ንጉሠ ነገሥቱን ለመጠየቅ ከሩቅ አካባቢ የሚመጡ እንግዶችን ሁሉ ለማስተናገድ ቤተ መንግሥቱ ብቻ በቂ አልነበረም፡፡ ይህም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው ጣይቱ ሆቴል እንዲገነባ ምክንያት ሆነ፡፡ አፄ ምኒልክ በአዲስ አበባ ያሉ ዲፕሎማቶችንና የውጭ አገር ሰዎችን በመጋበዝ ሆቴሉን ጥቅምት 25 ቀን 1900 ዓ.ም. አስመረቁ፡፡ ሆቴሉን የማስተዳደር ኃላፊነትም በእቴጌ ጣይቱ ላይ ተጣለ፡፡
እቴጌይቱ በተሰጣቸው ኃላፊነት እጅ የሚያስቆረጥም ምግብ እንዲዘጋጅ ቢያደርጉም ምግብ ገዝቶ መብላት ነውር ነበረና ወደ ሆቴሉ ዝር የሚል ጠፋ፡፡ የተዘጋጀውን ምግብ የሚበላ ደንበኛ በመጥፋቱ የሠራተኞች እራት ይሆንም ነበር፡፡ የሆቴሉ ገበያ ማጣት ያሳሰባቸው አፄ ምኒልክም አንድ ቀን በአካባቢያቸው ያሉ መኳንንቶችን ‹‹ጣይቱ ምግብ የሚሸጥበት ቤት ከፍታለችና ኑ እንሂድና ልጋብዛችሁ›› ብለው ወሰዷቸው፡፡ የሆቴሉ የመጀመሪያው እንግዶች በሉ ጠጡ፡፡ ንጉሡም 30 ብር ከፈሉ፡፡
ይህ ሆቴሉን ለማስለመድ በቂ ይሆናል ብለው አስበው ነበር፡፡ ይሁንና በማግሥቱ እንኳን ምግብ ፈልጐ ወደ ሆቴሉ የሄደ አልነበረም፡፡ ከዚያም አፄ ምኒልክ ችሎት ዘግተው ሲነሡ፣ በዙሪያቸው ለነበሩ መኳንንት በፈረንጅ አገር አንድ ቀን አንድ ሰው የጋበዘ እንደሆነ ተጋባዡ በሌላ ቀን ብድሩን መመለስ አለበት ብለው ነገሯቸው፡፡ ብድራቸውን ለመመለስ ምክንያት ይፈልጉ የነበሩት መኳንንትም ተራ በተራ ከሆቴል ቤቱ አፄ ምኒልክንና ጣይቱን ይጋብዙ ጀመረ፡፡ ቀስ በቀስም ገበያው ደራ፡፡ ‹‹ምሣችንን እቴጌ ሆቴል ሄደን እንብላ›› የሚሉም በዙ፡፡
ምግብ ከውጭ የመብላት ነውርነቱ ቀስ በቀስ እየቀረ መጣ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ሆቴል ቤቶችና ምግብ ቤቶችም ተከፈቱ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ቤቱ ገብቶ ምግብ ለመብላት ያላመቸው ወደ ምግብ ቤቶቹ ጐራ ማለት ጀመረ፡፡ አንድ ጊዜ የተጋበዙም ብድሬን ልመልስ እያሉ ምግብ ቤቶቹን ማዘውተር ሥራቸው አደረጉት፡፡ ዋጋውም ኪስ የማይጐዳ ነበር፡፡ እስከ ሀምሳዎቹ መጀመሪያ ክትፎ በ25 ሣንቲም፣ ጥብስ፣ ፍርፍር እና የመሳሰሉት ደግሞ ከ25 ሣንቲም በታች ይሸጡ ነበር፡፡
በሀምሳዎቹ መጨረሻ አካባቢ የነበሩ የምግብ ዝርዝሮችም ብዙ የዋጋ ለውጥ የማይታይባቸው ነበሩ፡፡ ትኩስ ነገሮች፣ ቁርስ፣ ምሣና እራት በሚል በተዘጋጀው የምግብ ዝርዝር ላይ ለቀረቡት የምግብ ዓይነቶች ከፍተኛው ዋጋ አንድ ብር ከ50 ሣንቲም ነው፡፡ ሻይ 15 ሣንቲም፣ ማኪያቶ 25 ሣንቲም፣ ዱለት 75 ሣንቲም፣ ክትፎ 1 ብር ከ25 ሣንቲም፣ ፓስታል ፉርኖ 1 ብር፣ ፓስታ 1 ብር በጥቁር አንበሣ ሆቴል የዋጋ ዝርዝር ላይ ከቀረቡ የምግብ ዓይነቶች መካከል ናቸው፡፡ 10 ብር ምግብና አልጋን ጨምሮ ሌሎችንም