Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሲኒማው በሐያሲው ዕይታ

ሲኒማው በሐያሲው ዕይታ

ቀን:

ሪቻርድ ፔኛ ለ25 ዓመታት በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የፊልም ፕሮፌሰር ሆኖ አገልግሏል፡፡ ዓለም አቀፉ የኒውዮርክ ፊልም ፌስቲቫል ዳይሬክተርም ነው፡፡ ስለፊልም ዝግጅትና ሂስ በበርካታ አገሮች በመዘዋወር ሥልጠና የሰጠ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር፡፡

ከኢትዮጵያውያን ፊልም ሠሪዎች ጋር ተገናኝቶ ከፊልም ይዘትና አሠራር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል፡፡ የኢትዮጵያን ፊልም ለማሳደግ፣ ሲኒማውን የሚፈታተኑ ችግሮችን ለመፍታትና ዓለም አቀፍ ተቀባይነቱ እንዲጨምር ለማድረግ ባለድርሻ አካሎች ምን ማድረግ አለባቸው? በሚል ተነጋግረዋል፡፡

ሪቻርድ ከፊልም ሠሪዎቹ ጋር ከተወያየ በኋላ ከሪፖርተር ጋር አጭር ቆይታ አድርጎ ነበር፡፡ ከፊልም ሠሪዎቹ ጋር የተነጋገረባቸውን ጉዳዮች ማለትም የኢትዮጵያን ፊልም ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ማሳደግ፣ በፊልሙ ዘርፍ ዋነኛ የሚባሉትን የበጀት፣ የፊልም ይዘትና ሙያዊ ብቃት ውስንነትን በተመለከተ አስተያየቱን ሰጥቶናል፡፡

የኢትዮጵያ ፊልም እንደ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ባሉ ባለሙያዎች እንዲሁም እንደ ‹‹ላምባ›› (ዳንግሌ) ባሉ ፊልሞች ጥረት ዓለም አቀፍ ዕውቅና እያገኘ ቢመጣም ብዙ እንደሚቀረው ባለሙያው ይናገራል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ፊልም ከመግለጹ አስቀድሞ የተቀሩት የአፍሪካ አገሮች እንዲሁም ከአውሮፓ ውጭ ያሉ አገሮችም እንዴት ተቀባይነታቸው እንደጨመረ ያወሳል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1988 ጀምሮ የኒውዮርክ ፊልም ፌስቲቫል ዳይሬክተር ሲሆን፣ በተለይም ከአውሮፓ ውጪ ያሉ ፊልሞችን ወደ ፌስቲቫሉ በማምጣት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ የአፍሪካ፣ የላቲን አሜሪካና የእስያ ፊልሞች በፌስቲቫሉ እንዲካተቱ ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል፡፡  ‹‹ለምሳሌ የኢራን፣ የቻይናና የአፍሪካ አገሮች ፊልሞች በዓለም አቀፍ መድረክ ብዙም ቦታ ሳይሰጣቸው ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ተመልካች አላቸው፤›› ይላል፡፡

ከኒዮርክ ፊልም ፌስቲቫል በተጨማሪ በቺካጎ የብላክ ላይትና በኒውዮርክ ሊንከን ሴንተር የአፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል መሥራችም ሲሆን፣ የአፍሪካውያንና የአፍሪካውያን ዳያስፖራዎችን ፊልም በፌስቲቫሎቹ ለማሳየት ሠርቷል፡፡

በዓለም አቀፍ መድረክና በፌስቲቫሎቹም የምዕራብ አፍሪካ ፊልሞች የበለጠ ተመልካች በማግኘት ይጠቀሳሉ፡፡ የማሊ፣ ሴኔጋል፣ ቡርኪናፋሶና ኮትዲቯር ፊልሞች ከቀድሞ ቅኝ ገዥ አገሮች ጋር ባላቸው ትስስር የገንዘብ ድጋፍና መድረክም የሚያገኙበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ፊልሞች እንደ ምዕራብ አፍሪካ ባይሆንም ቀስ በቀስ በዓለም አቀፍ ፌስቲቫሎች እየተቀላቀሉ መሆኑን ይናገራል፡፡

ሪቻርድ እንደሚለው፣ ከምሥራቅ አፍሪካ የኢትዮጵያ ፊልሞች በዓለም አቀፍ መድረክ ብቅ ብቅ ካሉት ይጠቀሳሉ፡፡ የፊልም ባለሙያዎችም ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያና ሌሎችም የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በየአገራቸው ሲኒማ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ ከቻሉ ደግሞ አሁን ካለው በበለጠ የመላው ዓለምን ትኩረት የሚያገኙበት ቀን ሩቅ አይደለም፡፡

