Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቆርኪው ዕጣ

የቆርኪው ዕጣ

ቀን:

አንዳች ዓይነት ውድድር ማሸነፍ ወይም በሎተሪ ዕድለኛ መሆን ደስታን የሚፈጥር ነገር ነው፡፡ የደስታው ልክ ግን እንደ ተወዳደሩበት ነገር ክብደት ወይም እንዳሸነፉት ሎተሪ ሽልማት ዋጋ ሊለያይ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ ብዙዎች ዕጣና ሎተሪን በሚመለከት ስሜታቸው የተለያየ ነው፡፡ አንዳንዶች ለእቁብ እንኳ ዕድለኛ አይደለንም ዓይነት ስሜት ስለሚሰማቸው በብሔራዊ ሎተሪ የሚዘጋጁ ሎተሪዎችንም ሆነ የተለያዩ የለስላሳ መጠጦች ወይም ቢራዎች ዕጣን ለመሞከር ፍላጐት የላቸውም፡፡ በሌላ በኩል እራሳቸውን እንደ ዕድለኛ የሚመለከቱት ሎተሪ ብቻም ሳይሆን የተለያዩ ምርቶች ላይ የሚደረጉ ዕጣዎችን ለመሞከር ወደኋላ አይሉም፡፡

በተለያዩ ጊዜአት እንደ ኮካኮላ፣ ሚሪንዳ፣ አምቦ ውኃና የመሳሰሉ ምርቶች ዕጣ ነበራቸው፡፡ የተለያዩ ቢራ አምራች ድርጅቶችም የገበያ አድማሳቸውን ለማስፋት የዚህ ዓይነቱን ምርትን በዕጣ የማጀብ ስትራቴጂ ተጠቅመውበታል፡፡ ትልልቅ ኩባንያዎችም የተለያዩ ምርቶቻቸውን ለማሻሻጥ ተመሳሳይ አካሔድን ሲጠቀሙ ይስተዋላል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ምርቶቻቸው ላይ የተለያዩ ሽልማቶችን የሚያስገኙ ዕጣዎችን አድርገው ደንበኞችን ለመሳብ እየሞከሩ ያሉ የመጠጥና የምግብ አምራች ኩባንያዎች አሉ፡፡ ብዙ ሰዎች የራሳቸው የመጠጥና የምግብ ፍላጐት ስላላቸው እንዲሁም ዕድልን ስለመሞከርና ስለዕድለኝነት ያላቸው ነገር ስለሚለያይ የምርቶች የዕድል ዕጣ ሰዎችን ምን ያህል እነዚያን ምርቶች እንዲጠቀሙ ሊያነሳሳ ይችላል የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል?

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ምግብና ሌሎች ምርቶች ላይ የዕድል ዕጣዎች በማድረግ የሰዎች ፍላጐት ላይ ተፅዕኖ ማድረግ ቀላል እንደማይሆን በተቃራኒው የቢራ ወይም የለስላሳ መጠጥ ምርጫን ለዕጣ ብሎ የመቀየር ነገር በሰዎች በኩል እንደሚኖር የገለጹልን አሉ፡፡ በተለይም ዕጣ ባላቸው መጠጦች ላይ የዕጣውን መጀመር ተከትሎ በካፍቴሪያዎችና መጠጥ ቤቶች የተለያዩ ትዕይንቶች እንደሚስተዋሉ የነገሩን አሉ፡፡

የመጀመሪያው እንግዶች ለወትሮው የት እንደወደቀ ትዝ የማይላቸውን ቆርኪ ወስደሀል አልወሰድኩም በሚል ከአስተናጋጆች ጋር እሰጥ አገባ መግጠም ነው፡፡ ምንም እንኳ የያዙት ጨዋታ ኃይለኛ ቁም ነገር ቢሆን ትኩረታቸው ቆርኪ መላጥ ላይ ሆኖ ጨዋታቸውንም ለመቀጠል የሚታገሉ መኖር ሌላው ነገር ነው፡፡ አስተናጋጆችም ለወትሮ ጠርሙስ ከፈት አድርገው ጠረጴዛ ላይ ወይም አንዱ ጥግ ወርወር የሚያደርጉትን ቆርኪ ከኪሳቸው ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን ያደርጋሉ፡፡

