማሳየት ሞክሬያለሁ። አይሆንም የሚል ካለ አሁንም ኢሕአዴግ በሦስቱም ዓምዶቹ ድጋፍ ይድናል፡፡ እንወራረድ!

እርግጥ ነው መንግሥታዊ ሥርዓት እየመራ ያለ ፓርቲ ተቃውሞ ሲበዛበት የማኅበረሰቡ እውነተኛ ወቅታዊ አጀንዳ በበቂ ሁኔታ ማንፀባረቅ ያለመቻሉን ያሳያል። ይህ ማለት ግን ዘላቂ ጠቀሜታ ያላቸው ራዕዮችና ዕቅዶች የሉትም ማለት አይደለም። ነገር ግን በሥርዓቱ የፖለቲካ ልሂቃን የፍልስፍና ቀመር ዋጋ ያልተሰጣቸው ሕዝቡን ግን ጥይት ሆነው ባይገድሉትም፣ መርፌ ሆነው ህሊናውን የሚያሰቃዩት የፍትሕ፣ የዕለታዊ ኑሮ፣ ሌሎች ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እርካታ ያሳጡት ነገሮች አደባባይ ሊያስወጡት ይችላሉ። አደባባይ መውጣት ብቻ ሳይሆን ከእነዚህ ችግሮች እፎይታ ለማግኘት የተሳሳተ መንገድ ሊመኝ ይችላል። ታድያ በዚህ ጊዜ የመንግሥት ፖለቲካዊ ብቃቱ ይመዘናል። በመሆኑም አሪፍ ፖለቲከኛ ራሱን ከሕዝብ ፍላጎት ጋር አጣጥሞ ይቀርባል። ኢሕአዴግም በጥቂት ታጋዮቹ ብርታት ከሕዝቡ ጋር ሳይሆን ከራሱ ጋር ትግል አድርጎ ራሱን ያድናል። ለአገሪቱ ወቅታዊ ጥያቄ ፖለቲካዊ መልስ ይዞ ይመጣል። ታድያ መልሱ ያለው እየተበራከቱ ካሉ ሞሎች፣ የተንፈላሰሱ ሆቴሎች፣ ሱፐር ማርኬቶች ወይም ከፖለቲካዊ ብልጣ ብልጥነት አይደለም። መልሱ ያለው ከትግሉ ሰማዕታት መቃብር ነው። ‘ከመቃብር መልስ የለም’ አለ የሞጋቼ ድምፅ።

የሰማዕታቱ መቃብር ሁለት ዓይነት ነው። አንደኛው ሁሉም የአዳም ፍጥረት የሚቀበርበት ሰውና መሬት የሚዛመዱበት ግዑዙ መቃብር ነው። ሁለተኛው መቃብር የህሊና መቃብር ነው። በዚህኛው መቃብርም የትግሉ ሰማዕታት በሁለት መንገድ ይቀበራሉ። ቀዳሚው መቃብር በቀሪው ህያው የትግል ጓድ ህሊና ውስጥ በጥልቀትና በውህደት መቀበር ሲሆን ይህ ዓይነቱ ቀብር በሌላው ታማኝ ጓድ ህሊና፣ ሥጋና ደም ውስጥ ህያው ሆኖ መቀጠል ማለት ነው። እንዲህ ሲሆን ሁሌም ለአዲስ ትግል አዲስ ጉልበትና ስንቅ እየሆኑ በአዲስ ታሪክና ሕዝባዊ ፍቅር እየደመቁ መኖር ይሆናል። ሁለተኛው መቃብር በቀሪው ህያው የትግል ጓድ ህሊና ውስጥ መረሳት ነው። ይህ የከፋ መቃብር ነው። ሁሉም ዓይነት መቃብሮች በገሃዱ ዓለም እውን ሆኗል። ይሁን እንጂ ሰማዕታቱን ከህሊናቸው ጓዳ፣ ከሥጋና ደማቸው በማዋሀድ እያኖሩ ያሉ ታጋዮች እውነተኛው መልስ ከሰማዕታት መቃብር ይዘው ይመጣሉ። ስለዚህ ኢሕአዴግ ይድናል። ሞጋቼ ‘እንዲህ ሊያደርጉ የሚችሉት ሰዎች ቁጥራቸው ጥቂት ነው’ አለኝ። እውነት ነው። ግን እነዚያ ብዙዎችስ ምንና ምን ናቸው? አልኩት። እነሱ … አስመሳዮች፣ ዘራፊዎች፣ ለአለቃ ተላላኪዎች፣ ለምስኪን ደግሞ ነገሥታት፣ ሙሰኞች…’ አለኝ። አሁንም ስሙን አልጠራውም። ለምን ጠቅለል ባለ ቅፅል ሌቦች አትልም? አልኩት። ዝም አለ። በል ስማ እንኳንስ በባህሪው ደንጋጣና ስግብግብ ከሆነው ሌባ ጋር ከታንኮች፣ በርቀት አልመው ሕይወት ከሚቀጥፉ ዘመናዊ ብረቶችና በሺዎች የሚቆጠሩ የሠለጠኑ ገዳዮች ጋር ጥቂት ታጋዮች ገጥመው ሲፋለሙ የሐሳባቸውን ብርታትና ራዕይ የተመለከቱ እውነተኛ ህሊና ያላቸው ኢትዮጵያውያን ደርሰውላቸው፣ ይኸውና እየተቀባበሉ የምናየው ሁሉ ሆኗል። እመነኝ ይህ ስሜት ከውስጣቸው ያልጠፋባቸው ታጋዮች ኢሕአዴግን እየበሉት ከከረሙና አሁን ሊውጡት ከተዘጋጁ ሆዳሞች አፍና ጥርስ በሕዝብ አጀብ ያድኑታል። እንወራረድ! ኢሕአዴግ ይድናል።

መልካም አዲስ ዓመት!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...