Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  መንግሥት በቁጥጥሩ ሥር ላሉ እስረኞች ኃላፊነትም ተጠያቂነትም አለበት!

  በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት እንዳላቸው የሚደነግገው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 21 ነው፡፡ ይህ መብት በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተካተተው፣ መንግሥት በቁጥጥሩ ሥር ላዋላቸው እስረኞች ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዳለበት ለማሳየት ነው፡፡ ሰሞኑን በቂሊንጦ እስር ቤት በእሳት ቃጠሎ ሳቢያ በርካታ እስረኞች ሞተዋል፡፡ ከዚህ በፊትም በጎንደርና በደብረ ታቦር በእሳት ቃጠሎ ምክንያት እስረኞች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ከዚህ ቀደም ብሎም በእሳት እስር ቤቶች ተቃጥለው ያውቃሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አደጋ ሲያጋጥም እስረኞች በከፍተኛ ኃላፊነት መጠበቅ አለባቸው ሲባል፣ ለመብቱ የተሰጠውን ላቅ ያለ ሥፍራ ያሳያል፡፡ አሁንም ሆነ ከዚህ በፊት በደረሱ የእስር ቤት ቃጠሎዎች ምክንያት እስረኞች ሕይወታቸው ማለፉ በተደጋጋሚ ሲነሳ፣ በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ያገኘው መብት እየተከበረ አይደለም ያሰኛል፡፡

  በሕገ መንግሥቱ ከአንቀጽ 14 እስከ 17 የሕይወት፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብቶች ባለቤት ፍርድ ቤት መሆኑ የክብሩ ሌላ መገለጫ ነው፡፡ የእነዚህ ድንጋጌዎች መውጣት ብቻ ሳይሆን፣ ተፈጻሚነታቸው ታላቅ የሕዝብ ጥቅም ነው፡፡ ስለዚህም የታሰሩ ሰዎች ጉዳይ የታሳሪዎቹ፣ የቤተሰቦቻቸው፣ የሃይማኖት አባቶቻቸው፣ የሐኪም ወይም የመሳሰሉት ብቻ ሳይሆን የአጠቃላዩ ሕዝብ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ነው የፍትሕ አስተዳደሩ፣ የዳኝነት ሥራ አካሄዱና የእስር አያያዙ ጭምር በግልጽ በአደባባይ በሙያው በተካኑና ሥነ ምግባር ባላቸው ሰዎች እንዲመራ የሚያስፈልገው፡፡ ይህም ሆኖ ከፍተኛ ባለሙያዎች በሚያስተዳድሩት እስር ቤት ውስጥም ቢሆን እስረኞች አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ ጥያቄዎች ይኖሩዋቸዋል፡፡ ሆን ተብሎም ሆነ በአጋጣሚ ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡ ሆኖም እስረኞችን ከማናቸውም አደጋ የመጠበቅ ኃላፊነት በመንግሥት ትከሻ ላይ ነው፡፡

  በጎንደርም ሆነ በደብረ ታቦር፣ በቂሊንጦም ሆነ በሌላ ሥፍራ እስረኞችን በተደጋጋሚ እየጎበኘ ያለው እሳት አደጋ ጉዳይ መንስዔው አጠያያቂነቱ እንዳለ ሆኖ፣ የእሳት ቃጠሎ ሲያጋጥም ከምንም ነገር በላይ በሕይወት ላይ አደጋ እንዳይደርስ መደረግ ነበረበት፡፡ በሰሞኑ በቂሊንጦ እስር ቤት በደረሰ ቃጠሎ መንግሥት 23 ሰዎች መሞታቸውን አምኖ፣ 21 ታሳሪዎች በተፈጠረው መጨናነቅ ተረጋግጠው ሲሞቱ ሁለቱ ሊያመልጡ ሲሉ እንደተገደሉ አስታውቋል፡፡ የእስር ቤቱ አስተዳደር በተቻለ መጠን እስር ቤቱ የእሳት አደጋ እንዳይነሳበት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ፣ አደጋው ቢያጋጥም እንኳ በቶሎ ለማጥፋት የሚያስችል የመከላከል አቅም መገንባት ነበረበት፡፡ ከእስር ቤት ግንባታ ጀምሮ እሳት የመከላከል የውስጥ አቅም መፍጠር፣ ወይም በቅርብ ርቀት ላይ የእሳት አደጋ መከላከያ ድርጅት እንዲኖር ማስደረግ የማን ኃላፊነት ነው? በሺዎች የሚቆጠሩ ታሳሪዎች ያሉባቸው መጠለያዎች ላይ እሳት ሲነሳ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለእስረኞች ደኅንነት ወይስ ለሌላ?

  በቂሊንጦ እስር ቤት ላይ በደረሰው አደጋ ሳቢያ በርካታ ታሳሪዎች ሞተዋል፡፡ መንግሥት በርካታ ታሳሪዎችን ወደ ሌሎች ሥፍራዎች በማጓጓዙ ሳቢያ የታሳሪ ቤተሰቦች በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ናቸው፡፡ ታሳሪ ቤተሰቦቻቸው በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ ማወቅ ባለመቻላቸውም በከፍተኛ እንግልት ውስጥ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሊያመልጡ ሲሉ ተገደሉ የተባሉ እስረኞች ጉዳይ ደግሞ የበለጠ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ እሳት ተነስቶ ታሳሪዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍም ለማምለጥ ባገኙት መንገድ ሁሉ ሲሸሹ ሊያመልጡ ነው ብሎ በጥይት ከመግደል ይልቅ፣ ታሳሪዎቹ አምልጠው ሕይወት ቢተርፍ ይሻላል፡፡ አለበለዚያ በእስር ቤት ውስጥ አደጋ በተፈጠረ ቁጥር ሕይወትን ለማትረፍ የሚደረገው ጥረት በጥይት ፍራቻ ለበለጠ አደጋ መጋለጥን ያመጣል፡፡ እስረኞች ሊያመልጡ ነው በሚል ሰበብ እየተኮሱ ከመግደል የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት እንዲኖር ማድረግ ይመረጥ ነበር፡፡ ነገር ግን በብዙ እስር ቤቶች በደረሱ የእሳት አደጋዎች እየተሰማ የለው የሞት መርዶ ነው፡፡ በጣም የሚያሳዝን መርዶ፡፡ ያውም ሊያመልጡ ሲሉ ተገደሉ የሚል መርዶ፡፡