የቀን ወጪዎች ይሸፍን ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በ10 ብር እንኳንስ ምግብ የምግብ መጠቅለያውን መግዛት ከማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ በ15 ሣንቲም ይሸጥ የነበረው ሻይ በአሁኑ ወቅት እስከ 20 ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ በአንድ ወቅት በፌስቡክ ላይ የተለጠፈ ደረሰኝ፣ አንድ ሻይ ከ50 ብር በላይ የሚሸጥባቸው ቤቶች መኖራቸውን አመልክቷል፡፡
ቦሌ አካባቢ የሚገኝ የአንድ ሬስቶራንት የምግብ ዝርዝር ያለውን የምግብ ዋጋ ንረት ያሳያል፡፡ ፓስታ በቲማቲም ሶስ 109 ከ59 ሣንቲም፣ ፓስታ በሥጋ 113 ብር ከ5 ሣንቲም፣ ፓስታ በአሣ 113 ብር፣ ፓስታ በአትክልት 91 ብር ሌሎችም ተቀራራቢ ዋጋ ያላቸው የምግብ ዓይነቶች በዝርዝሩ ተካትተዋል፡፡ ከሥሩ ደግሞ 15 ብር ቫት ጭማሪ መኖሩን የሚገልጽ ጽሑፍ ሰፍሯል፡፡ እንደ ሽሮ እና በየዓይነቱ ያሉ የፆም ምግቦች ዋጋም ከ80 ብር በላይ ነው፡፡
በምግብ ዝርዝሩ ላይ የተቀመጠው ዋጋ የናረ ቢሆንም በከተማው ከሚታየው ዋጋ አንፃር ተመጣጣኝ ያስከፍላሉ ከሚባሉት ሬስቶራንቶች የሚመደብ ነው፡፡ ተመሳሳይ ሬስቶራንቶች በመሥሪያ ቤቶች አካባቢ የሚገኙ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ደንበኞቻቸውም የቢሮ ሠራተኞች ናቸው፡፡ ነገር ግን ለአንድ ምግብ የሚጠይቁት ዋጋ ከደንበኞቻቸው አቅም ጋር አብሮ የሚሄድ አለመሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡
ጥቂት የማይባሉ የቢሮ ሠራተኞችም ምሣ በመያዝ ኪስ የሚያራቁተውን የሬስቶራንት ምግብ ለማስቀረት ይሞክራሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የተጠየቁትን ከፍለው የሬስቶራንት ምግብ መብላትን ይመርጣሉ፡፡
ሚካኤል ኃይለየሱስ የ6,000 ብር ደመወዝተኛ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ምሣውን የሚመገበው ካዛንቺስ እና መገናኛ አካባቢ በሚገኙ ምግብ ቤቶች ነው፡፡ እንደ ጥብስ፣ ቅቅል፣ ሽሮ እና በየዓይነቱ ያሉ ምግቦችን ይመርጣል፡፡ ለአንድ ምግብ ከ40 እስከ 55 ብር ይከፍላል፡፡ ዋጋው በከተው ከሚገኙ አብዛኛዎቹ ሬስቶራንቶች የተሻለ ቢሆንም በወር ከሚያገኘው ጋር አይመጣጠንም፡፡ ስለዚህም ወጪውን ለመቀነስ ሲል አመጋገቡን ለማስተካከል ተገድዷል፡፡ ብዙ ጊዜ ቁርስ አይበላም፡፡ ረፈድ አድርጐ አምስት ሰዓት አካባቢ ብዙዎች ‹‹ቁምሣ›› የሚሉትን በቁርስና በምሣ መካከል ባለ የምግብ ሰዓት፣ እራቱን ደግሞ 11 ሰዓት ገደማ ይበላል፡፡ በዚህም በቀን ለምግብ የሚያወጣው ከ100 ብር እንዳይበልጥ ለማድረግ መቻሉን ይናገራል፡፡
