ሐሙስ ነሐሴ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ ከአገሪቱ የተለያዩ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ3,000 በላይ ወጣቶች ሞልተውታል፡፡
የወጣቶቹ በሥፍራው መሰባሰብ ይደረጋል ከተባለበት ቀን በሁለት ሳምንታት የተራዘመውን የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የወጣቶችን ውይይት ለመታደም ነበር፡፡
ነሐሴ 12 እና 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትሩና የወጣቶች ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለባቸው የሥራ ብዛት ሳቢያ መራዘሙ ይታወሳል፡፡
ሐሙስ ዕለት ከተከናወነው የጠቅላይ ሚኒስትሩና የወጣቶች የፊት ለፊት ውይይትና ጥያቄና መልስ አስቀድሞ ቂሊንጦ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት፣ ‹‹የወጣቶች ሚና በኅብረ ብሔራዊነት ላይ›› በሚል ርዕስ የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለብርሃን የመሩት ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ውይይት ወቅት ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ ወጣቶች ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶች፣ የአካል ጉዳተኛ ወጣቶች፣ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ወጣቶች እንዲሁም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲን የወከሉ ወጣቶች ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
ለተቃዋሚ ፓርቲ ወጣቶች በተዘጋጀው ሥፍራ አብዛኞቹ መቀመጫዎች ባዶ ስለነበሩ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲን ወክሎ የመጣ ወጣት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕድል በመጠቀም ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ያቀረበው ግን አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የሚጠይቁት ዓይነት ‘አባሎቻቸችን በዚህ በዚህ ሥፍራ ታስረዋል፣ እስራትና ወከባ እየደረሰባቸው ነው፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዋች እኩል አይደለም’ እና የመሳሰሉትን ዓይነት መሠረታዊ ጥያቄዎች አልነበረም፡፡
በአንፃሩ ይህ ከአዲስ ትውልድ ፓርቲ የተወከለው ወጣት ያቀረበው አስተያየት ለአገሪቷ ሰላም ወሳኝ መሆኑን፣ እንዲሁም የአገሪቱ ወጣቶች ሥራ አጥ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ አብዛኛዎቹ ብዙውን ጊዜያቸውን የሚያሰልፉት በየቡና ቤቱ ነው የሚል ነበር፡፡
‹‹ለተለያዩ ሥራዎች ወደ ክልል ስንንቀሳቀስ አንድ ቡና ቤት ውስጥ 30 እና 40 የሚሆኑ ወጣቶች ተቀምጠው ነው የምናየው፡፡ ለምን እንዲህ እንደሚያደርጉ ስንጠይቃቸውም መደበሪያችን ነው በማለት መልሰውልናል፤›› በማለት ወጣቶች ቡና ቤት ቁጭ ብለው መዋላቸውን መንግሥት ተመልክቶ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ጠይቋል፡፡
ከየክልሎቹ ተወክለው የመጡት ወጣቶች ከየክልሎቻቸው አንፃር ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ የአብዛኛዎቹ ጥያቄዎች ማጠንጠኛም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ እንዲሁም ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ነበር፡፡
በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ካለችበት አለመረጋጋት አንፃር ወጣቶቹ ጉዳዩን በተመለከተ የተለያዩ ጥያቄዎች ያነሳሉ የሚል ግምት የነበረ ቢሆንም፣ ከአማራ ክልል ተወክሎ ከመጣው ወጣት በስተቀር ስለወቅታዊ ጉዳዮች ጥያቄ ያነሳ የለም፡፡
ለአብነት ያህልም ከሐረሪ ክልል ተወክሎ የመጣው ወጣት የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ፣ አንዱ ጥያቄ የነበረው አዲስ አበባ የሚገኙ የሐረሪ ክልል የተለያዩ ቅርሶችን ወደ ሐረሪ መመለስ የሚቻልበትን መንገድ መንግሥት እንዲያፈላልግ የሚጠይቅ ነበር፡፡
ለዚህ ጥያቄም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመልሱ፣ ‹‹ኢትዮጵያን ለመጐብኘት የሚመጣ አንድ ቱሪስት ሁሉንም ቦታዎች ተዘዋውሮ መመልከት ላይችል ይችላል፡፡ ስለዚህ በአዲስ አበባ የአገሪቱን ሁሉንም ክፍሎች የሚወክል ቅርስ ቢኖር ጉዳት አይኖረውም፤›› ብለዋል፡፡
አዲስ አበባን ወክላ ጥያቄ ያቀረበችው ወጣት ደግሞ ያቀረበቻቸው ጥያቄዎች ከመዝናኛ ሥፍራዎችና የስፖርት ማዘውተሪያዎች ዕጦት፣ ከሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ይገነባል ተብሎ ከአሥር ዓመት በላይ ስለዘገየው የአፍሪካ ወጣቶች ማዕከል ግንባታ ነበር፡፡
በአዲስ አበባ በስፋት የሚታየውን የወጣቶች ሥራ አጥነት፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረጉ ፍልሰቶችና የመሳሰሉ ዓበይት ጉዳዮች እያሉ እነዚህን ጥያቄዎች ማቅረቧ ግርታ የፈጠረባቸው ተስተውለዋል፡፡
ከትግራይ ክልል ተወክሎ የመጣው ወጣት ደግሞ ያነሳቸው ጥያቄዎች ከጥቃቅንና አነስተኛና ከመሬት ይዞታ ባለቤትነት ጋር የተያያዙ ነበሩ፡፡ ‹‹የቤተሰቦቻችን መሬት ወደ ከተማ ክልል በሚካለልበት ጊዜ የመውረስ መብት የማይኖረን ለምንድን ነው?›› የሚል ጥያቄም አቅርቧል፡፡
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጣው ወጣት ደግሞ አሁንም ድረስ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እንዳልተገታ፣ በቤኒሻንጉል በኩል የሚደረጉ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውሮች መኖራቸውን ጠቁሞ፣ መንግሥት ይህን ለመቅረፍ ምን እየሠራ እንደሆነ ጠይቋል፡፡
