Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክስለ ችሎት አመራር አንዳንድ ነጥቦች

ስለ ችሎት አመራር አንዳንድ ነጥቦች

ቀን:

በዮሴፍ አዕምሮ

በኢትዮጵያ የሕግና ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት አንድ ዓይነት የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት ፍርድ ቤቶች የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ በአገሪቱ ሕገ መንግሥትና ሌሎች ሕጎች የተመለከቱ ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ፣ ሕጋዊ ውሎች እንዲከበሩ፣ የንብረት መብቶች እንዳይጣሱ የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ እነዚህን የዜጎች መሠረታዊ መብቶች በዳኝነት ሲመለከቱ ደግሞ ሕጉን በእኩልነት ተግባራዊ ማድረግ፣ በነፃነት መሥራት፣ ውሳኔያቸውን በተቻለ ፍጥነትና ወጥነት ባለው መልኩ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የማንኛውም መንግሥታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ዓላማ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት በመስጠት የሕዝብ አመኔታ ማትረፍ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶችም የሕዝብ አመኔታ ለማትረፍ በእኩልነት፣ በነፃነትና በሕግ መሠረት ፍትሕ መስጠት አለባቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች በሕግ መሠረት ውሳኔ መስጠት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ውሳኔ ላይ የሚደርሱበት ሒደትም ፍትሐዊ መሆን ይገባዋል፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚባለው የፍትሕ ሥራ የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው አይደለም፡፡ ውሳኔ የተሰጠበት ሒደት ራሱ የሕዝብ አመኔታ ለማትረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ስለዚህ ሒደቱ ራሱ ቀልጣፋና የተከራካሪዎችን ሰብዓዊ መብት የሚያከብር መሆን አለበት፡፡

የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ የሚሰጡት የሥነ ሥርዓት ሕጎችን ተከትለው በመሠረታዊ ሕጎች /Substantive Laws/ ነው፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጎች በራሳቸው ግብ አይደሉም፡፡ ዋናው ግብ ተከራካሪዎች ያነሷቸውን ክርክሮች ከመሠረታዊ ሕግ አንፃር ተመልክተው መብትና ግዴታቸውን መወሰን ነው፡፡ የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማ፣ ፍርድ ቤቶች በውሳኔ መስጠት ሒደት መከተል የነበረባቸውን ግን የተዘነጉ የችሎት አመራር ሥርዓቶችን መመርመር ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ፍርድ ቤቶች በአብዛኛው በዕረፍት ላይ ስለሆኑ፣ ባለፈው የሥራ ዘመን ያጋጠሙ ጉድለቶችን በማስተካከል በሚቀጥለው የሥራ ዘመን የተሻለ አፈጻጸም እንደሚያሳዩ እምነቴ ነው፡፡ የዚህ ጸሐፊ ዓላማም በችሎት አመራር ሥርዓት ላይ የተመለከትኳቸውን ጉድለቶች ማመላከት ነው፡፡

የችሎት አመርራርን በተመለከተ በተለይ የወጣ ሕግ ወይም ደንብ የለም፡፡ በእርግጥ አንድ ዳኛ የወንጀልም ሆነ የፍትሐ ብሔር ጉዳችን የሚመራው በሥነ ሥርዓት ሕጎች መሠረት ነው፡፡ የችሎት አመራር ግን በሥነ ሥርዓት ሕጎች ከተደነገጉት ደንቦች በላይ በርካታ ነገሮችን ግምት ውስጥ ያስገባል፡፡ የችሎት አመራር የተከራካሪዎችን ማንነት ሥነ ልቦና፣ ባህል የተገነዘበ መሆን ይኖርበታል፡፡ የአገራችን ታሪክ ለዳኝነት ሥራ ከፍተኛ ቦታ ይሰጣል፡፡ ይህ ሁኔታም በጽሑፍና በቃል ሲገለጽ የኖረ ነው፡፡ በ1444 ዓ.ም. በአፄ ዘርዓያቆብ በሥራ ላይ በዋለው ፍትሐ ነገሥትም ስለ ዳኛና ዳኝነት በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ የተወሰኑት ከዳኛ ሥነ ምግባርና ዳኝነት አሰጣጥ ጋር የተያያዙት ደንቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡

 • የዳኛ መሾምስ በሕግና በፍጥረት ፍፃሜ የተገባ ነው፡፡ …በሰዎች መካከል የቀና ፍርድ ይፈርዱ ዘንድ ለራሳችሁ ዳኞችን ሹሙ፡፡ በፍርድ ጊዜ የሚያዳሉ፣ ፊት አይተው መማለጃ (ጉቦ) የማይቀበሉ፣ መማለጃ እውነትን እንዳያዩ የብልሆችን ዓይን ያሳውራልና፡፡ የቀናውንም ፍርድ ይለውጣልና፡፡
 • በተጣሉ ሰዎች መካከል ለብርቱና ለደካማ ለአዋቂና ላላዋቂም ቅን ለመሥራት እንደሚገባ የሚፈርድ ዳኛ ከሌለ በመልካም አይፈፀምም፡፡
 • ዳኞችና ምስክሮች ቅን ሥራ መሥራት ይገባዋቸል፡፡ መጀመሪያ ግን የታመነ፣ ብልህ፣ ከመነቀፍ የራቀ፣ ከነውር የዳነ፣ ለምሕረትና ለመውደድ ዝግ ያለ፣ በቁጣ ጊዜ የሚታገስ፣ እንግዚአብሔርን የሚፈራ፣ በዓለሙ ውስጥ እምነቱ የቀና ይሆን ዘንድ ይገባል፡፡ ፊት አይቶ ከማድላት የራቀ ይሁን፡፡ ፀጥታንና ትዕግሥትን ገንዘብ ያደረገውን ሰው አይናቁት፡፡ ነፃነት ያለው ይሁን፡፡ ራሱን ለማስተዳደር ሥልጣን ያለው ያልሆነ ሰው ሌሎችን ሊያስተዳድር አይቻለውምና፣ ዳኛ ሕግን የሥሩንና የጫፉንም የዳኝነት ፍርድ የሚያውቅ ይሁን፡፡
 • እውነተኛ ፍርድ ፍረዱ እንጅ በአድልዖ አትፍረዱ፣ በፍርድ ጊዜ ለባለፀጋ ፊት አታድላ፣ ለድሃውም አትዘንለት፣ በፍርድ ውስጥ ምሕረት የለምና፡፡
 • ዳኛ ፀጥ ያለ የማይታበይ ይሆን ዘንድ ይገባዋል፡፡ አሳቡን የሚለውጥ ነገር እያለበት አይፍረድ፡፡ ይኸውም እንደሚያውኩ፣ እንደ ቁጣና እንደ ፍርኃት፣ እንደሚያዘነጉ እንደ ሐዘንና እንደ ደስታ፣ እንደሚነኩ እንደ ረሃብና እንደ መጠማት፣ እንደሚያሳምሙ እንደ ደዌና እንደ ሕመም፣ ድል እንደሚነሱ እንደ እንቅልፍና እንደ ሽልብታ፣ እንደሚያሳዝኑ እንደ ስንፍናና እንደ ድካም ያሉ ናቸው፡፡ በስካርና በመቅለል፣ ፍርድን ከመፍረድ ብዛት የተነሳም በመሰልቸት አይፍረድ፡፡ ለዕረፍትና ፈቃድን ለመፈፀም በተወሰነ ጊዜ ካልሆነም በቀር ሊሰወር (ከሥራ ቦታው) አይገባውም፡፡  
 • የተጣሉ ሰዎች ወደ እርሱ ከመጡ ጀማሪ በሆነው (መጀመሪያ በመጣው) በፊተኛው ሰው ይጀምር፡፡ ኋለኛውን ከብዙዎቹ ያለ ምክንያት አያስቀድመው፣ ከተከራካሪዎች ከአንዱ ጋር ብቻ አያሾክሹክ (ቆይታ አያድርግ)፡፡ የተጣሉት ከተከራከሩ በኋላ ጽኑ ችግር ካልሆነ በቀር ፍርድ መስጠትን ወደኋላ አይበል፡፡
 • ለራሱ፣ ከወላጆቹም ለአንደኛው ወይም ለአያቱ፣ ለልጆቹ፣ ለልጅ ልጆቹም ወይም ለወንድሞቹ ለሚስቱም ከሌሎች ጋር አይፍረድ፡፡
 • በክርክር ጊዜ የመሃላ ቃል ያስፈልጋል፣ ተከራካሪ በሐሰት ስለመማሉ ዳኛ ይቅጣው፣ መሃላም በእግዚአብሔር በነገሮቹና በወገኖቹ ካልሆነ በቀር አይገባም፡፡
 • ብርድና ሐሩር፣ ክፉ ሽታም ከማያገኛቸው ንፁህና ጥሩ መቀመጫ ለዳኞች ሊዘጋጅ ይገባል፡፡ ጠብና ጩኸት በውስጡ ሊሆን አይገባም፡፡
 • ስለ ፍርዳችሁ ከሰኞ ጀምሮ ይሁን፣ እስከ ቅዳሜ ድረስ የተጣሉ ሰዎችን ነገር ከሰማችሁ በኋላ በመካከላቸው በእውነትና በቅን ፍረዱ፣ ባለጋራው ሳይመጣ በአንዱ ባለጋራ ቃል አትፍረዱ፣ ሁለቱ ተከራካሪዎች በተገናኙ ጊዜ በመካከላቸው በቅን ፍረዱ እንጂ፡፡
 • የማስረጃ ምስክር ማምጣት ለከሳሽ እንደሆነ እወቅ፣ መሃላ ግን ለሚክድ ነው፡፡
 • ሁለቱ ተከራካሪዎች ለመፋረድ ከቀረቡ ዳኛው በሉ ተናገሩ ይበላቸው፡፡ እነርሱም እስኪናገሩ ድረስ ዝም ይበል፡፡ ከእነርሱም እያንዳንዱ ቢካሰሱ አስቀድሞ የከሰሰው ይቅደም፡፡ (ከሳሽ) የጠቡን ነገር ከፈፀመ በኋላ የሌላውን (የተከሳሽን) ክርክር ይስሙ፡፡ አንዱ ሌላውን በነገር ቢነካው ወይም ክፉ ቃል ቢናገር ይከልክለው፣ ቢደግምም ይቅጣው፡፡

