Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአቶ መኩሪያ ኃይሌ ከከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትርነታቸው ተነስተው በአማካሪነት ተሾሙ

አቶ መኩሪያ ኃይሌ ከከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትርነታቸው ተነስተው በአማካሪነት ተሾሙ

ቀን:

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ ከሚኒስትርነት ሥልጣናቸው ተነሱ፡፡ አቶ መኩሪያ ከሚኒስትርነታቸው የተነሱ ቢሆንም፣ ከመስከረም 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የከተማ ልማት ጉዳዮች ፖሊሲ ጥናትና ምርምር አማካሪ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡

አቶ መኩሪያ ከከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትርነታቸው የተነሱበት ምክንያት ያልተገለጸ ቢሆንም፣ አማካሪ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ግን ነሐሴ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ፊርማ በተሰጣቸው ደብዳቤ ተገልጿል፡፡

‹‹የመልካም አስተዳደርን ችግር ለመቅረፍ›› በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በ2007 ዓ.ም. ባጠናው ጥናት፣ ከፍተኛ ችግሮች ከተከሰተባቸው የመንግሥት ተቋማት መካከል አንዱ አቶ መኩሪያ የሚመሩት የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መሆኑን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት  የውይይት መድረክ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በወቅቱ በጥናቱ ላይ በተደረገው ውይይትና ክርክር ከኃላፊነታቸው ሊነሱ ይችላሉ ተብሎ ግምት ከተሰጣቸው ባለሥልጣናት አንዱ አቶ መኩሪያ የነበሩ ቢሆንም፣ አቶ መኩሪያ ለሁለት ከተከፈለው የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር አድርጎ በ2008 ዓ.ም. መጀመርያ ላይ ሾሟቸዋል፡፡

አቶ መኩሪያ እንደ አዲስ በተዋቀረው ከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ለአንድ ዓመት የሠሩ ሲሆን፣ በ2008 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለሕግ አውጭው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰኔ ወር 2008 ዓ.ም. ሲያቀርቡ ተቃውሞ ገጥሟቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡

በበጀት ዓመቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ካቀረባቸው ዝርዝር የሥራ አፈጻጸም ክንውኖች መካከል  ስለጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ያከናወናቸውን ሥራዎች በሚመለከት ባቀረቡት ሪፖርት፣ የፓርላማ አባላት ስለጠፉ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡

አቶ መኩሪያ በወቅቱ ስለጠፉ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ ይኼና ሌሎች ተያያዥ ክርክሮች በመነሳታቸው በፓርላማ ታሪክ ሪፖርቱ ሁለት ቀናት ሊወስድ ችሏል፡፡

በወቅቱ የሕግና የፍትሕ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ በሰጠው አስተያየት ‹‹ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እርስ በርሱ የሚጋጭ መመርያ ከማውጣት ውጪ ምንም አልሠራም፤›› የሚል ትችት በማቅረቡ፣ ሪፖርቱ በዕለቱ ሳይጠናቀቅ ቀርቶ በሚቀጥለው ቀን እንዲታይ ተደርጓል፡፡

አቶ መኩሪያ ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ተመካክረው በማግሥቱ  ጠፉ ስለተባሉት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ምንም ያሉት ነገር ባይኖርም፣ ችግሮቹ በሒደት እንደሚቀረፉ በመግለጽ ሪፖርታቸውን ማጠቃለላቸው ይታወሳል፡፡ ጠፉ ስለተባለው የኮንዶሚኒየም ቤቶች በተደረገ ጥናት፣ ቤቶቹ ጠፍተው ሳይሆን በዕቅድ የተያዙ የቤቶች ብዛትና የተገነቡ ቤቶች ቁጥር ሊለያዩ የቻለው በተለያዩ ምክንያቶች ያልተገነቡ ቤቶች በመኖራቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡ ላልተሠሩት ቤቶች የተያዘው በጀት ተቀናሽ ሆኖ ሳለ ሪፖርት አለመደረጉ ቆይቶም ቢሆን መገለጹ ይታወሳል፡፡ አቶ መኩሪያ ምናልባትም ከከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትርነታቸው የተነሱት በተቋማቱ በተደጋጋሚ በቀረቡ ሪፖርቶች ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚሉ አካላት አስተያየት አመዝኗል፡፡

ምንም እንኳን አቶ መኩሪያ ከሚኒስትርነታቸው የተነሱበት ምክንያት በተደጋጋሚ በቀረቡባቸው ሪፖርቶች ሊሆን ይችላል ተብሎ ቢገመትም፣ ተመልሰው ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በዛው ሪፖርት በቀረበባቸው ዘርፍ አንዲያማክሩ መሾማቸው በተለያዩ አካላት ግርምትን ፈጥሯል፡፡ ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት የክልሉ የአስተዳደርና የደኅንነት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ሰለሞን ኩቹ ከኃላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ፣ የክልሉን ፕሬዚዳንት በፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች እንዲያማክሩ መሾማቸው ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ በተለያዩ ጊዜያት ከመንግሥት ኃላፊነታቸው ተነስተው በአማካሪነት የሚሾሙ ባለሥልጣናት ጉዳይ ግራ እንደሚያጋባቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡

አቶ መኩሪያ ከ1997 ዓ.ም. በፊት በደቡብ ክልል የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በ1997 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ተከስቶ የነበረውን ግጭት በማብረድና የማግባባት ሥራ በማከናወን የተዋጣላቸው እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ በነበራቸው የሥራ አፈጻጸም ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባትና አለመረጋጋት፣ በባለ አደራ አስተዳደር ሥር ለሦስት ዓመታት ቆይታ የነበረች አዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ሆነው በ1999 ዓ.ም. ተሹመው እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ ሠርተዋል፡፡ በኋላም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡ አቶ መኩሪያ የኢሕአዴግ አባል ድርጅት ደኢሕዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባል ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...