የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) ቦርድ የአማራ ክልል መገናኛ ብዙኃን ኃላፊ የነበሩትን አቶ ሥዩም መኮንንን ለዋና ሥራ አስፈጻሚነት መምረጡ ታወቀ፡፡
የአማራ ክልል የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊ ሆነው ላለፉት አራት ዓመታት ያገለገሉትን አቶ ሥዩም፣ በአቶ ጌታቸው ረዳ ሊቀመንበርነት የሚመራው ቦርድ በቅርቡ እንደመረጣቸው ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ከፍተኛ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን በአዲሱ የኢብኮ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 858/2006 መሠረት የአቶ ሥዩም ሹመት ሙሉ ለሙሉ የሚፀናው፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሲያፀድቀው ነው፡፡
ኢብኮን ላለፉት ሦስት ዓመታት በሥራ አስፈጻሚነት ሲመሩት የቆዩት አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም ከተነሱ በኋላ በተጠባባቂ ድርጅቱ ሲመራ ቆይቷል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አቶ ብርሃነን መንግሥት ለዲፕሎማሲ ሥራ ወደ ውጭ አገር ሄደው እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል፡፡ አሜሪካ ሄደው በቆንስላነት እንዲያገለግሉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መመደባቸው ታውቋል፡፡
አቶ ሥዩም በባህር ዳር ለሚገኘው የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ከመሾማቸው በፊት፣ በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ማገልገላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1993 ዓ.ም. አግኝተዋል፡፡ የመጀመሪያውን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ሲያጠናቅቁ ሁለተኛውን ሁለተኛ ዲግሪ ደግሞ በቅርቡ እንግሊዝ አገር ከሚገኝ ክራንፊልድ ዩኒቨርሲቲ በኢንቫይሮመንታል ማኔጅመንት ፎር ቢዝነስ አግኝተዋል፡፡