  በተደጋጋሚ የእስር ቤቶች መቃጠል ዜና ይሰማል፡፡ እስር ቤቶች ለምን ይቃጠላሉ? ሁልጊዜ እንደሚባለው የመንግሥት አሠራር ግልጽነት በጎደለው ቁጥር በተከታታይ ተደጋጋሚ ችግሮች ሲከሰቱ መንስዔአቸው አይታወቅም፡፡ አሁንም ቂሊንጦን ጨምሮ በተለያዩ ሥፍራዎች በእስር ቤቶች ላይ የእሳት አደጋዎች ሲያጋጥሙ ምክንያታቸው በግልጽ አይነገርም፡፡ በአደጋዎቹ ግን በረጃጅም አጥሮች ውስጥ የታሰሩ ሰዎች ሞትና ጉዳት ይሰማል፡፡ በእሳት አደጋ ምክንያት በታሳሪዎች ላይ የደረሰው ሞት በጣም የሚያንገበግብ ከመሆኑም በላይ፣ ሊያመልጡ ሲሉ ተገደሉ የሚለው ደግሞ የበለጠ ያማል፡፡ ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የበለጠ አመኔታ እንዲኖራቸው ሲባል፣ በደረሰው አደጋ ሳቢያ እስረኞች ‹‹ሞቱ›› ከሚባል ‹‹አመለጡ›› ቢባል የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ያመለጠ እስረኛን አፈላልጎ ማግኘት የሚቻል ሲሆን፣ የሞተ ግን እስከወዲያኛው አይገኝም፡፡ መንግሥት በዚህ መንገድ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባው ነበር፡፡ ሊያመለጡ ሲሉ ተገደሉ የሚለው ሪፖርት የተጠያቂነት መጥፋት ማሳያ ነው፡፡

  ቂሊንጦን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ እስር ቤቶች ላይ የደረሱ የእሳት ቃጠሎዎች በታሳሪዎች ላይ ያስከተሉት አደጋ መጣራት አለበት፡፡ ይህ ማጣራት በነፃና በገለልተኛ አካላት መካሄድ ይኖርበታል፡፡ በሌሎች አገሮች እንዲህ ዓይነት አደጋዎች ሲያጋጥሙ በፍጥነት የሟቾችን ማንነትና ቁጥራቸውን ማስታወቅ፣ የሟቾችን ቤተሰቦች ማረጋጋትና ማፅናናት፣ ነፃና ገለልተኛ አካል በአስቸኳይ መሥርቶ ምርመራ መጀመር የተለመደ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምን እያደረገ እንዳለ አይታወቅም፡፡ በመንግሥት በጀት የሚንቀሳቀሰው ይህ ተቋም የገለልተኝነቱ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ምን እያደረገ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ኃላፊነት ያለበት መንግሥት በፍጥነት ምላሹ መታወቅ አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ እያስቸገረ ያለው ከሕግ በላይ ሆኖ ለሕግ የበላይነት ዘብ ነኝ ማለት፣ ከተጠያቂነት በላይ ሆኖ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ከሚባሉ የተሸፋፈኑ አሠራሮች መውጣት አለመቻል ነው፡፡

  የመንግሥት አሠራር በግልጽነትና በተጠያቂነት መንፈስ መመራት አለበት የሚለው መርህ ጥያቄ ውስጥ ወድቆ፣ በተደጋጋሚ የተሸፋፈኑና የተድበሰበሱ ድርጊቶች ሕዝብና መንግሥትን አቀያይመዋል፡፡ ከኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመንግሥት ላይ የተነሳው ተቃውሞ አንዱ ምክንያት የግልጽነትና የተጠያቂነት መጥፋት ነው፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ የሚመራው መንግሥት ሕዝብን በአግባቡ ማዳመጥ ባለመቻላቸው ምክንያት፣ የተደራረቡ ጥያቄዎች የቀሰቀሱዋቸው ግጭቶች በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሞት፣ አካል ጉዳትና ንብረት ውድመት መንስዔ ሆነዋል፡፡ ግጭቶቹ መርገብ ባለመቻላቸው ሳቢያ አገሪቱ ጭንቅ ውስጥ እያለች የእስር ቤቶች ቃጠሎ ከየቦታው ይሰማል፡፡ በቃጠሎዎቹ ምክንያትም ዜጎች እየሞቱ ነው፡፡ ከሞታቸው የአሟሟታቸው ሁኔታ ጥርት ብሎ አለመታወቁ ደግሞ ሌላው የአገር ራስ ምታት ነው፡፡ ይኼኔ ነው እንግዲህ መንግሥት በቁጥጥሩ ሥር ላሉ እስረኞች ደኅንነት ኃላፊነትም ተጠያቂነትም አለበት የሚባለው፡፡

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

  የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

  ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...

  በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ አገልግሎት የተካተተበት አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

  የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ወይም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች በፈቃደኝነት...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...

  የጉድለታችን ብዛቱ!

  ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ጎዳናውን ትውስታ እየናጠው ሁለትና...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...