Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየባህልና ቱሪዝም ዘርፍ የተፈተነበት ዓመት

የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ የተፈተነበት ዓመት

ቀን:

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዘንድሮ በአዲስ ሚኒስትርና ሚኒስትር ዴኤታዎች የጀመረውን ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ አንደኛ ዓመት መጠናቀቅ ምክንያት በማድረግ የዓመቱን ክንውኖች እየገመገመ ነው፡፡ በግምገማው በቱሪዝምና ባህል ዘርፍ ስላሉ ልዩ ልዩ ጉዳዮች የተነሳ ሲሆን፣ መነጋገሪያ ከሆኑት መካከል ፓርኮች ላይ ያንዣበበው አደጋና የመልካም አስተዳደር እጦት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከነሐሴ 25 እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2008 ዓ.ም.  በግዮን ሆቴል እየተካሄደ በሚገኘው የምክክር መድረክ ላይ የተገኙ የክልሎች የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች በፓርኮች አያያዝ ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

የዱር እንስሳትና የዕፀዋት ህልውና አደጋ ውስጥ መሆኑን በአጽንኦት ከተናገሩት መካከል የኦሮሚያ፣ የአፋርና የደቡብ ክልል ተወካዮች ይገኙበታል፡፡ ሕገወጥ የሕዝብ ሠፈራን ጨምሮ ፓርኮች ተገቢው ጥበቃ እየተደረገላቸው አለመሆኑ በተደጋጋሚ በባለሙያዎች ቢተችም አሁንም ለውጥ አለመምጣቱ ተገልጿል፡፡ ‹‹የብሔራዊ ፓርኮቻችን ተፈጥሯዊ ይዘት እየተመናመነ ነው፡፡ የዱር እንስሳት አጠቃቀም አዋጅ ማሻሻያ ዝግጅት ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አሁንም ድረስ ተሻሽሎ አለመጽደቁ ክፍተት ፈጥሯል፤›› ያሉት ከኦሮሚያ የተወከሉት አቶ ጨመረ ዘውዴ ናቸው፡፡ 

አገሪቷ በፓርኮች ውስጥ ያላት የተፈጥሮ ሀብት እየተመናመነ በመምጣቱ ደንብና መመርያዎች በአፋጣኝ መተግበር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ፓርኮችን በመጠበቅ ረገድ የክልል ቢሮዎችና ሚኒስቴሩ እየተናበቡ እየሠሩ አለመሆኑንም አክለዋል፡፡ ሐሳባቸውን የተጋሩት ከደቡብ ክልል የተወከሉት ወ/ሮ አልማዝ በየሮ፣ ‹‹በፌዴራል ሥር ያሉት ፓርኮች ወድቀዋል፡፡ በቀጣይ በክልልና በፌዴራል መሠራት ያለበት መለየት ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ፓርኮች በቀጣይ ዓመታት መድረስ ያለባቸው ደረጃ በግልጽ በዕቅድ ተቀምጦ መሠራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የዱር እንስሳትን እየጠበቀ አይደለም በማለትም፣ ፓርኮች ሙሉ በሙሉ ከመጥፋታቸው በፊት አፋጣኝ ዕርምጃ እንዲወሰድ አሳስበዋል፡፡