ለአንድ ምግብ ቢያንስ እስከ 100 ብር የሚያስከፍሉ ሬስቶራንቶች ብቻ ባሉባቸው አካባቢዎች የሚሠሩና ምግባቸውን በእነዚህ ሬስቶራንቶች ለመብላት የሚገደዱ ሰዎች ግን እንደ ሚካኤል በቀላሉ መገላገል አይችሉም፡፡ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የመጣው የምግብ ዋጋ ከባድ ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡
አቶ ዓለማየሁ ሠይፈሥላሴ የምሣ ዕቃ መያዝ አይወድም፡፡ ምሣ ሰዓት ላይ ከጓደኞቹ ጋር በአቅራቢያ በሚገኙ ሬስቶራንቶች አብሮ ይበላል፡፡ ለአንድ ምሣ እንደ ምግቡ ዓይነት ከ70 እስከ 100 ብር ይከፍላሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ የመጣው የምግብ ዋጋ ግን ራስ ምታት ሆኖባቸዋል፡፡ ‹‹ከጥቂት ዓመታት በፊት ምሣ በ11 ብር እበላበት የነበረው ቤት አሁን ለአንድ ምሣ 90 ብር ያስከፍሉኛል፡፡ በሚገርም ፍጥነት ነው የዋጋ ልዩነት እየተፈጠረ ያለው፡፡ ከቀናት በፊት ቦሌ አካባቢ በሚገኝ አንድ በርገር ቤት የአንድ በርገር ዋጋ 130 ብር ነበር፡፡ ባለፈው ሣምንት ግን ለተመሳሳይ በርገር 200 ብር ነው ያስከፈሉኝ›› በማለት ሬስቶራንቶች የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ መሆኑን ገልጿል፡፡
ይህንን ያህል ገንዘብ ተከፍሎባቸው የሚቀርቡት ምግቦች ሁሉም ፅዳታቸው የተጠበቀ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ጥንቃቄ በጐደለው አሠራር ከምግብ ውስጥ ፀጉር፣ ጥፍር እና ነፍሳት ማግኘት ተለምዷል፡፡ ምግቡ የሚዘጋጅበት ዘይትና ሌሎች ግብዓቶች ምን ያህል አስተማማኝ ናቸው የሚለውም አጠያያቂ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ለአንድ ምግብ የሚከፈለው ዋጋ ከአንዱ ሬስቶራንት አንዱ እንደሚለያየው ሁሉ የምግቡ ጣዕም እና መጠን የተለያየ ሲሆን ይታያል፡፡ በምግብ ዝርዝሩ ላይ የሚታየው እና ምግቡ ተዘጋጅቶ ሲቀርብ የሚለያይበት አጋጣሚም አለ፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ዓለማየሁ ያጋጠመውን እንዲህ አስታውሷል፡፡ ‹‹ቦሌ አካባቢ የሚገኝ አንድ ሬስቶራንት ገብቼ ከምግብ ዝርዝሩ ላይ ያየሁትን አንድ ስሙን የማላውቀውን የውጭ አገር ምግብ አዘዝኩኝ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ምግቡ ሲመጣ ደነገጥኩኝ፡፡ መሀል ሰሀኑ ላይ ትልቅ የተከተፈ ጥሬ ሽንኩርት አለ፡፡ ዳርዳሩ ላይ ደግሞ የጣት ቁራጭ የሚያካክሉ ትንንሽ ሚትቦሎች አሉ፡፡ በጣም ትንሽ ነበር፡፡ አንድ ምግብ ሆኖ መቅረብ አይችልም፡፡ እንደዚያም ሆኖ 150 ብር ነበር ያስከፈሉኝ››