እነዚህ ጥንታዊ ደንቦች በአብዛኛው በአሁኑ ጊዜ ባሉን የሥነ ሥርዓት ሕጎችንና በዳኞች የሥነ ምግባር ደንብ ላይ ተካተው ይገኛሉ፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኞች የሥነ ምግባር ደንብም ዳኞች በችሎት አመራር ሒደት ተግባራዊ ማድረግ የሚገባቸውን ዘርዝሯል፡፡ ይኸውም፣

 1. ሕጎችን በትክክል ሥራ ላይ ማዋል፣
 2. የባለጉዳዮችን መብት በእኩልነት መጠበቅ፣
 3. ትጋትና ጥረት ማሳየት፣
 4. ቀጠሮ አለማብዛት፣
 5. የፍርድ ቤቱን ክብር መጠበቅ፣
 6. ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ተግባብቶ መሥራት፣
 7. በትዕግሥት ማዳመጥና ነገርን ማስጨረስ፣
 8. ተከራካሪዎችን መቆጣጠር፣
 9. ጭብጥ ለይቶ በማስረጃና በሕግ መሠረት ፍርድ መስጠት፣
 10.  የልዩነት ሐሳብን በተቻለ ፍጥነትና በጨዋነት መስጠት፣
 11.  የችሎት ሠራተኞችን የሥራ አፈፃፀምና ሥነ ምግባር በአግባቡ መቆጣጠር፣
 12.  የፍርድ ቤት መዛግብትን ከፀያፍ፣ አስነዋሪ ቃላትና አስተያየት ነፃ ማድረግ፣
 13.  አቤቱታዎች/ክስ፣ መልስ፣ ይግባኝ/በአግባቡ ተዘጋጅተው የቀረቡ መሆናቸውን መቆጣጠር፣
 14.  አስተዋይና በአሠራር ጥንቁቅ መሆን፣
 15.  በአለባበሱ፣ በጠባዩ፣ በአድራጎቱ መጥፎ አካባቢዎችን በማዘውተር የዳኝነት ክብሩን እንዳያዋርድ ጨዋ መሆን፣
 16.  ከንቱ ውዳሴን አለመሻትና በሕግ መሠረት ብቻ መሥራት፣
 17.  የሥራ ሰዓትን ማክበር፣
 18.  በውሳኔ ያላላቁ ጉዳዮችን ሚስጥራዊነት መጠበቅ፣
 19.  ጉዳዩን ለማየት የማያስችል ሁኔታ ካለ ከችሎት መነሳት፣
 20.  መደለያ አለመቀበል፣
 21.  በአማላጅ አለመሥራት፣
 22.  የዳኝነት ሥልጣንን ለግል ጥቅም አለማዋልና
 23.  የዳኝነት ሥራን ከግል ጥቅም ጋር አለማጋጨት ናቸው፡፡

በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 79(3) ላይም፣ ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነፃነት እንደሚያከናውኑና ከሕግ በስተቀር በሌላ ሁኔታ እንደማይመሩ ተደንግጓል፡፡ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 26 እና 27 ላይ ዳኞች በግልጽ ችሎት ማስቻል እንዳለባቸውና ጉዳዩን ለማየት የማያስችላቸው ሁኔታ ካለ ከችሎት መነሳት እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች መረዳት የሚቻለው የዳኝነት ተግባር በነፃነት በተጠያቂነትና ክብርን በጠበቀ መልኩ መከናወን እንዳለበት ነው፡፡

ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሥነ ሥርዓት ሕጎችና በሥነ ምግባር ደንቦች መሠረት ማካሄድ የሚገባቸው ሲሆን፣ ችሎት በሚመሩበት ጊዜ ግን በሕግ ያልተደነገጉ ጉዳዮችም ያጋጥሟቸዋል፡፡ የተለያዩ አገር ፍርድ ቤቶች የችሎት አመራርን በተመለከተ መመርያዎችን ያወጣሉ፡፡ እነዚህም መመርያዎች (Rules of Court Decorum, Court Room Etiquette or Judicial Bench Book) እያሉ ይጠሯቸዋል፡፡ እነዚህ መመርያዎች በችሎቱ ውስጥ የሚደረጉና የተከለከሉ ሁኔታዎች፣ የጠበቆችን ባህሪ፣ የችሎቱ ሥነ ሥርዓት አስከባሪ ባህሪ፣ ዳኛው የሚጠሩበትን ሁኔታ፣ የችሎቱ ታዳሚዎች አለባበስን በተመለከተ በዝርዝር ይዘዋል፡፡ (ለምሳሌ United States District Court of Illinois Court Decorum, Murphy Municipal Court Rules of Court Decorum, New Holstein Court Room Etiquette, South Carolina Judicial Bench Book መመልከት ይቻላል፡፡

በእኛም አገር ተግባራዊነቱ ምን ያህል እንደሆነ ባይታወቅም፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች የችሎት አሠራርና የሥነ ምግባር መመርያ ወጥቷል፡፡ መመርያው በሌሎች ሕጎችና የሥነ ምግባር ደንቡ የተካተቱ ሁኔታዎችን የያዘ ቢሆንም፣ ሌሎች ለየት ያሉ ዝርዝር ጉዳዮችንም ይዟል፡፡ ይህ የችሎት አሠራር መመርያ ከያዛቸው ነገሮች መካከል የሚከተሉት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

 1. በግልጽ ችሎት ማስቻል፣
 2. የተከራካሪዎችን የመሰማት መብት ማስከበር፣
 3. እያንዳንዱ ችሎት የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ በዚሁ መሠረት እንዲፈጽም፣ ለቃል ክርክር ጊዜ ወስኖ መስጠት፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በጊዜ እንዲመራ ማድረግ፣
 4. የሥራ ሰዓት በማክበር በሥራ ቦታ ላይ መገኘት፣
 5. ባለጉዳዮችን ማክበር፣
 6. ጉዳዮችን በገለልተኝነት ማስተናገድ፣
 7. ጉዳዮችን በተቻለ ፍጥነት መወሰን፣
 8. የችሎት መድፈር ሥልጣንን በተመለከተ በአግባቡ መጠቀም፣
 9. የፍርድ ቤቱን ክብር ማስከበርና ማክበር፣
 10.  ዓቃቤ ሕግን፣ ነገረ ፈጆችንና ጠበቆችን እንደ ሥራ አጋር መገንዘብ፣
 11.  ዳኞች በችሎት ላይ ከጉዳዩ ጋር ተዛማጅነት የሌላቸው ትችቶችንና ሐሳቦችን ከመሰንዘር መቆጠብ፣
 12.  በቀጠሮው ሰዓት ተገኝቶ ማስቻል፣
 13.  ችሎት ሲገቡ ሰላምታ መስጠት፣
 14.  ባለጉዳዮችን በአንቱታ ማነጋገር፣ ባለጉዳዮችን ባላቸው ማዕረግና ክብር መጥራት፣
 15.  ችሎቱን ለማገዝ የመጡ ምስክሮችን፣ ኤክስፐርቶችን ማመስገን፣
 16.  ለቃል ክርክር ተራው ያልሆነው ባለጉዳዩ እንዲቀመጥ ማድረግ፣
 17.  ባለጉዳዮችን በእኩል ዓይን ማየት፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻቸውን ማክበር፣
 18.  በቀጠሮ ቀን ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ ካልደረሰ ምክንያቱን ገልጾ ይቅርታ መጠየቅ፣
 19.  መዝገቦች ተመርምረው ያላለቁ ከሆነ፣ ይህንኑ ተናግሮ ባለጉዳዮችን በጊዜ መሸኘት፣
 20.  የወንጀል ይግባኝ በሁለት ቀጠሮ፣ የፍትሐ ብሔር ይግባኝ ያስቀርባል ከተባለ በሦስት ቀጠሮዎች፣ የሰበር ያስቀርባል/አያስቀርብም በመጀመሪያው ቀጠሮ፣ ያስቀርባል የተባለ የሰበር መዝገብ በሁለተኛው ቀጠሮ ውሳኔ መስጠት፣
 21.  የመዛግብት አወሳሰንም በተመለከተ የእስረኛ መዝገብ፣ ዕግድ ያለባቸውን የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች፣ የሥራ ክርክር ጉዳዮች፣ ከክልል የሚመጡ ጉዳዮችና ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ መዛግብት ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው መመርያው ይገልጻል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በችሎት የተፈቀዱና የተከለከሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል፡፡ ኮፍያ ማድረግ፣ መነፅር ማድረግ፣ እግር ማነባበር፣ ዣንጥላ መያዝ፣ ካፖርት ወይም ጋቢ መልበስ የተፈቀዱ ናቸው፡፡ ሞባይል ስልክ ማነጋገር፣ ሲጋራ ማጨስ፣ በድምፅ (በምልክት) ወይም በሌላ ተመሳሳይ መንገድ መረበሽ፣ መብላት፣ መጠጣት፣ መተኛት፣ የጦር መሣሪያ መያዝ፣ ጫት መቃም፣ ማስቲካ ማኘክ፣ ያለፈቃድ ካሜራ ወይም መቅረጽ ድምፅ ይዞ መግባት የተከለከሉ ናቸው፡፡ ከፍርድ ቤቱ አስተዳደርና ሬጅስትራር ጽሕፈት ቤት የሚጠበቁ ተግባራትንም መመርያው አካቷል፡፡