ይህ ዕውን እንዲሆን በኢትዮጵያ ሲኒማ ያሉ ችግሮች በአፋጣኝ መቀረፍ አለባቸው ይላል፡፡ የሪቻርድና የፊልም ሠሪዎቹ ውይይትም ይህንን የተመረኮዘ እንደነበር ይገልጻል፡፡ በውይይታቸው ስለ ዘጋቢ፣ አጫጭርና ፊቸር ፊልሞች አሠራርና የበጀት ጥያቄን በተመለከተ፣ ችግሩን ለመቅረፍ ለሲኒማው የመንግሥት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ይገልጻል፡፡

‹‹ በአገሪቱ ከፊልም ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች ሊኖሩ ቢችሉም የአገሪቱን ፊልም መንግሥት መደገፍ አለበት፤›› ይላል፡፡ ብዙ ፊልም ሠሪዎች መንግሥት ለዘርፉ በቂ ትኩረት አልሰጠም ብለው ያምናሉ፡፡ እሱም በዚህ ይስማማል፡፡ ፊልም ሠሪዎች የመንግሥትን ትኩረት የሚያገኙበት መንገድ መቀየስ እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡ መንግሥት ለሲኒማው ድጋፍ ሲያደርግ ዘርፉ ስኬታማ እንዲሆን የሚያስፈልጉ ነገሮች ባጠቃላይ ይሟላሉ ብሎ ያምናል፡፡

በእርግጥ መንግሥት ፈልሞችን በተለያየ መንገድ ሲደግፍ የፊልሙን ይዘት በመወሰን (ቅድመ ምርምራ በማድረግ) ለሚፈልገው ዓላማ ብቻ ሊያውለው ይችላል የሚል ሥጋት በፊልም ሠሪዎች ዘንድ መኖሩን ይናገራል፡፡ ‹‹እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የፊልም ሠሪዎች አቅም ስላልጎለበተ የመንግሥት ድጋፍ ቢያስፈልግም የፊልም ባለሙያዎችን ነፃነት ይጋፋል የሚለው ሥጋትም አለ፤›› ይላል፡፡ ቢሆንም ግን ፊልም ሠሪዎች በገለልተኝነት ለመሥራት የመንግሥትን ጫና መቋቋም ይችላሉ ይላል፡፡ ጫናውን መቋቋም ከሚችሉበት መንገድ አንዱ ከመንግሥት ጋር በግልጽ ስምምነት ላይ መድረስ ነው፡፡ ፊልም ሠሪዎች ከመንግሥት ጋር የሚያደርጉት ስምምነት የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ምን ድረስ እንደሆነ መወሰን እንዳለበት ይገልጻል፡፡

ከፊልም መሥሪያ በጀት በተያያዥ፣ ሪቻርድ ስለፊልም ይዘትም ይናገራል፡፡ ከፊልሞች ይዘት ጋር በተደጋጋሚ የሚነሳው ነጥብ የፊልሞች ታሪክ አዲስ (ኦሪጅናል) ያለመሆን ጉዳይ ነው፡፡ ፊልሞችን ከሆሊውድና ቦሊውድ በመውሰድ የመሥራት ነገር ሙያውን እየቀጨው እንደሆነ የሚያምኑ ባለሙያዎች  አሉ፡፡ እሱ በበኩሉ፣ በአንድ አገር የተሠሩ ፊልሞች ሌላ አገር በተመሳሳይ ቢሠሩ የጥበብ ሥራዎች መወራረስ የተለመደ በመሆኑ ጉዳት አይኖረውም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ዓይነት ፊልሞች መወረስ የለባቸውም፡፡ የፊልሞች ይዘት ታይቶና ተመርጠው ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ መሥራትም ያስፈልጋል፡፡ ‹‹አንዳንድ ፊልሞች ከአንድ አገር ወደ ሌላው ቢወረሱ መልካም ነው፡፡ አንዳንዴ ግን ይዘታቸው ጥሩ ያልሆነ ፊልሞች ይወረሳሉ፡፡ ይህ አንዱ ባለሙያ የሠራውን ስህተት ደግሞ መሳሳት ይሆናል፤›› ይላል፡፡

ስለፊልሞች ይዘት ከሚነሱ ጥያቄዎች ሌላው የአገሪቱ ፊልሞች በአስቂኝና የፍቅር ይዘት መወሰናቸው ነው፡፡ ባለሙያው እንደሚለው፣ በኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ዐውድ ላይ የሚያጠነጥኑ ፊልሞች የመሥራት ፍላጎት ያላቸው ፊልም ሠሪዎች ለፊልም ግብዓት የሚሆን ብዙ መረጃ አላቸው፡፡ ይህንን ግብዓትም መጠቀም አለባቸው፡፡