‹‹ሜኑ ላይ የምግብ ዓይነት ሲዘረዘር፣ በዝርዝሩ መሠረት ምግብ እናቀርባለን ብሎ ቃል መግባት ነው›› የሚለው የምግብና የመጠጥ ቁጥጥር ባለሙያ ፕራይቬት ሼፍ አላዛር በሪሁን፣ ሜኑ ከማውጣት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውን ይናገራል፡፡ አብዛኛዎቹ ሬስቶራንቶች ደረጃውን የጠበቀ ምግብ አያቀርቡም፡፡ ስለሚያዘጋጁት ምግብም በቂ ዕውቀት የላቸውም፡፡ ለምሣሌ ፒዛ የመጣው ከጣልያን ነው፡፡ ያሉትም የተወሰኑ የፒዛ ዓይነቶች ብቻ ናቸው፡፡ እዚህ ግን ወፍራም፣ ስስ፣ የአሜሪካ ፒዛ እያሉ የማይታወቁ የፒዛ ዓይነቶችን ሠርተው ያቀርባሉ፡፡ ሀምበርገር ሲባል ሀም ያለው በርገር ማለት ነው ብለው በርገር የሚያቀርቡ ሬስቶራንቶችም ብዙ ናቸው፡፡
አንድን ምግብ ለማዘጋጀት የሚውሉ የተወሰኑ ግብዓቶችና ቅመማ ቅመሞችም እያሉ፣ አብዛኛዎቹ ሬስቶራንቶች ሌላ የራሳቸውን ምጥን ይጨምሩበታል፣ አልያም ምግቡን ለማዘጋጀት ከሚውሉ ግብዓቶች መካከል አንዱን አጓድለው ይሠራሉ፡፡ ይህም ያዘጋጁት ምግብ ደረጃውን የጠበቀ ጣዕም እንዳይኖረው ያደርጋል፡፡ ‹‹በርገር ለማዘጋጀት አስፈላጊ ከሆኑ ግብዓቶች ላይ የተጨመሩ ካሉ አልያም ከተጓደሉ ለተዘጋጀው ምግብ በርገር የሚባለው ስያሜ ተስማሚ አይሆንም፡፡ ሌላ የራሳቸውን ስም ሊሰጡት ይገባል›› ይላል ባለሙያው፡፡
እንደ አላዛር ምንም ዓይነት የኑሮ ውድነት ቢፈጠር አንድ ምግብ መሸጥ ያለበት ምግቡን ለማዘጋጀት የወጣውን ወጪ እስከ 3 እጥፍ በመብለጥ ነው፡፡ ከፍተኛ ደረጃ ባላቸው ቅንጡ ሆቴሎች የሚዘጋጁ ምግቦች ደግሞ እስከ 80 በመቶ በሚደርስ የትርፍ ህዳግ ሊሸጡ ይችላሉ፡፡ ይህም ከሚሰጡት የተለያዩ ደረጃቸውን ከጠበቁ አገልግሎቶች አኳያ የሚታይ ነው፡፡
እንደ ሼፍ አላዛር ገለጻ፣ በከተማው የሚገኙ ሬስቶራንቶች የሚያስከፍሉት ለምግቡ ሳይሆን ለቤቱ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አግባብነት የለውም፡፡ የተጠየቀውን ዝም ብሎ ከመክፈልም ለምን ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ይንንም ለማድረግ ለአንድ ምግብ የሚከፍለው ዋጋ ምን ያህል ምክንያታዊ ስለመሆኑ ምግቡ ከምን እና እንዴት እንደሚዘጋጅ ማወቅ ግድ ይላል፡፡ ነገር ግን ብዙዎች ይህንን አያውቁትም፡፡ ይህም ደንበኞችን ለብዝበዛ አጋልጧቸዋል፡፡
ከአንዳንድ የምግብ ዓይነቶች ውጪ ለአንድ ሰው የሚቀርብ የምግብ መጠን ከ300 እስከ 350 ግራም መሆን ይገባዋል፡፡ ይሁንና መሥፈርቱን ጠብቀው የሚያዘጋጁ ሬስቶራንቶች ባለመኖራቸው፣ ለአንድ ሰው ተብሎ የሚቀርብ ምግብ መጠን ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲኖሩም ተጠቃሚው ጭማሪ ምግብ አዝዞ ከመመገብ ባለፈ የሚያደርገው የለውም፡፡ ሳይንሱን የሚያውቁ አንዳንድ ሰዎችም፣ ‘ከስንቱ ጋር ተጨቃጭቄ እችላለሁ’ በሚል አይተው እንዳላዩ ማለፍን ይመርጣሉ፡፡