ቦሌ አካባቢ በሚገኝ አንድ ትልቅ መዝናኛ አስተናጋጅ ነው ወጣቱ፡፡ ዕጣ ያላቸው የለስላሳ መጠጦች ወይም ቢራዎች ሲኖሩ የተስተናጋጆችን ሁኔታ አይቶ ቆርኪ ለማስቀረት እንደሚሞክር ይናገራል፡፡ ለምሳሌ ተስተናጋጆች ምርቱ ዕጣ እንዳለው የማያውቁ ወይም በያዙት ወሬ ምክንያት ቆርኪ ላይ ላለው ዕጣ የተረፈ ትኩረት እንደሌላቸው ሲጠረጥር የከፈታቸውን ጠርሙሶች ቆርኪ ከኪሱ ይከትታል፡፡ አንዳንዶች ግን ለወዲያው የቆርኪውን ነገር የዘነጉት ቢመስሉም ቶሎ አስታውሰው አስተናጋጆች ራመድ እንዳሉ ቆርኪ ይጠይቃሉ፡፡ እዚህ አስቀምጨው ነበር ወይም ወደዚያ ወረወርኩት ዓይነት የአስተናጋጆች መልስን ባለመቀበል የሚያመሩም አይታጡም፡፡ በዚህ ዓይነቱ አጋጣሚ እንደ እሱ ያሉ አስተናጋጆች የዘየዱት መላ ቢጤ እንዳለ ያነጋገርነው አስተናጋጅ ይገልጻል፡፡

አራት ኪሎ አካባቢ ብዙዎች በሚያዘወትሩት አንድ መጠጥ ቤት ስታስተናግድ ያገኘናት ሌላ ወጣትም የተከፈተላቸው መጠጥ ዕጣ እንዳለው ከማያውቁ፣ ቢያውቁም እንዲሁ ጥለው ከሚሔዱ ሰዎች የሰበሰበቻቸውን ቆርኪ ከቦርሳዋ እንደምታደርግ ገልጻልናለች፡፡ ቆርኪዎቹን የምትልጠው ቤት ከደረሰች በኋላ ሥራዬ ብላ ቁጭ በማለት ነው፡፡ ለወትሮ ለመጫወቻ ቆርኪ የሚሰበስቡት ሕፃናት በመሆናቸው አዋቂ ቆርኪ ሰብስቦ የመዞሩነገር ፈገግ ሊያሰኝ ይችላል፡፡

ብስራት ታመነ በሚኖርበትና በሚሠራበት አካባቢ ቢራ ለመጠጣት የሚያዘወትራቸው የተወሰኑ ቤቶች አሉ፡፡ እሱ ያን ያህልም ቆርኪ እየላጠ ሥራዬ ብሎ ቢራ ላይ የሚደረጉ ዕጣዎችን ለመሞከር ፍላጎት ባይኖረውም እንዲሁ ከስንት አንድ እጁ የገባን ቆርኪ ለማየት ይሞክራል፡፡ በተቃራኒው ያስከፈቱትን ጠርሙስ ቆርኪ ሁሉ ዕጣ ይኖረዋል ብሎ በመጠርጠር የሚልጡ ዓይነት ዕንግዶች ብዙ ያጋጥማሉ፡፡ አስተናጋጆች እንደዋዛ ወርወር ሲያደርጉ የሚወድቁ ቆርኪዎችን ሳይቀር ጨዋታቸውን አቋርጠው ተንጠራርተውና አጐንብሰው የሚያነሱን ሁሉ አስተውሏል፡፡ ‹‹ዕጣ አለው ሲባል የረዥም ጊዜ ምርጫው የሆነውን መጠጥ እርግፍ አድርጐ ወደ ሌላ የሚዞር አይታጣምም›› ይላል፡፡