 የተለያየ ዓይነት ዘርፍ ያላቸው ፊልሞች ቢበራከቱም ተመልካቾች ምርጫ ይኖራቸዋል፡፡ ባለሙያዎች ፊልምን መልዕክት ለማስተላለፍ፣ ለመዝናኛነት ወይም ለምርምር ማዋልም ይችላሉ ይላል፡፡

በእሱ እምነት፣ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ የሚያሳዩ ፊልሞች የዓለምን ትረኩት ሊስቡ ይችላሉ፡፡ የአገሪቱ የዓመታት ታሪክም ለብዙ ፊልሞች መነሻ መሆን ይችላል ይላል፡፡ በዚህ ረገድ ፊልሞችን ከይዘትና ከቅርፅ አንፃር የሚተቹ የፊልም ሐያሲያን ቢበራከቱ ዘርፉን ትክክለኛ አቅጣጫ እንደሚያስይዙም ያክላል፡፡

ሪቻርድ፣ የፊልም ሂስ ለአንድ አገር ሲኒማ ዕድገት የጀርባ አጥንት ከሆኑ ነገሮች አንዱ መሆኑን በመግለጽ፣ ሂስ ትኩረት እንዲሰጠው ያሳስባል፡፡ ከሂስ ባልተናነሰ ፊልም ሠሪዎች የሌሎች አገሮች ፊልሞችን በመመልከትና ከሌሎች አገሮች ፊልም ሠሪዎች ጋር ሙያዊ ውይይት በማድረግ መጠናከር እንደሚችሉ ያምናል፡፡ ‹‹ፊልም ሠሪዎች ሌሎች አገሮች የሚሠሩ ፊልሞችን በመመልከት አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ መረዳት ይችላሉ፤›› ይላል፡፡

በተያያዥም ፊልም ሠሪዎች በተለያየ አጋጣሚ የሚያገኙትን ዓለም አቀፍ ዕውቅና በመጠቀም፣ በፌስቲቫሎችና በውድድሮች ቢሳተፉ ለፊልሙ ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ያምናል፡፡ ‹‹አሁን ብዙዎች በዓለም ፊልም ኢንዱስትሪ የኢትዮጵያን ፊልም እየተጠቀሰ ነው፡፡ ፊልም ሠሪዎቹም የሚሸለሙበትና ፊልማቸው በዓለም አቀፍ መድረክ የሚታይበት ዕድል አለና ይህን ከባለሙያዎች ጋር ትስስር ለመፍጠር መጠቀም አለባቸው፤›› ይላል፡፡

የፊልም ሠሪዎችን ሙያዊ ብቃት በማሳደግ ረገድ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የፊልም ትምህርት ቤቶች የተማሩና የዓመታት ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ በመጋበዝ የተሞክሮ ልውውጥ ማድረግ ይቻላል፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሆነው በሌሎች አገሮች የሚኖሩ ፊልም ሠሪዎችም ለዘርፉ አጋዥ እንደሚሆኑ ይናገራል፡፡

ጠቅለል ባለ መልኩ በፊልሙ የበጀት፣ የባለሙያ እጥረትና ሌሎችም ችግሮች ሲነሱ፣ ባለሙያዎች ነጥሎ አንድን ችግር ለመፍታት ብዙ ጥረት ሲያደረጉ ይስተዋላል፡፡ አንድ ችግር መፍታት ብቻውን ለውጥ ስለማያመጣ ዕቅዱ ሁሉም ችግሮች ጎን ለጎን የሚፈቱበትን መንገድ ማመላከት መቻል አለበት ይላል፡፡  በሪቻርድ እምነት፣ የፊልም ባለሙያዎች ባጠቃላይ ተሰባስበው ፊልሙ በቀጣይ ዓመታት መድረስ ያለበትን ደረጃ ዕቅድ ማውጣት አለባቸው፡፡

‹‹አነስተኛ በጀት ያላቸው ፊልሞች መሥራት፣ ከመንግሥት ድጋፍ መጠየቅ በገንዘብ ረገድ የሚነሱ ጥያቄዎችን በመጠኑ ሊመልስ ይችላል፡፡ ዓለም አቀፍ ፊልም ሠሪዎችን በወርክሾፕ በመጋበዝ ልምድ እንዲያካፍሉ ማድረግና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያገኙ ፊልም ሠሪዎች የሚፈጥሩትን ትስስር መጠቀም ከሙያዊ ብቃት ጋር ለተያያዙ  ችግሮች መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ፤›› ይላል ባለሙያው፡፡ ጉልህ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብሎ የሚያምንበት የባለሙያዎች የጋራ ዕቅድ፣ ሁሉንም ፊልም ሠሪ ያማከለ መሆን እንዳለበት ይገልጻል፡፡  የሚወጣው ዕቅድ ከኢትዮጵያ በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ ያለፉ አገሮችን ተሞክሮ የሚያጣቅስ ቢሆን እንደሚመረጥም ያክላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...