የኑሮ ውድነት በሣንቲም ደረጃ የነበረውን የምግብ ዋጋ ወደ ላይ እንዲተኮስ አድርጓል፡፡ ነገር ግን እየታየ ላለው የምግብ ዋጋ ውድነት የኑሮ ማሻቀብ ብቻ ምክንያት አይመስልም፡፡ ምግብ የሚሸጥበት ዋጋ ከአንዱ ቤት አንዱ የሰማይና የምድር ያህል መለያየትም ከኑሮ ውድነት ባሻገር ሌሎች ነገሮች መኖራቸውን አመላካች ነው፡፡ በአንዳንድ ምግብ ቤቶች ለአንድ ምግብ የሚከፈለው ዋጋ በሌሎቹ ለተጨማሪ እሴት ታክስ የሚከፈለው ዓይነት ነው፡፡
ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ የሚገኘው ሙሉ ምግብ ቤት ፓስታ፣ ዱለት፣ ፍርፍር፣ ተጋቢኖ፣ በየዓይነት የመሳሰሉ ምግቦች አዘጋጅተው ይሸጣሉ፡፡ ዋጋቸውም ከ16 ብር እስከ 23 ብር ባለው ውስጥ ነው፡፡ ‹‹የገበያው ሁኔታ እግዜር እንደሰጠ ነው፡፡ ተማሪ ሲኖር ይደራል ሳይኖር ደግሞ ትንሽ ቀዝቀዝ ይላል›› የሚሉት የሙሉ ምግብ ባለቤት ወ/ሮ ሙሉ ገበያው ሥራው አዋጭ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ወ/ሮ ፈቲያ ሽፋም እንደዚሁ እንደ ፍርፍር፣ ፓስታ፣ ያሉ ምግቦችን አዘጋጅተው ይሸጣሉ፡፡ በሥራው 3 ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ የጀመሩ አካባቢም አንድ ፓስታ በ13 ብር ይሸጡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ‹‹የሽንኩርት፣ የቲማቲም የዘይት እና ሌሎች ግብዓቶች ዋጋ ጨምሯል፡፡ በመሆኑም አንድ ፓስታ በ13 ብር ለመሸጥ አያዋጣኝም፡፡ የአራት ብር ጭማሪ አድርጌበታለሁ›› በማለት በዚህ ሦስት ዓመታት ውስጥ በታየው የተለያዩ ግብዓቶች የዋጋ ጭማሪ በአንድ ምግብ ላይ ከአራት ብር ያልበለጠ ጭማሪ ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡
መጠነኛ ብር በመጨመር እንደዚህ ማስተካከል እየተቻለ በአብዛኛዎቹ ሬስቶራንቶች የሚታየው የተጋነነ የዋጋ ውድነት ከበስተጀርባው ምን ይኖር ይሆን? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ ይህንንም በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ይደመጣል፡፡ በከተማው የሚገኙ ለአንድ ምግብ ከሺሕ ብር በላይ የሚያስከፍሉ ሬስቶራንቶች የሚሸጡት ምግብ ሳይሆን ደረጃ (ክላስ) ነው የሚሉ አሉ፡፡ ተመሳሳይ ሬስቶራንቶችን የሚያዘወትሩ በምርጫ በመሆኑ እንዲከፍሉ የሚደረገው ዋጋ ውድ መሆን እንደ ችግር እንደማይታይ፣ ይልቁኑ አብዛኞችን ለማገልገል ተብለው የተከፈቱ ሬስቶራንቶች ዋጋቸው የሕዝቡን አቅም ያላገናዘቡና ኪስ የሚያራቁቱ ናቸው ይላሉ፡፡