ከየክልሎቹና ከከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት ተወክለው የመጡት ወጣቶች ጥያቄዎቻቸው ከክልላቸው አልያም ከየተወከሉበት ተቋም አንፃር የተቃኙ ነበር፡፡
የወጣቶቹን ጥያቄዎች በጠቅላላ አዳምጠው ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በቀጥታ ጥያቄዎቹን ከመመለሳቸው በፊት፣ ስለአገሪቱ አጠቃላይ የወጣቶች ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የአገሪቱ አብዛኛው ዜጋ ወጣት እንደሆነ በመተንተን ንግግራቸውን የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጥያቄዎቹን አንድ በአንድ እያነሱ ከመመለስ ይልቅ ስለአገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታ በሚሰጡት ትንታኔ ውስጥ እየመለሷቸው ማለፍን መርጠዋል፡፡
‹‹70 በመቶ የሚሆነው የአገራችን ሕዝብ ከ30 ዓመት በታች ነው፡፡ ይህም ማለት ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር ናት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር ከሆነች በሕዝቦች ፈቃድ ወደ ሥልጣን የሚመጣ መንግሥት የወጣቶቹ መንግሥት መሆን አለበት፤›› በማለት ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ ፖሊሲ መንግሥታቸው እንደሚከተል ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ ወደ ጥያቄዎቹ ምላሽ ከመግባታቸው በፊት በሰጡት የኢትዮጵያ ወጣቶች ሁኔታ ትንታኔ ውስጥ የነገሮች ሁሉ ማጠንጠኛ መሆን ያለበት ሕገ መንግሥቱ እንደሆነ አስምረውበታል፡፡
‹‹አሁን ያለው ሥርዓት የተመሠረተው በወጣቶች ነው፡፡ በዚህም መሠረት ለዘመናት ሲጠየቁ የነበሩ ጥያቄዎችን መመለስ የቻለ ሕገ መንግሥት እንዲኖረን አስችሏል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ የሕገ መንግሥት ጉዳይ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል፤›› በማለት ሕገ መንግሥቱ የነገሮች ሁሉ ማጠንጠኛ እንደሆነ ለወጣቶቹ አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም፣ ‹‹ሕገ መንግሥታችን ከዚህ በፊት የነበሩ የተዛቡ ግንኙነቶቻችንን ለማከም የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የተዛቡ ግንኙነቶች ነበሩ፡፡ ነገር ግን የዛሬ 20 ዓመት ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ እነዚህ የተዛቡ ልዩነቶች ለሚቀጥለው ትውልድና ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የማይተላለፉ ሆነው አልፈዋል፤›› ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በሥራ ፈጠራ፣ የሥራ አጥ ቁጥርን ከመቀነስ፣ እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር የተሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም ሙሉ በሙሉ ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ አግኝተዋል ማለት እንዳልሆነም ጠቅሰዋል፡፡
ሥራ አጥነትን ለመዋጋት ወጣቶች ራሳቸው ሥራ ፈጣሪ መሆን እንደሚገባቸው ጠቁመው፣ ለአብነትም ከታች ተነስተው ዛሬ የዓለማችን ታላላቅ ስለሆኑት የሳምንሰንግና የቶዮታ ኩባንያዎች ባለቤቶች የሥራ ስኬት ለወጣቶቹ ሐሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
መንግሥታቸው የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ብዙ ሥራዎችን እንደሠራ ገልጸው፣ ከዚህ በተጨማሪ ግን ማኅበራዊ ግንኙነታቸውንም ለማሻሻል እየሠራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
‹‹የሰው ልጅ ማኅበራዊ እንስሳ ነው፡፡ ስለዚህ ማኅበራዊ ተጠቃሚነታችንና ትስስራችን መጐልበት አለበት፡፡ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ብቻውን በቂ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
የመልካም አስተዳደር ጥያቄን በተመለከተ ወጣቶች በቻሉት መጠን ሁሉ የመልካም አስተዳደር ችግር ያለባቸውን አመራሮች በማጋለጥ ሚናቸውን መጫወት ይኖርባቸዋል በማለት ተናግረዋል፡፡
ወጣቶች ተስፋ ሳይቆርጡ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ጥያቄዎቻቸውን በማቅረብ፣ በአገሪቱ አሉ የተባሉ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ጥያቄዎችን ለማስመለስ መንቀሳቀስ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
በቅርቡ በተለያዩ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች የተከሰቱትን አለመረጋጋቶች አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ ጥያቄ ያላቸው ወጣቶች ጥያቄያቸውን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ማቅረብ ሲችሉ ድንጋይ በመወርወርና በሌሎች እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ መሆናቸው ማንንም እንደማይጠቅም አብራርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወጣቶች የተነሱትን ጥያቄዎች ከመለሱና አጠቃላይ ማብራሪያ መስጠታቸውን ከአጠናቀቁ በኋላ ለማመስገን ወደ መድረኩ የወጣው የዕለቱ የፕሮግራም መሪ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በማለት ፈንታ ‘ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ’ ብሎ የጀመረው የምሥጋና ንግግር አዳራሹ ውስጥ የነበሩትን ታዳሚዎች በሙሉ አስደንግጦ ነበር፡፡