የመመርያው መውጣትና በሥራ ላይ መዋሉ ተገቢና የሚመሰገን ሲሆን፣ የመመርያው ተፈጻሚነት ግን በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ላይ ብቻ ስለሆነና ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ያልሆነ በመሆኑ፣ ከዚህ በተጨማሪም ማካተት ያለበትን ጉዳዮች ለምሳሌ የአለባበስ ደንብ ያልያዘ በመሆኑ በፍርድ ቤቶች የችሎት አመራርና አሠራር ላይ ሥር ነቀል ለውጥ አላመጣም፡፡

በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተለያዩ ደረጃዎችና ችሎቶች በችሎት አመራር ረገድ ሊታረሙ የሚችሉ ጉድለቶች ይስተዋላሉ፡፡    

 1. የጊዜ አጠቃቀምን በተመለከተ

አብዛኛውን ጊዜ ችሎቶች ሥራ የሚጀምሩት የችሎት ሰዓት ተብሎ ከተገለጸው ጊዜ ከ30 ደቂቃ እስከ 1 ሰዓት በመዘግየት ነው፡፡ ተገማች የሆነ የችሎት መጀመሪያ ሰዓትም የለም፡፡

 1. የቀጠሮ አሰጣጥ

በአሁኑ ጊዜ የሚሰጠው ቀጠሮ ረጃጅምና ተደጋጋሚ ቀጠሮ ነው፡፡ በአንዳንድ ችሎቶች በሰዓት የመቅጠር ሁኔታ ቢኖርም፣ በሰዓቱ አያስተናግዱም፡፡ በሰዓት የሚቀጥሩ ችሎቶችም በተመሳሳይ ሰዓት በርካታ መዝገቦችን ይቀጥራሉ፡፡ ከችሎቱ አቅም በላይ መዝገቦችን ይቀጥራሉ፡፡ ባለጉዳዮች በሰዓት ሊቀጠሩ የሚገባው በሰዓቱ የሚስተናገዱ ከሆነ ብቻ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሰዓት የተቀጠሩ ባለጉዳዮች አንዱ ወገን በሰዓቱ ሲገኝ፣ ሌላውን ወገን ጠብቅ እየተባለ ለመጠበቅ ይገደዳል፡፡ ቀጠሮ በሰዓት ከተሰጠ በሰዓቱ የደረሰው ባለጉዳይ ሊስተናገድ ይገባዋል፡፡ በአንዳንድ ችሎቶች ግን ሰዓቱ ቢደርስም፣ ሁለታችሁም ካልተሟላችሁ አናስተናግድም ጠብቁ ይባላል፡፡ ስለዚህ በቀጠሮ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ያለው የጊዜ አጠቃቀም ጥብቅ በሆነ ሁኔታ ሊተገበር ይገባዋል፡፡

