Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየኦባማን ዕቅድ ያስቀለበሰው የፊሊፕሊንስ ፕሬዚዳንት ስድብ

የኦባማን ዕቅድ ያስቀለበሰው የፊሊፕሊንስ ፕሬዚዳንት ስድብ

ቀን:

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በቡድን ሃያ አባል አገሮች ጉባዔ ላይ ባቀረቡት አስተያየት የተቆጡት የፊሊፒንስ ፕሬዚዳንት ሮድሪጎ  ዱትሬት  ኦባማን መሳደባቸው የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ኦባማም ከዱትሬት በተሰነዘረባቸው ስድብ ሳቢያ ከእሳቸው ጋር ሊያደርጉ የነበረውን ወሳኝ ውይይት ሰርዘዋል፡፡

ባለፈው ሰኞ ከተጠናቀቀው የቡድን ሃያ ጉባዔ በኋላ ማክሰኞ በላኦስ በተጀመረውና አሥር አባል አገሮች ባሉት የደቡብ ምሥራቅ አስያ አገሮች ጉባዔ ጎን ለጎን በሚካሄዱ የመሪዎች ውይይት፣ ኦባማ ከፊሊፒንስ አቻቸው ጋር ‹‹ዲፕሎማሲያዊ›› ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ ይዘው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ ኦባማን ከተሳደቡ በኋላ መፀፀታቸውን የገለጹ ቢሆንም፣ ኦባማ ግን የጎንዮሽ ውይይቱን ሰርዘዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የውይይቱ መሰረዝም ሆነ የዱትሬት ስድብ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነትም ያሻክረዋል ተብሏል፡፡

የቡድን ሃያ አባል አገሮች ጉባዔ በቻይና ሐንግዙ ሲካሄድ በሩሲያና በፊሊፒንስ ላይ ትችት የሰነዘሩት ኦባማ፣ ከፊሊፒንስ ፕሬዚዳንት የተቸራቸው አስፀያፊ ስድብ እንጂ በተነሱ አጀንዳዎች ላይ መወያየት አልነበረም፡፡ ሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. የቡድን ሃያ አባል አገሮች ጉባዔ ሲጠናቀቅ፣ ኦባማ በፊሊፒንስ በዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግድያ ካወገዙና በቀጣይም በ28ኛው እና 29ኛው የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ማኅበር (ኤስያን) ጉባዔ ላይ ተገኝተው ስለጉዳዩ እንደሚሰወያዩ ከገለጹ በኋላ፣ ‹‹አንተ ማነህና ነው እኔን የምትናገር? የ. . . ልጅ ብለው በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መናገራቸው ኦባማ በቀጣዩ ጉባዔ ፕሬዚዳንቱን በግላቸው እንዳያነጋግሩ አድርጓል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኦባማ በላኦስ ተገኝተው ከእስያ አገሮች መሪዎች ጋር ለማድረግ ያቀዱት ውይይት በአሜሪካና በእስያ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ወሳኝ ነበር፡፡ በእስያ በተለይም በቻይናና በአሜሪካ መካከል ያለውን የኃይል ሽኩቻ ለማርገብ፣ በአንፃሩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ነበር፡፡ ከዚህ ባለፈም ከላኦስ ጉባዔ ጎን ለጎን ከፊሊፒንሱ ፕሬዚዳንት ጋር በተናጠል የሚያደርጉት ውይይት አሜሪካና ቻይና ያላቸውን ሽኩቻ ለማርገብ የሚያስችል እንደነበር ተገልጿል፡፡

ከሥልጣን ለመሰናበት የወራት ዕድሜ የቀራቸው ኦባማ በኤስያን ጉባዔ ላይ መገኘት ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከእስያ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ለማቅለል፣ ብሎም ከዚህ ቀደም የነበሩ ውዝግቦችን ለማርገብና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከየአገሮቹ መሪዎች ጋር የሚደረግ የጎንዮሽ ውይይትም እንዲሁ፡፡

 ሆኖም እየዋዥቀ የሚገኘው የዓለም ፖለቲካ ኦባማን አላወላዳቸውም፡፡ ኦባማ ከሩሲያ፣ ከሰሜን ኮሪያና ከቻይና ጋር ባላቸው ውዝግብ አገሮቹ ለአሜሪካ ያላቸው አመለካከት አሉታዊ ነው፡፡ በየመድረኩ በተገናኙ ቁጥርም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች እርስ በርስ ከመናቆር አልተቆጠቡም፡፡  የአሜሪካ ወዳጆች በአሜሪካ ላይ  ትችትና ነቀፋ መሰንዘራቸው ይህንንም ያህል የተለመደ ባይሆንም፣ የቡድን ሃያ አባል አገሮች ጉባዔ ላይ ግን የአሜሪካ ቀኝ እጅ የሚባሉት ቱርክና ፊሊፒንስ እምቢተኝነታቸውን ገልጸዋል፡፡