የአፋር ክልል ተወካዩ አቶ መሐመድ ያዩ፣ በክልልና ፌዴራል አመራሮች መካከል መናበብ አለመኖሩ የሥራ ግጭት እየፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ብዙ ጊዜ ፌዴራል የሚሠራው ከክልል ጋር ይጋጫል፤›› በማለትም ችግሩ እንዲቀረፍ ጠይቀዋል፡፡ የፓርኮች ችግር የምክክር መድረኩ ከመካሄዱም አስቀድሞ በተለያዩ መድረኮች ቢነሳም አንዳች የመፍትሔ አቅጣጫ የተቀመጠ አይመስልም፡፡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተጋረጡባቸው ፓርኮች እስከወዲያኛው ሳይጠፉ በፊት መፍትሔ እንዲበጅ የክልሎች ባህልና ቱሪዝም ተወካዮች ያሳሰቡትም ከጉዳዩ አንገብጋቢነት አንፃር ነበር፡፡ አብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች ችግሩ እስከሚፈታ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ጥያቄ ከማቅረብ ወደ ኋላ እንደማይሉም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ፓርኮች ከሚፈታተኗቸው ችግሮች ውስጥ የመልካም አስተዳደር እጦትም ተነስቷል፡፡ የቱሪዝምና ባህል ጋዜጠኞች ክበብ ተወካዩ አቶ ሔኖክ ሥዩም በጉዳዩ ዙሪያ በሰጠው አስተያየት መሠረት፣ ከፓርኮች አለመጠበቅ ባሻገር የመልካም አስተዳደር እጦትም ችግሩን አባብሶታል፡፡ የፓርኮች ውስጣዊ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲቀረፍም ጠይቋል፡፡ ይህ ችግር የሚታየው በፓርኮች አስተዳደር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የባህልና ቱሪዝም ዘርፎች እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ነሐሴ 25 ቀን 2008 ዓ.ም. የዘንድሮው የዘርፉ እንቅስቃሴ ሪፖርት በአቶ ወርቅነህ አክሊሉ ሲቀርብ፣ በሪፖርቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በየክልሉ የተያዙት ዕቅዶች ከሞላ ጎደል እንደተሳኩ ቢጠቀስም፣ የውይይቱ ተሳታፊዎች ግን አሁንም የመልካም አስተዳደር እጦት የዘርፉ ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የመልካም አስተዳደር እጦትን ለመቅረፍ የችግሩ መንስዔዎች ተለይተው የመፍትሔ አቅጣጫዎች በቀጣይ ዓመት ዕቅድ መካተት እንዳለባቸው የተናገሩ ነበሩ፡፡ ‹‹በሪፖርቱ ዘንድሮ የመልካም አስተዳደር እጦትን በመቅረፍ ረገድ ከ70 እስከ 100 ፐርሰንት በዕቅዳቸው መሠረት የሠሩ ክልሎች እንዳሉ ተገልጿል፡፡ እውነት ይኼ በተግባር ታይቷል?›› ሲሉ የጠየቁ ተሳታፊዎችም ነበሩ፡፡ በሪፖርቱ ላይ እንደተገለጸው፣ ችግሩ አሁንም ሙሉ በሙሉ ባይቀረፍም ጥሩ ጅማሮዎች አሉ፡፡ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ዘርፉ ብዙ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል፡፡

በውይይቱ የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ልማት ጉዳይም ተነስቷል፡፡ የመዳረሻ አካባቢዎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታና በዘርፉ ያለው የሰው ኃይል አቅርቦት ውስንነትም ተጠቅሷል፡፡ በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ካሉ ባለሙያዎች 23 በመቶው ብቻ በዘርፉ የሠለጠኑ መሆናቸውን በውይይቱ የቀረበው ሪፖርት የሚያመላክት ሲሆን፣ ዘርፉ በበለጠ የባለሙያዎች ተሳትፎ እንደሚያሻው ተመልክቷል፡፡

 የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረጻዲቅ ሐጎስ፣ የሰው ኃይል ችግር መኖሩ በዘርፉ አዳዲስ ተቋሞች ሲከፈቱ ዘርፉን የሚቀላቀሉ አዳዲስ ባለሙያዎች ስለሌሉ ቀድሞ ከነበሩት ተቋሞች ባለሙያ እንዲቀማው ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ከተቋሞች በባህልና ቱሪዝም ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ቁጥር ቢጨምርም በዘርፉ የሚፈለገውን ያህል አልሆነም፡፡ በተያያዥም በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች የቱሪስቶችን ቆይታ ሊያራዝሙ የሚችሉ ነገሮች በስፋት እንደማይታዩ ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው የተቋቋሙ ድርጅቶችም ትችት ተሰንዝሮባቸዋል፡፡ ከተተቹ ድርጅቶች አንዱ በአገሪቱ ያሉ የባህልና ቱሪዝም ሀብቶችን በማስተዋወቅ ጎብኚዎች የመሳብ ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ሲሆን፣ ድርጅቱ ሥራውን በአግባቡ እያከናወነ እንዳልሆነ አስተያየት የሰነዘሩ ነበሩ፡፡ ድርጅቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ጉልህ አስተዋጽኦ ሲያበረክት አለመታየቱን የገለጹ የክልል ተወካዮች፣ ድርጅቱ ከክልሎች ጋር በመሥራት ረገድም ክፍተት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ይሠራቸዋል በሚል ብዙ አስፈላጊ ክንውኖች በክልል የቱሪዝም ቢሮዎች እየተካሄዱ አለመሆኑም ተመልክቷል፡፡ ‹‹የቱሪዝም ድርጅቱ ከተቋቋመ በኋላ ዘርፉን ከመለወጥ ይልቅ ብዙ ነገሮች ወደ ኋላ የተመሰሉ ይመስላል፤›› በማለት የተናገሩ ነበሩ፡፡ ተመሳሳይ ጥያቄ የተነሳው በቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ላይ ነው፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኖችና የባህልና ቱሪዝም ባለሙዎች የሚገኙበት ምክር ቤቱ በዘርፉ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በግልጽ እንዲታወቅ ተጠይቋል፡፡

