Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹የማይነበብ››

‹‹የማይነበብ››

ቀን:

በፍቅርተ ተሾመ

አገሮች እንደደረሱበት ዕድገትና እንደየማኅበረሰቡ አኗኗር የመግባቢያም ይሁን የመረጃ መለዋወጫ መንገዳቸው ይለያያል፡፡ በየጊዜው የሚመጡትን አዳዲስ ግንኙነት መፍጠሪያ ቴክኖሎጂዎች ለመቀበል፣ ለመላመድ፣ በአግባቡ ለመጠቀምና ለውጥን ቶሎ ለመቀበል ያላቸው አዝማሚያም እንደቀድሞ ልማዳቸው ይወሰናል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ከግላዊ አኗኗር ይልቅ አኗኗራቸውን ማኅበራዊ ያደረጉ ማኅበረሰቦች በቃል ግንኙነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ሆኖም ከቃል ግንኙነት ባለፈም መረጃዎች በየመሥሪያ ቤት ሰሌዳዎች፣ በማስታወቂያ ቦርዶች ይለጠፋሉ፣ በጋዜጣ ይወጣሉ፡፡ በየመንገዱም መረጃ የያዙ በራሪ ወረቀቶች ይበተናሉ፡፡ ከዚህም አልፎ መረጃዎች በእጅ ስልክ ይመጣሉ፡፡ ታዲያ ሰዎች ይህንን እንዴት ይቀበሉታል? መረጃን ያነባሉ ወይስ ሰው እስኪነግራቸው ይጠብቃሉ?

ልማዳችን በቃል ንግግር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በማኅበረሰቡ ግንኙነቶች ውስጥም የቃል ግንኙነት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፣ የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል የሥነ ተግባቦት መምህር ዳግም አፈወርቅ ናቸው፡፡ ሰዎች በቃል መረጃ ላይ ጥገኛ ከመሆናቸው የተነሳም ያነበቡትን መረጃ የሚያምኑት ከሌላ ሰው ሰምተው ካረጋገጡ በኋላ ነው ይላሉ፡፡

የሕንፃዎችን መረጃ ማለትም የቢሮ ቁጥሮችንና አገልግሎቶችን፣ ካፌዎችን እንዲሁም የተለያዩ መረጃዎችን የያዙ አቅጣጫ ጠቋሚዎች ባሉባቸው ሕንፃዎች ላይ፣ መረጃውን ከማንበብ ይልቅ ሰዎችን ሲጠይቁ ይስተዋላሉ፡፡

በአንድ ሕንፃ ላይ በጥበቃነት የሚሠሩት አቶ ፈቃዱ ዘመድኩንም፣ ‹‹ከመሥሪያ ቤቱ ጠቋሚ ማስታወቂያ ጎን ቆሜ የሚገባውን ስፈትሽ፣ አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ ሰዎች ማስታወቂያውን ከማንበብ ይልቅ ቢሮዎች የት እንደሚገኙ የሚጠይቁት እኔን ነው›› ይላሉ፡፡

ከተለጠፉ ማስታወቂያዎችም ባሻገር ምግብ ቤቶች ለመስተናገድ የሚገቡ፣ የምግቡን ዓይነትና ዋጋ በዝርዝር የሚገልጽ ማውጫን ከማንበብ ይልቅ አስተናጋጆች መጠየቅ እንደሚመርጡ የተለያዩ አስተናጋጆች ይናገራሉ፡፡

‹‹አብዛኛው ተገልጋይ የቀረበውን የምግብ ዝርዝር ከማንበብና ከማዘዝ ይልቅ በመጠየቅ የሚስተናገድ ነው›› የምትለው በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ በተቆጣጣሪነት የምትሠራው ሰብለ ለማ ነች፡፡ ሰዎች ስለ ምግቦች ዓይነት ከተጻፈላቸው ይልቅ አስተናጋጆች እንዲነግሯቸው የሚፈልጉትን ያህል፣ አስተናጋጆች አሟልተው ሊነግሯቸው ባይችሉም፣ መረጃ መስጠቱን በአስተናጋጆች ላይ የሚጥሉ ቀላል አይደሉም፡፡ ሰብለ እንደምትለው፣ የምግብ ዓይነቶች በቃል ከተዘረዘሩላቸው በኋላ የሚያስደግሙ፣ የሚሰጣቸው መረጃ የወረቀቱን ያህል የተሟላ ባለመሆኑም በሚፈጠሩ ክፍተቶች የሚቆጡና የሚናደዱ አሉ፡፡  የምግብ ማውጫን ካለማንበብ ጋር ተያይዞ በክፍያ ላይ የሚጣሉም በተደጋጋሚ እንደሚገጥማቸው ትናገራለች፡፡

መረጃ ማንበብ የጎላ ጠቀሜታ ቢኖረውም፣ በየመንገዱና ታክሲ ላይ የሚሠራጬ መረጃዎች አንዳንዶችን ሲያሰለቹ ይታያሉ፡፡ ማስታወቂያዎችን ተቀብለው ምን እንደሚል ሳያዩ የሚጥሉ፣ አልቀበልም ብለው የሚያልፉ፣ ኮስተር ብለው ዞርበል የሚሉትን ማየትም የተለመደ ነው፡፡ በመንገድ ላይ የሚበተኑ እና የሚለጠፉ አጫጭር የጽሑፍ ማስታወቂያዎችን ምንነት ለመረዳትም እምብዛም ፍላጎቱ አይታይም፡፡

የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ርብቃ ገብረ ማርያም፣ ማስታወቂያዎች አይመለከቱኝም ብላ ስለምታስብ አታነብም፡፡ ስለምን እንደሆነ ማወቅ ስትፈልግም ሰዎችን እንደምትጠይቅ ትናገራለች፡፡  

በመንገድ ላይ ቆመው ወረቀቶችን የሚበትኑ ሰዎች ብዙ ጊዜ ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች አንዱ የሚቀበሏቸው ሰዎች ጥቂት መሆን ነው፡፡ ቢቀበሉትም እንኳን ሳያዩት እና ሳያነቡት እዚያው እንደሚጥሉትም ይገልጻሉ፡፡

የቋንቋ እና ኮምፒውተር ትምህርት ቤት ባለቤት የሆኑት አቶ ማይክ አያሌው፣ እንደዚህ ያሉ ተግዳሮቶች ማጋጠማቸው የተለመደ እንደሆነ ገልጸው፣ ዓላማቸውም ማስተዋወቅ እንደመሆኑ፣ ርዕሱን ካዩት በቂ መሆኑን፣ የሚመጡትም ሆነ ሙሉ መረጃውን የሚያነቡት የሚፈልጉት ብቻ በመሆናቸው ይናገራሉ፡፡

ጉዳዩ ከማንበብ ባህልና ፍላጐት ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣ ጥሩ የማንበብ ባህል ያላቸውና የተማሩ ናቸው የሚባሉትም ማስታወቂያዎችን ያነባሉ ለማለት ያስቸግራል፡፡ አቶ ዳግም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ከሚያጋጥሟቸው ክስተቶች በመነሳት ይህንን የሚገልጹት የተማረውን የማይጠቀምበት ብለው ነው፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ የሚያነሱት የሥነ ተግባቦት ትምህርት በሚሰጥበት ትምህርት ቤት ውስጥ፣ ተማሪዎችም ይሁኑ መምህራን የተለጠፉ ማስታወቂያዎችን ባለማየታቸው የሚስተጓጎሉ ሥራዎች፣ የሚያመልጡ ፈተናዎች እና ማስጠንቀቂያዎች መኖራቸውን ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነችው ቤተልሄም ሲሳይ፣ ‹‹የፈተና ፕሮግራም የማንበብ ልምድ ስለሌለኝ ሰዎች የነገሩኝን የተዛባ መረጃ ሰምቼ ያልተዘጋጀሁበትን ፈተና ወስጃለሁ፤›› በማለት ያጋጠማትን ታስታውሳለች፡፡

በጋዜጣዎች ላይ የሚወጡ የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎች፣ የፍርድ ቤት ጥሪዎች እና የሥራ ማስታወቂያዎችን ባለመመልከታቸው ከጉዳያቸው የሚስተጓጐሉም አሉ፡፡

ሙሴ መለሰ ከተመረቀ ዓመት ሆኖታል፡፡ ካመለከታቸው ክፍት የሥራ ዕድሎች አንዱን ያጣው ያመለከተበት መሥሪያ ቤት ስም ሲለጥፍ ባለመከታተሉ ነው፡፡ ይህም የሆነው የስልክ ጥሪ ሲጠብቅ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በተለጠፈ ማስታወቂያ ብቻ ይጠራሉ የሚል ግምት እንዳልነበረው፣ ካለው ልምድም የሚያውቀው በስልክ ሲጠራ እንደሆነ የሚናገረው ሙሴ፣ ነገሮች ለእሱ አዲስ እንደሆኑበት ይናገራል፡፡

የተለጠፉ፣ የተበተኑ ወይም በጋዜጣ የወጡ መረጃዎችን የማያነቡ፣ ለማየት ፍላጎቱ የሌላቸው ቢኖሩም፣ ጠቃሚ መረጃዎችን ለማግኘት ሲሉ ጋዜጣዎችን የሚያገላብጡ፣ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን የሚያነቡም አሉ፡፡

መረጃዎች በተለያየ መንገድ የሚበተኑትን ያህል ጊዜ አልፎባቸውም ሳይነሱ የሚቆዩም አሉ፡፡ አንድ ቢሮ በስብሰባ ምክንያት ለግማሽ ቀን ዝግ መሆኑን በማስታወቂያ ሰሌዳ ለጥፎ፣ ጉዳዩ ሲያልቅ የማያነሳበት፣ ለተወሰነ ጊዜ የተለጠፈ መረጃ ለዓመታት የሚቆዩበት ጊዜም አለ፡፡

‹‹ይነበብ›› እና ‹‹ማስታወቂያ›› የሚሉ በየቦታው የሚለጠፉ አሊያም በጋዜጣ የሚያወጡ ወይም በአዟሪዎች የሚያስበተኑ ድርጅቶችም መረጃዎቹ ትኩረት ማጣታቸው በማሰብ፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ‹‹የማይነበብ›› የሚል ርዕስ ሰጥተው መረጃዎችን መልቀቅ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...