በጉባዔው ማብቂያ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት አዲሱ የፊሊፒንስ ፕሬዚዳንት፣  ‹‹በፍሊፒንስ በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ የሚፈጸመው ግድያ የበዛ ነው ብሎ የሚናገረው እሱ ማነው? እኔ የሉዓላዊት ፊሊፒንስ ፕሬዚዳንት ነኝ፡፡ የአሜሪካ ቅኝ ግዛት የምንሆንበት ጊዜ አክትሟል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ፊሊፒንስ ከአደኛ ዕፅ ጋር ተያይዞ የሚፈጸም ወንጀልን ለመከላከልና አዘዋዋሪዎቹን ለማጥፋት የጀመረችውን ሥራ አጠናክራ ትቀጥላለች፣ አሜሪካም ጉዳዩ አይመለከታትም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ኦባማ ፊሊፒንስን በሰብዓዊ መብት ረገጣ ሲወቅሱ፣ ሩሲያና ሌሎች አገሮችን በአሜሪካ ላይ የሳይበር ጥቃት እየፈጸሙ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ሁላችንም አቅማችን ጎልብቷል፡፡ ሌሎችን ለማነሳሳትም ሆነ ራሳችንን ለመከላከል በምንችልበት ደረጃ ላይ እንገኛለን፤›› ሲሉ መልዕክት አዘል ንግግር አድርገዋል፡፡

ኦባማ ለሦስት ቀናት በተካሄደው የቡድን ሃያ አባል አገሮች ጉባዔ ከቻይና፣ ከእንግሊዝና ከቱርክ መሪዎች ጋር ዲፕሎማሲን በማስፈን ረገድ መወያየታቸውን፣ አሜሪካ ከሦስቱም አገሮች ጋር ግንኙነት ቢኖራትም፣ ግንኙነቶቿ የተወሳሰቡ እንደሆኑ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ኦባማን ‹‹የ. . . ልጅ›› ብለው ፀያፍ ንግግር ካደረጉ በኋላ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መነጋገሪያ የሆኑት  ዱትሬት፣ በዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ ፊሊፒንስ የጀመረችውን ሥራ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል፡፡

ከሁለት ወራት በፊት በምርጫ ወደ ሥልጣን የመጡት  ዱትሬት፣ ከመመረጣቸው በፊት በአገሪቱ የተንሰራፋውን ከዕፅ ጋር የተያያዘ ወንጀል እንደሚያፀዱ ቃል ገብተው ነበር፡፡ በገቡት ቃል መሠረትም በዕፅ ንግድ የተሰማሩና የሚያዘዋውሩትን በሞት ፍርድ እየቀጡ ነው፡፡ በዚህም ተግባራቸው ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ከዲፕሎማቶችና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውግዘት እየገጠማቸው ነው፡፡

ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 2,400 ሰዎች ከዕፅ ወንጀል ጋር በተያያዘ ተገድለዋል፡፡ ኦባማም በጉባዔው ያነሱት የሰዎች መገደል ይብቃ የሚል ነበር፡፡ አያይዘውም በእስያ በሚኖረው የጎንዮሽ ውይይት ከፊሊፒንሱ ፕሬዚዳንት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ እንደሚመክሩበት አመልክተው ነበር፡፡

ፊሊፒንስ፣  ቬትናም፣ ማሌዥያ፣ ብሩኒና ታይዋን፣ ቻይና አገሮቹን በሚያዋስነው ባህር በደቡባዊ ክፍል በምትገነባቸው አርቴፊሻል ደሴቶች ቅሬታ አላቸው፡፡  ዱትሬት ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት፣ ፊሊፒንስ ወታደራዊ ግንኙነቷን ከአሜሪካ ጋር በማጠናከር በቻይና በኩል ሊመጣ የሚችልን ሥጋት ለመከላከል ትሠራ ነበር፡፡ አሁን ላይ የአሜሪካውን ግንኙነቷን አርግባ ከቻይና ጋር አዲስ ግኙነት ፈጥራለች፡፡

ኦባማ በላኦስ በሚኖራቸው ቆይታም ከፊሊፒንሱ ፕሬዚዳንት ጋር ከሚወያዩባቸው ጉዳዮች አንዱ፣ ቻይና በባህሩ ደቡብ አቅጣጫ ስለምትገነባቸው ደሴቶች ጉዳይ ነበር፡፡ ሆኖም አልተሳካም፡፡

ኤስያን አሥር አባል አገሮች ያሉት ሲሆን፣ ለሦስት ቀናት የሚቆየው የአገሮቹ ጉባዔ ማክሰኞ በላኦስ ተጀምሯል፡፡ ከጉባዔው ጎን ለጎንም የየአገሮቹ መሪዎች ከአሜሪካ፣ ከጃፓን፣ ከቻይናና ከደቡብ ኮሪያ መሪዎች ጋር ውይይት ያደርጋሉ፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኦባማ ግን ከፊሊፒንስ አቻቸው ጋር የሚያደርጉትን ውይይት ሰርዘውታል፡፡

ኦባማ በቡድን ሃያ አባል አገሮች ጉባዔ ላይ ሩሲያንና ፊሊፒንስን  ሲያወግዙ፣ አሜሪካዊው እግር ኳስ ተጫዋች ኮሊን ኬፐርኔክ የአሜሪካ ፖሊሶች በአፍሪካ አሜሪካውያን ላይ የሚያደርጉትን ግድያ በመቃወም፣ ባለፈው ሳምንት በነበረ ጨዋታ ላይ የአገሪቱ ሕዝብ መዝሙር ሲዘመር በመቆም ፈንታ መንበርከኩና ያነሳውም ጥያቄ ሕጋዊ መሆኑን አምነዋል፡፡ ለተጨዋቹም ድጋፋቸውን አሳይተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...