በውይይቱ የተነሱ ጉዳዮች በርካታ ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔራዊ ሙዚየም አለመኖሩም ጥያቄ አስነስቷል፡፡ አገሪቷን የሚወክል ሙዚየም ያለመኖሩን ጉዳይ ካነሱ  መካከል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ ይገኙበታል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ያስፈልጋታል የሚለው ጥያቄ የኛም ጭምር ነው፤›› ሲሉ ከሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ጋር ተስማምተዋል፡፡ የአገሪቱ ብሔራዊ ሙዚየም የማጣት ጉዳይ ከውይይቱ ተካፋዮች በተጨማሪ የብዙዎች መነጋገሪያ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡

በውይይቱ የተነሱት ጥያቄዎች የሚመለከቷቸው ቢሮዎች አብዛኞቹን ቅሬታዎች ተቀብለው፣ ለጥያቄዎቹ መልስ ሰጥተዋል፡፡ ከዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን በተሰጠው ምላሽ፣ የፓርኮች ህልውና ላይ የተነሱ ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ተፈጥሯዊ ሀብቱን በመጠበቅና የመልካም አስተዳደር እጦትን በመቅረፍ ረገድም ባለሥልጣኑ የተቻለውን እየሠራ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ከክልሎች ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት ረገድ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትን በተመለከተ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሰለሞን ታደሰ፣ አገሪቱን አስተዋውቆ ቱሪስቶችን ለመሳብ ያወጧቸውን ዕቅዶች በቅርቡ ለክልሎች እንደሚያካፍሉ ገልጸዋል፡፡ በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በመሳተፍ አስጎብኚዎች ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ በማድረግ ረገድ ድርጅቱ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በበኩላቸው፣ ከባህልና ቱሪዝሙ ዕቅዶች ዘንድሮ ግብ የመቱና ክፍተት የታየባቸው ዘርፎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦትና ኪራይ ሰብሳቢነት በዘርፉ ክፍተት መፍጠራቸውን ተናግረው፣ ችግሮቹን ለመቅረፍ ባደረጉት ጥረት የተሻለ ተሞክሮ ያላቸው ክልሎች እንዳሉና የተቀሩት ክልሎችም እንደየአካባቢያቸው ሁኔታ መፍትሔ እንደሚሰጡ አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሯ በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ያሉ ችግሮችን በተመለከተ በየክልሉ የተሠሩ ጥናቶች እንዳሉና ጥናቶቹን የተመረኮዘ አዋጅ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ችግሮቹ ተጠንተው አገራዊ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ ከሚመለከታቸው አካሎች ጋር ተስማምተናል፡፡ ችግሩ ለዘለቄታው እንዲፈታ ያዘጋጀነው አዋጅ ዘንድሮ ከምናጸድቃቸው አዋጆች አንዱ ነው፤›› ብለዋል፡፡  በዘርፉ ያለውን የተማረ የሰው ኃይል ችግር ለመቅረፍ፣ አጫጭር ሥልጠናዎች ከመስጠት በተጨማሪ ችግሩን የሚቀርፍ ፍኖተ ካርታ እንደተዘጋጀም ሚኒስትሯ አክለዋል፡፡

በሚኒስትሯ ገለጻ፣ በዓመቱ በባህልና ቱሪዝም 3.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ለዘርፉ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ዘንድሮ የአክሱም ሐውልት አስመላሽ ኮሚቴ መሸለሙና የሉሲ ቅሬተ አካል በተገኘበት አካባቢ ሙዚየም ለመገንባት የተጀመረው እንቅስቃሴም መልካም ውጤት ነው፡፡ በሚቀጥለው ዓመት የባህልና ቱሪዝሙ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የሚሆነው አዲሱን የቱሪዝም መለዮ ‹‹ላንድ ኦፍ ኦሪጅንስ›› ማስተዋወቅ ይሆናል ብለዋል፡፡

‹‹በ2009 ዓ.ም. በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ከተቀመጡ የትኩረት አቅጣጫዎች በተጨማሪ ዋነኛ ሥራችን ብራንዱን በአገር ውስጥና በውጭ ማስተዋወቅ ነው፡፡ ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም፣ የባህል እሴቶችን በማልማት፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን በመሸጥ፣ የኪነ ጥበብ ሥራዎች እንዲታዩ በማድረግ እንሠራለን፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...