ሐሙስ ነሐሴ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ከረፋዱ አራት ሰዓት የረር ጎሮ በሚባል አካባቢ ጠጠር የጫነ ሲኖትራክ ተገልብጦ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ፡፡ ለግንባታ የሚሆን የተፈጨ ጠጠር ጭኖ ወደ ጎሮ ሲጓዝ በተለምዶ ምንየ ሕንፃ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ሲደርስ ፍሬን እምቢ ሲለው፣ ወደ ተቃራኒው መንገድ ዘሎ በመግባት በአካባቢው ሁለት የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች በመጣል ቆሞ የነበረ ዲኤክስ ታክሲ ላይ ተገልብጧል፡፡ ከታክሲው ኋላ ቃሪያ ጭኖ ወደ ጉልት ሊታጠፍ የነበረ በብስክሌት የሚጓዝ አንድ ግለሰብ ላይም ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡
የአካባቢው የኮሚኒቲ የቀጣናው ኦፊሰር ሳጅን ሳሙኤል ሰለሞን የደረሰውን ጉዳት ለሪፖርተር ሲገልጹ፣ ‹‹በብስክሌት ይጓዝ የነበረው ወጣት ዕድሜው በግምት ከ18 እስከ 21 ይሆናል፡፡ አትክልቶችን በበስክሌት በመጫን ለሆቴሎችና ለትናንሽ ጉልቶች በማቅረብ የሚተዳደር ነበር፡፡ በአደጋው የቀኝ እግሩ ሙሉ በሙሉ፣ እንዲሁም የግራ እግሩን ጣቶቹን ሙሉ በሙሉ አጥቷል፡፡ በአካባቢው ቆሞ የነበረ ዴክስ ታክሲ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡ በአደጋው ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ የሆነው ታክሲ በግምት 170 ሺሕ ብር ሊያወጣ እንደሚችልም አብራርተዋል፡፡ አሥራ ሰባት ሜትር ኪዩብ ጠጠር በጫነው ሲኖትራክና በአሽከርካሪው ላይ ጉዳት አለመድረሱ ተገልጿል፡፡ ሦስት የመንገድ የኤሌክተሪክ መስመር ምሰሦዎች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል፡፡ የአደጋው መንስዔም የፍሬን ችግር እንደሆነ ሳጅን ሳሙኤል ገልጸዋል፡፡
ሪፖርተርም አደጋው በደረሰበት ወቅት በሥፍራው ተገኝቶ ለመገንዘብ እንደቻለው፣ አደጋው የደረሰበት ቦታ ከፍተኛ ቁልቁለትና ዳገት ያለው ሲሆን፣ ምንም ዓይነት የአደጋ ማስጠንቀቂያ ምልክት የለውም፡፡ እንዲሁም መንገዱ ፍጥነት ለመቀነስ የሚረዳ ምልክት የሌለው በመሆኑ፣ አሽከርካሪዎች በመጡበት ፍጥነት ነው የሚጓዙት፡፡ በቅርቡ የአዲስ – አዳማ የፍጥነት መንገድ መግቢያ በመሆን ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ይህ መንገድ፣ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ይታይበታል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ በመንገዱ ላይ የፍጥነት መቀነሻ እንዲሠራለት ቢጠይቁም ምላሽ እንዳላገኙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