 1. አስቀድሞ አለመዘጋጀት

አንዳንድ ችሎቶች መዝገቦችን የሚሰይሙት ችሎት ከተጀመረ በኋላ በችሎት ነው፡፡ መዝገቦች አስቀድሞ በዳኛው፣ በረዳቱ ወይም በጸሐፊው ተሰይመው ሊዘጋጁ ይገባል፡፡ ይህም የዳኛውንና የባለጉዳዮችን የቆይታ ጊዜ ይቀንሳል፡፡ በሌላ በኩልም መዝገቦች አስቀድመው ተጠንተው የማይቀርቡበት ጊዜ ያጋጥማል፡፡ ባለጉዳዮች በችሎት ቆመው መዝገብ ይመረመራል፣ ባለጉዳዮች ቆመው ትዕዛዝ ብይን ይጻፋል፡፡ አንዳንድ ችሎቶችም ለክርክር የተቀጠሩ መዝገቦች ላይ የክርክር ነጥቦችን /Issues/ ለይቶ አለመቅረብ ይስተዋላል፡፡ በደፈናው ክርክርህን አስረዳ በሚል መልኩ የሚደረግ የክስ ወይም የይግባኝ አሰማም ሒደት ለጉዳዩ አወሳሰን ብዙም ጠቀሜታ የለውም፡፡ ክርክር መደረግ ያለበት አስቀድመው በተለያዩ ነጥቦች ወይ በክርክር ጊዜ በታወቁ የፍሬ ጉዳይ ወይም የሕግ ነጥብ ላይ መሆን ይገባዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድ ያለው ጉድለት ቢስተካከል መልካም ነው፡፡ 

 1. ችሎት እያለ በቢሮ ማስቻል

በግልጽ ችሎት ማስቻል በሕግ የተቀመጠ የዳኞች ግዴታ ነው፡፡ ግዴታ ከመሆኑ በተጨማሪ በችሎት ማስቻል ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል፡፡ በአንዳንድ ችሎቶች የማስቻያ ቦታ እጥረት ቢኖርም፣ እጥረት የሌለባቸው ችሎቶችም በቢሮ ሲያስችሉ ይስተዋላል፡፡ ዳኞች በቢሮ በሚያስተናግዱበት ጊዜ ደግሞ አንዳንድ የችሎት አስተናጋጆች ባለጉዳዮችን በአግባቡ አያስተናግዱም፣ ባለጉዳዮችም ከፍተኛ የሆነ መጉላላት ሲደርስባቸው ይስተዋላል፣ ዳኞችም በቢሮ ውስጥ ስለሆኑ ይህንኑ ለማየት አይችሉም፡፡ በቢሮ ማስቻል ደግሞ ቅልጥፍናን ይቀንሳል፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን የተዘጋጀ ችሎት ካለ በችሎት ማስቻል ሕጋዊና ተገቢ ነው፡፡ በበቂ ምክንያት በቢሮ የማያስችሉ ከሆነም፣ የችሎቱ አስተናጋጆች ባለጉዳዮችን እንዳያጉላሉ ቁጥጥር ቢያደርጉ መልካም ነው፡፡

 1. የረዳት ዳኞች አጠቃቀም በተመለከተ

ዳኞች ረዳት ዳኞቻቸውን በአግባቡ ሲጠቀሙ አይስተዋልም፣ ረዳት ዳኞችን በችሎት ይዞ በመግባት ትዕዛዝ እንዲጽፉ በማድረግ ሥራውን ማቀላጠፍ ይቻላል፡፡ ዳኛው ራሱ በችሎት ትዕዛዝ ከሚጽፍ ለረዳት ዳኛው አቅጣጫ በመስጠት ማጻፍ ይችላል፡፡ ዳኛው በሌሎች እንደ ክስና ይግባኝ መስማት ተግባራት ላይ ጊዜያቸውን ማዋል ይችላሉ፡፡ ረዳት ዳኞችም የወደፊቱ ዳኞች ስለሆነ፣ የችሎቱን አሠራር በአግባቡ እንዲረዱት ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡

 1. መዝቦች የሚስተናገዱበት ቅደም ተከተልን በተመለከተ

አንድ ችሎት ለባለጉዳዮች ቀጠሮ ሲሰጥ መዝገቦቹ ቀጠሮ የሚይዙት ለተለያየ ጉዳይ ነው፡፡ መዝገቦቹ ቀጠሮ የያዙት መልስ ለመቀበል፣ የቃል ክርክር ለማካሄድ፣ ይግባኝ ለመስማት፣ ክርክር ለማካሄድ፣ ትዕዛዝ ብይን ውሳኔ ለመስጠት ወይም ምስክሮችን ለመስማት ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ተግባራት በባህሪያቸው የሚጠይቁ ጊዜ የተለያየ ነው፡፡ መልስ መቀበል ከሁለት ደቂቃ በላይ አይፈጅም፡፡ ምስክር መስማት እንደ ምስክሮች ብዛትና ዓይነት የሚወሰን ሆኖ በትንሹ ግን ከአንድ ሰዓት በላይ ይወስዳል፡፡ ስለዚህ ዳኞች ችሎት በሚመሩበት ጊዜ መጀመሪያ ሲቀጥሩም ሆነ በቀጠሮው ቀን ሲያስተናግዱ ይህንን ግምት ውስጥ ቢያስገቡት መልካም ነው፡፡ አንዳንድ ችሎቶች ሥራቸውን በምስክር መስማት፣ አንዳንዶቹ በክስ መስማት ይጀምራሉ፡፡ ለሁለት ደቂቃ መልስ መቀበል ወይም የአምስት ደቂቃ ውሳኔ ለመስማት፣ አምስት ወይም አሥር ምስክሮች እስኪሰሙ መጠበቅ የለባቸውም፡፡ እንደ እኔ እምነት በመርህ ደረጃ መጀመሪያ ብይን /ትዕዛዝ/ ውሳኔ ቢነገር፣ በመቀጠል መልስ መቀበል፣ ከዚህ በኋላ ክስ ቢሰማና መጨረሻ ላይ ምስክሮች ቢደመጡ ተገቢ ነው፡፡ የባለጉዳዮች ወይም የጉዳዩ ዓይነት ወይም የምስክሮች ሁኔታ ቅድሚያ የሚያሰጥ ከሆነ ግን ይህን ልዩ ሁኔታ /Exception/ መከተል መቻል ተገቢ ነው፡፡

 1. በትህትና አለመስተናገድ

በሁሉም ችሎቶች ባይሆንም በአንዳንድ ችሎቶች ባለጉዳዮችን በኃይለ ቃል የመናገር፣ የመሳደብ፣ የማዋረድ ሁኔታ ይታያል፡፡ ባለጉዳዮችን በትህትናና በክብር ማስተናገድ ለራስም ክብር ነው፡፡ ስለዚህ በችሎት አመራር ጊዜ በትህትናና በክብር ማስተናገድ ይገባል፡፡

 1. የውሳኔ /ትዕዛዝ/ ብይን አሰጣጥ

በሥነ ሥርዓት ሕጎቻችን መሠረት ውሳኔ ከተጻፈ በኋላ ለባለጉዳዮች መነበብ ወይም መገለጽ ይገባዋል፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ችሎቶች ውሳኔ ሳይጻፍ በቃል ይነገራል፣ ውሳኔ ተሰጥቷል በጽሕፈት ቤት ተከታተሉ ይባላል፡፡ የውሳኔውን ግልባጭ ለማግኘትም ባለጉዳዮቹ በምልልስ ይጉላላሉ፡፡ በሌላ በኩልም ውሳኔ በቀጥታ በሚገለጽ ጊዜ፣ በተለይ ባለጉዳዮች የሕግ ባለሙያ ካልሆኑ በሚገባቸውና በቀላል ቋንቋ እንዲረዱት ሊደረግ ይገባል፡፡ አንዳንድ ባለጉዳዮች ውሳኔ ከተነበበላቸው በኋላ ግራ ሲገባቸው ይታያሉ፡፡ ስለዚህ ውሳኔ ሳይጽፉ አለመንገር፣ ውሳኔው ከተጻፈም በሚገባ ቋንቋ ለባለጉዳዮች መግለጽ ቢቻል መልካም ነው፡፡

 1. የመቅረፀ ድምፅ አጠቃቀም

የችሎቱ ሒደቶች በመቅረፀ ድምፅ እንዲቀረፁ መደረጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ነገር ግን መቅረፀ ድምፅ ዳኞችን ሊተካ አይችልም፡፡ ስለዚህ ዳኞችም ክርክር ሲሰማ ወይም ምስክሮች ሲሰሙ፣ ዋና ዋና ያሟሏቸውን ነጥቦች በመዝገቡ ቢያሰፍሩ መልካም ነው፡፡ በመቅረፀ ድምፅ የተመዘገበው ቃልም በወቅቱ ተገልብጦ ስለማይያያዝ፣ ለቀጠሮ መለወጥና ለጉዳይ መዘግየት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ በአንዳንድ ችሎቶችም በመቅረፀ ድምፅ የተቀረፀው ተገልብጦ እንዲያያዝ አድርጉ እየተባለ ለባለጉዳዮች ይነገራል፡፡ ባለጉዳዮች የፍርድ ቤቱን ሠራተኞች የማዘዝ ወይም የመቆጣጠር ሥልጠን የላቸውም፡፡ ስለዚህ የፍርድ ቤቱ ዳኞችና አስተዳደሩ፣ በመቅረፀ ድምፅ የተቀረፀው በጊዜው ተገልብጦ እንዲያያዝ ቁጥጥር ቢያደርጉ መልካም ነው፡፡