‹‹የምግብ ዋጋ ሊተመን የሚገባው ምግቡን ለማዘጋጀት ከወጣው ወጪ አኳያ ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የምግብን ዋጋ እየተቆጣጠረ ያለው የቤት ኪራይ ነው›› ያሉት፣ በከተማው የሚገኝ አንድ ሬስቶራንት ባለቤት አቶ አሰግድ (ስማቸው ተቀይሯል) ናቸው፡፡ በሬስቶራንታቸው ጥብስ፣ ፍርፍር፣ ሽሮ ያሉ የተወሰኑ የአገር ውስጥ ምግቦችና ከ300 የሚበልጡ የውጭ አገር ምግቦችን በማዘጋጀት ለደንበኞች ያቀርባሉ፡፡ ለአንድ ምግብ ቫትን ሳይጨምር እስከ 120 ብር ድረስ ያስከፍላሉ፡፡ ለውጭ ድርጅቶችና ለልዩ ልዩ ተቋማትም በኮንትራት ተቀጥረው ምግብ ያዘጋጃሉ፡፡ ለዚህም በሰሀን ከ250 እስከ 350 ብር ድረስ እንደሚያስከፍሉ ተናግረዋል፡፡
‹‹ዋጋው ተቃውሷል፡፡ የግብዓቶች ዋጋ ከፍ ዝቅ ይላል፡፡ አሁን ላይ አንድ ኪሎ ቲማቲም 20 ብር ገብቷል፡፡ እስካሁን ለቤት ኪራይ የምከፍለው በወር 76,000 ብር ነው፡፡ ከሁለት ወር በኋላ ግን 115,000 ብር እንድከፍል አለዚያ እንድለቅ ተነግሮኛል፡፡ ኪራዩን ለመክፈል የምግብ ዋጋው ላይ ጭማሪ አደርጋለሁ፡፡ አለዚያ ቤቱን እለቃለሁ፡፡›› የሚሉት አቶ አሰግድ፣ የቤት ኪራይ ዋጋ መናር ለሚታየው የምግብ ውድነት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ያለው የምግብ ዋጋ ለሸማቹ ፈተና ሆኗል፡፡ የሸማቹን መብት ለማስከበር የተቋቋመው የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣንም ‹‹አንድ ሸማች ለሚያወጣው ዋጋ ተመጣጣኝ ዕቃ ወይም አገልግሎት የማግኘት መብት አለው›› በሚል መርህ በግብይት ሥርዓቱ ላይ የሚታዩ አግባብነት የጐደላቸውን ተግባራት እንዲታረሙ እያደረገ ይገኛል፡፡ እንደ ዱቄት፣ ስኳር፣ ዘይት ያሉ የመሠረታዊ የምግብ ግብዓቶች ዋጋ ላይ የሚደረግን ጭማሪ ካልሆነ በስተቀር የሆቴሎች፣ የሬስቶራንቶች የምግብ ዋጋን በተመለከተ ግን ሥልጣን የለውም፡፡ ‹‹የሆቴልና ሬስቶራንት የምግብ ዋጋዎችን በተመለከተ ሥልጣን የለንም፡፡ አገሪቱ የምትከተለው ነፃ ገበያ ነው፡፡ እኛ ማድረግ የምንችለው በርካታ ተቋማት ወደ ንግዱ እንዲገቡ በማድረግ በሚፈጠረው ፉክክር ዋጋው ተመጣጣኝ እንዲሆን ማስቻል ነው›› ያሉት የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ፀጋዬ፣ ዋናው ነገር የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ አለመጨመሩ እንደሆነ፣ ከፍሎ መብላት የማይችል ቤት ውስጥ አዘጋጅቶ በመብላት ችግሩን መወጣት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በከተማው ጥቂት ሬስቶራንቶች በነበሩበት ሁኔታ የምግብ ዋጋ ተመጣጣኝ ነበር፡፡ ነገር ግን የሬስቶራንቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት ለአንድ ምግብ የሚጠየቀው ዋጋ በመቀነስ ፈንታ ከማኅበረሰቡ የመግዛት አቅም በላይ ሆኗል፡፡ ሁኔታው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የያዘውን እስትራቴጂ ተመልሶ ሊፈትሸው እንደሚገባ አመላካች ነው፡፡