ካዛንቺስ፣ ስድስት ኪሎና ሌሎች የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ያሉ መደብሮችና ግሮሠሪዎች ውስጥም በየጊዜው ዕጣ ያላቸው ምርቶች በብዛት ጠያቂ እንደሚኖራቸው ተገልጾልናል፡፡ ይህ ዕጣን ተከትሎ የምርት ፍላጐትን መቀያየር ዕድልን ከመሞከር፣ የዕጣ አሸናፊ ከመሆን ፍላጐት ጋር ይያያዛል፡፡ ዕድለኛ አይደለሁምና ዕጣው አይደርሰኝም የሚሉ ደግሞ ምርቱን ለዕጣው ሲሉ አይጠቀሙም ከተጠቀሙም የሚጠቀሙት ፍላጐታቸውን ብቻ በመከተል ይሆናል፡፡

ራሱን ዕድለኛ አድርጐ ነው የሚመለከተው፡፡ ዕድል የሚጠይቁ ዓይነት ዕጣዎችን ሲሞክር ስሜቱን ተከትሎ ነው፡፡ ቴዎድሮስ ተስፋዬ ሲቪል መሐንዲስ ሲሆን፣ አሥራ ሁለት ዓመታት በሥራ ዓለም ቆይቷል፡፡ ባለፈው ዋሊያ ቢራ ምርቶቹ ላይ አድርጐ ከነበረው ዕጣ የአንዱ አሸናፊ ሆኖ በሽልማቱ ወደ ሲሸልስ ሔዶ የመዝናናት ዕድል ገጥሞት ነበር፡፡ ዕድለኛ ነኝ ብሎ ቢያስብም ሎተሪ ቆርጦ ግን አያውቅም፡፡ ሲሸልስ የመሔድ ዕድል እንዴት እንደገጠመው ጠይቀነው ነበር፡፡

ዕድለኛ ያደረገው ቢራ ሦስተኛ ምርጫው ነበር፡፡ ዕድሉን ለመሞከር እንደ ብዙዎች ምርጫውን ወደ ጐን የማለት ችግር ባይኖርበት እንኳ እንዲሁ ስታስቲካል ፕሮባብሊቲን (ዕድልን) የሚሞክር ሰው አይደለም፡፡ ስለዚህም ስሜቱን ተከትሎ ባደረገው አንድ ሙከራ ነው ዕድለኛ መሆን የቻለው፡፡

‹‹የዚያን ዕለት ጓደኞቼን እንጠጣ ዕድለኛ እሆናለሁ ብዬ በእርግጠኝነት ነበር የነገርኳቸው፡፡›› በማለት የሚያስታውሰው ቴዎድሮስ ብዙ ጊዜ በሕይወቱ ስለሚያጋጥሙት መልካምም ይሁን መጥፎ ነገሮች ቀድሞ አንዳች ስሜት እንደሚኖረው ይናገራል፡፡ በዚህም ራሱን ስድስተኛ የስሜት ህዋስ እንዳለው ሰው ይመለከታል፡፡

ከጓደኞቹ ጋር ከሥራ በኋላ አንድ ሁለት ለማለት ተሰየሙ፡፡ የመጀመሪያው ቢራ ተከፈተ ሁለተኛውም ምንም የተገኘ ነገር አልነበረም፡፡ ቴዎድሮስ ግን ዕድለኛ እንደሚሆን ያውቅ እንደነበር ይናገራል፡፡ ሦስተኛው ቢራ ሲከፈት ዕድለኛ መሆኑ ተረጋገጠ፡፡