 1.  የምስክር አሰማምና የዳኛው ሚና

በውሳኔ አሰጣጥ ማስረጃ ቁልፍ ቦታ አለው፡፡ በስፋት ከሚቀርቡ የማስረጃ ዓይነቶች አንዱ ምስክርነት ነው፡፡ አንድን ጉዳይ የማስረዳት ሸክም ያለበት ወገን ማስረጃውን አቅርቦ ያሰማል፡፡ ምስክሮችን የሚያቀርብ ተከራካሪም ምስክሮችን አቅርቦ የማሰማት መብት አለው፡፡ በመርህ ደረጃ ምስክሮች በሦስት የጥያቄ ደረጃ ያልፋሉ፣ በዋና ጥያቄ፣ በመስቀለኛና በድጋሚ ጥያቄ ዳኞች ደግሞ በማንኛውም ደረጃ ጥያቄ የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡ ይህ ሲባል ግን ምስክር አቅራቢውን ወይም ሌላውን ወገን ተክተው ጠያቂ ይሆናሉ ማለት አይደለም፡፡ ዳኞች ምስክር የሚሰማበትን ነጥብ መለየት፣ የምስክርነት ሒደቱን በንቃት መከታተልም ይገባቸዋል፡፡ በአንዳንድ ችሎቶች ግን ምስክር እየተሰማ ዳኞች ሌላ ሥራ ሲሠሩ ይስተዋላል፡፡ አንዳንድ ዳኞች ደግሞ ዋና ጥያቄውን ወይም መስቀለኛ ጥያቄውን ራሳቸው ሲመሩ ይታያል፡፡ ስለዚህ የምስክሮች አመራርን በተመለከተ በገለልተኝትና እውነትን በመፈለግ ሚና ብቻ ዳኞች ችሎቱን ቢመሩት መልካም ነው፡፡

 1.  በሕግና በማስረጃ መወሰን

የሕግ ባለሙያ ሰው እንደመሆኑ መጠን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ያሉት ከስሜት ነፃ ያልሆነ፣ ፍላጎቶችና ግቦች ያሉት ነው፡፡ ዳኞችም ይህንን ስሜት ሊጋሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ዳኝነት የሕዝብ አደራ ስለሆነ፣ ዳኛ የሆነ ሰው የግል ስሜትና አስተሳሰቡ ላይ ወይም የግል ሕይወቱ አመራር ላይ ገደብ አለበት፡፡ ስለዚህ የግል ስሜቱን ወደ ጎን በማድረግ፣ ችሎቱን መምራት ያለበት በሕግና በማስረጃ መሆን ይገባዋል፡፡

12. የአለባበስ ሁኔታ

ዳኛ በአለባበሱ የዳኝነት ክብሩን እንዳያዋርድ መጠንቀቅ እንዳለበት በፌዴራል ዳኞች የሥነ ምግባር ደንብ ላይ ተመልክቷል፡፡ ነገር ግን አለባበሱ ምን ዓይነት ይሁን በሚለው ላይ የወጣ ደንብ ወይም መመርያ የለም፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው አለባበስም የተዘበራረቀ ነው፡፡ በእርግጥ የአለባበስ ሁኔታ በዓቃቤ ሕጎችም ሆነ በጠበቆች ላይ የሚስተዋል ችግር ነው፡፡ የታወቀና ሥርዓት ያለው የአለባበስ ሥርዓት /Court Decourum/ መኖር ይገባዋል፡፡ ወንድ ዳኞች ምን ዓይነት ልብስ ይልበሱ? ሴት ዳኞች ምን ዓይነት ልብስ ይልበሱ? ጠበቆችና ዓቃቤ ሕጎች ችሎት ሲቀርቡ ምን ዓይነት ልብስ ይልበሱ? የሚለውን ፍርድ ቤቱ በመመርያ ሊወስነው ይገባል፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን የዳኝነት ክብርን ይጠብቃል የሚባለው አለባበስ፣ ለወንድ ኮት፣ ሸሚዝና ክራባት ማሰር፣ ለሴቶችም ተመጣጣኝ የሆነ ገላን የማያጋልጡ አለባበሶች ስለሆኑ፣ ይህ አለባበስ ተግባራዊ ቢሆን መልካም ነው፡፡

በአጠቃላይ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በሕግ የተጠለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣትና የሕዝብ አመኔታን ለማትረፍ የበለጠ መሥራት ከሚገባቸው ዘርፎች አንዱ በችሎት አመራር ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ፍርድ ቤቶች የችሎት አመራርን በተመለከተ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ደረጃ ተፈጻሚ የሆነ ዝርዝር ደንብ ወጥቶ ተግባራዊ ቢደረግ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል እምነቴ ነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...