ምርቶች ላይ የሚደረጉ ዕጣዎች በተለያየ መንገድ ደንበኛ ሊስቡ ይችላሉ፡፡ ለጊዜውም ቢሆን ፍላጐትን ሙሉ በሙሉ ቀይሮ ዕጣ ያለው ምርት ተጠቃሚ በመሆን ዕድለኛ ለመሆን የሚሞክሩ ብዙዎች መሆናቸውን በተለያዩ መዝናኛዎች ከሚታየው፤ ከእንግዶችና ከአስተናጋጆች ሁኔታም መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ምናልባትም በጣም ጥቂት ቢሆኑ እንደ ቴዎድሮስ ያሉ ስሜታቸውን ተከትለው ዕድለኛ ለመሆን ጥቂት ሙከራዎችን ብቻ የሚያደርጉ አይጠፉም፡፡

ማርታ ፍቅሬም እንደ ቴዎድሮስ ሲሸልስ ለመሔድ ዕድለኛ ሆና ነበር፡፡ አምስት ዓመት ከቆየችበት ከዱባይ መጥታ ጥቂት ቀናት ብቻ እንደተቆጠሩ ከቤተሰብ ጋር ለመዝናናት በወጣችበት አጋጣሚ ነበር ዕድለኛ የሆነችው፡፡ በወቅቱ ስለዕጣው የምታውቀው ምንም ነገር ባይኖርም ቤተሰቦቿ ነግረዋት በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ በሚል ዕድሏን እንድትሞክር አደረጉ፡፡ እሷም በጀ ብላ እንዳሏት አድርጋለች፡፡

ማርታ እንደምታስታውሰው ምንም እንኳ ቤተሰቦቿ ለዕጣው ትኩረት በመስጠት እንድትሞክር ግፊት ቢያደርጉም ቆርኪውን መመልከት ላይ ሁሉም ችላ ብለው ነበር፡፡ እያወራች ድንገት ቆርኪዋን ስትልጥ እህቷ ባየችው ምልክት በደስታ ጮኸች፡፡ ዕጣው ምን እንደሚያስገኝ በደንብ ታውቅ ያልነበረው ማርታም ዕድለኛ መሆኗ ስለገባት ብቻ ተደሰተች፡፡ ‹‹ዘንድሮም በደንብ እሞክራለሁኝ ዕድለኛ እንደምሆንም ተስፋ አለኝ›› በማለት ሙከራዋን እንደምትቀጥል ገልጻልናለች፡፡

ምርቶች ላይ የተለያዩ ሽልማቶችን ማድረግ በጊዜአዊነት ለአምራች ኩባንያዎቹ ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል፤ በዘላቂነት ግን የምርት ጥራትን ማሻሻል፣ ዋጋና የመሳሰሉት ነገሮች ላይ መሥራት እንደሚያዋጣ በፋና ኮርፖሬት ከፍተኛ ማርኬቲንግ አናሊስት የሆነችው ዓለም ፀሐይ ተሾመ ትገልጻለች፡፡ ‹‹ዛሬ አንድ ካምፓኒ ለተወሰነ ጊዜ ምርቶቹን የተጠቀሙ ሽልማት የሚያስገኝ ዕጣ እንደሚኖራቸው ይናገራል፡፡ ሰዎች ስሜታዊ ሆነው በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ያን ምርት ይጠቀማሉ፡፡ ነገ ሌላው ኩባንያ ተመሳሳይ ነገር ይዞ ሲመጣ ደግሞ ወደዚያ ይዞራሉ›› ትላለች፡፡

ዓለም ፀሐይ እንደምትለው ሰዎች ጥቅማቸውን ዓይተውና ዕድላቸውን ለመሞከር ሲሉ ምርጫቸውን ሊያጥፉ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን የሚዘልቅ አይደለም፡፡ ይልቁንም እንደ ጥራት፣ ዋጋና አቅርቦት ያሉ ነገሮች ላይ መሥራት ያዋጣል፡፡              

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...